Friday, September 30, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ከጠላት ይልቅ ወዳጅ ማብዛት ላይ ይተኮር!

  በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ያለችበት ወቅታዊ ሁኔታ ከጠላት ይልቅ ወዳጅ ማብዛት ላይ ጠንክሮ መሥራትን ይጠይቃል፡፡ ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ አልፎ ከመላው አፍሪካውያን ጋር፣ እንዲሁም በሰሜንና በደቡብ አሜሪካ፣ በእስያ፣ በአውሮፓና በሌሎችም ዘንድ ተቀባይነት እንድታገኝ ጥረት ያስፈልጋል፡፡ አገሮች ከሌሎች አገሮችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር የሚኖሯቸው የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ግንኙነቶች ጥቅምን መሠረት ያደረጉ መሆናቸው የታወቀ ነው፡፡ ግንኙነቶቹ ግን የጋራ ጥቅም ላይ ያተኮሩ እንዲሆኑ ብልህ መሆን አስፈላጊ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት በአዲሱ መንግሥት ምሥረታና በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በዓለ ሲመት ላይ የተገኙት የአፍሪካ መሪዎች መልዕክት ላይ የተንፀባረቀው አንዱ ጉዳይ፣ ኢትዮጵያ ጥንታዊትና ለአፍሪካዊያን ነፃነት ተጋድሎ ያደረገች አገር መሆኗ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በበርካታ ወጀቦች ውስጥ አልፋ ከቅኝ ገዥዎች ጋር ጉሮሮ ለጉሮሮ በመተናነቅ ክብሯን ያስጠበቀች የአፍሪካ መከታ መሆኗ ሲወሳ፣ ዛሬ ደግሞ በእርስ በርስ ጦርነት እየደቀቀች እንደሆነ ለአፍታም መዘንጋት የለበትም፡፡ ለሌሎች አገሮች አርነት ትልቅ ዋጋ የከፈለች አገር የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ሲበረታባት፣ ምክንያቱ ምን እንደሆነ በሚገባ ተረድቶ መስተካከል ያለባቸውን ነገሮች ማከናወን ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ የበርካቶች ወዳጅ መሆን እየተቻላት ጠላት ሊበረክትባት አይገባም፡፡ ይህ ጉዳይ አፅንኦት ያስፈልገዋል፡፡ 

  ኢትዮጵያ የፀረ ቅኝ አገዛዝ ትግል ቀንዲልና የፓን አፍሪካኒዝም ፅኑ መሠረት ሆና ዘመናትን የተሻገረች አገር ናት፡፡ በዚህ ታሪካዊ ተጋድሎዋ ምክንያትም የአፍሪካውያን የጋራ ቤት ከመሆን አልፋ፣ ለዓለም የተጨቆኑ ሕዝቦች ተምሳሌት መሆኗን አስመስክራለች፡፡ ይህንን የመሰለ አኩሪ ታሪክ ያላት አገር በብዙዎች የአፍሪካ የነፃነት እናት ተብላ ስትንቆለጳጰስ፣ ኢትዮጵያዊያን ደግሞ ከአፍሪካውያን ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ጋር ጠንካራ ቁርኝት ለመፍጠር መነሳት ይኖርባቸዋል፡፡ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ ከመሆን ባለፈ፣ ከሁሉም የአፍሪካ አገሮች ጋር በዲፕሎማሲ፣ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በባህል፣ በትምህርት፣ በኪነ ጥበብና በተለያዩ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ጠንካራ ግንኙነት መፍጠር ይገባል፡፡ “ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔዎች” በሚለው መርህ መሠረትም፣ አፍሪካ ሰላማዊ አኅጉር ሆና ዕድገት እንድታስመዘግብ የበኩልን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ከሌሎች ሰላም ወዳድና በትብብር ለመሥራት ከሚፈልጉ አገሮች ጋር ወዳጅነትን በማጠናከር፣ በእኩልነት መርህ አብሮ ለመሥራት ማቀድና መተግበር የግድ መሆን አለበት፡፡ የምዕራባውያንን ጫና በመቀልበስ የተረጋጋ ምኅዳር ለመፍጠርም፣ መሠረታዊ በሚባሉ ልዩነቶች ላይ በሠለጠነ መንገድ ለመነጋገር መዘጋጀት ተገቢ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የውስጥ ችግሯን በፍጥነት በመፍታት የልማትና የዕድገት ጎዳናን መያዝ አለባት፡፡ ይህንን ማድረግ ስትችል ከጠላት ይልቅ ወዳጆቿ ይበዛሉ፡፡

  የኢትዮጵያን ወቅታዊ ገጽታ ለመለወጥ ከሚያስችሉ በርካታ ጉዳዮች መካከል አንዱ የመንግሥት ባህሪ ነው፡፡ መንግሥት ለአገር በሚያስቡ ዜጎች ሲደገፍና አመራሮቹም በዚህ መሠረት ሲሰማሩ፣ የመንግሥት የተለመደ አሳዛኝና አስከፊ ባህሪ ይለወጣል፡፡ ለዚህም ሲባል የፓርቲና የመንግሥት አሠራር እንዳይደበላለቁ ማድረግ፣ ከአገር ጥቅም በፊት ራሳቸውን የሚያስቀድሙ ስግብግቦች ወደ አመራርነት እንዳይመጡ ማገድ፣ የመንግሥት ተቋማት በነፃነትና በገለልተኝነት ሥራቸውን እንዲያከናውኑ የሚያስችላቸውን አቅም መገንባት፣ የአመራሮችና የባለሙያዎች ምደባ በብቃት ላይ ብቻ እንዲሆን ቁርጠኛ መሆን፣ ኋላቀሩን ቢሮክራሲ በማዘመን የአገልግሎት አሰጣጥን ማቀላጠፍ፣ ለሞራልና ለሥነ ምግባር እሴቶች ትልቅ ዋጋ በመስጠት ሌብነትን በተግባር የሚያስወግድ አሠራር ማስፈንና የመሳሰሉት ተግባራት ሊታሰብባቸው ይገባል፡፡ ከዚህ ቀደም የመንግሥት ተቋማት የአምባገነኖችና የዘራፊዎች ሲሳይ የሆኑት፣ የመንግሥት ባህሪ ከዘመኑ አስተሳሰብ ጋር ሊመጣጠን ባለመቻሉ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በማንነትና በእምነት እየተቧደኑ የአገርን ክብር ማዋረድና ትውልዱን ተስፋ ማስቆረጥ በመለመዱና የመንግሥት ተቋማት በመሽመድመዳቸው፣ አገር ዛሬ ከፍተኛ መስዋዕትነት እየከፈለች ነው፡፡ ከእንዲህ ዓይነቱ የዘቀጠ ድርጊት ውስጥ በመውጣት ኢትዮጵያን ከፍ ማድረግ የግድ መሆን አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ጠላት አልባ ሆና በወዳጆች የምትከበበው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡

  የዲፕሎማሲው ግንባር እጅግ አታካችና ተለዋዋጭ ሁኔታዎች የበዙበት መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ የአንድ አገር ዲፕሎማሲ ብስለትና ውጤታማነት የሚለካውም ከአገሮች ጋር በሚኖር ግንኙነት ብቻ ሳይሆን፣ ከታወቁ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በሚኖረው መስተጋብር ጭምር ነው፡፡ እንደሚባለው ግንኙነቶቹ ከፍተኛ ትጋትና አርቆ አሳቢነት የሚጠይቁ በመሆናቸው፣ የመንግሥት ፖሊሲም ሆነ ስትራቴጂ ብልኃት ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህ ብልኃት በምኞት የሚገኝ ሳይሆን በዲፕሎማሲ ጥርሳቸውን የነቀሉ ጎምቱ ባለሙያዎችን፣ ለዚህ ተግባር ራሳቸውን ካዘጋጁ ወጣት ዲፕሎማቶች ጋራ በማቀናጀት ሊሆን ይችላል፡፡ የመንግሥት አመራሮችም ሆኑ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ውስጥ ያሉ ሰዎች እየተናበቡና ጠቃሚ ልምዶችንና ምክሮችን እየቀሰሙ ሥራ ላይ የሚያውሉት ፖሊሲና ስትራቴጂ ውጤታማ የሚሆነው፣ ከነባራዊ ሁኔታዎች ጋር ተጣጥሞ ተግባራዊ እንዲሆን ሲደረግ ነው፡፡ የወቅቱን የዓለም አሠላለፍ በሚገባ የተረዳ፣ የአገርን ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅም የሚያሰላ፣ የጋራ ተጠቃሚነት መርህን የተገነዘበና በዕውቀት ላይ ተመሥርቶ የሚከናወን ሲሆን ከጠላት ይልቅ ወዳጆችን ማበርከት ይችላል፡፡ አንዳንድ እውነታዎች ሲያጋጥሙም ለመደራደርና ፈር ለማስያዝ አይቸግረውም፡፡ በስሜት ሳይሆን በምክንያት ላይ ሲመሠረት ደግሞ፣ ያለፉት ዘመናትን ውጣ ውረዶች ከታሪክ ማኅደር እያገላበጠ ይረዳል፡፡ ከስህተቶች በመማርም ዕርምት ያደርጋል፡፡ ያኔ ወዳጆች ይበረክታሉ፡፡

  ኢትዮጵያ የበርካቶችን ቀልብ ለሚስበው የቀይ ባህር ጂኦ ፖለቲካዊ የስበት ማዕከል በጣም ቅርብ ነች፡፡ ይህ አካባቢ የዓረብ ባህረ ሰላጤ አገሮችን ጨምሮ እነ አሜሪካ፣ ፈረንሣይ፣ ቻይና፣ ጃፓን፣ ሩሲያና የመሳሰሉት ከጦር ሠፈር ግንባታ በተጨማሪ በርካታ ፍላጎቶችን ይዘው የሚንቀሳቀሱበት ስለሆነ፣ ለብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅም ሥጋት የሆኑ ጉዳዮች ይስተዋሉበታል፡፡ ኢትዮጵያ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ምክንያት ከግብፅና ከሱዳን ጋር የፈጠረችው አተካራ፣ አሜሪካን ጨምሮ የተለያዩ አገሮችን አሠላለፍ ውስጥ ከቷል፡፡ በዚህም ምክንያት በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ጦርነት የውጭ ጣልቃ ገብነትን ለመጋበዝ ምክንያት ሆኗል፡፡ አሜሪካና ቻይና የገቡበት የንግድ ጦርነት በዓለም አቀፍ ደረጃ የፈጠረው እሰጥ አገባ፣ ጦሱን ይዞ ወደ ቀይ ባህር ጂኦ ፖለቲካዊ ፍጥጫ ውስጥ ሳይቀር እያመራ ነው፡፡ ኢትዮጵያንም ከመቼውም ጊዜ በላይ የምዕራቡ ዓለም እየተናበበ እንዲነሳባት ሰበብ እየሆነ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሰባት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሥራ ኃላፊዎች ተገቢ ያልሆነ ድርጊት ሲፈጽሙ በመገኘታቸው በኢትዮጵያ መንግሥት በ72 ሰዓታት ውስጥ ከአገር እንዲወጡ መወሰኑ፣ ለምዕራባውያንን ጩኸትና ማስፈራራት ተጨማሪ ምክንያት  ሆኗል፡፡ በዚህም ሳቢያ ጠላትነት እየበዛ ነው፡፡

  አንዲት አገር ሉዓላዊነቷን ለማስከበር በምትወስደው ዕርምጃ ዓለም አቀፍ ሕግጋትን ማክበር እንዳለባት ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ኢትዮጵያም በቬና ኮንቬንሽን መሠረት ሉዓላዊነቷን ለማስከበር ዕርምጃ ብትወስድምና በፀጥታው ምክር ቤት ሳይቀር ይህ መብቷ አፅንኦት ተሰጥቶት በተደጋጋሚ ቢገለጽም፣ የምዕራቡ ኃይል ጎራ ግን ሊዋጥለት የፈለገ አይመስልም፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ የአገሪቱ ልሂቃን እዚህ ላይ ቆም ብለው ማሰብ ይገባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ወሳኝ ጊዜ ለምን ይሆን ከምዕራቡ ዓለም አሉታዊ ምላሽ እያገኘች ያለችው የሚለው መልስ ማግኘት አለበት፡፡ በውስጥ ጉዳይዋ ከመጠን በላይ ጣልቃ ለመግባት የተፈለገበት ምክንያት ማብራሪያ ማግኘት ይኖርበታል፡፡ ከ110 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የሚኖርባትና በበርካታ የተፈጥሮ ፀጋዎች የታደለች አገር የብዙዎችን ወዳጅነት ማፍራት ሲገባት፣ በምን ምክንያት ነው አሉታዊ አቋም እየተራመደባት ያለው ተብሎ በብርቱ ማነጋገር አለበት፡፡ አሜሪካና የአውሮፓ ኅብረት ማዕቀቦችን ለመጣል እየተጣደፉ ያሉት ከኢትዮጵያ በኩል ምን ቢጎድልባቸው ነው ብሎ መጠየቅ የግድ ነው፡፡ ቀደም ሲል ወዳጅ የነበሩ አገሮች ጀርባቸውን ሲሰጡ በደፈናው ሉዓላዊነትን መጋረጃ ከማድረግ ይልቅ፣ እነሱ ምን ፈልገው ቢያጡ ነው እዚህ ደረጃ ላይ የደረሱት የሚለውን ማወቅ ከጠላት ይልቅ ወዳጅ ለማብዛት ይጠቅማል!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  በቤንዚንና ነጭ ናፍጣ ላይ ጭማሪ ተደረገ

  ከዛሬ መስከረም 18 ቀን 2015 ዓም እኩለ ሌሊት ጀምሮ...

  የሰሜን ኢትዮጵያን ግጭት ለመፍታት በሚያስችል የአሠራር ማዕቀፍ ላይ መወያየታቸውን የኬንያው ፕሬዚዳንት ተናገሩ

  በቅርቡ የኬንያ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ዊሊያም ሩቶ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ...

  ኦፌኮ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን ጨምሮ ስምንት አመራሮች እንደታሰሩበት አስታወቀ

  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለክልሉ ደብዳቤ ጽፏል የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ...

  የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት ሕገወጥ ገንዘብ አስተላላፊዎችን አስጠነቀቀ

  የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት በሕገወጥ የገንዘብ ማስተላለፍ ድርጊት ተሰማርተዋል ያላቸው...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች