Thursday, December 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ዝም ማለትን የምዕራቡ ዓለም እንደ ድክመት የሚወስደው ይመስለኛል›› እናውጋው መሐሪ (ዶ/ር)፣ የፒፕል ቱ ፒፕል መሥራች

ዓለም አቀፍ ሁኔታዎች በፍጥነት በሚቀያየሩበትና አዳዲስ ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮች እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮችን ይበልጥ በሚደቁሱበት በዚህ ዘመን፣ ዕውቀት መር የሆኑ ውሳኔዎችን ለመወሰን ተጋላጭነት ካላቸው አካላት ምክረ ሐሳብ መውሰድ የተለመደ አሠራር ነው፡፡ ኢትዮጵያ በውጭ አገሮች የተማሩና አገራዊውን ዓውድ በአግባቡ የሚረዱ ባለሙያዎችን ያፈራችና ለዘመናትም በአገራዊ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ስትጠቀማቸው የቆዩ ባሙያዎች የነበሩ ቢሆንም፣ የሁኔታዎች መቀያየርና መብዛት እነዚህ ብቻ ብቁ አለመሆናቸውን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያስመሰከሩ መጥተዋል፡፡ በዚህም ሳቢያ የውጭ ባለሙያዎችን ቀጥሮ እስከ ማሠራት የደረሰ ውሳኔ ሲወሰን ተስተውሏል፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን በውጭ አገር የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ያላቸውን ሀብት ብቻ ሳይሆን ዕውቀትና ልምዳቸውንም ጭምር ለአገራቸው እንዲያበረክቱ ለማድረግ ታልሞ፣ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡበት የመጋቢት ወር 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ሲሠራበት ቆይቷል፡፡ ለዚህም ይረዳ ዘንድ የዳያስፖራ ኤጀንሲ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሥር እንደ አንድ የሥራ ክፍል ከመሆን ወጥቶ ለብቻው እንዲመሠረት ተደርጓል፡፡ ይኼ አዲስ ጅማሮ ቢሆንም፣ ከሁለት አሥርት ዓመታት አስቀድሞ በአገሪቱ በተለያዩ የሰብዓዊና ቁሳዊ የልማት ሥራዎች ላይ ሲሠማሩ የነበሩ እንደ ፒፕል ቱ ፒፕል ያሉ ተቋማት አሻራቸውን ሲያኖሩ ቆይተዋል፡፡ ፒፕል ቱ ፒፕል ከተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት ጋር በመተባበርና ከዳያስፖራውና ከምዕራቡ ዓለም ተቋማት ጋር ትስስር በመፍጠር አገራዊ ተቋማት ማግኘት የሚችሉትን ያህል ዕውቀትና ልምድ እንዲያገኙ ሲያግዝ ቆይቷል፡፡ ለመንግሥትም የተለያዩ የፖሊሲ ምክረ ሐሳቦችን በማቅረብ የሚያግዝ ሲሆን፣ በተለይ በትምህርትና በጤናው ዘርፍ በርካታ ሥራዎችን ከመንግሥት ጋር በመተባበር ሠርተዋል፡፡ ከዓመት በፊት ለዓለም አዲስ ክስተት የሆነውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምንነት፣ የመከላከል መንገዶችንና የሕክምና ዘዴዎችን ለመወያየትና ለመማማር የሚያግዙ መድረኮችን አዘጋጅተው ሥልጠና ሲሰጡም ቆይተዋል፡፡ ከዚህ ባለፈ፣ ኢትዮጵያ ከትግራይ ክልል ጦርነት ጋር በተያያዘ ያለባትን ዓለም አቀፍ ጫና ለማቃለል ከሚሠሩ የዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላት ጋር በመተባበር፣ በተለይ ከአሜሪካ መንግሥትና ከሕዝብ ተወካዮች ጋር ይነጋገራሉ፡፡ የፒፕል ቱ ፒፕል መሥራች ከሆኑት የነርቭ ሕክምና (ኒውሮሎጂ) ባለሙያ እናውጋው መሐሪ (ዶ/ር) ጋር ብሩክ አብዱ በተለያዩ የጤና፣ አገራዊና አገር አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- ፒፕል ቱ ፒፕል ሲመሠረት የአገሪቱን የጤና ሥርዓት ለማገዝና የበሽታዎችን ሥርጭት ለመግታት ዓላማው አድርጎ እንደተቋቋመ በድረ ገጹ ላይ ያትታል፣ ከተቋሙ ታሪክ አንፃር ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ ቆይታው ይኼንን ግብ ምን ያህል አሳክቷል?

ዶ/ር እናውጋው፡- ፒፕል ቱ ፒፕል የተመሠረተው በ1999 ዓ.ም. በመጋቢት ወር ነው፡፡ ጊዜው ኤችአይቪ ኤድስ ከፍተኛ ሥርጭት ያሳየበትና በወቅቱ ከዓለም አንድ በመቶ የሚሆነው የሥርጭት ምጣኔ በኢትዮጵያ የነበረበት፣ በዓለም ከሚገኙ የቫይረሱ ተጠቂዎች ደግሞ ዘጠኝ በመቶ የሚሆኑት በኢትዮጵያ ይገኙ የነበረበት ነበር፡፡ ከመጀመሪያዎቹ አንዱ ሊሆን የሚችል የመጀመሪያውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኮንፈረንስን በዚያው ዓመት ጥር ላይ እንዲደረግ አደረግን፡፡ በዚህ በርካታ በቫይረሱ ላይ ዕውቀት ያካበቱና የኖቤል ሽልማት ይገባቸው ነበር በሚባሉ ሰዎች አስተባባሪነት ወደ ኢትዮጵያ መጣን፡፡ ያኔ ከእነርሱም ጋር ሆነን ኢትዮጵያን እየዞርን ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አንስቶ ያሉትን የጤና ተቋማት ተመለከትን፡፡ የጤናውን ችግር በዚያ ኮንፈረንስ ምክንያት ስንገነዘብ ምን ማድረግ ይቻላል በማለት የሰዎች ችግር በሰዎች ነው የሚፈታው በሚል መርህ ነው ፒፕል ቱ ፒፕል የተቋቋመው፡፡

በወቅቱ ፋይዘር የተባለ የአሜሪካ የመድኃኒት አምራች ድርጅት ከ40 በላይ ለሆኑ አገሮች የኤችአይቪ መድኃኒቶችን በነፃ ለመስጠት ፕሮግራም ነበረው፡፡ እናም ኢትዮጵያ ይኼንን ያህል ጫና እያለባት ለምን አትረዳም ብለን በማግባባት በዝርዝሩ ውስጥ እንድትገባ ሆነ፡፡ ካስገቧት በኋላ ግን ያንን ምግብ ለመዋጥ ሲቸግር የሚወሰድ መድኃኒት በአገሪቱ በመድኃኒቶች ዝርዝር ውስጥ ስላልተመዘገበ ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት ዓመታት ፈጀ፡፡ ፒፕል ቱ ፒፕል በዚህ ረገድ ትልቅ ሚና ነው የተጫወተው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ወላጅ አልባ የሆኑ ልጆችን ሰብስበን ምሳ እናበላ ነበር፡፡ ይኼ ጊዜያዊ ነው ብለን ወደ ሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት ከደብረ ማርቆስ በ30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው አማኑኤል ከፈትንና ማስተማር ጀመርን፡፡ አሁን በርካቶች ከዩኒቨርሲቲ የተመረቁ አሉ፣ የሕክምና ትምህርትም የተከታተሉ አሉ፡፡

የፒፕል ቱ ፒፕል ዋናው ዓላማ ደግሞ ድልድይ መሆን ነው፡፡ አንድ አገር ለማደግ የሰው ኃይል፣ ጥራት ያለው ትምህርትና ጥሩ ጤና ያስፈልጋታል፡፡ በዓለም ላይ ያደገ አገር እነዚህ ሦስቱ ሳይኖሩት አይሆንም፡፡ የሚሠራ፣ የሚያማክርና መልካም የሥራ ሥነ ምግባር ያለው የሰው ኃይል ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ትምህርትና ጤናማ ዜጋ ያስፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያ ተወላጅ የሆኑ ጥሩ ትምህርትና የሥራ ልምድ ያላቸው ዳያስፖራዎች አሉ፡፡ አገራችን ደግሞ ያላት የሰው ኃይል በተለያዩ የፖለቲካ ምክንያቶች አገሩን ለቆ ሄዷል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቻችን ጠንካራ አይደሉም፣ አዳዲስም ናቸው፡፡ ስለዚህ ውጭ ያለውን የተማረና ልምድ ያለውን ሰው በአገር ውስጥ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ የእኛ መድረክ ይኼንን የማድረጊያ ድልድይ ነው፡፡ በዚያ ዓለም አቀፍ ድልድይ ውስጥ አንዱ መርሀችን የሦስትዮሽ ግንኙነት ነው፡፡ ከአሁን ቀደም የሁለትዮሽ ግንኙነት ነው የተለመደው፡፡ የእኛ የሦስትዮሽ አጋርነት ዳያስፖራውን፣ የምዕራቡ ተቋማትና የኢትዮጵያ ተቋማትን ያካትታል፡፡ ሦስቱ አብረው የሚሠሩ ከሆነ የአገር ውስጥ ተቋማትን አቅም ማጎልበት ይቻላል፣ በቀላል በጀትም ብዙ መሥራት ይቻላል በማለት ነው የተጀመረው፡፡ ይኼንን የሚያብራራ መጽሐፍም ጽፈን አሠራጭተናል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኒውሮሎጂ ትምህርት እንዲጀመር አድርገናል፡፡ ይኼንን ከተለያዩ የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎችና እንደ ዓለም ባንክና ናሽናል የጤና ተቋም (The National Institutes of Health (NIH)) ባሉ ተቋማት ድጋፍ ተደርጎ ነው የተመሠረተው፡፡ ይኼ የትምህርት ክፍል አሁን ከሌላ አገሮች ሠልጣኞች እየመጡ የሚሠለጥኑበት ሆኗል፡፡ ፒፕል ቱ ፒፕል ለጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሐኪሞች የድንገተኛ ሕክምና ሥልጠና እንዲያገኙ አድርጎ፣ ወደ ሆስፒታሉ የሚሄድ ማንኛውም የድንገተኛ ታማሚ ይኼንን ሥልጠና ባገኙ ሐኪሞች ነው የሚታከመው፡፡ በተመሳሳይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ግቢ ከሺጎ ዩኒቨርሲቲ በሄደች አንዲት ፕሮፌሰር ነው ፈንድ ተገኝቶ የተጀመረው፣ አሁን የማስተርስና የሦስተኛ ዲግሪ ፕሮግራም እየሰጠ ነው የሚገኘው፡፡ ይኼ ትስስር ከበርካታ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር አብሮ ወደ መሥራት አድጓል፡፡ በዚህ ሳቢያ የኢትዮጵያን የጤና ታሪክ መጽሐፍ አዘጋጅተን አበርክተናል፡፡ በተለይ በኮቪድ ጊዜ ደግሞ የተለያዩ የአፍሪካ አገሮችን ጨምሮ የማስተማሪያ የድረ ገጽ ስብሰባዎችን አድርገናል፡፡ የኢትዮጵያ ደግሞ በየሳምንቱ ሐሙስ ሐሙስ በአሜሪካ ከኢትዮጵያ አምባሳደር ጋር ኮቪድ ካውንስል የሚል ከ15 እስከ 20 አባላት ያሉት ኮሚቴ አቋቁመን ስብሰባ እናደርጋለን፡፡ ይኼንን ካውንስል እኔ ነኝ የምመራውና ከፒፕል ቱ ፒፕል ጋር በመተባበር በርካታ የሥልጠና ስብሰባዎችን አካሂደናል፡፡ አንዱ ትልቁ ነገር አብሮ መሥራት ነው፡፡ መጀመሪያ ላይ የዓለም የጤና ድርጅት የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ መጠቀምን ያልመከረ ቢሆንም፣ እኛ ሕዝቡ በጋቢም ቢሆን አፉን ይሸፍን ብለን ታግለን ነበር፡፡ ለዚህ ደግሞ በርካታ ሥልጠናዎችን ሰጥተናል፡፡

ሪፖርተር፡- የኮቪድን ጉዳይ ካነሱ ላይቀር በፒፕል ቱ ፒፕል፣ በተለያዩ ተቋማትና ባለሙያዎች ለኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ተከታታይ የግንዛቤ መፍጠሪያና ማሳወቂያ መርሐ ግብሮች ተቀርፀው ሲሠሩባቸው ዓይተናል፡፡ ይሁንና እነዚህን ድጋፎች ያገኘውና ዕገዛ የተደረገለት መንግሥት ቫይረሱን በሚጠበቀው ደረጃ መከላከል ችሏል ማለት ይቻላል?

ዶ/ር እናውጋውቫይረሱ ለሁሉም ሰው አዲስ ነበረ፡፡ የዓለም የጤና ድርጅት ሳይቀር ከቆይታ በኋላ ነው የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ እንዲደረግ ያሳወቀው፡፡ ምክንያቱም ቫይረሱ አይታወቅም፡፡ መጀመሪያ የነበረው አንዱ ወቀሳ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቻይና ከሚያደርገው በረራ ጋር በተያያዘ ነበር፡፡ ትክክል አይደለም የሚሉ ተከራካሪዎች ነበሩ፡፡ ሙሉ ለሙሉ አገራዊ ውሸባም (Quarantine) እንዲኖር ሲጠየቅ ነበር፡፡ በዚህ ግን የነበረው ክርክር ኢኮኖሚው ቢዘጋ ሀብታም አገሮች በርካታ ነገሮችን መቋቋም ይችላሉ፣ ሠራተኛውም የሚኖርበት ቤት ለውሸባ ምቹ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በአንዲት ጠባብ ቤት ውስጥ በርካታ ሰዎች ስለሚኖሩ ከእውነታው ስንነሳ ለውሸባ አይመችም፡፡ ስዚህም አንዳንድ ሰዎች በኮቪድም ባይሆን ሰው በረሃብ ይሞታል ማለት ጀመሩ፡፡ ስለዚህም በመጀመሪያው ስድስት ወራት በነጋሪት ጋዜጣ ላይ አዋጅ ወጥቶ ክልከላ ሲጣል ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ ተጀምሮ ነበር፡፡ ሰው መንገድ ያጥብ ሁሉ ጀምሮ ነበር፡፡ የታሰበውም ይኼ ቫይረስ መጥቶ ጠራርጎን ሊሄድ ነው የሚል ፍራቻ ነበር፡፡ እና በስድስት ወራት ውስጥ የታሰበውን ያህል ብዙ ችግር አልፈጠረም፡፡ ከአሁን ቀደም በነበሩ ልምዶች ደግሞ መጥፎ ነገሮች በታዳጊ አገሮች ተከስተው ላደጉ አገሮች ሥጋት ሊሆኑ ይችላሉ እንጂ፣ ያደጉ አገሮች ጋር ተከስቶ አይደለም ወደ እኛ የሚመጣው፡፡ በኮቪድ ግን መጥፎው ነገር ባደጉ አገሮች ነው የተከሰተው፡፡ ያንን በማየት ኢትዮጵያ ትጎዳለች ሲባል ለመጀመሪያው ስድስት ወራት ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደረገ ግን በተፈራው ልክ አልተከሰተም፡፡ መንግሥት እንዲያውም ከስድስት ወራት በኋላ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲገባደድ አላደሰውም፣ ቀለል አድርገው ነው የሄዱት፡፡

ከዚያ የመጀመሪያው ደግሞ የካቢኔ አጀንዳ ሆኖ ነበር የሚታየው፡፡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነበሩ ኮሚቴውን የሚሰበስቡት፡፡ ነገር ግን ከስድስት ወራት በኋላ መዘናጋት ተፈጠረ፡፡ በዚህ ላይ ሌላ ስድስት ወራት ሲጨመር ቁጥጥሮች እየላሉ ሄዱ፡፡ ነገር ግን እንደ እኛ አስተያየት የማስተባበር ሥራው ተመልሶ ወደ ማዕከል መምጣት አለበት የሚል ጩኸት አሰማንና በድጋሚ እንደቀደመው ለማድረግ እንቅስቃሴዎች ተጀመሩ፡፡ አፍሪካ ውስጥ ቫይረሱ በሌሎች በአሜሪካ፣ እንዲሁም በአውሮፓና በእስያ አገሮች ያስከተለውን ያህል ጉዳት አላስከተለም፡፡ ያስከተለው የሞት መጠንም አይመጣጠንም፡፡ እንደተፈራው ሆኖ ባይገኝም ግን ብዙ የተጎዳ ሰው አለ፡፡ ኢትዮጵያ ያደረገችው ትልቁ ጥረት በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ ብቻ ነበር፡፡ ይኼ ጥረት ደግሞ የሕዝብም ድጋፍ ታክሎበት ነው፡፡ ሰው ችግሩን ተገንዝቦ ጥንቃቄ አድርጓል፡፡ ከዚያ በኋላ ግን በሚገባው ደረጃ ትኩረት የተሰጠው አልመሰለኝም፡፡ ግን በተለያዩ ጊዜያት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ ከትራንስፖርት ሚኒስቴር፣ ወዘተ ተቋማት ጋር በትብብር አንሠራለን፡፡

ነገር ግን በተለይ አሁን ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ አስቸጋሪ የሚያደርገው ነገር ካለው አገራዊ እንቅስቃሴ ጋር ይገናኛል፡፡ አሁን የብሔራዊ ደኅንነት ጉዳይ ሆኖ ጦርነቱ ወታደር መመልመልን ያካትታል፡፡ ታዲያ ያንን እንዴት አድርጎ ነው መቆጣጠር የሚቻለው? ከባድ ነው፡፡ የሰው የኑሮ ሁኔታና ለጥንቃቄ የሚታዘዙ ዕርምጃዎች ይለያያሉ፡፡ ለምሳሌ በአንድ ቤት ውስጥ ስንት ሰው ቢኖር እጅ ታጠቡ ሊባል ይችላል? ግን አካላዊ ርቀታችሁን በሁለት ሜትር ጠብቁ ቢባል አይቻልም፡፡ አንድን ሰው ደግሞ በቤትህ ተወሸብ ብትለው ሰው በየቀኑ እየሠራ ነው የሚያገኘውና እንዴት አድርጎ ሊያከብረው ይችላል? በእርግጥ አንዳንድ ኃላፊነት ላይ ያሉ ሰዎች ደግሞ ምሳሌ መሆን ሲችሉ፣ ሁልጊዜ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብልና ትንንሹን ነገር ማድረግ እየቻሉ የማያደርጉ ይታያሉ፡፡ አንዳንዴ ሕዝባዊ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ተብሎ አታድርጉ እየተባለ፣ ጤና ጥበቃ ሳይቀር እያገደ ይደረጋሉ፡፡ ከላይ ያለው ልልነት አንዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ እነሱም እንደ ኢኮኖሚ ያለ በርካታ ጫናና መሰል ጉዳዮች ያሳስቧቸው ይሆናል፣ ክልከላዎቹ ምን ያህል ሊያዛቡ እንደሚችሉ ስለሚያውቁ፡፡

ሪፖርተር፡- ሌላው ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር የተያያዘው ደግሞ የክትባት ጉዳይ ነው፡፡ በተለይም ያደጉት አገሮች ቅድሚያ ለራሳችን ብለው ክትባት ማግኘት ለታዳጊ አገሮች አስቸጋሪ ሆኖ ነበር፡፡ ቫይረሱን በመከላከል ረገድ የዚህ ተፅዕኖስ ምን ያህል ነው ማለት እንችላለን?

ዶ/ር እናውጋው፡- የክትባት ችግር በቫይረሱ ከመጠቃት ባለፈ ሥነ ልቡናዊ ጫናም ይኖረዋል፡፡ አንድ ሰው መድኃኒት ሳይኖር ብታመም እኮ አለቀልኝ ብሎ ማሰብ ራሱን የቻለ ጭንቀት ይፈጥራል እኮ፡፡ እንዲያውም ውጭ ያለው ሁሉም ሰው ክትባት እወስዳለሁ ቢል ኖሮ ታዳጊ አገሮች ምንም አያገኙም ነበረ፡፡ አሜሪካውያን ሁሉም እፈልጋለሁ ቢሉ ለአፍሪካ ብለው ሌላ ይሠሩ ነበር ወይስ ምን ያደርጋሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ እንወስዳለን ብለው ካልተጠቀሙበት ጊዜው ሊያልፍ ይችላል፡፡ ግን አገሮች ይኼንን ያደረጉት እንደ ኤችአይቪ/ኤድስ ነው፡፡ ያኔ እንደ ብራዚልና ህንድ ያሉ አገሮች ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት አሳይተው እንቢ ብለው ማምረት ጀመሩ፡፡ አሁን እንዲያውም የኢትዮጵያ የክትባት ኢንስቲትዩት ለማቋቋም አንድ እንቅስቃሴ አለ፡፡ እና እንዴት ነው አፍሪካውያን ተሰባስበው ይኼንን ሊያሳኩ የሚችሉት? ኩባ ክትባት አምርታ ለአንድ አገር ልካለች፡፡ የዚህ ባለሙያ የሆኑ ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡ እና ለዚህ የሚሆን ገንዘብ ቢኖር እንደ ሞደርናና ፋይዘር መሰሉ ባይሆንም ማምረት ይቻላል፡፡ ዕውቀቱ አለ፡፡ ክትባቶቹ ብዙ ዓይነት ናቸው፡፡ የምዕራቡ ዓለም የሚሠራው ሜሴንጀር አርኤንኤ የሚባል ቴክኖሎጂ የሚቆምና ከአሁን ቀደም ተሠርቶ የማይታወቅ ክትባት ነው፡፡ ለዚያች ለቫይረሷ ብቻ ነው እንጂ ሌላ የሰውነት አካልን ስለማይነካ ከሌሎቹ በተለየም ደኅንነቱ የተጠበቀ ነው፡፡ ሌሎቹ ግን ሰውነት ለቫይረሱ የሚሆን አንቲቦዲ ስለሆነ የሚያመጣው የጎንዮሽ ጉዳት ይኖራል፡፡ ስለዚህ ያን መሰል እንኳን ባይሆን ክትባት መሥራት ይቻላል፡፡ አሁን በርካታ አገሮች እየጀመሩ ነው፡፡ ግብፅም፣ ደቡብ አፍሪካም ሌሎችም፡፡ ኢትዮጵያም ማሰብ ይኖርባታል፡፡

የምዕራቡ አገር እንደፈለገው ሲከተብ ኢትዮጵያ ከ100 ሚሊዮን ሕዝብ መካከል ሁለት ሚሊዮን ብቻ ሲከተብ እጅግ አናሳ ነው፡፡ አለበለዚያ ግን ኢትዮጵያም እንደ ስንዴ ለማኝ ሆና ነው የምትኖረው፡፡ እየለመኑ ደግሞ ብሔራዊ ኩራት የሚባል አይኖርም፡፡ ሁለቱ አብረው አይሄዱምና ትውልዱ ያንንም ችግር የሚፈታበትን መንገድ መቀየስ ይኖርበታል፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ ግን ፍትሐዊ ነው ለማለት አያስችልም፡፡ ለአብነት የሕፃናት ወታደሮች በእንግሊዝ አልያም በሌላ የምዕራቡ ዓለም ቢታዩ ሚዲያው በጠቅላላ እዚያ ላይ ብቻ ነው ትኩረት የሚያደርገው፣ ትልቅ ጉዳይም ያደርገው ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ሲሆን ግን በአግባቡ እንኳን ሽፋን አያገኝም፡፡ አሜሪካኖች መጀመሪያ ላይ ምንም ዓይነት ክትባት ወደ ሌላ አገር እንዳይላክ ነው ያሉት፡፡ በእርግጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በኮቪድ ሀብታሙም ደሃውም አትንቀሳቀስ አርፈህ ቁጭ በል የተባለበት ነው፡፡ ከዚህ በፊት ያለው ሰው ለሕክምናና ለምርመራ ወደ ውጭ አገር ይሄዳል፡፡ አሁን የተገነዘብነው ነገር ግን ጤና የብሔራዊ ደኅንነት ጉዳይ መሆኑን ነው፡፡ የራስህን ደኅንነት መፈለግ መቻል አለብህ፡፡ ለዚህ ደግሞ ክትባቱንም ራሳችን የምናመርትበትን መንገድ መፈለግ የግድ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ዳያስፖራው በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ለመንግሥት ምክር የሚለግሱና ዕውቀት የሚያካፍሉ ማኅበራት ያሉት ሲሆን፣ በተለያዩ ዘርፎች የቴክኒክና የማማከር አገልግቶችን ለመንግሥት ይሰጣል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ምክሮችና ዕገዛዎች ምን ያህል የፖሊሲ ውሳኔዎች አካል ሲሆኑ ይታያሉ? ነው ወይስ በከንቱ የሚፈስ ዕውቀትና ጊዜ ነው እየባከነ ያለው?

ዶ/ር እናውጋው፡- ምናልባት በዳያስፖራው መካከልና በኢትዮጵያ ወገን ካሉት ጋር መተማመንና አንዱ ለአንዱ ክብር ያለው መሆን አስፈላጊ ናቸው፡፡ ከዳያስፖራው በኩል በኢትዮጵያ ያለውን ነባራዊ ችግር ከባህሉ ጋር አስተሳስሮ መገንዘብ አስፈላጊ ነው፡፡ ዝም ብሎ በጽንሰ ሐሳብ የሚታወቀውን ከነባራዊው ሁኔታና ከአካሄዱ ጋር የማይጣጣም ከሆነ አስቸጋሪ ነው፡፡ ያንን ማወቅ ብቻ ሳይሆን መልካም የሥራ ግንኙነት ካለ የሚመጡ ሐሳቦችን የመቀበል ዕድሉ ከፍተኛ ነው የሚሆነው፡፡ ግን እኔ የበለጠ አውቃለሁ የሚል አስተሳሰብ ካለና በቃል ባይገለጽም፣ እርስ በርስ መከባበርና መደማመጥ ከሌለ ያስቸግራል፡፡ እኔ እበልጣለሁ በሚል መደማመጥ ከጠፋ ሁሉም ነገር ይበላሻል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ብዙ ጊዜ የውይይት መድረኮችና ሌሎች ሥፍራዎች የሚታየው መደማመጥ ማጣት ነው፡፡ መንግሥትና ዳያስፖራ ሲባል ሰው ከላይ ያለ ነገር አድርጎ ቢጠብቅም፣ ዋናው የግለሰቦች ግንኙነት ነው፡፡ እኔ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርን አማክራለሁ፡፡ ወደ ዘጠኝ የሚሆኑ እያንዳንዳቸው የየራሳቸው ሰብሳቢ ያላቸው ኮሚቴዎች አሉ፡፡ እኔ የፋኩልቲና የስታፍ ዴቨሎፕመንት ኮሚቴን እመራለሁ፡፡ እንዲሁ ሌሎችም አሉ፡፡ ይኼንን ሰብስቦ ደግሞ የሚያስተባብር ሰው አለ፡፡ በግለሰብ ደረጃ ጥሪ ግንኙነትና መተሳሰብ ሲኖር እኛ የምንጠይቃቸውን እነርሱም የሚይቁንን በጋራ ማድረግ እንችላለን፡፡ እኛ ስንጋብዛቸው ይመጣሉ፣ እነሱም ሥራ ሲሰጡን እናግዛቸዋለን፡፡ ስለዚህ የዚህ ዓይነት መልካም ግንኙነት አለ፡፡ ሌላው ደግሞ የኢኮኖሚ ኮሚቴ ተብሎ የተቋቋመ ቢሆንም፣ የቡድን ሥራው በሚጠበቀው ደረጃ የተሳለጠ አልመሰለኝም፡፡ ለዚህም ሰዎች ከኮሚቴው ሊወጡ ችለዋል፡፡ መንግሥት ደግሞ ዳያስፖራው ሲተባበርና ሲቀናጅ ካላየ መተማመን አያሳድርም፡፡ እርስ በርስም መግባባት ያስፈልጋል፡፡ አሁን ደግሞ ፌስቡክና ትዊተር ባለበት ዓለም እንዴት አድርገን ነው የሚፈሰውን መረጃ የምንቆጣጠረው ብሎ ማሰብም ያስፈልጋል፡፡ ግን መንግሥት ደግሞ ይበልጥ የሚሰማው ሲቸግረው ነው፡፡ በሌላ ጊዜ ችግሩ ይኼንን ያህል ካልመሰለው አያዳምጥም፡፡ ለዚህ አንድ ጥሩ ምሳሌ ልንገርህ፡፡ መንግሥት መጀመሪያ ምዕራባውያን አገሮችን ለማሳመን (ሎቢ ለማድረግ) የሚሠራ ድርጅት ቀድሞ መቅጠር ያልፈለገው ለምን ነበር? ይቀጠር እያልን ስንጠይቅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው ወጥተው ይኼንን ያህል ገንዘብ ካለኝ ዳቦ አላበላበትም ብለዋል፡፡ በሌላ ጊዜ ደግሞ ዓይተው ዓይተው እርሳቸውም አምነው አሁን ሎቢ ተቀጠረ ተብሏል፡፡ አሃ ተባለ ማለት ነው፡፡

ከዚያ አስቀድሞ ደግሞ ለምንድነው ቋሚ የሆነ መግለጫ ተሰጥቶ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡን ስለወቅታዊ ሁኔታዎች ማስረዳት ያልተቻለው ተብሎ ሲጠየቅ፣ እንደ ኋይት ሀውስ ፕሬስ ሴክሬታሪ ክፍል በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ሥር ያለው ክፍል የማይሠራው ሲባል ዝም ብለው ቆይተው ዘግይተው ጀመሩ፡፡ መንግሥት ጦርነቱን በመሬት አሸንፎ በዲፕሎማሲው ግን ተሸንፏልና ለምን ይኼ ይሆናል ብሎ ሕዝቡ ሲጮህ ነበር፡፡ ሁላችንም ጮኸናል፡፡ በመጨረሻም ሰሙ፡፡ ጊዜ ይወስዳሉ፣ ወዲያው እንደሚፈለገው አይደለም፣ እና ደግሞ ከባዱ ነገር ያለው ዝም ብሎ ግትር መሆን ሳይሆን በርካታ ነገር የማስተባበር ሥራ ነው፡፡ ለማስተባበሩ ሥራ ነው ደግሞ ጥሩ ጥሩ ትምህርትና የሰው ኃይል የሚያስፈልገው፡፡ በህዳሴ ግድቡ ላይም ተመሳሳይ ችግር አለ፡፡ የግብፅ ኤምባሲ ድረ ገጽ ጋ ብትሄድ መጀመሪያ የምታገኘው ስለዓባይ ነው፣ የእኛ አምባሳደሮች ግን አያደርጉም ነበር፡፡ ታዲያ ይኼ ነገር ለምንድነው ተብሎ ሲጠየቅ ተቋማዊ ትውስታ አለመኖሩ ነው በአገሪቱ፡፡ ስለዚህም ለማስተባበር ከባድ ነው፡፡ እኔ ከ20 ዓመት በላይ በሆነው ፒፕል ቱ ፒፕል የተማርኩት ነገር ቢኖር፣ አንድ ቦታ ሄጄ እኔ አዋቂ ነኝ አልልም፣ ሌላውም እኔ ጋ መጥቶ እንደዚያ ማለት የለበትም የሚለውን ነው፡፡ በዚያ አካባቢ ያሉ ሰዎች ናቸው አዋቂዎቹ፡፡ እዚያ የሚኖሩ ሰዎች መውጫ መግቢያውን ሁሉ ያውቃሉና ከእነሱ ጋር መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ይኼ ደግሞ የመንገድ፣ የትራንስፖርትና መሰል ችግሮች እንዳሉ ሁሉ ይኼም የዚያ ችግር አንዱ ነው፡፡ አብሮ የመሥራት ችግር አለና ይኼንን ከሌሎች ችግሮች ነጥሎ ማየት ከባድ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ የሚሰጡ ምክረ ሐሳቦች የፖሊሲ ተፅዕኖ እንዳያደርጉ እያደረጋቸው ያለው ከሁለቱም ወገን ያለው ክፍተት ነው ማለት ነው?

ዶ/ር እናውጋው፡- በትክክል፡፡ ለምሳሌ ጦርነቱን በተመለከተ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የሚሰጠው መረጃ ከስድስት ወራት በኋላ ሳይሆን ከመጀመሪያው ቀን አንስቶ መሆን ያልቻለው ለምንድነው? ለምንድነው ጦርነቱን መንግሥት መሬት ላይ አሸንፎ በዲፕሎማሲው የተሸነፈው? በእርግጥ በዚያኛው ወገን ያሉት ብዙ ገንዘብ አላቸው፣ ወትዋች (ሎቢ) አላቸው፡፡ በመጨረሻም መንግሥት ወትዋች ቀጠረ፡፡ ከቆይታ በኋላ ነው፡፡ ለምንድነው ዳያስፖራውስ ይኼንን ተገንዝቦ ከመጀመሪያው ያልቀጠረው? ግን  ይኼ አንዱ ድካም ነው፡፡ መንግሥትስ ለምን ይሆን ለዚህ ክፍተት ዕውቅና መስጠት ያልቻለው? ለምንስ ነው በርካታ መረጃዎች እጁ ላይ ሳሉ አደባባይ አውጥቶ እንዲታወቅና ውይይት እንዲደረግባቸው ያላደረገው የሚለው ትልቅ ጥያቄ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ዳያስፖራው በእርግጥ በተበታተነ መንገድ ይወተውታል፡፡ ከተለያዩ የአሜሪካ አስተዳደር ሰዎች ጋርና ከሕዝብ ተወካዮች ጋርም ይነጋገራሉ፡፡ ይኼ ውጤት ሊያመጣ ያልቻለው መንግሥት ተገቢውን ትኩረት ስላልሰጠው ነው ማለት ነው? በዚህስ ሳቢያ አላስፈላጊ ጫናዎች በኢትዮጵያ ላይ እየደረሱ ነው ብለው ያስባሉ?

ዶ/ር እናውጋው፡- ይመስለኛል፡፡ ዝም ማለትን የምዕራቡ ዓለም እንደ ድክመት የሚወስደው ይመስለኛል፡፡ ብዙን ጊዜ አገሮች ኮስተር ያለ አቋማቸውን ሲያሰሙ ያላቸው አረዳድ ይለወጣል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ እነ ሳማንታ ፓወር ሲመጡ አግኝተው አለማወያየታቸውን ብዙዎች የሚደግፉ ይመስለኛል፡፡ እነዚህ ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ንቀውና አናንቀው ነበር የመጡት፡፡ እነሱን ሳያስተናግዱ የደቡብ ሱዳንን መሪ በትልቅ ዝግጅት ማስተናገዱ መልዕክት መስደድ ነው ለእነዚህ አካላት፡፡ አሜሪካኖች ወደ ተለያዩ አገሮች ሲገቡ ከ13 በላይ አገሮችን ይጋብዛሉ እኮ፡፡ ኢትዮጵያም የምትፈልገውን አገር መጋበዝ ትችላለች፡፡ እንዲህ ዓይነት አቋም መውሰዱና አለመለማመጥ በጣም ያዋጣል፡፡ አለበለዚያ እንዳይከፋቸው ሲባል እነዚህ አገሮች የማያውቁት ነገር ስለሌለ እንደ ሽንኩርት እየላጡ እስር ድረስ ይገባሉ፡፡ ስለዚህ ዝም ሲባልና ሳይነገር ሲቀር እንደ ድክመት ይቆጥሩታል፡፡

ለምሳሌ ከ400 በላይ ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ ተልከው አልተመለሱም፡፡ ነገር ግን በአማራና በአፋር ክልሎች የሰብዓዊ ድጋፍ ይደረግ ሲባል ደኅንነቱ አያስተማምንም ይላሉ፡፡ ይኼ ሚዛናነት የጎደለው አሠራር ነው፡፡ ይኼንን ደግሞ ከመጀመሪያው ጀምሮ ደጋግሞ መናገርና ማጋለጥ አስፈላጊ ነው፡፡ በአጠቃላይ ግን በመርህ ጠንከር ብሎ መቆም ያስፈልጋል፡፡ በመለሳለስ የተጠቀመ አገር የለም፡፡ ዝምታው ጉዳት አስከትሏል፡፡ ዳያስፖራውም ውይይት ሲያደርግ ስትራቴጂ አልነበረውም፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይሆንና መልዕክቱ ማንም ጋር ሳይደርስ ይቀራል፡፡ ወትዋች ድርጅትንም አስቀድሞ መቅጠር ይቻል ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ካነሱልኝ ጉዳዮች በመነሳት በመንግሥት ረገድ ይኼንን ዓለም አቀፍ የተለዋዋጭ ፍላጎቶች ሁኔታ መረዳት አለ ብለው ያስባሉ? በተጨማሪም አሁን እየታየ ካለው ተፅዕኖ አንፃር ለወደፊት ምን ዓይነት ሁኔታዎች ሊፈጥሩ ይችላሉ?

ዶ/ር እናውጋው፡- ይኼንን ኢትዮጵያ ላይ ያለው ዋናው ችግር የኢትዮጵያና የሕወሓት ችግር አድርጌ ሳይሆን የምወስደው፣ የምሥራቅ አፍሪካ ስትራቴጂካዊ ሥፍራ ፍትጊያ ነው፡፡ የምሥራቅ አፍሪካ የህንድ ውቅያኖስን ይዞ የዓለም 40 በመቶ ንግድ የሚተላለፈው በዚያ አካባቢ ስለሆነ የአሜሪካን ብቻ ሳይሆን፣ የበርካታ አገሮችን ፍላጎት የሚነካ ነው፡፡ ይኼ አካባቢ የደም ቧንቧ ነውና መዘጋቱ ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ቀውስ ያስከትላል፡፡ እነሱ በሚፈልጉት መንገድ እንዲሄድ ነው የሚፈልጉት፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ተነስታ ሶማሊያን ከህንድ ውቅያኖስ ዓሳ ለኢትዮጵያ ገበያ እንድታቀርብ፣ ኤርትራ ወደቧን ለኢትዮጵያ ብታስጠቅም፣ ኢትዮጵያ ደግሞ ውኃ ብታቀርብላቸውና ቢተባበሩ ስለሚያድጉ ምዕራቡ ዓለም አይፈልገውም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከእናንተ በፊት መንግሥት ነበረንና ተከባብረን እንኑር ሲሉ የምዕራቡ አገሮች አይፈልጉም፡፡ ስለዚህ ያንን እነርሱ የሚሉትን ሊሰማ የሚችል ሌላ አካል ካለ ይደግፋሉ፡፡ ይኼ ደግሞ የአሜሪካን ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ፍላጎት ስለሚነካ ይኼንን መሰል አረዳድ አይፈልጉትም፡፡ የግብፅ የዓባይ ግድብ ጥቅም ጥያቄ የሚታወቅ ሲሆን፣ ሌላው የሚፎካከሩበት የቻይና ፍላጎት ደግሞ አለ፡፡ በዚህ ምክንያት በኢትዮጵያ ላይ ጫና ያደርጋሉ፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ጠቃሚ መሆኗን የሚያሳዩ ጉዳዮች አሉባቸው፡፡ አሜሪካ ኢትዮጵያ የብሔራዊ ደኅንነት ሥጋታችን ናት ስትል ገልጻለች፡፡ ነገር ግን ዕውን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ነው? ወይስ ኢትዮጵያ ናት ለአሜሪካ የብሔራዊ ደኅንነት ሥጋት የሆነው? ምክንያቱም አልሸባብን የምትዋጋ ኢትዮጵያ ናት፡፡ አልሸባብ ደግሞ የአሜሪካን ብሔራዊ ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል ነው፡፡ ሁለቱ ታዲያ እንዲት ነው የሚጣጣሙት? አንዱን መምረጥ ያስፈልጋል፡፡ አልሸባብን ከተዋጋች የአሜሪካን የብሔራዊ ደኅንነት የምትደግፍ ናት ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የእነሱ ፖሊሲ ነው ወይስ ኢትዮጵያ ናት የብሔራዊ ደኅንነታቸው ጠንቅ የሆችው? እና ኢትዮጵያ ሠራዊቴን አወጣለሁ፣ እኔ ላይ አደጋ አድርሰውብኝ ሳይሆን ከአሜሪካ ጋር ስለተባበርኩ ነው ብትል ምን ይፈጠራል? ኢትዮጵያ አሁንም ጠንክራ ከቆመች ሁሉም ነገር መረጋጋቱ አይቀርም፡፡ ምክንያቱም አለመረጋጋቱ የሚያመጣው ጣጣ የበለጠ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ፈራርሳ እንድትወድቅ የሚፈልጉት ክስተት አይደለም፣ ለእነርሱም አይጠቅማቸውም፡፡ እርግጥ አቅም ካለ መልካም የሚሆነው በአገራችን ያለውን ግጭት ማሸነፍ ሁሉንም ነገር ለመግራት ይረዳል፡፡ አንድ ሰው ካሸነፈ በዚህ ነው የምደራደረው ይላል፡፡ ግን ኢትዮጵያም አቅም ከሌላት ግጭቱ ወደማይፈለግ መራዘምና የኢኮኖሚ ውድቀት፣ እንዲሁም ያልተጠበቁ ችግሮችን ማስከተሉ አይቀርም፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹መንግሥት ለአገር ውስጥ የኅትመት ኢንዱስትሪ ገበያ ከመፍጠር ጀምሮ ሥራ የመስጠት ኃላፊነት አለበት›› አቶ ዘውዱ ጥላሁን፣ የኢትዮጵያ አሳታሚዎችና አታሚዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ

የኅትመት መሣሪያ በጉተምበርግ ከተፈበረከ ከ400 ዓመታት በኋላ በኢትዮጵያ በ1863 ዓ.ም. በምፅዋ የተጀመረው የኅትመት ኢንዱስትሪ ከአፍሪካ ቀዳሚ ቢሆንም፣ ዕድገቱ ውስን መሆኑ ይነገራል፡፡ ከኢትዮጵያ በኋላ የኅትመት...

‹‹ከጨረታ በስተጀርባ ያሉ ድርድሮችን ለማስቀረት ጥረት እያደረግን ነው›› ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር)፣ የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ (የቀድሞ ሜቴክ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር) በተባበሩት ዓረብ ኤሜሬትስ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ፣ ከጥር 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የቦርድ...

‹‹ባለፉት 25 ዓመታት ባለን አቅም ሁሉ የተለያዩ አጀንዳዎችን ለመዳሰስ ሞክረናል›› የራስወርቅ አድማሴ (ዶ/ር)፣ የፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

‹‹ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ›› በመባል የሚታወቀውን በኢትዮጵያ ታሪክ ከመንግሥትም ሆነ ከሌላ አካል ገለልተኛ ሆኖ የተቋቋመ ሐሳብ አመንጪ የጥናት ተቋም (ቲንክ ታንክ) ከመሠረቱት አንዱ መሆናቸውን...