Thursday, June 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአየር ትራንስፖርትና በቱሪዝም ዘርፎች ላይ ያደረሰው ጉዳት

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከፍተኛ ጉዳት ካደረሰባቸውና አሁንም እየፈተናቸው ከሚገኙ የንግድ ዘርፎች መካከል የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት በዋነኝነት ይጠቀሳል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ አየር መንገዶች ወረርሽኙ መስፋፋት ከጀመረበት  ከመጋቢት 2012 ዓ.ም. በኋላ ለከባድ ኪሳራ ተዳርገዋል፡፡

የበረራ አገልግሎቶች በእጅጉ መገደባቸውና አገሮች ኮቪድ-19 ለመከላከል በመንገደኞች እንቅስቃሴ ላይ የሚጥሉት ገደብ በአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ብቻ ሳይሆን፣ አጠቃላይ የዓለምን ኢኮኖሚ አቃውሷል፡፡

የመንገደኞች እንቅስቃሴና የአየር ትራንስፖርቱ በከፍተኛ ሁኔታ መገታት ደግሞ ተያያዥ የሚባሉ ዘርፎችንም ጎድቷል፡፡ ከእነዚህ አንዱ ደግሞ የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ነው፡፡ በቱሪዝምና በተያያዥ ጉዳዮች ላይ ሰሞኑን በተዘጋጀ መድረክ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ አገልግሎት ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ለማ ያደቻ ባቀረቡት ጽሑፍም. ኮቪድ-19 አየር መንገዶች ላይ እያሳረፈ ያለው ተፅዕኖ ከፍተኛና ከ1950ዎቹ ወዲህ ባሉት ዓመታት ያልታየ ጉዳት በኢንዱስትሪው እያደረሰ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በበረራ አገልግሎቶች ላይ የተወሰነ መሻሻል ቢታይም፣ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ የተጣሉ የበረራ ገደቦች ሙሉ ለሙሉ አለመነሳታቸው ተፅዕኖው እንዲቀጥል አድርጓል፡፡ የአየር ትራንስፖርት አሁን የገጠመው ፈተና ቀጣይ ስለመሆኑም ዓለም አቀፉን የአቪዬሽን ድርጅት (አያታ)ን መረጃ ዋቢ በማድረግም፣ የአየር ትራንስፖርቱ እ.ኤ.አ. በ2019 ወደ ነበረበት አቋሙ ለመመለስ እስከ 2024 ድረስ መጠበቅ እንደሚኖርበት ተናግረዋል፡፡  

ኮቪድ-19 ከተከሰተ ወዲህ፣ በተለይ ከ2019 በኋላ የመንገደኞች ቁጥር በእጅጉ ማሽቆልቆሉ የአየር መንገዶች የገቢ መጠን በእጅጉ እንዲቀንስ አድርጓል፡፡ ብዙዎቹ አየር መንገዶች እንዲከስሩ ማድረጉንም የገለጹት አቶ ለማ፣ የአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ከሚሰጣቸው የመንገደኞችና የጭነት ትራንስፖርት አገልግሎቶች በኮቪድ-19 ምክንያት በእጅጉ የተጎዳው የመንገደኞች ትራንስፖርት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የጭነት አገልግሎቱ ደግሞ በተቃራኒው መልካም ዕድል ያገኘበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከመንገደኞች ያጣውን ገበያ በጭነት አገልግሎት ለማንሳት ዕድል የሰጠው ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ የበረራ አገልግሎት እጅግ ተጎድቶ እንደነበር ለማሳየት በተጠቀሰ አኃዛዊ መረጃ መሠረትም፣ እ.ኤ.አ. ከ2019 አንፃር ሲታይ የመንገደኞች በረራ መጋቢት በ2020 ላይ በ66 በመቶ ቀንሷል፡፡

አገሮች በጣሉት ገደብ ምክንያት ረዣዥም የጉዞ መዳረሻዎች ተዘግተው መቆየታቸው የመንገደኞችን እንቅስቃሴ መግታቱም ለአየር መንገዶች ኪሳራ ምክንያት መሆኑን አቶ ለማ አስታውሰዋል፡፡ በአገሮች በገደብ ምክንያት በረራዎች እንዲቀንሱ መደረጉ ያደረሰውን ጉዳት ለማመላከት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ህንድ ያደርገው የነበረውን በረራ በምሳሌት እንስተዋል፡፡ የአየር ትራንስፖርቱ በዋናነት የሚመራው አገሮች በሚፈራረሙት የሁለትዮሽ ስምምነት መሆኑን ያስታወሱት አቶ ለማ፣ ይህ ስምምነት ግን በኮቪድ-19 ጊዜ እንዲቀር ተደርጓል ብለዋል፡፡ በመሆኑም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የህንድ መንግሥት ወደ ህንድ የሚደረጉ በረራዎች ላይ በጣለው ዕግድ ምክንያት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ህንድ በሳምንት ያደርጋቸው የነበሩ 31  በረራዎች ወደ ሁለት ዝቅ እንዲሉ ተደርጓል፡፡ ይህ ገደብ ሳምንታዊ በረራዎች በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንሱ ያደረገ ብቻ ሳይሆን፣ በሳምንት ሁለቴ በሚኖረው በረራም ማጓጓዝ የሚችለው 440 መንገደኞችን ብቻ መሆኑ ኪሳራው ከፍተኛ እንዲሆን ማድረጉን ተናግረዋል፡፡    

ዕቀባዎች ያስከተሉት ጉዳት ቀላል ያለመሆኑና አሁንም ያለመነሳታቸው የአየር ትራንስፖርቱ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ የቱሪስት እንቅስቃሴዎችን በመግታት የቱሪዝም ዘርፉ ለአገሮች ይሰጥ የነበረውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንደጎዳው ተናግረዋል፡፡   

በአፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ በአብዛኛው የዕቀባ ወይም የቁጥጥር ሥራው የላላ ቢሆንም፣ የቱሪዝም ዘርፉ ከአውሮፓ፣ ከላቲን አሜሪካ፣ ከእስያና ከሰሜን አሜሪካ ጋር የተሳሰረ በመሆኑ፣ ቱሪስቶችን ማምጣት እንዳላስቻለ ጠቅሰዋል፡፡

ይህንን ትስስር ለማስቀጠልና ቱሪስቶችን ለማምጣት አገሮች የጣሉትን የጉዞ ዕቀባ ማንሳት ይኖርባቸዋል ያሉት አቶ ለማ፣ አፍሪካ ውስጥ የቱሪዝም እንቅስቃሴው ብዙም አመርቂ እንዳልነበረ አመልክተዋል፡፡

ከ2019 አንፃር ሲታይ በ2020 የአየር በረራ በ66 በመቶ ወርዶ የነበረ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በማርች ወር 2021 መጨረሻ ላይ ደግሞ 50 በመቶ መቀነሱን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድም ከዚህ የተለየ ታሪክ እንደሌለው የጠቀሱት አቶ ለማ፣ ‹‹በ2019 የነበረው የመንገደኞች ምልልስ 60 በመቶ አካባቢ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ወደ 70 በመቶ አድጓል፡፡ መሻሻሎች ታይተዋል፤›› ብለዋል፡፡

የአየር ትራንስፖርቱ ኪሳራ በቀጣይ ምን ሊሆን ይችላል የሚለውን በተመለከተም እ.ኤ.አ. በ2022 አየር መንገዶች 11.6 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ ይገጥማቸዋል ተብሎ የሚጠበቅ መሆኑን አክለዋል፡፡

የአያታን መረጃ ጠቅሰውም ኢንዱስትሪው እ.ኤ.አ. በ2020፣ 137 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ የገጠመው መሆኑንና እ.ኤ.አ. በ2021 ደግሞ 58.1 ቢሊዮን ብር ኪሳራ እንደሚያስመዘግብ መተንበዩን አመልተዋል፡፡ ጉዳቱ ግዙፍ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ለማ፣ በአፍሪካ ደግሞ በ2021 1.9 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ ይደርሳል ተብሎ እንደሚታሰብ ገልጸዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ አብዛኞቹ የአየር ትራንስፖርቶች ወደ ሥራ እየተመለሱ መሆኑን እንደ መልካም ዕድል የጠቀሱት አቶ ለማ፣ እስካሁን 21,057 አውሮፕላኖች ወደ ሥራ መመለሳቸውንና ይህም በበረራ ፕሮግራም ሊበሩ ከሚችሉት 98 በመቶውን የሚሸፍን በመሆኑ የአየር ትራንስፖቱ የአገሮች ገደብ ቢኖርበትም ወደ በረራ እየተመለሰ መሆኑን ያመለክታል ብለዋል፡፡  

ለውጡ የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃት ተስፋ ሰጪ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያንም ሆነ የዓለምን ቱሪዝም እንቅስቃሴ ለመመለስና የቱሪስቶችን ቁጥር ለመጨመር መንግሥታት የበረራ ማዕቀባቸውን ማንሳት እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት አገሮች በረራዎችን የሚፈቅዱት ያስቀመጡትን መሥፈርት ለሚያሟሉ አየር መንገዶች እንደሆነ፣ የአውሮፓ አገሮች ከሌላ አገር ለሚመጡ አየር መንገዶች የበረራ ፈቃድ ለመስጠት አየር መንገዱ የተመዘገበበት አገር ያለውን የኮቪድ-19 ሥርጭትና የሞት መጠን፣ እንዲሁም የክትባት ሁኔታን እንደሚጠይቁ ገልጸዋል፡፡ ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ከተፈለገም እንዲህ ያሉ መሥፈርቶችን እንዴት ማሟላት እንደሚቻል ሊታሰብበት ይገባል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኮቪድ-19 ምክንያት ቀንሶ የነበረውን በረራ ለመመለስ እየሠራ ሲሆን፣ በአፍሪካም ከሦስትና አራት አገሮች በስተቀር በሌሎች መዳረሻዎች በረራዎቹን መጀመሩ ተገልጿል፡፡

በዋናነት ግን ቱሪስቶች የሚመጡባቸው አገሮች የተጣለው ገደብ እንቅፋት እንደሆነና ይህንን ፈተና ለማለፍና በረራዎችን ለማሳደግ አገሮች ያስቀመጡትን ቅድመ ሁኔታ ለማሟላት የሚያስችሉ ሥራዎችን መሠራት ይገባል ብለዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ የኮቪድ-19 ተከታቢዎችን ቁጥር ማሳደግ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች