Saturday, December 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በሶማሌ ክልል የተገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ ልማት ያዘገየው የቻይና ኩባንያ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ማስተማመኛ እንዲያቀርብ ታዘዘ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በሶማሌ ክልል የተገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ አልምቶ ኤክስፖርት ለማድረግ፣ በማዕድን ሚኒስቴር ፈቃድ የተሰጠው የቻይናው ኩባንያ ፖሊ ጂሲኤል፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ልማቱን ማካሄድ የሚችል መሆኑን ሁለት ቢሊዮን ዶላር ብሔራዊ ባንክ በማስቀመጥ እንዲያረጋግጥ በመንግሥት ታዘዘ።

ኩባንያው በሶማሌ ክልል ካሉብና ኢላላ የተገኘውን ከፍተኛ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት አልምቶ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ፈቃድ ያገኘው ... 2013 ቢሆንም፣ በአካባቢው የሚገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ አልምቶ ለገበያ ለማቅረብ እያደረገ ያለው ጥረት እጅግ ደካማ ከመሆኑም በላይ፣ ለመንግሥት ባቀረበው መርሐ ግብር መሠረት እያከናወነ አለመሆኑን በማስታወቅ የማዕድን ሚኒስቴር የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ በሰኔ ወር 2013 ዓ.ም. ሰጥቶት እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል።

ይህንን ተከትሎ ኩባንያው የተፈጥሮ ጋዙን ለማልማት ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ  የሚገልጽ  ዝርዝር ለማዕድን ሚኒስቴር ያስገባ ቢሆንም፣ ባቀረበው ዝርዝር መረጃ ላይ ሁለቱ ተዋዋዮች ማለትም የማዕድን ሚኒስቴርና ኩባንያው መተማመን እንዳልቻሉ ሪፖርተር ከምንጮች ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። 

በዚህም መሠረት የማዕድን ሚኒስቴር ለኩባንያውድጋሚ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንዲደርሰው ከማድረጉ በተጨማሪ ልማቱን ለማካሄድ የሚያስችል የፋይናንስ አቅም እንዳለው፣ ለማዕድን ሚኒስቴርና ለመንግሥት በተግባር እንዲያረጋግጥ መታዘዙን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በማዕድን ሚኒስትሩ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ተፈርሞ መስከረም 19 ቀን 2014 ዓ.ም. ለኩባንያው የተላከው ደብዳቤ፣ ‹‹የማዕድን ሚኒስቴር ከኩባንያው ፖሊ ጂሲኤል ጋር የገባውን ውል ለማቋረጥ ወይም ኩባንያው ልማቱን በማካሄድ አስተማማኝ የኢትዮጵያ  አጋርነቱን ለማረጋገጥ እንዲቻል፣ የሚከተሉትን ሁኔታዎች በተቀመጠው ቀነ ገደብ እንዲያሟላ ተጠይቋል፤›› በማለት ኩባንያው እንዲያሟላ ያላቸውን ግዴታዎች ዘርዝሯል።

በዚህም መሠረት በቀዳሚነት የተቀመጠው ፖሊ ጂሲአል የተፈጥሮ ጋዙን ለማልማት በቂ ካፒታል ያለው መሆኑንማዕድን ሚኒስቴር (የቀድሞ መጠሪያው ማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር) ማረጋገጥ እንዲችል እስከ ዲሴምበር 29 ቀን 2021 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ፣ ሁለት ቢሊዮን ዶላር በብሔራዊ ባንክ አካውንት ማስቀመጥ አለበት የሚለው ግዴታ ነው።

ኩባንያው የተባለውን የካፒታል ማስተማመኛ ገንዘብ በብሔራዊ ባንክ እንዳስቀመጠ የማዕድን ሚኒስቴር የኩባንያውን የካፒታል አቅም በማጣራት፣ የተፈጥሮ ጋዙን ለማልማት መቻሉን እንደሚገመግም በዚሁ ደብዳቤ ለኩባንያው አስታውቋል።

ኩባንያው ከስምንት ዓመት በፊት ፈቃድ ሲሰጠው በሶማሌ ክልል ካሉብና ሂላላ አካባቢዎች የተገኘውን የተረጋገጠ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት አምርቶ በፈሳሽ መልክ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ፣ የተወሰነውን ደግሞ በአገር ውስጥ ለሚገነባ የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካም በግብዓትነት እንዲያቀርብ ነው። 

 

በፈቃድ ስምምነቱ መሠረትም ኩባንያው የተገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ ወደ ፈሳሽ በመቀየር ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንዲችል፣ ከአካባቢው አንስቶ እስከ ጂቡቲ ወደብ የሚዘረጋ የተፈጥሮ ጋዝ ማመላለሻ የቧንቧ መስመር አራት ቢሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ ለመዘርጋት ማቀዱን ይፋ አድርጎ እንደነበር ይታወሳል።

ኩባንያው በቀድሞ የልማት ዕቅዱ ላይ ማሻሻያ በማድረግ የተፈጥሮ ጋዙን ወደ ኃይድሮጅን በመቀየር ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ተስፋ ሰጪ ጥረት እያደረገ መሆኑን በመግለጽ፣ 2013 ዓ.ም. የመጨረሻ ሳምንት ላይ ለማዕድን ሚኒስቴር በጽሑፍ ያስታወቀ መሆኑን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ይሁን እንጂ በልማት ዕቅዱ ላይ የተደረገው ለውጥ የኢትዮጵያ መንግሥትን ያላሳተፈ በመሆኑ፣ በማዕድን ሚኒስቴር ተቀባይነት አላገኝም፡፡ ነገር ግን የዕቅድ ለውጡ ሙሉ በሙሉ ውድቅ አለመደረጉንም የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ለሁሉም የኩባንያው ቀጣይ የልማት አንቅስቃሴ የተፈጥሮ ጋዙን በመጀመርያው ዕቅድ መሠረት ለማልማት የሚያስችል የካፒታል አቅም ያለው መሆኑን፣ ሁለት ቢሊዮን ዶላር በብሔራዊ ባንክ በማስቀመጥ ካረጋገጠ በኋላ የሚወሰን እንደሚሆን መረጃው ያስረዳል።

በዚህ የሶማሌ ክልል ካሉብ፣ እኒ፣ ሂላላ በተባሉ አካባቢዎች የተገኘው የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ስምንት ትሪሊየን ኪዩቢክ ጫማ በላይ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህንን የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት አውጥቶ ለገበያ ለማቅረብ መሠረተ ልማቱን ማሟላት ብቻ የሚጠይቅ እንደሆነ ቢገለጽም፣ ክምችቱን ወደ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለመቀየር ሳይቻል ሁለት አሥርት ዓመታት መጠበቅ ግድ ሆኗል።

 

ፖሊ ጂሲኤል በሶማሌ ክልል የፔትሮሊየም ልማት ፈቃድ እንዳለው የሚታወቅ ሲሆንየዛሬ ሦስት ዓመት ገደማ በተጠቀሰው የሶማሌ ክልል የኦጋዴን ተፋሰስ ውስጥ የነዳጅ ዘይት እንዳገኘ ማስታወቁና ይህንንም ተከትሎ በወቅቱ የነበሩ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት ሥነ ሥርዓት ይፋ መድረጉ ይታወሳል።

ፖሊ ጂሲኤል አገኘ የተባለው የነዳጅ ዘይት መጠን እርግጡ ባይታወቅም በኦጋዴን የነዳጅ ዘይት መኖሩ ከተረጋገጠ በርካታ አሥርት ዓመታት ማለፋቸውን፣ ነገር ግን ያለው የነዳጅ ዘይት ክምችት መጠን በትክክል እንዳልተለየ መረጃዎች ያመለክታሉ።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች