Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርመነቃቃት ያለበት የዕድገት ጉዞና የምሁራን ሚና

መነቃቃት ያለበት የዕድገት ጉዞና የምሁራን ሚና

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው

       በአገራችን የተካሄደውን ስድስተኛውን ብሔራዊ ምርጫ ተከትሎ፣ የብልፅግና ፓርቲ የአብላጫ ድምፅ አግኝቶ መንግሥት መሥርቷል፡፡ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በጠቅላይ ሚኒስትርነት የቀጠሉ ሲሆን፣ ዘንድሮ አዲሱ ነገር የተለያዩ ተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎች በክልልና በፌዴራል አስፈጻሚ መዋቅሮች መካተታቸው ነው፡፡ እንዲሁም ካለፉት ጊዜያት በተሻለ በርካታ ምሁራንና ባለሦስት ዲግሪ ሙያተኞችን በካቢኔ ደረጃ እንዲገቡ መደረጉ መጭውን ጊዜ በተስፋ እንድንመለከት አድርጓል፡፡

     እውነት ለመናገር ምሁርነት መለኪያው ‹‹ዶክተርነት›› ብቻ ነው ባይባልም፣ ባለፉት 30 ዓመታት በተገነባው የግልም ሆነ የሕዝብ አቅም አማካይነት በአገራችን ሁለተኛ ዲግሪ የሌለው የፌዴራል አይደለም የክልል ቢሮ ኃላፊ አለ ማለት አይቻልም፡፡ በፈጻሚ ደረጃም ቢሆን የበዛው ሙያተኛ በአንድም በሌላም ዲግሪዎችን እየሰበሰበ ነው፡፡ ችግሩ ግን ጋናዊው ኢኮኖሚስት ጆርጅ አይቴ እንደሚሉት፣ ‹‹የአፍሪካ ምሁራን ችግር ከበዝባዥ መንግሥታት ጋር እየተሞዳሞዱ የግል ጥቅማቸውን የሚሳድዱ መሆናቸው ነው፤›› እንዳያስብል መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡

- Advertisement -

      በአገራችን የዕውቀት፣ የክህሎትና ቁርጠኝነትም ይሁን የተቆርቋሪነት ደረጃው መለያያት እንደተጠበቀ ሆኖ ቶማስ ሶዌልን እንደሚለው፣ ‹‹የአዕምሮ ብቃትን (Mental Capacity) ተጠቅሞ ሐሳብ በማመንጨት ለኅብረተስብ ጥቅምና ለአገራዊ ፋይዳ ሐሳቡን የሚተገብር ምሁር ማግኘት ግን ትልቁ ችግራችን ነው፤›› ማለት ግነት የለውም፡፡ በዚህ ላይ ምሁራዊ አድርባይነትና ካፒታሊስታዊ የመደብ ፍላጎት ጫናው ቀላል እንዳልሆነ የታወቀ ነው፡፡ አሁን የሚፈለገው እነዚህን ነባራዊ እውነታዎች የሚቀይር ቁርጠኝነትና ትጋት ሊሆን ይገባል፡፡

በዘንድሮው የዓብይ (ዶ/ር) ካቢኔ ግማሽ ያህሉ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ የገፉ ናቸው፡፡ በሚኒስትር ዴኤታ ደረጃ ካሉትም ከ30 በመቶ በላይ ይደርሰዋል፡፡ እንደ አማራ፣ ደቡብና ኦሮሚያን በመሰሉ ክልሎችም ከሞላ ጎደል የዚሁ ዓይነት ነፀብራቅ ይታያል፡፡ በምርምር ተቋማት፣ ዩኒቨርሲቲዎችና ልዩ ልዩ መንግሥታዊ ተቋማት ያለው የፖለቲካ ልሂቅ የሚናቅ ደረጃ ላይ የሚገኝ አይደለም፡፡ የእነዚህ ምሁራን መበርከት ከነባሩ ካድሬ ብዛት አንፃር ሲታይ መንግሥት ለቢሮክራሲው መለወጥና ለብልፅግና ያለውን ፍላጎት ከማንፀባረቁ ባሻገር፣ ምሁር የተባለው የአገራችን የፖለቲካ ልሂቅ ላይ የወደቀውን ሸክም ያመለክታል፡፡

      ከዚህ አንፃር መንግሥት ከዚህ ቀደም ተጀምረው የተስተጓጎሉትን የዕድገትና የለውጥ ዕቅዶችን በመከለስም ሆነ የራሱን የብልፅግና የጥርጊያ መንገዶችን በመቀየስ፣ በፍጥነት ወደ ልማት ለመመለስና የምሁራንና የሕዝቡን አቅም ለመጠቀም ትኩረት መስጠት ይጠበቅበታል፡፡ አገሮች በፖሊሲያቸውና ባስቀመጡት ግብ መጠን ያላቸውን ሀብትና ሌላ ግብዓት ከአንዱ የኢኮኖሚ ዘርፍ ወደ ሌላው የኢኮኖሚ ዘርፍ በከፍተኛ መጠን የሚያዘዋውሩበት የፖሊሲ አማራጭን አስቀምጠው የሚተጉት፣ በእንዲህ ያለው ጊዜ መሆኑንም ማስታወስ ግድ ይለዋል፡፡

እርግጥ ነው አሁን ጊዜው የመዋቅር ማስተካከያ (ስትራክቸራል አጀስትመንት)  አይደለም፡፡ ጊዜው የመዋቅር መሠረታዊ ለውጥ (ስትራክቸራል ትራንስፎርሜሽን) ወይም ዕድገትና ብልፅግና  መመዝገብ ያለበት ነው፡፡ ያለ ዕውቀትና ክህሎት ብሎም ያለ ቴክኖሎጂና ተወዳዳሪነት አነስተኛ ገቢ ያላቸው አገሮች ወደ መካከለኛና ከፍተኛ ገቢ ባለቤትነት ሊሸጋገሩ አይችሉም፡፡ ለዚህ ዓይነት ሥር ነቀል ለውጥ መሠረቱ ደግሞ ከጠራ ሐሳብ በመነጨ የማኅበረሰባዊ ለውጥ መሣሪያ ላይ ተመሥርቶ የሚያቅድ፣ ሕዝብን የሚነቃንቅና ሒደቱን እየገመገመ የሚመራና የሚፈጽም መዋቅር መኖር አለበት፡፡ የመንግሥት ትልቁ ሸክምም ይኼው ነው፡፡

     ለአብነት ያህል የአንድን አገር አጠቃላይ ዓመታዊ ገቢ በፈጣን ሁኔታ ለማሳደግ የሚቻለው ከግብርና የኢኮኖሚ ዘርፍ ወደ ኢንዱስትሪ መሸጋገር ሲቻል ነው፡፡ ቴክኖሎጂ በከፍተኛ መጠን በመጠቀም በየዘርፉ ምርታማነትን በብዙ እጥፍ ማሳደግ ሲቻል ነው፡፡ ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገው ሽግግር በከፍተኛ መጠንና ጥራት የሥራ ዕድልን ይፈጥራል፡፡ የነፍስ ወከፍ ገቢን ያሳድጋል፣ የተለያዩ ዘርፎችን ያበዛል፣ የወጪ ንግድንና ከዚያ የሚገኘውን ገቢ በብዙ እጥፍ ይጨምራል፡፡

    ጉዳዩ እሴት የመጨመር ነው፡፡ የግብርናውን ዘርፍ ምርቶች እንዳሉ በጥሬው ለአገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ገበያ ከማቅረብ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በጥቃቅንና አስተኛ፣ በማኑፋክቸሪንግና በኢንዱስትሪ ውስጥ አሳልፎ እሴት ጨምሮ ማቅረብ ለአምራቹም ሆነ ለገበያው መጠነ ሰፊ ገቢ ያስገኛል፡፡ ለዚህ ደግሞ ጠንካራ፣ የሚመጋገብና የሚደጋገፍ መዋቅርና የሰው ኃይል ዕውን መሆን አለበት፡፡

    ከዚያ በኋላ? ሌላ ትልቅ ሥራ አለ፡፡ ወጪ ቆጣቢ፣ እሴት ጨማሪና ውጤታማ ተግባር፡፡ ለምሳሌ አሁን እያልን ያለነው የቆዳ ሀብታችንን በጥሬው ከመላክ ወደ ጫማ፣ ጃኬት፣ ቦርሳ፣ ወዘተ. ቀይረን እንላክ ነው፡፡ ይህን የምናደርግበት ቴክኖሎጂ ማለትም የጫማ ፋብሪካው ማሽነሪ ግን ከውጭ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ተገዝቶ የሚመጣ ነው፡፡ ወደፊት የሚሆነው ይህ አይደለም፡፡ የጫማ ሀብትን ለገበያ ለማቅረብ የሚያስፈልገን የጫማ ፋብሪካ ሳይሆን፣ የጫማ ፋብሪካውን ራሱን እዚሁ የሚሠራ ሌላ ግዙፍ ፋብሪካ ነው፡፡

     ቴክኖሎጂውን ማስመጣት ሳይሆን እዚሁ መሥራት ነው ያለብን፡፡ ይህ ደግሞ የብረት ማዕድን ሀብትን ማጎልበት፣ ብረቱን ከአፈር ለይቶ የሚያወጣና የሚያቀልጥ መሥራትና ሞዴል ማውጣትን ይጠይቃል፡፡ ይህ በተራው ደግሞ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨትን (ኤሌክትሪፊኬሽን) የግድ ይላል፡፡ ያለ ኤሌክትሪክ ኃይል የትም መድረስ አይቻልም፡፡ እዚህ ላይ ያለፈው ሥርዓት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራበት ያለውን መስክ ከልሶ መጠናከር ግድ ነው፡፡

     የሶቪየት ኅብረት መሪ የነበረው ጆሴፍ ስታሊን ‹‹Electrification of Russia›› የሚል የፖሊሲ መጽሐፍ ነበረው፡፡ መጽሐፉ በትራንስፎርሜሽን በተለይይ በኤሌክትሪፊኬሽን ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በአገራችን አሁን እየተገባደደ ያለው የታላቁ ህዳሴ ግድብ፣ የጊቤ (1፣ 2 እና 3)፣ የተከዜ… ወደፊትም በተለያዩ ወንዞቻችን ላይ የሚሠሩት የኃይል ማመንጫ ሥራዎች ለቤት፣ መብራትና ለከተማ ባቡር ማንቀሳቀሻና ለጎረቤት አገሮች ከመሸጥ እጅግ በጣም ባለፈ መጠን ለአገራችን ኢንዱስትሪላይዜሽን ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ለአፍታም መዘንጋትም አይገባም፡፡

      በአንድ አገር ብልፅግና ውስጥ የኢኮኖሚ ዘርፍ የምንላቸው ግብርና፣ አግሮ ፕሮሰሲንግ፣ ማኑፋክቸሪንግና ኢንዱስትሪ፣ የኃይል ማመንጨትና ማከፋፈል ዘርፍ ዓይነቶቹ ብቻ አይደሉም ሚናቸው የሚጎላው፡፡ የሰው ኃይል ሀብት ልማት፣ መልካም አስተዳደር፣ የኢኮኖሚና የፋይናንስ አስተዳደር፣ መሠረተ ልማት፣ ትምህርት፣ ጤና፣ ትራንስፖርት፣ የውኃ ልማት፣ ሥራ አጥነትን መቀነስ፣ ድህነትን ማጥፋት፣ ኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን፣ አካባቢ ጥበቃ፣ ወዘተ. ሁሉ ላይ ጥራትና ስፋትን በሁሉም ዘርፍ ማረጋገጥ የማይነጣጠሉ ሥራዎች መሆን አለባቸው፡፡

ዋናው ጥያቄ ለእነዚህ ዘርፎች እንደ መንግሥትና እንደ ሕዝብ የሚኖረን አቀራረብ ምንድነው? ዝንባሌያችን ወይም አመለካከታችን እንዴት ነው? የቅደም ተከተል አሰጣጣችን በዋናዎቹ መነሻዎቻችን መመርመር ሊሆን ይገባል፡፡ በተለይ አሁን የተዋቀረው መንግሥታዊ መዋቅርና ምሁር የበዛባት መንግሥታዊ ሥሪት፣ ነባራዊውን ሁኔታ በመመርመር የለውጥ መልህቅ መትከል ግድ የሚለው ይሆናል፡፡ እየመጣ ካለው ዓለም አቀፋዊ ጫናና አገራዊ ሁነታ አንፃርም ራሱን ማዘጋጀት ግድ ይለዋል፡፡

ምንም ተባለ ምን ለመሠረታዊ ለውጥ የቆረጠ አመራር፣ ሩቅ አሳቢና ግልጽ የሆነ የጠራ ራዕይ ያለው መሆን አለበት፡፡ አመራሩ በኢኮኖሚው ውስጥ ያሉትን ኃይሎች በሙሉ ከልማት ራዕዩ ጀርባ ማሠለፍ መቻል አለበት፡፡ አመለካከቱን ከመዋቅር ማስተካከያ ወደ መዋቅራዊ መሠረታዊ ለውጥ መቀየር አለበት፡፡ የመሠረተ ልማት ጥራትና በሰው ኃይል ልማት ላይ ትኩረት ያደረገ መሆን አለበት፡፡

    አመራሩ በተለይ አዲሱ አመራር አገራችን በዘላቂነት ከቀውስ መውጣትና ብልፅግና መሳካት፣ በቅድሚያ የአገር ውስጥ ሀብትንና ግብዓትን ለማንቀሳቀስ መሥራት አለበት፡፡ የረዥም ጊዜ ዕቅዶችን ማዘጋጀት የሚችልና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን ማስተባበር የሚችል የቢሮክራሲ አቅምን መገንባትና ማጠናከር ይጠበቅበታል፡፡ ማኅበረሰቡን በተለይ የሴቶችንና የወጣቶችን የኢኮኖሚ አቅም ማጎልበትም ለነገ ሊባል የማይገባው ሥራ ነው፡፡

ለተጀመረው ለውጥ ሥር መስደድና መጠናከር፣ ሴቶች በፖለቲካና በኢንቨስትመንት ያላቸው ተሳትፎ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ማደግ አለበት፡፡ የማኅበረሰቡን ግማሽ ያህል ቁጥር ያላቸው በመሆኑ ለልማታችን ያላቸው አስተዋጽኦ በጥልቅ መታመን አለበት፡፡ የሴቶች ተሳትፎ ይረጋገጥ ስንል በፖለቲካ ውስጥ ያላቸውን የፓርላማ/የአስፈጻሚ ወንበር ድርሻ ማለት ብቻ አይደለም፡፡

ይልቁንም በፖለቲካ ተሳትፏቸው ወይም በተመራጭነታቸው በፓርላማ በሚቀርቡ ብሔራዊ ጉዳዮቻችን ላይ ያላቸውን አሻራ ማሳደግ፣ በተለይም በየፖሊሲ ሰነዶቻችን ውስጥ የራሳቸውን (የሴቶችን ሚናና ጥቅም) ለማስከበር የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ወደ ከፍታ ማሸጋገር አለባቸው ማለት ነው፡፡ ከፖለቲካው ውጭ በኢንቨስትመንት ዘርፍ አቅም እንዲኖራቸው ልናበቃቸውም ይገባል፡፡ ይህ እነሱ ቁጪ ብለው የሚጠብቁት ነገር ሳይሆን፣ ራሳቸው በተሳትፏቸውና በሚናቸው ታግለው የሚቀዳጁት ውጤት  መሆኑ ግን ሊዘነጋ አይገባም፡፡

ለአገር ብልፅግናው ፍጥነት አመራሩ ሊያንቀሳቅሰው የሚገባው ሌላው ግብዓት ወጣቱ ኃይል ነው፡፡ ምክንያቱም ወጣቱ ትኩስ ኃይል ነው፡፡ ለልማት የሚሆን ጉልበት አለው፡፡ ከቴክኖሎጂ ጋር የተዋወቀ ነው፡፡ ወይም በቀላሉ ሊተዋወቅ የሚችል ነው፡፡ የፈጠራ ችሎታ አለው፡፡ በቀላሉ ማስተባበር ይቻላል፡፡ ከተሠራበት የወጣቱ ሐሳብ በተለያዩ ጎታች እምነቶችና አመለካከቶች የተበከለ አይደለም፡፡ አሁን በህልውና ዘመቻው እንደታየውም የወደፊቱን መጪ ጊዜ አሻግሮ ማየት የሚችል ራዕይ ያለው ኃይል እየበዛ  ነው፡፡ ይህን ወጣት ኃይል ለአገር ለውጥ መጠቀም የማይታለፍ ብሔራዊ ኃላፊነት ነው፡፡

     በሁሉም ማኅበረሰብ ውስጥ በውሱን መጠን በአቋራጭ መክበር፣ አታላይነት፣ ሥራ ለመሥራት ወይም ከታች ለመጀመር ያለ መፈለግ ወይም ቸልተኛና ዳተኛ የመሆን፣ የሱስ ተጠቂነት ዝንባሌ ቢኖርም ያለ ሴቶችና ያለ ወጣቶች የነቃ ተሳትፎ ብልፅግና ሊረጋገጥ አይችልም፡፡ ከዚህ አንፃር በየደረጃው እየተመደበና በአዲስ ተነሳሽነት ወደ ሥራ እንደሚገባ እየተጠበቀ ያለው አመራር፣ በፈጠራና በዕውቀት ላይ ተመሥርቶ የሚተገብራቸው ሰፋፊ ሥራዎች ይጠብቁታል፡፡ እንደ ደሃ አገር መሪ ከራስ ይልቅ ለሕዝብ የመኖሩ መመዘኛም ሰፊ ቦታ ሊሰጠው እንደሚገባ መዘንጋት አይገባም፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ ባለፉት 30 ዓመታትም ቢሆን ከእነ ጉድለቱ አገራችን በሥልጣኔም ሆነ በልማት እጅግ ብዙ ተራምዳለች፡፡ ምንም እንኳን በፍትሐዊነት ችግር፣ በዘረፋና በሀብት ብክነት የምንወቀስ ቢሆንም እንደ አገር አንገታችንን ቀና አድርገን የተራመድንባቸው፣ በአፍሪካም ሆነ በዓለም ዙሪያ ‹‹ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ነው››  መባላችንን መካድ አይገባም፡፡ አሁን ግን ቢያንስ እነዚህ የተጀማመሩ መልካም ገጽታዎች ተዳክመዋል፡፡ በራሳችን ውስጥ በተፈጠሩ ቀውሶች አገር ተናውጣለች፡፡ ይህንን እውነት ገለባብጦ በመቀየር በአዲስ ማርሽ አገርን ወደፊት የሚወስድ መሪና መዋቅር ነው አሁን የሚያስፈልገው፡፡ 

     ዛሬም ቢሆን በአገራችን ከሰላምና ደኅንነቱም ባሻገር በርካታ ችግሮች አሉብን፡፡ ብዙ መስተጓጎሎች አሉ፡፡ በከተማ ብቻ ሳይሆን በገጠርም የምግብ እጥረትና ችግር የሞላባቸው ሚሊዮን ቤተሰቦችን ተሸክመናል፡፡ ሥራ የሌላቸውና ተቀምጠው የሚውሉ ወጣቶች ብዙ ናቸው፡፡ የመኖሪያ ቤት ችግሩ በተለይ በከተሞች አብጦ ሊፈነዳ የደረሰ ነው፡፡ ትራንስፖርት ጥበቃ ብቻ ሳይሆን መሠረታዊ ፍላጎቶችንም ለማግኘት ሠልፍ መያዛችን እውነት ነው፡፡ የመብራትና የውኃ መቆራረጥ ችግሩ የበረታ ነው፡፡

በከተማም በገጠርም የኑሮ ውድነትና የአብዛኛው ሕዝብ ገቢ ፈጽሞ የማይገናኝበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ የብር የመግዛት አቅም ወድቋል፡፡ የአገር ውስጥ ምርት እየተጠናከረ ገበያውን እየሸፈነ ካልመጣ የመጭው ጊዜ ፈተና ከኑሮ መላሸቅ የሚመነጭ ነው፡፡ በእኛ ዕድሜ እንኳን በአንድ ብር ስምንት እንቁላል ይገዛ ነበር፡፡ አሁን ላይ አንድ እንቁላል ስምንት ብር ገብቷል፡፡ ‹‹ዋጋው እንደ ድሮ ይሁንልን›› እያልን በድሮ በሬ የማረስ ፍላጎት ባይኖረንም፣ የዋጋ ንረቱ ያውም እምብዛም የመግዛት አቅም ባልተገነባበት ሁኔታ አደገኛ ጣጣ ሊያመጣ እንደሚችል አንስተውም፡፡

      በየደረጃው አንዳንድ መሻሻሎች ቢኖሩም አሁንም የመልካም አስተዳደር ችግራችን መፍትሔ ይፈልጋል፡፡ የትምህርት ጥራት ላይ ያለን ቅሬታ አልተወገደም፡፡ በጤናው መስክ እንደ ኮቪድ-19 እና ኤችአይቪ ከመሳሰሉት ዓለም አቀፍ ወረርሽኞች ባሻገር ገና ብርቱ ሥራ ሚፈልጉ የማኅበረሰብ ችግሮች አልተወገዱም፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ከደረስንበትና ወደፊት ልንደርስበት ከምንፈልገው ዕድገት አንፃር ሲታዩ ችግሮቻችን ተስፋ የሚያስቆርጡ አይደሉም፡፡ የሚፈልጉት ቁርጠኛ መንግሥትና ሕዝብን ብቻ ነው፡፡

     የዕድገት ሒደት በራሱ ጊዜ ይዞት የሚመጣው ችግር አለ፡፡ አሁን ያለው ዕድገት ብሔራዊ ቅርፅ ያለው ነው፡፡ ድሮ የምግብና የመጠጥ ዋጋ ዝቅተኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ያኔ መንገድ፣ መብራት፣ ውኃ፣ መሠረተ ልማት፣ ትምህርት ቤትና ጤና ተቋም የለም፡፡ የእናቶችና የሕፃናት ሞት ቁጥር የትየለሌ እንደነበር እናውቃለን፡፡ ከተማ አካባቢ የተሻለ ቢመስልም በገጠር ያለው 90 በመቶ ሕዝብ የኑሮ ሁኔታ እንዴት እንደነበር እናስታውሳለን፡፡

      ዛሬ ባለንበት ሁኔታ የተከናወኑትን የዕድገትና የልማት ሥራዎችና የተመዘገቡትን ውጤቶች ስንመለከት፣ አሁን ላሉብን ጊዜያዊ ችግሮች ጥንፋፊ ትዕግሥት ልናጣ አይገባም፡፡ ሁሉም ችግሮች በየደረጃው የሚፈቱ መሆናቸውን ከመገንዘብ ባሻገር በየተሰማራንበት ዘርፍ በትጋት፣ በአገር ፍቅር ስሜትና በታማኝነት መረባረብ ይኖርብናል፡፡ ለዚህ ደግሞ በአብዛኛው ምሁራንና አሰላሳይ የሚባሉ አካላትን እየሰበሰበ ያለው አዲሱ መንግሥት ከፍተኛ ኃላፊነት ወድቆበታል፡፡

አገራችን መድረስ ከምትፈልግበት የልማትና የዴሞክራሲ ከፍታ አንፃር፣ መንግሥት የሚከተለውን አዲስ ወይም የተሻሻለ ፖሊሲ በጠንካራ ዕቅዶችና የአፈጻጸም መተግበሪያቸው አስደግፎ መምራት አለበት፡፡ አነስተኛ ገቢ ያላቸው አገሮች በሙሉ እንደ ችግራቸው አመል የኢኮኖሚ ተግባራትን ቅደም ተከተል ይለዋውጡ ይሆናል እንጂ፣ ያለዚህ ዓይነቱ ኢኮኖሚያዊ ብልፅግና ፖሊሲና ዕቅድ ወደ ዕድገት ለመመንጠቅ የሚችሉበት ሁኔታ የለም፡፡ ዋናው ነገር የአመራሩ ብቃትና ቁርጠኝነት፣ የዕድገትና ለውጡ ባለቤትና ተጠቃሚ የሚሆነው መላው ሕዝብ ተሳትፎና ተቆርቋሪነት መረጋጋጡ ነው፡፡

እዚህ ላይ በልዩ ትኩረት መስተካከል ያለበት አንዱ ጉዳይ የአገራችንን ሰላምና ደኅንነት፣ የዜጎችንም በየትኛውም አካባቢ በነፃነት ተንቀሳቅሶ የመሥራትና የመኖር መብትን የማረጋገጡ ጉዳይ ነው፡፡ አሁን እየታየ እንዳለው የሰው ጉልበት፣ ዕውቀትም ሆነ ካፒታል እንደፈለገው በዚያም በዚህም መንቀሳቀስ ሳይችል ሊመጣ የሚችል ብልፅግና ህልም ከመሆን አያልፍም፡፡ እንዲያውም ቀስ በቀስ የአገር መናወጥ ምንጭ እየሆነ ችግር ነው የሚቀፈቅፈው፡፡

     በመሠረቱ እኮ ማንኛውም ዜጋ ከየትኛውም ብሔርና ከየትኛውም ክልል ወደ የትኛውም ክልል ሄዶ የሥራ ዕድሉ ተጠቃሚ ለመሆን፣ የመዘዋወር መብቱ በሕገ መንግሥቱም የተረጋገጠ ነው፡፡ ይህን ሕገ መንግሥታዊ ምሰሶ መነቅነቅ ደግሞ  አይቻልም፡፡ ለጥቂት ፅንፈኞችና አገር ጠሎች ሲባል ይህ ዓይነቱን ተፈጥሯዊና ሕገ መንግሥታዊ ፀጋ ማፍረስ መዘዙም ብዙ ነው፡፡ እናም አዲሱ አመራር በልዩ ትኩረት ሊሠራበት የሚገባው ጠቃሚ የማኅበረ ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ እሴት መነሻ ከዚህ ይቀዳል ማለት እሻለሁ፡፡

       በማንኛውም ደረጃ የሚያቆጠቁጥ ዘረኝነትን፣ ትምክህተኝነትንና ጥገኝነትን ከሥሩ መንግሎ መጣል ያስፈልጋል፡፡ የሕዝባችንን አንድነት መጠበቅ አለበት፡፡ ችግራችንን በመነጋገር እንፍታ፡፡ ተቃውሞ አይኖርም ማለት አይደለም፡፡ ተቃውሞ መኖር አለበት፡፡ መጥፋት የለበትም፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያዊ ጨዋነታችንንና ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸውን የመቃወም አስተሳሰቦች መከተል ዛሬ እንዲጀመር መትጋት ያስፈልጋል፡፡ የመነጋገር፣ የመደራደርና የመቻቻል ባህልም መጠናከር ይኖርበታል፡፡

      በመጨረሻም በማንኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ ያሉ ምሁራን ለለውጥና ዕድገት ያላቸውን ወሳኝ ሚና መረዳት ጠቃሚ ነው፡፡ ነገር ግን በእኛም ሆነ በብዙ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ እንደሚታየው ምሁራን በጠባብነት/ትምክህት የታመሙ፣ አድርባይነት የከበባቸው፣ የግል ጥቅም ፈላጊነታቸው የበዛና ከፍ ዝቅ ብለው የማይሠሩ ሆነው መታየታቸው የተለመደ ነው፡፡ ታሪክ ከፊታቸው ቆሞ፣ የሕዝብ አደራ ተሸክመው አሁን አገራችንን ሊመሩ የተሰናዱ ወገኖች ግን በተቻለ መጠን ከዚህ ዓይነቱ ልክፍት ወጥተው ሕዝባቸውን እንዲያገለግሉ አደራ እንላለን፡፡ ግዴታቸውም ነው፡፡

      ከዚሁ ጎን ለጎን የአገር ብልፅግናም ሆነ የኅብረተሰብ ለውጥና አጠቃላዩ የአገራችን ሁለንተናዊ እምርታ ሊረጋገጥ የሚችለው አገራችን ሰላም ስትሆን ብቻ ነው፡፡ ሰላም ውድ ዋጋ የሚከፈልበት ተቀዳሚ አስፈላጊ ግብዓት ነው፡፡ ሰላም ከሌላ ዕድገት የለም፣ ልማት የለም፣ ብልፅግና የለም፡፡ ሌላው ቀርቶ ያለ ሥጋት ወጥቶ መግባት የለም፡፡ ስለዚህ ለአገራችን ሁለንተናዊ ሰላምና ደኅንነት መትጋትና መረባረብ የሁላችንም ኃላፊነት መሆኑን መዘንጋት አይገባም፡፡  

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው  [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

      

 

 

   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...