ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) አቶ እስከንድር ነጋንና ሌሎች የፓርቲው አመራሮችን ከእስር የማስፈታት ግፊት እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)ን ጨምሮ፣ ለ15 አገሮች ኤምባሲዎች ጥሪ አቀረበ፡፡
የባልደራስ ፓርቲ የሕግ ጉዳዮች ኃላፊና የእነ አቶ አስክንድር ነጋ ጠበቃ አቶ ሔኖክ አክሊሉ ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ ለ15 አገሮች ኤምባሲዎች፣ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ደብዳቤ አስገብተዋል፡፡ በቀጣይ ደግሞ መንግሥታዊ ላልሆነው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) ደብዳቤ ለማስገባት እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
ፓርቲው በመግለጫው እንዳስታወቀው መንግሥት በአትዮጵያ ውስጥ ያለውን የፍትሕ ሁኔታ ለማስተካከል ሚና ይጫወታል ብሎ ቢጠብቅም፣ ምንም ማድረግ አልቻለም ብሏል፡፡ ለአብነት ያህልም የፓርቲው አመራር በሆኑት አቶ እስከንድር ነጋ፣ አቶ ስንታየሁ ቸኮል፣ ወ/ሮ አስቴር ሥዩምና ወ/ሮ አስካለ ደምሌ ላይ የተደረገው ሕግን የተላለፈ እስር አንዱ ጉዳይ እንደሆነ አስታውቋል፡፡
ፓርቲው ለ15 አገሮች ኤምባሲዎችና ለኢሰመኮ ያቀረበው ጥሪ ዋነኛ ይዘት፣ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ አመራር የሆኑት አቶ እስክንድር ነጋ ለረዥም ጊዜ ፍትሕ ሳያገኙ ስለመቆየታቸው መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሔኖክ፣ ይህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ለሕዝቡ ቃል ከገቡት የወጣ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ አቶ እስከንድር ታስረው የሚገኙት በፖለቲካ አቋማቸው በመሆኑ የህሊና እስረኛ መሆናቸውን፣ አጋር አካላትና የኢትዮጵያ ወዳጅ አገሮች ከመንግሥት ጋር ባላቸው ግንኙነት ተፅዕኖ በመፍጠር ከእሳቸው ጋር ያላግባብ የታሰሩት ሌሎች አመራሮች ከእስር ወጥተው ሰላማዊ የፖለቲካ ሕይወታቸውን እንዲቀጥሉ የሚል ይዘት ያለው እንደሆነ አቶ ሔኖክ ጠቁመዋል፡፡
በሰብዓዊ መብት ጉዳይ ላይ ትኩረት እንዳላቸው፣ ትልልቅና የኢትዮጵያ መንግሥት ደጋፊ በመሆናቸው፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ትልቅ ጫና ሊያሳድሩ ይችላሉ ተብለው ለሚታሰቡት የምዕራብ አገሮች ኤምባሲዎች ጥሪው እንደቀረበ ያስታወቁት አቶ ሔኖክ፣ አሜሪካንን ጨምሮ ታላቋ ብሪታንያ፣ ፈረንሣይ፣ እስራኤል፣ ቻይናና ሩሲያ ተጠቃሾቹ እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡
ጥያቄው በዋነኛነት የመንግሥት አስፈጻሚው አካል ያላግባብ ታስረው የሚገኙትን አቶ እስክንድር ነጋና ሌሎች የፓርቲው የትግል አጋሮች እንዲፈቱ ግፊት ማድረግ እንደሆነ የገለጹት አቶ ሔኖክ፣ የመንግሥት የፍትሕ አካላት የመጨረሻ ውሳኔ ሰጪዎች እንደ መሆናቸው ከዚህ በፊት ለጥያቄው ምላሽ እንዲሰጡ ተጠይቆበት እንደነበረ አስታውሰው፣ በዚህ ወቅት ግን ለእነዚህ አካላት በቀጥታ ጥያቄው እንዳልቀረበ አስታውቀዋል፡፡
‹‹በቀጣይ በተለያዩ መንገዶች አቶ እስክንድር ነጋና የትግል አጋሮቻችን ከእስር እንዲለቀቁ በፍትሕ አደባባይ የሚደረገው ሙግት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በማኅበራዊ ሚዲያ የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ይጠናከራሉ፤›› ያሉት የፓርቲው የሕግ ጉዳዮች ኃላፊ፣ በቀጣይ በጽሑፍ ጥያቄ የቀረበላቸውን ኤምባሲዎች በአካል ለማግኘትና ጉዳዩን ለማሳወቅ ጥረቶች እንደሚደረጉ አመላክተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የፓርቲው አመራር የሆኑት አቶ እስክንድር ነጋ በምን ምክንያት ሊታሰሩ ቻሉ? የታሰሩበት ምክንያት የሚያሳስር ነው ወይ? የፍትሕ ሒደቱ ምን ይመስላል? የሚለውን በተለያየ መንገድ ለኅብረተሰቡ በማሳየት ተፅዕኖ ለመፍጠር እየተሞከረ እንደሚገኝ የተናገሩት አቶ ሔኖክ፣ በዚህም በሕዝቡ ዘንድ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሁነቶችን የመፍጠር ሥራን በማጠናከር አመራሮቹን ከእስር የማስለቀቅ ሰላማዊ እንቅስቃሴው በዘመቻ መልክ ሳይሆን በዘላቂነት የሚቀጥል እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
የፓርቲው መደበኛ እንቅስቃሴ ከምርጫው በኋላም ውስጡን በመመልከት የአደረጃጀቱንና የምርጫውን አጠቃላይ ሁኔታ ግምገማ ማካሄድ መቀጠሉን፣ በዚህም ሰፊ የሆነ መዋቅራዊ ማሻሻያዎችን አድርጎ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ፣ አመራሮቹን በተመለከተ ብዙም የተለየ ለውጥ ባይኖርም፣ እስከ ዛሬ የመጣበትንና የምርጫውን ውጤት ገምግሞ፣ ተቋማዊ ቁመናውን አሻሽሎ፣ ጠንካራና ተፎካካሪ ኃይል ሆኖ ለመውጣት ሰፊ ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝ አቶ ሔኖክ አስረድተዋል፡፡