Friday, June 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉየሚያዋጣን ምፅዋት በቃን ብለን በአንድነት ለአገራችን መነሳት ነው!

የሚያዋጣን ምፅዋት በቃን ብለን በአንድነት ለአገራችን መነሳት ነው!

ቀን:

በአሰፋ አደፍርስ

ምፅዋት ጠባቂነታችን ምን ያህል እንዳስጠቃን እያየን ነው፡፡ ለስንዴና ለዶላር ጉርሻ ከመንበርከክ ራሳችንን ነፃ እናውጣና ተዓምር ለማሳየት እንነሳ፡፡ ነጮች ያላቸው እኛ የሌለን ምን ይሆን? ዕውቀት እንዳንል፣ ቀላውጠንም ሆነ ለምነን የሚበቃንን ይዘናል፡፡ እንዲያውም ለሌላ የምንተርፍ መሆናችን የታወቀ ነው፡፡ የዓለምን አገሮችን በር አንኳክተን በቴክኖሎጂ፣ በምህንድስና፣ በሕክምና፣ በትምህርት፣ ምኑ ቅጡ የሚጎድለን የለም፡፡ በዓለም የተመሰከረላቸውን የሕክምና ምሁራንን፣ በየትምህርት ቤቱ የሳይንስ ምሁራንን፣ በከተማ ልማት ከዋና መሐንዲስነት እስከ በርካታ ዘርፎች መሪነት የተሰማሩ አሉ፡፡ በተለያዩ አገሮች በየፍርድ ቤቱ በዳኝነት የሚያገለግሉትን ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ የዕውቀት ቅልውጡም ሆነ በልመና ያገኘነውን ችሎታ ለአገር፣ ለወገንና ለራስ ማዋልና ከሚመፃደቁብን ድርጎ ሰጪዎቻችን ተፅዕኖ መላቀቅ ይኖርብናል፡፡ በእኩልነት አብሮ የመራመድን ቁርጠኝነት አንግበን ማንም ከማንም የማይለይ መሆኑን፣ ኢትዮጵያዊነት እንጂ ልዩ የሚያደርገን ነገር ስለሌለ በቁርጠኝነት መነሳት አለብን።

ለዚህም መሪዎች በራቸውን ከፍተው ለልማትና ለብልፅግና የተዘጋጁ፣ በቀናነት አዕምሮዋቸውን ከፍተው በእውነተኛ መሪነት እንዲራመዱ የሁላችን አደራና ተማፅኖ መሆኑን ተገንዝበው ኃላፊነታቸውን ይወጡ። ይህንን ካልኩ በኋላ እንዲያው ዝም ብዬ ላፍ ማሟሻ ሳይሆን፣ እግረ መንገድ ምን ማድረግ እንዳለብን ለማሳየትና በተቻለኝም የሐሳቡም ሆነ የሥራው ተካፋይ ለመሆን ወደኋላ እንደማልል ለማረጋገጥ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ስለኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብት አስረድቻለሁ፡፡ ነገር ግን ሀብታችንን በዝርዝር ስላላቀረብሁኝ ለወገኖቼ እንደሚከተለው አቀርባለሁ።

- Advertisement -

ኢትዮጵያ ሰፊ ለም መሬት፣ በርካታ ወራጅ ወንዞች፣ ሥራ በማጣት በየአገሩ እየተሰደደ የዓሳ ነባሪ ምሳና እራት የሚሆነው ወጣት ኢትዮጵያዊ፣ በአገር ውስጥ ያሉ በተማሩት ደረጃ ሳይሆን ለመኖር ያህል ብቻ ተከፍሏቸው የነፍስ ማቆያ ያህል እየተከፈላቸው የሚንከራተቱ ምሁራንና ከላይ የጠቀስኳቸው በተለያዩ አገሮች ዕውቀታቸውን የሚለግሱትን ሁሉ ማንሳት ይቻላል፡፡ በትክክለኛና በሚገባ ሁኔታ ወደ አገር ቤት በማሰባሰብ የዕለት ጥቅምን ሳይሆን፣ ዘለቄታውን የአገር ጥቅም መሆን ይኖርበታል፡፡

የአገርን ክብርና ኩራት መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ከስድስት የማያንሱ የአፍሪካ መሪዎች እንደ መሰከሩላት ስናስብ፣ ጥንታዊቷን ነባሯን አገራችንን ከኋላዋ ተነስተው በልማት ከበለጧትና መፅዋች ሆነው ወደፊት እንዳትራመድ መንገድ ዘግተው የሚያስቸግረንን ለጊዜው መብለጥ እንኳ ባንችል ተስተካክለን ለመዋብ እንድንችል ተነሱ፣ እንነሳ፡፡ አይገርማችሁም ከ60 እስከ 65 በመቶ የተፈጥሮ ሀብት ያላትና የምዕራባዊያን ሲሳይ የሆነችው አፍሪካ ሁሌም ተመፅዋች፣ እነሱ ግን በሌላቸውና የራሳቸው ንብረት ያልሆነውን የተፈጥሮ ሀብት እየዘረፉ እዚህ ሲደርሱ የእኛ ወደኋላ መቅረትና ተመፅዋች መሆን አያሳዝንም?                                              

ወገኖቼ የቁጭትና የእልህ አነጋገር እንዳይመስል ወደ ዋናው ሐሳቤና ተባብረን እንድንሠራ ወደ አሰብኩት ጉዳይ ልውሰዳችሁ፡፡ ለአንድና ለሁለት ዓመታት ብቻ ጠንክረን ብንሠራ ትልቁን የልማት ወኔ ውጤት እናያለን። እንዴት? ብዙዎች ኢኮኖሚስቶች የሚያስቡት በሠለጠነውና የዘመኑ ኢኮኖሚ በሚያዘው የፈሪዎች ጎዳና ስለሆነ፣ ብዙ ጊዜ በማውጣትና በማውረድ ጊዜ ከመጥፋቱም በላይ ወላዋይነት እየበዛ ለአገር መደረግ ያለበት ጥረት በከንቱ ይባክናል። ይህ በመላው ዓለም ያለ ስለሆነ አንደነቅ። እንዲህም ስል ሁሉንም ነገር በጭፍን እናከናውን ማለቴ አይደለም።

የተራቀቀውንና በዓለም ተወዳዳሪ የሚያደርገንን ታላቅ ሥራ ለማከናወን በጎን ምሁራንን አዘጋጅተን፣ እነሱ በማጥናት ላይ እያሉ እኛ ግን ተራውን ሥራ በመሥራት የዕለት ተዕለት የወገናችንን ምግብና አልባሳት በሚገባ እያቀረብንና የስንዴ ምፅዋት ጥበቃ አቁመን ከደጅ ጥናት በመውጣት በራሳችን መቋቋም መቻል አለብን። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ቀላሉና በፍጥነት የሚደርሱ ምርቶችና እንስሳት ማርባት ላይ ማተኮር ተገቢ ነው፡፡ ለምሳሌ በቀላሉ ዓረቦች ለረመዳን ጊዜ በዓመት ስንት በጎችና ፍየሎች ይሻሉ? ጌሻ (ካፋ)፣ ደብረ ብርሃን፣ ወላይታና ሌሎች አካባቢዎች በጎችና ፍየሎች እንዲያረቡ ሰዎች ቢመረጡና ድጋፍ ቢደረግላቸው ከፍተኛ ውጤት ይገኛል፡፡

በቦረና፣ በአዳሚ ቱሉ፣ በሐረርና በፎገራ አስቸኳይ የሆነ የቀንድ ከብት ማደለብ ሥራ ቢከናወን እምብዛም ዘመናዊ ሳይንስ የማይሻና ፈጣን ኢኮኖሚ መንገድ ከፋች በመሆኑ፣ ይህ ደግሞ በነዳጅ ዘይት ሀብት የበለፀጉ አገሮች ወደው ሳይሆን ከኢትዮጵያ የሚቀርባቸው ስለሌለ፣ ይህ በርብርብ ቢካሄድ ኢኮኖሚውን ስለሚደግፍ ጊዜያዊ ተስፋ ሲሰጥ ለሌላው የኢኮኖሚ ዕድገት በተራቀቁና ጊዜያቸውን በመስኩ የሚያውሉ ተረጋግተው ሌሎች ወደ ደረሱበት ለመድረስ ይቻላል።

ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብት ብዛት ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም አምስተኛ ሆና ሳለ በእንስሳት ሀብት አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ወይም የሌላቸው ለምፅዋት ሳይሠለፉ፣ ለዓለም ለመጀመሪያ ጊዜ ሀብታምና ደሃ፣ ዓይነ ሥውርና ዓይናማ፣ ወጣትና ሽማግሌ፣ ጤነኛና በሽተኛ፣ ነጭ ወይም ጥቁር ሳይባባል በጠቅላላው የሰው ዘር በየዕለቱ የሚጎነጩትን ቡና የተባለን ውድ ምርት የፈጠረች አገር ዳቦ ለማኝ ከመሆን ወጥታ ተዓምር ማሳየት  እንድትችል የሁላችንም ርብርቦሽ ያሻልና ቆርጠን መነሳት ይገባናል።

ሁላችሁም ታውቁት ይሆናል፣ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ በቀን 600,000 ሊትር ወተት ሲፈለግ፣ አሁን ማቅረብ የሚቻለው 60,000 ሊትር ብቻ መሆኑ አይገርምም? እስኪ በዚህ ደረጃ እንኳን ይታሰብበት። በአዲስ አበባ ብቻ በዚህ መጠን ከተፈለገ ሌላውን ስናካትት ምን ያህል እንደሆነ ገምቱት። የወተት ወጤቱ (ቅቤው፣ እርጎው፣ ዓይቡና የመሳሰሉትን ለጎረቤት አገሮች የመላክን ዕድልም ተመልከቱልኝ። ዛሬ ገንዘብ አይደለም ችግሩ፡፡ ችግሩ ቢማሩም የመልማት ጉዳይ በሥርዓቱ ያልገባቸው የየአካባቢው ባለሥልጣናት እንዲገባቸው ተደርጎ በቆራጥነት ቢሠራ፣ በመጪዎቹ ከአምስት እስከ አሥር ዓመታት ውስጥ አገራችን እየለሙ ካሉ አገሮች ባትቀድምም እንደምትስተካከል ግን ጥርጥር የለኝም።

እንደሚታወቀው ገንዘብ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ችግር አይደለም። ችግሩ ጉዳዩን አውቆ መሠለፍ እንደሆነ በተደጋጋሚ ዓይቼያለሁ። በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን በተለይም በ1940ዎቹና 1950ዎቹ ገንዘብ በጣም ችግር እንደነበረ የምናስታውሰው ነው። እ.ኤ.አ. በ1949 አሜሪካ ለኢትዮጵያ አምስት ሚሊዮን ዶላር ስትለግስ ጉድ ተባለ፡፡ በ1960ዎቹ መጨረሻ ላይ የዓለም ሁኔታ ተቀየረና በፕሬዚዳንት ሪቻርድ ኒክሰን ዘመን ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ 270 ሚሊዮን ዶላር ብድር ቢጠይቁ፣ ኒክሰን ስለማይወዳቸው ቢከለክላቸውም አጅሬ ግን ወደ ሩሲያው ፕሬዚዳንት ኒኪታ ኩሩቼቭ መስመራቸውን ለውጠው ያ ያሰቡትን 270 ሚሊዮን ዶላር ብድር አገኙ፡፡ በዘመኑ የተናደደችው አሜሪካም የኃይል ጨዋታ (Power of the Game) በሚል አሽሙር ብትለፈልፍም እንደ ምንም ብላ ንጉሠ ነገሥቱን አግባብታ ወደ ሰላም ተመለሱ፡፡

ኢትዮጵያ በወቅቱ ከሩሲያ ባገኘችው ገንዘብ የአሰብ የነዳጅ ማጣሪያ፣ የባህር ዳር ፖሊ ቴክኒክ ትምህርት ቤት፣ እንዲሁም ወጣት ኢትዮጵያዊያን ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላ በቤት ኪራይ እንዳይቸገሩ አስበው “ኢሾፓ” የተባለ ትንሽ ባንክ ተመሥርቶ ዛሬ “ቦሌ ሆምስ” በመባል በሚታወቀው ሠፈር ቤቶች ተሠሩ፡፡ ከሩሲያ የተገኘው ብድር ለኢትዮጵያ ልማትና ለወጣቱም ተስፋ የሰጠ ነበር። አሁንም በቆራጥነት ከተዘጋጀንና በዓላማ ሁላችንም ከተነሳሳን ገንዘብ ችግር አይሆንም ለማለት ነው።

ልባችንን፣ ኅብረታችንንና ኃይላችንን አስተባብረን በመነሳት ለሕዝባችን በመሥራት አገራችንን እንታደግ። አሜሪካን በመሰለ ታላቅ የ360 ሚሊዮን ሕዝብ አገር በአንድነት ተባብረውና አብረው “One Nation One Country” ሲሉ፣ እኛ ትናንት አንድ የነበርን ኢትዮጵያዊያን አሁንም አንድነታችንን ይዘን ለልማትና ለታላቅ ሥራ እንነሳ!

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ግለ ሕይወታቸውንና የጉዞ ታሪካቸውን የከተቡበት ‹‹ከባቹማ እስከ ቨርጂኒያ›› በሚል ርዕስ ለአንባቢያን ያቀረቡት መጽሐፍ ደራሲ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...