የሰብል እህል ምርቶች ዋጋ እንደ ነሐሴ ወር ሁሉ የዋጋ ለውጥ ያልታየበት በመሆኑ፣ የሸማቾችን የመግዛት አቅም እየተፈታተነ መቀጠሉ ተጠቆመ፡፡
ሪፖርተር በተለያዩ የገበያ አካባቢዎች ተዘዋውሮ ያነገራቸው ሸማቾችና ነጋዴዎች እንዳስታወቁት፣ እንደ ዘይትና መኮረኒ ባሉት የፍጆታ ዕቃዎች ዋጋ ከነሐሴ ወር ጋር ሲነፃፀር፣ አንፃራዊ የሆነ የዋጋ ቅናሽ ቢታይበትም፣ የሰብል ምርት የሆኑት ጤፍ፣ ስንዴና በቆሎ ምርቶች ዋጋቸው አሁንም አልተሻሻለም፡፡
በመስከረም ወር መጨረሻ በነበረው የሰብል፣ ጥራጥሬና የዕለት የምግብ ፍጆታ ዕቃዎች ግብይት፣ በቄራ አካባቢ በሚገኙ መደብሮችና የሸማቾች የኅብረት ሥራ ወፍጮ ቤቶች ቀይ ጤፍ በኪሎ ከ43 እስከ 44 ብር፣ ሠርገኛ ከ45 እስከ 50 ብር፣ እንዲሁም ነጭ ጤፍ በኪሎ ከ55 እስከ 57 ብር እየተሸጠ እንደሆነ ሸማቾችና ነጋዴዎች ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል በሽሮ ሜዳ ገበያ ነጭ ጤፍ በ55 ብር፣ ሠርገኛ በ50 ብር፣ እንዲሁም ቀይ ጤፍ 46 ብር በኪሎ እየተሸጠ መሆኑን በአካባቢው የሚገኙ ሸማቾችና ነጋዴዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በቆሎ እስከ 24 ብር እንደሚሸጥና ዋጋው ከቀደሙት ወራት ለውጥ እንዳልታየበት፣ ሆኖም አዲሱ የምርት ወቅት እየደረሰ በመሆኑ ዋጋው ይቀንሳል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
ለአዲስ ዓመት መዳረሻ በነበረው ገበያ በሸማቾች ማኅበራት ሱቆች ነጭ ጤፍ በኪሎ 56 ብር አከባቢ ይሸጥ የነበረ ሲሆን፣ ሠርገኛ ከ46 እስከ 50 ብር፣ እንዲሁም ቀይ ጤፍ ከ40 እስከ 43 ብር መሸጡን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ስንዴ በበዓል መዳረሻ ሰሞን ከነበረው ዋጋ ከአምስት አስከ ሰባት ብር ጭማሪ በኪሎ እንደታየበት ያስታወቁት፣ በቄራ አካባቢ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ በላይነሽ ለማ ናቸው፡፡ በክረምቱ መባቻ ላይ ኪሎው እስከ 40 ብር ድረስ ሲሸጥ የነበረው ስንዴ በዚህ ወቅት ከ45 እስከ 47 ብር በሚደርስ ዋጋ እየሸመቱ መሆናቸውን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ በተመሳሳይ በበቆሎ ዋጋ ላይ ከቀደመው ወር እስከ አምስት ብር የሚደርስ ጭማሪ እንደተስተዋለ፣ በዚህ ወቅት አንድ ኪሎ በቆሎ በ30 ብር እየተሸጠ እንደሆነ ወ/ሮ በላይነሽ ተናግረው፣ መንግሥት ለኅብረተሰቡ አስፈላጊ የሆኑትን የሰብል እህሎች በሸማቾች ማኅበራት በሚገኙ ወፍጮ ቤቶች ከዚህ በተሻለ ዋጋ ሊያቀርብ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ እንደዚያ ካልሆነ እሳቸውም ሆነ መሰል ነዋሪዎች አሁንም ችግር አፍጦ እንደሚጠብቃቸው በሥጋት አስረድተዋል፡፡
ከሰብል እህሎች በተጨማሪ ባለፈው ነሐሴ ወር መጨረሻ በጥራጥሬ ምርቶች ላይ የነበረው የዋጋ ጭማሪ በመስከረም ወር ባለበት የቀጠለ ሲሆን፣ ለአብነትም በምስር ላይ ከቀደመው ወር ጋር ተቀራራቢ የሆነ የመሸጫ ዋጋ እንዳለ ሸማቾችና ነጋዴዎች ተናግረዋል፡፡ የአገር ውስጥ ተብሎ የሚጠራው የምስር ክክ በኪሎ ከ130 እስከ 140 ብር፣ እንዲሁም የውጭ ተብሎ የሚሸጠው ደግሞ በመርካቶና በሌሎችም ገበያዎች ኪሎው ከ100 እስከ 110 ብር እንደሚሸጥ ተገልጿል፡፡
በመርካቶ፣ በሽሮሜዳና በቄራ ገበያዎች በአንፃራዊነት ለውጥ ታይቶበታል ተብሎ የሚጠቀሰው ዘይት ሲሆን፣ በመርካቶ ገበያ የአገር ውስጥ የአኩሪ አተር ዘይት ሁለት ሊትር በጅምላ በ200 ብር፣ እንዲሁም ቸርቻሪዎች እስከ 220 ብር በሚደርስ ዋጋ ለገበያ እያዋሉት እንደሆነ አቶ ጌታሁን ሀብቴ የተባሉ ነጋዴ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ከውጭ የሚገባው ባለ አምስት ሊትር ዘይት ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀር ዋጋው እስከ 50 ብር የሚደርስ ቅናሽ እንደተስተዋለበት ሸማቾችም ሆኑ ነጋዴዎች ያረጋገጡ ሲሆን፣ 600 ብርና ከዚያም በላይ ሲሸጥ የቆየው አምስት ሊትር ዘይት ከ495 እስከ 500 ብር በሚደርስ ዋጋ እየተሸጠ ነው ብለዋል፡፡
በመርካቶና በቄራ ገበያ ቅናሽ ታይቶባቸዋል ከሚባሉት የፍጆታ ዕቃዎች አንዱ ማካሮኒ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በነበሩት ወራት እስከ 52 ብር በኪሎ ደርሶ የነበረ ቢሆንም፣ በዚህ ወቅት ከ42 እስከ 45 ብር በሚደርስ ዋጋ እየተሸጠ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ ሸማቾች መብት ተቆርቋሪዎች ድርጅት መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ቁምላቸው አበበ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት ሲንከባለል ቆይቶ አሁን ላይ ጣሪያው የደረሰ መስሏል፡፡ መንግሥት ገበያው ውስጥ አፋጣኝና የእውነት የሆነ ጣልቃ ገብነት ሊኖረው ይገባል ያሉት አቶ ቁምላቸው፣ በዚህ ወቅት በሚመለከተው የመንግሥት መሥሪያ ቤት እየተወሰደ ያለው ዕርምጃ ነገሮች ሲከሰቱ በመገናኛ ብዙኃን ቀርቦ ይህን አድርገናል የሚል አንድምታ ያለው እንደሆነ ተናግረው፣ ገበያው ውስጥ የመንግሥት ሀቀኛ ጣልቃ ገብነት ሊኖር እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
በደላላ ምክንያት የሚደርሰውን የገበያ ጡዘት መንግሥት ሊከላከለው እንደሚገባ ያስታወቁት ሥራ አስኪያጁ፣ በዚህ ወቅት ከምግብ ፍጆታ ዕቃዎች አንስቶ እስከ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ድረስ የምርት ሒደት ውስጥ ደላላው ያልተሰገሰገበት ነገር እንደሌለ ገልጸዋል፡፡
እየታየ ያለው የምግብ ሸቀጦችና የሌሎች ምርቶች ዋጋ ማሻቀብ የአቅርቦትና የፍላጎት አለመጣጣም ተደርጎ ቢነገርም፣ የአቅርቦትና የፍላጎቱ ጉዳይ ቢስተካከል እንኳን ሕገወጥ ደላላው ከገበያ እስካልወጣ ድረስ ዋጋን ማረጋጋት አይቻልም ብለዋል፡፡
የንግዱ ማኅበረሰብም የሞራል ልዕልና እያጣ ነው ያሉት አቶ ቁምላቸው፣ አንድ ነጋዴ ከመርካቶ ላመጣው ምርት የሚጠይቀው የዋጋ ጭማሪ እጅግ በጣም አስፈሪ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ መተሳሰብና መተዛዘን የሚባል ነገር እንደጠፋና ለንግዱ ማኅበረሰብ እቆረቆርለታለሁ የሚለው የንግድ ምክር ቤትም ነጋዴውን ማነጋገር እንዳለበት፣ በሸማቾችም ላይ ይህንን ያህል ዋጋ እንዴት ይጨመራል የሚለውን መጠየቅ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የዋጋ ግሽበትን አንድ ተቋም ብቻ የሚፈታው እንዳልሆነ፣ ባለድርሻ አካላት በጉዳይ ተባብረው የመፍትሔው አካል እንዲሆኑ መንግሥታዊ ተቋማት በራቸውን ክፍት ሊያደርጉ እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡ ይህ የሚመቻችበት መንገድ በመንግሥት በኩል ከሌለ መንግሥት የዋጋ ግሽበት ችግርን እንዲፈታ ፍላጎት አለው ወይ የሚል ጥያቄ እንደሚያጭር፣ የኢኮኖሚው ቀውስም ወደ ደኅንነት፣ ሰላምና ፀጥታ ችግርነት እያደገ ሊሄድ እንደሚችል አቶ ቁምላቸው አስረድተዋል፡፡
አሁንም ቢሆን የቱንም ያህል ፍላጎትን ያሟላ ምርት ቢኖርም ከታች እስከ ላይ ያለው ደላላ ከግብይት ሥርዓቱ ውስጥ እስካልወጣ ድረስ ገበያው ሊረጋጋ እንደማይችል የሚነገሩት የሸማቾች ተቆርቋሪ ድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ፣ መንግሥት የመጀመርያው ሥራ ሊሆን የሚገባው ደላላውን ከግብይት ሥርዓቱ ውስጥ ማስወጠት ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በጥቂት ተቋማትና ግለሰቦች ላይ የተንጠለጠለውን የአስመጪነት ሥራ ማስፋት እንደሚያስፈልግ፣ በመንግሥት በኩል ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡