Sunday, February 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበአማራ ክልል የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑ ተነገረ

በአማራ ክልል የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑ ተነገረ

ቀን:

በአማራ ክልል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት በተፈረጀው በሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ታጣቂዎች ወረራ ምክንያት፣ የተፈናቃዮች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የአማራ ክልል አስታወቀ፡፡

በክልሉ የሕወሓት ታጣቂዎች በተቆጣጠሯቸው የሰሜን ወሎ፣ የሰሜን ጎንደር ዋግ ህምራና የደቡብ ጎንደር አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር 800 ሺሕ መጠጋቱን የአማራ ክልል አደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትናና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ኢያሱ መስፍን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ኃላፊው በክልሉ እየተካሄደ ባለው የሕግ ማስከበር ዘመቻ የተፈናቃዮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን፣ በቀጣይም መንግሥት እያካሄደ ካለው ዘመቻ ጋር ተያይዞ ቁጥሩ ሊያሻቅብ እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

በአማራ ክልል ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ በግጭትና መሰል ምክንያቶች የተፈናቃዮች ቁጥር ከ1.7 ሚሊዮን በላይ መድረሱን የተናገሩት አቶ ኢያሱ፣ በሕግ ማስከበር ዘመቻው ከቀያቸው ለተፈናቀሉት ዜጎች በዋግ እብናት፣ በደሴ ከተማና በሰሜን ጎንደር በደባርቅ ከተማ በጊዜያዊ መጠለያዎች ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

ይሁን እንጂ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ዕርዳታ ለማቅረብ በአገር ውስጥ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ በአማራ ክልል እያደረጉት ያለው ድጋፍ እዚህ ግባ የማይባልና አለ ለማለት የማያስደፍር እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

‹‹ለዓለም አቀፍ ተቋማት በተደጋጋሚ ጩኸት ብናሰማም የዕርዳታ ድርጅቶቹ የሚያደርጉት ድጋፍ እስካሁን ውጤታማ ሆኖ አላየንም፤›› ሲሉ አቶ ኢያሱ አስረድተዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥትና የክልሉ መንግሥት ለተፈናቃዮች በማስተባበርያ ማዕከላት ድጋፎችን እያቀረቡ እንደሆነ የገለጹት ኃላፊው፣ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች በትግራይ ክልል ያሳዩትን ርብርብ በአማራ ክልል ማሳየት እንዳልቻሉ  ጠቁመዋል፡፡

የዓለም የምግብ ድርጅት ከሰሞኑ በአፋር በኩል አድርጎ ድጋፉን ወደ አማራ ክልል ለማስገባት ጥረት ቢያደርግም፣ የተጨበጠ ውጤት አለማየታቸውን አክለው ተናግረዋል፡፡

የተፈናቃዮች ቁጥር እየጨመረ በመሆኑ በአገር ውስጥ የሚደረገው ድጋፍ ወጥነት ስለሌለው፣ ያለ ማስተባበሪያ ማዕከላት ዕውቅና እየተደረገ ያለው አሠራር ጩኸት እየተሰማበትና የፍትሐዊነት ጥያቄ እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ባለሀብቶች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ግለሰቦች ለተፈናቃዮች ድጋፍ ለማቅረብ ሲፈልጉ በሕጋዊ ደረሰኝ አስመዝግበው እንዲያስረክቡና ድጋፍ ለሚያሻቸው ዜጎች በሥርዓቱ እንዲደርስ ዕገዛ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

በሰሜን ወሎ፣ በዋግ ህምራና በጎንደር የተለያዩ አካባቢዎች በምግብና በመድኃኒት ዕጦት በርከታ ዜጎች እየተሰቃዩ እንደሆነ የገለጹት ኃላፊው፣ ጉዳዩ የህልውና በመሆኑ ሁሉም አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ምሥረታ ዝግጅቶችና ከገበያው የሚጠበቁ ዕድሎች

ኢትዮጵያ ከ50 ዓመት በኋላ ዳግም የምታስጀምረውን የካፒታል ገበያ ዘመኑን...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...

መንግሥት የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ድንበር ጥሰው የሚያደርሱትን ጥቃት እንዲያስቆም ተጠየቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ...