Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየእግር ኳስ አሠልጣኞች የደረጃ ብቃት ማረጋገጫ ሥልጠናና አዲሱ የካፍ መመርያ

የእግር ኳስ አሠልጣኞች የደረጃ ብቃት ማረጋገጫ ሥልጠናና አዲሱ የካፍ መመርያ

ቀን:

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ቀደም ሲል በአኅጉር ደረጃ ሲሰጥ የነበረውን የአሠልጣኞች የደረጃ ብቃት ማረጋገጫ (ላይሰንስ) ሥልጠና ከጥራት ጋር ተያይዞ በሁሉም አገሮች ሥልጠናው እንዳይሰጥ አድርጎ ቆይቷል፡፡ ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ በተለይም የሥልጠናው ደረጃና የጥራት ሁኔታ ከፍ በሚልበት ሁኔታ ላይ ከአባል ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ጋር ከተወያየ በኋላ ሥልጠናው ከ“ዲ” ጀምሮ እስከ “ኤ” እና ከዚያም በላይ ጥራትና ደረጃውን ጠብቆ እንደሚሰጥ፣ ሆኖም ሥልጠናው የሚሰጥበት የማስተማሪያ መርሐ ትምህርት (ሲለበስ) ዝግጅት ከፍተኛ ባለሙያ የሚጠይቅ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ዝቅተኛውን መሥፈርት ካሟሉ አገሮች በመካተቷ ሥልጠናውን በራሷ ሙያተኞች አማካይነት እንድትሰጥ ፈቃድ ማግኘቷ እየተነገረ ይገኛል፡፡ መሥፈርቶቹን አስመልክቶ ፌዴሬሽኑ ምን ይላል? በሌላ በኩልም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከታዳጊዎች እስከ ዋናው ብሔራዊ ቡድን በሁለቱም ፆታ በማደራጀት ላይ ይገኛል፡፡ ቀደም ሲል በፌዴሬሽኑ ውስጥ የነበሩ ከፋይናንስና መሰል ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ሲነገሩ የነበሩ ክፍተቶች አሁን ላይ አይደመጡም፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ዋሊያ ቢራን ጨምሮ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር የስፖንሰርሺፕ ስምምነት መፈጸሙ ይነገራል፡፡ እነዚህንና ሌሎችም ወቅታዊ ጉዳዮች አስመልክቶ የፌዴሬሽኑን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራን ደረጀ ጠገናው አነጋግሯቸዋል፡፡

 

ሪፖርተር፡- የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ከጥራት ጋር ተያይዞ ላለፉት አምስት ዓመታት አቋርጦት የነበረውን የእግር ኳስ አሠልጣኞች የብቃት ማረጋገጫ (ላይሰንሲንግ) ፕሮግራም እንደገና አንዲጀመር ማድረጉ ተሰምቷል፡፡ ከሰሞኑም በባህር ዳር ከተማ ሥልጠና በመስጠት ላይ ናችሁ፡፡ በካፍ በኩል ከሥልጠናው ጋር የደረሳችሁበት ስምምነት ይኖር ይሆን?

አቶ ኢሳያስ፡- ካፍ ቀደም ሲል ኢትዮጵያን ጨምሮ በሁሉም አባል አገሮች ሲሰጥ የነበረው ሥልጠና እንዲቋረጥ የወሰነው ከጥራት ጋር ተያይዞ ነው፡፡ ሁሉም እንደሚያውቀው ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ እግር ኳስ ከተቀሩት አገሮች ጋር ሲነፃፀር ደረጃው ዝቅ ያለ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ካፍ ለዚያም ነው ሥልጠናውን ላለፉት አምስትና ስድስት ዓመት ያህል እንዲቋረጥ ከውሳኔ ላይ የደረሰው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ስመጣ፣ በወቅቱ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የነበሩት ቴክኒክ ዳይሬክተር በመልቀቃቸው የተነሳ የሥልጠና ማስተማሪያ መርሐ ትምህርት (ሲለበስ) ለማዘጋጀት የሙያተኛ ክፍተት ስለነበረብን ካፍ ከሥልጠናው ጋር ተያይዞ እንድናሟላ የጠየቀን ማኑዋል ከዚሁ የሙያተኛ ክፍተት ጋር ተያይዞ የሲለበስ ዝግጅቱ በመጓተቱ ሥልጠና መስጠት የሚያስችለንን ፈቃድ ማግኘት ሳንችል ቆይተናል፡፡ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ግን ፌዴሬሽኑ በሙያው ውስጥ የነበሩ ኢንስትራክተሮችን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጋር በማቀናጀት ካፍ ካስቀመጠው ቅድመ ሁኔታ ጋር ተዛማጅ የሆኑ ማኑዋሎችን በማዘጋጀት፣ የተዘጋጀውን ማኑዋል ለካፍ አሳውቀን ተቀባይነት አግኝተናል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በባህር ዳር ከተማ የ“ዲ” የእግር ኳስ አሠልጣኝነት ደረጃ (ላይሰንስ) መስጠት ጀምረናል፡፡ ካፍ በዚህ ደረጃ ሥልጠና የመስጠት ፈቃድ ከሰጣቸው አሥር አገሮች ኢትዮጵያ አንዷ ለመሆን በቅታለች፡፡

ሪፖርተር፡- የላይሰንስ ሥርዓቱ  ከ“ዲ” ወደ “ሲ” እና “ቢ” እንዲሁም “ኤ” ከፍ እያለ እንዲሄድ፣ ካፍ ካስቀመጠው ቅድመ ሁኔታ ጋር የተጣጣመ እንዲሆንም ለማድረግ ጭምር በፌዴሬሽኑ በኩል ምን ዓይነት ዝግጅት እየተደረገ ነው?

አቶ ኢሳያስ፡- የሥልጠና ሥርዓታችን ከዚህ በኋላ ሊሆን የሚችለው ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደሞከርኩት ካፍ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ብቻ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ሥርዓቱን ተከትላ ለመሥራት ከካፍ ጋር ስምምነት (ኮንቬንሽን) ፈርማለች፡፡ በዚህ ስምምነት መሠረት ከኢትዮጵያ በፊት አምስት አገሮች በዚህ ሒደት ውስጥ ቀድመውናል፡፡ አሁን ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ካፍ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ዕውቅናውን ለማግኘት ሲሠራ የነበረው ከመጀመርያዎቹ አሥር አገሮች አንደኛው ለመሆን ነበር፣ ያም ተሳክቶለታል፡፡ በስምምነቱ መሠረት ፌዴሬሽኑ “ዲ” ላይሰንስ መስጠት እንዲችል ባገኘው ፈቃድ መሠረት ሥልጠናውን መስጠት ጀምሯል፡፡ ይሁንና ከ“ሲ” ጀምሮ ያለውን ሥልጠና በተመለከተ ግን እንደገና ካፍን ማሳወቅ ይጠበቅብናል፡፡ ምክንያቱም ከ“ሲ” ጀምሮ እስከ ፕሮፌሽናል ያለው የሥልጠና ዓይነትና ፕሮግራም በካፍ ሥር ማለፍ ስላለበት ማለት ነው፡፡ የሥልጠና አሰጣጥ ቅደም ተከተሉን በሚመለከት የ“ሲ” ደረጃ ሥልጠና በስድስት ክፍል ተከፋፍሎ በእያንዳንዱ ክፍልና የሥልጠና ፕሮግራም 30 ሠልጣኞች በብቃታቸው ተመርጠው ሥልጠና እንዲሰጣቸው ይደረጋል፡፡ በዚህ የሥልጠና ሒደት በአጠቃላይ 180 ሰው እንዲካተት ከተደረገ በኋላ ነው ወደ ቀጣዩ ደረጃ ወይም “ቢ” ከዚያም “ኤ” እና ፕሮፌሽናል ደረጃ መምጣት የሚችለው፡፡ ይህ ማለት እንደ ቀድሞ የፈለገውን ያህል ቁጥር በማግበስበስ አታሠለጥንም ማለት ነው፡፡ ለጥራት ሲባል በቁጥር መገደብ ያስፈለገውም ለዚያ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ካፍ የሥልጠና ጊዜውን በተመለከተ ምን ዓይነት አቅጣጫ ነው እንድትከተሉ የሚፈልገው? ምክንያቱም ቀደም ሲል ከ15 ቀን ሥልጠና በኋላ ላይሰንስ የሚሰጥበት አሠራር ስለነበረ ማለት ነው?

አቶ ኢሳያስ፡- አዲሱ ሥልጠና ከዚህ በፊት ልምድና ሌሎችም ተሞክሮዎች እየተባለ በ15 ቀን የሚጠናቀቅ ሳይሆን፣ በተቀመጠለት ሰዓት መሠረት በሞጁላር ሲስተም የሚሰጥ ነው የሚሆነው፡፡ ይህ ማለት አንድ አሠልጣኝ ክለብ እያሠለጠነ የሚመቸው ቀን ተጠይቆ፣ በተቀመጠለት ማኑዋል መሠረት ለሥልጠናው ከተወሰነው ሰዓት የተወሰነውን ኮርስ ወስዶ ወደ መደበኛ ሥራው የሚመለስበት የሥልጠና ሥርዓት የሚከተል ሆኖ፣ ጊዜው ግን እስከ ሦስት ወር ድረስ የሚፈጅ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ሥልጠና እንደ ቀድሞው በደቦ ሥልጠና ወስዶ ማለፍ ሳይሆን፣ እያዳንዱ ሠልጣኝ በበይነ መረብ በራሱ መለያ ኮድ ኮርሱ እየተላከለት፣ ከዚህም በተጨማሪ እያንዳንዱን የሥልጠና ዓይነት በተግባር ሠርቶ የሚያሳይበት ድሪል እየተሰጠው፣ የተጠየቀውን በተግባር ሠርቶ ማሳየት እንዳለበት ጭምር የካፍ ማኑዋሉ ያስገድዳል፡፡ ይህ ለአገሪቱ የእግር ኳስ ሲባል ከየት መመንጨት እንዳለበት የሚያግዝ ጭምር ይሆናል ማለት ነው፡፡ ለእያንዳንዱ ድሪል ከሀርድ ኮፒው በተጨማሪ ሶፍት ኮፒ እንዲኖረውም ያስገድዳል፡፡ ካፍ እነዚህን ሒደቶች ላለፈ ሠልጣኝ ብቻ ነው የብቃት ማረጋገጫ ወይም ላይሰንስ የሚሰጠው፡፡ እያንዳንዱ ጥያቄ የሚቀርበውም ሆነ የሚመጣው ቀደም ሲል ሠልጣኙ በሞላው ኮዱ መሠረት በኦን ላይን ነው፡፡ በባህር ዳር እየተሰጠ በሚገኘው የ“ዲ” ላይሰንስ ሥልጠና ላይም የእያንዳንዱ ሠልጣኝ የራሱ መለያ ኮድ እንዲኖረው ይደረጋል፡፡ ይህንን ተከትሎ ሠልጣኙ እስከ ፕሮፌሽናል ላይሰንስ ድረስ በዚህ ኮድ መሠረት ነው ሥልጠናውንም ሆነ ላይሰንሱን ማግኘት የሚችለው፡፡ እዚህ ላይ በተጫዋችነት ከክለብ እስከ ብሔራዊ ቡድን ተጫውተው ያሳለፉ ሰዎች በተጫወቱበት ሰዓት ልክና መጠን ካፍ “ፋስት ትራክ” በሚል ልዩ ዕድል ስለሚሰጥ፣ በዚህ ውስጥ የሚገኙ ሠልጣኞች በ“ዲ” ደረጃ ያለው ሥልጠና አይመለከታቸውም፡፡ ቀጥታ ወደ “ሲ” እንዲሄዱ የሚደረግበት የአሠራር ሥርዓት አመቻችቷል፡፡ ይህ ሲባል በ“ዲ” ደረጃ የሚሰጠውን ሥልጠና ማንኛውም ፍላጎት ያለው ሰው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መውሰድ ይችላል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ፌዴሬሽኑ ከወትሮው በተለየ በሁለቱም ፆታ ከታዳጊ እስከ ዋናው ብሔራዊ ቡድን ገንብቷል፣ በዚህ ደረጀ እስከ የት ድረስ ለመዝለቅ አቅዷል? 

አቶ ኢሳያስ፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከተሰጠው የሥራ ኃላፊነት ውስጥ ብሔራዊ ቡድኖችን በየደረጃ ማዋቀርና ውድድሮችን በበላይነት መምራት አንዱና ዋናው ነው፡፡ ተቋሙ ከዚህም በተጨማሪ ሥልጠናዎችን ይሰጣል፣ የልማት ሥራዎችን ያከናውናል፣ በዋናነት ደግሞ በአቅም ራሱን እንዲችል የተለያዩ ሥራወችን አቅዶ ይሠራል፡፡ ቀደም ሲል በነበረው የፋይናንስ እጥረት ሊሆን ይችላል፣ ፌዴሬሽኑ ዋናውን ቡድን ካልሆነ ልክ እንደ አሁኑ ከታዳጊ ጀምሮ ተመጋጋቢነት ያለው የብሔራዊ ቡድን ግንባታ አልነበረውም፡፡ ለእግር ኳሱ ውድቀት ይህ እንደ አንድ ምክንያት ተደርጎ ሲነገር መቆየቱ የሚታወቅ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ታች ላይ ለሚሠሩ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኞች ቢበዛ ሦስት ወር እንጅ እንዲህ እንደ አሁኑ ዓመትና ከዚያም በላይ የሥራ ቅጥር ኮንትራት አልነበረም፡፡ እኛም በመጀመርያዎቹ ዓመታት ውስጥ በዚሁ የቀጠልንበት አሠራር ነበር፡፡ ቆይቶ ግን እንደማያዋጣን ስናውቅ የተለያዩ የገቢ ማስገኛ ዕቅዶችን በመንደፍ የስፖንሰርሺፕ ስምምነት ሥራዎችን በመሥራት ቀድሞ ስሙ በዕዳ ሲብጠለጠል የነበረው ፌዴሬሽን በአሁኑ ወቅት ከራሱም አልፎ ክልሎችን የሚደጉምበት አቅም ፈጥሯል፡፡ እግር ኳስ ቅብብሎሽ ነው፣ ይህን እስካልተገበርን ድረስ የትም መድረስ አንችልም፡፡ ለዚህም ነው ከታዳጊ እስከ ዋናው ቡድኖቻችንን ለማዋቀር ያስገደደን፡፡ በሁሉም ደረጃ የተዋቀሩት ብሔራዊ ቡድኖቻችን ከዓለም ዋንጫ ማጣሪያ እስከ ምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ (ሴካፋ) የወዳጅነት ጨዋታዎችን ጨምሮ እየተሳተፉ ይገኛል፡፡ ቀደም ሲል ከዋሊያ ቢራና ሌሎችም ድርጅቶች ጋር ከነበረን የስፖንሰርሺፕ ስምምነት በተጨማሪ አሁን ላይ ደግሞ (ዋናውን የወንዶች ብሔራዊ ቡድኑን ብቻ) ኤልኔት ግሩፕ ድርጅቶች ከተሰኘ ካምፓኒ ጋር ለአራት ዓመት የሚቆይ የዓይነትና የገንዘብ ስምምነት ፈጽመናል፡፡ የገንዘብ መጠኑን በሚመለከት በየዓመቱ ሰባት ሚሊዮን ብር ሆኖ፣ በአራት ዓመት 28 ሚሊዮን ብር ገቢ የሚያስገኝልን ይሆናል፡፡ በዓይነት ደግሞ ድርጅቱ በየዓመቱ 1.8 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው ተሽከርካሪዎችን ለፌዴሬሽኑ የሚሰጥ ሲሆን፣ በተጨማሪም ብሔራዊ ቡድኑ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች የጨዋታው ኮከብ ለሚሆኑ ተጨዋች አልያም አሠልጣኝ ሊሆን ይችላል የመኪና ሽልማት ያበረክታል፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ ሲያሸንፍ ደግሞ በቦነስ መልክ የ500 ሺሕ ብር ሽልማትን የሚያካትት የስፖንሰርሺፕ ስምምነት ነው፡፡ ድርጅቱ የሚያገኘው ጥቅም በተመለከተ፣ ብሔራዊ ቡድኑ በልምምድ ወቅት በሚለብሳቸው አልባሳት ላይ የድርጅቱ ዓርማና ስም እንዲሁም ጨዋታ በሚያደርግበት ወቅት ባነሮችን ጨምሮ የድርጅቱን ምርቶችና የአገልግሎት ዓይነቶችን ማስተዋወቅ የፌዴሬሽኑ ግዴታ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- ከእነዚህ ድርጅቶች በተጨማሪ መንግሥታዊ ከሆነ አንድ ትልቅ ባንክ ጋር ስምምነት መፈጸማችሁ የሚናገሩ አሉ፣ ምን ያህል እውነት ነው የባንኩ ማንነትስ ይታወቃል?

አቶ ኢሳያስ፡- የመጨረሻው የስምምነት ውል ስላልተቋጨ የስምምነቱን ዓይነትና የባንኩን ማንነት ለጊዜው ከመግለጽ እቆጠባለሁ፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...