በተስፋ አራጋው ድረስ
ውሎ እስከሚነጋ መልካም ወሬ የምንሰማው መቼ ይሆን….? በውሎ ዘገባ ላይስ መልካም ነገር ብቻ የምናዳምጥበት ቀን መቼ ነው….? በሰው ልጆችስ ላይ የሚደርሰው ዕርዛትና ረሃብ፣ ቸነፈርና ሥቃይ የሚያባራበት ጊዜ እንዴት ይመጣ ይሆን….? መቼ ይሆን በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙ ግፎች፣ ክፉ ሥራዎችና የፖለቲካ ቁማር ሰቆቃዎች መታየት የሚያቆሙት…..? አደጉ ከሚባሉ አገሮች የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሴራ ነፃ የሆነች ዓለም ዕውን ሆና የምናየው እንዴት ይሆን…? የሚያውቅ የለም፡፡
ጤነኛ አዕምሮ ኖሮት እንደ ሰው ለሚያስብ ሁሉ የአሜሪካ አየር ኃይል 1109 ግዙፍ አውሮፕላን፣ ከአፍጋኒስታን ካቡል ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲነሳ የነበረው ትዕይንት መኖሩን እንደሚያስጠላው አልጠራጠርም፡፡ የሆነውን ነገር በአካልና በቦታው ኖሮ ለተመለከተም ይሁን የተቀረፀውን ቪዲዮ በዜናና በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ ተለጥፎ ያየ፣ ወይም ወሬውን በስሚ ስሚ ለሰማ በእውነትነት ሰቅጣጭና ዘግናኝ ነበር፡፡
ሁነቱ የተከሰተው የታሊባን አማፅያን የአፍጋኒስታንን በርካታ ግዛቶችና ከተሞች በመቆጣጠሩ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. ኦገስት 15 ቀን 2021 የአገሪቱን ዋና ከተማ ካቡልን መቆጣጠራቸውን፣ የአገሪቱ ርዕሰ ብሔርም ከአገር መውጣታቸውንና አሜሪካም ዲፕሎማቶቿን ከኤምባሲዋ በሔሊኮፕተር ማስወጣት መጀመሯን ተከትሎ፣ ባለፉት ቀናት አፍጋናውያንና በካቡል የነበሩ ነዋሪዎች ቤተሰቦች የአማፂውን ኃይል በመፍራት ለመሸሽ ከነበረው ሁኔታ ጋር የተያያዘ ነው፡፡
አንዳንድ አፍጋናውያን ከተወሰነው የሞት አደጋ ቢያመልጡም የወደፊት ሕይወት ዕጣ ፈንታቸው እርግጠኞች መሆን እንዳልቻሉ በመናገር፣ ከአፍጋኒስታን መውጣት ቁርጠኛ ውሳኔያቸው ስለነበር የዚያችን አገር ምድር ለመልቀቅ የነበው ትንቅንቅ፣ የቆይታቸውን ፍርኃት የሚያመላክት የሽሽት ፍላጎት የፈጠረው ሁነት ነበር፡፡
በሰዎች ማዕበል እንደተወረረ የአየር ኃይሉ ግዙፍ አውሮፕላን ለመብረር ማኮብኮብ ሲጀምር ከጎማው ሥር፣ በሞተሩ አካባቢ፣ በክንፎቹ ከላይና ከክንፎቹ የተለያዩ የውጭ አካላት ላይ ለመንጠላጠል እየሞከሩ የነበሩትን የዋሃን ካቡላውያን ሐዘናቸው በሐዘን ያስቆዝማል፡፡
ግዙፉ የአሜሪካ አየር ኃይል አውሮፕላን በምድር ላይ ሲያኮበኩብ በጎማውና በሞተሩ የሚጎዳውንና ማኮብኮቢያውን ለቆ በአየር ላይ ሲንሳፈፍ፣ በአውሮፕላኑ የውጭ ክፍሎች ተንጠላጥለው የነበሩት ሰዎች ትናንሽ እየሆኑ ሲወድቁ ምሥሉን ቀርፆ የለጠፈው በቀለም እየከበበ ሲያሳየን ልባችን በሐዘን ሲቃ ደምቶ የአሜሪካን የጭካኔና የግፍ ጫፍ ተረድተንበታል፡፡
የአፍጋኒስታን አማፅያን ቡድን መሪዎች ታሊባን ዋና ከተማ ካቡልን ከተቆጣጠረ በኋላ በዶሃ ስምምነት መሠረት፣ የአሜሪካም ሆነ የሌሎች አገሮች ኃይሎች እስከ ዲሴምበር 31 ድረስ ባለው ጊዜ ማንኛውም የውጭ ኃይል ከአፍጋኒስታን ምድር ለቆ እንዲወጣ በባለሥልጣናቱ አማካይነት ቁርጠኛ ትዕዛዝ ሲተላለፍ አሜሪካም ከመስከረም 11 ቀን 2001 ጥቃት በኋላ ገብታ የቆየችበትንና ሮሃድ አይስላንድ የሚገኘው ጆን ብራውን የግል ዩኒቨርሲቲ እንዳጠናው፣ እ.ኤ.አ. ከ2001 እስከ 2019 በነበሩ ዓመታት ወደ 975 ቢሊዮን ዶላር እንዳስወጣ የሚነገርበትን በአፍጋኒስታንን አሸባሪነትን መከላከል፣ የአገሪቱን ሰላም ማስከበርና ዴሞክራሲያዊ መንግሥትን መደገፍ በሚል ውስጠ ወይራ ሐሳብ በ‹‹አውቅ ባይ ቅቤ አንጓች›› አስመሳይነት ስታቡካካት ለ21 ዓመታት ቆይታ፣ ተልዕኮዋን በሽንፈት አጠናቃ ለመውጣት ተገድዳለች፡፡
የአሜሪካ ወታደራዊ ኃይል በቆይታው እንደተባለው የታሊባንንና የአልቃይዳን የአሸባሪነትን ተልዕኮ ከአፍጋኒስታን መንግሥት ጋር አብሮ በመዋጋት በአገሪቱ ውስጥ ሰብዓዊ መብት እንዲከበር ለማድረግ በመንግሥት የፀጥታ ሥራዎቻቸው ውስጥ አብረው ሲሠሩ የነበሩ ሲሆን፣ ከተማዋ በአማፅያኑ ቁጥጥር ሥር ስትውል ለአማፅያኑ መጥፋትና መዳከም ሲሠሩ የነበሩ ወገኖች ጭምር ለሕይወታቸው ሥጋት ገብቷቸው ከሰላም አስከባሪዋ አሜሪካ ጋር አብረው መውጣት ወይም በሌላ አማራጭ ወደ አውሮፓ መፍለስ ግድ ሆኖባቸው ተማፅኖ ማቅረባቸው የሚጠበቅም ከመሆኑ ባለፈ፣ አሜሪካም ሆነች የሌሎች አገሮች መንግሥታት የእነዚህን አካላት ጭንቀት ተረድተው መርዳት ይጠበቅባቸው ነበር፡፡
አሜሪካም ሆነች ሌሎች መንግሥታት ከአፍጋኒስታን በመውጣት ሒደትና በጊዜው ጉዳይ ከወሰዱት ስምምነት አኳያ ለመፈጸም ያለው ውጣ ውረድ ጊዜ ወስዶባቸው መራዘሙን የናፈቁ ቢሆንም፣ በአማፅያኑ መሪዎች በተወሰነው ጊዜ ገደብ መሠረት ጓዛቸውን ሲጠቀልሉ ‹‹በወዳጅነት ቆይታችን እንደነበረን ቀረቤታ ይዛችሁን ውጡ፣ ከጭንቅ አውጡን›› በማለት የሚያለቅሱና እስከ ሕይወት ማጣት ዕርምጃ የወሰዱ በአውሮፕላን ማረፊያው የአየር ኃይል አውሮፕላኑን ከበው እንደዚያ እንዳልሆኑ ሲሆኑ የታዩት ካቡላውያን አሳዛኝና ምስኪን ሰዎች ነበሩ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የሚመጣው ሁኔታ ያልተመቻቸው የአሜሪካ አየር ኃይል ያንን ያህል ዘመን ሲኖር በነበራቸው ቀረቤታ አንፃር ‹‹ሲለቅ አብሮ ይዞን ይሄዳል…›› በሚል ተስፋ ወደ አውሮፓና አሜሪካ ለመሄድ የፈለጉ አፍጋናውያን ምስኪኖች፣ የሚራሩላቸው መስሏቸው አሜሪካኖችን ለመማፀን የአውሮፕላኑ በሩ ተከርችሞ እስከሚያኮበኩብና በረራ እስከሚጀምር ድረስም ከጎማው ሥር ግር ብለው ይሮጡ የነበሩ፣ በአውሮፕላኑ አካላት ተንጠላጥለው ሞተሩ ቆራርጦ የአሞራ ቀለብ እስኪያደርጋቸው መፍለስን የኑሮ ተስፋ ያደረጉ ሕዝቦች ነበሩ፡፡ ሆኖም የሆነው ነገር ያሳዝናል፡፡
ይህ ሰቆቃ መነሻው ምን ይሆን….? ሕዝብ ምን ኃጢያት ኖሮበት ይሆን በዚያ ዓይነት የሰቆቃ ዕዳ የሚገረፈው…..? የሰብዓዊ መብት አስከባሪ አገር ነኝ ከሚል መንግሥት ይህ ግፍ እንዴት ሊመጣ ቻለ…? በሚል መጠየቅም የጤነኛ አዕምሮ መገለጫ ነው፡፡
እርግጥ ነው ‹‹The USA has been occupying Afghanistan since 2001. Why? Both supporters and opponents of US Afghan policy give murky answers. Supporters of US efforts say they are in the country to fight terrorism and help the country rebuild and move toward democracy.›› ተብሎ ይወራል፡፡
ከዚህ በመነሳትም በእውነት ሽብርተኝነትን ለመቆጣጠር ነው? ወይስ በአገሪቱ ያለውን የተፈጥሮ ማዕድን ለመቀራመት? የአሜሪካ ደጋፊዎች ይህ የሆነው በአፍጋኒስታን ውስጥ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ዴሞክራሲያዊ መንግሥትን ለማጠናከር እንደሆነ ሲገልጹ፣ የአሜሪካን በአፍጋኒስታን ውስጥ ጣልቃ መግባቷ የማይዋጥላቸው አካላት ደግሞ ‹‹… በአፍጋኒስታን ውስጥ የሚገኘውን ለኮምፒውተሮች ቺፕ ሥራዎች ጠቀሜታ ያላቸውን እንደ ኒኦዲየም፣ ኢንዲየም፣ ጋሊየምና ላንታኒየም የመሰሉ ማዕድናትን ለመዝረፍ እንዲመቻት ያደረገችው ነው…›› ሲሉ ለማጋለጥ ይሞክራሉ፡፡
ያም ሆነ ይህ አሁንም በአፍጋኒስታን የሽብርተኞች ቁጥር ጨምሯል፡፡ ትልቁና ዋናው አማፂ ታሊባን ደግሞ በጦርነቱ አሜሪካንንም ይሁን ደጋፊዎቿን እየቀጣ መላ አፍጋኒስታንን ተቆጣጥሯል፡፡ አሜሪካ በአፍጋኒስታን እጅግ ሰቆቃ ያስከተለ የግፍ ግፍ መፈጸሟን ይስማሙበታል፡፡
የቻይናው የውጭ ጉዳዮች ኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን ስለአሜሪካ ግፍ ሲገልጹ፣ ‹‹አፍጋኒስታን በወቅቱ በታሊባን አማፅያን በጦርነትና በሽብር ታምሳ ስለነበር ያንን ለመቆጣጠር በሚል አሜሪካ ሠራዊቷን አሠፈረች…›› ሲሉ ያብራራሉ፡፡ በመቀጠልም ‹‹…የኃይልና የፖለቲካ ጥቅሟን ለማስከበር እንጂ የአገሪቱ ችግር ለመቅረፍ አልነበረም የገባችው…›› ሲሉ አክለው፣ ‹‹…አሁን ደግሞ ታሊባን ተቀጥታ የውርደት ካባዋን አከናንቦ እንድትወጣ አድርጓል፤›› ይላሉ፡፡
‹‹አሜሪካ ወደ አፍጋኒስታን ሳትገባ ነበሩ ከሚባሉት አሸባሪዎች ይልቅ፣ አሜሪካ በዚያች አገር በቆየችባቸው 21 ዓመታት ገደማ ጊዜያት ተጨማሪ ሌሎች በርካታ አሸባሪ ኃይሎች ተፈጥረዋል…፤›› ሲሉ ጉዳዩን ሲከታተሉ የነበሩ አንድ የካቡል ነዋሪ ያስረዳሉ፡፡ ታዲያ የአሜሪካ በአፍጋኒስታን የመቆየት ፋይዳው ምንድን ነበር….? ሲሉ ይጠይቁና ‹‹ቆይታዋ በችግር ፈጣሪነት ወይስ በችግር አቅላይነት…? በማለት ያክላሉ፡፡
አሜሪካ በአፍጋናውያን ላይ ያደረሰችውን ከፍተኛ በደል ተከትሎ ስለጉዳዩ ሐሳቧን የገለጸች አገር ቻይና ብቻ ናት፡፡ ቻይና በውጭ ጉዳይ ኮሙዩኒኬሽኗ አማካይነት ሐሳቧን ስትገልጽ፣ ‹‹አሜሪካ በአፍጋኒስታን ቆይታዋ ከአሥር ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ስደተኛ እንዲሆኑ ማድረጓን ታስረዳለች፡፡ የአሜሪካ ግፍና በደል በአፍጋኒስታን በዚህ ሳያበቃ በርካታ አሸባሪዎች እንዲፈጠሩ ከማድረጓም በዘለለ፣ ከ1,600 በላይ ሕፃናት በኔቶ መራሹ ሠራዊት በአየር ጥቃት እንዲደበደቡ አድርጋለች…›› በማለት፣ ‹‹ከዚህ ባሻገርም ከ174,000 በላይ አፍጋኖችን (70,000 የአፍጋን ወታደሮች፣ ፖሊሶችና ከ47,000 በላይ ንፁኃን አፍጋናውን) እንዲገደሉ የሠራች ግፈኛ አገር ሆና ሳለ፣ አሁን ደግሞ በዚህ ሰቆቃ ውስጥ የቆዩ አፍጋናውያንን ‹የራሳችሁ ጉዳይ› ብላ በባሰ ችግር ውስጥ ጥላቸው መውጣቷ ዘግናኝ ነው…›› ብላለች፡፡
የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ዲፓርትመንት ቃል አቀባይ ሊ ጃንዝሆ አሜሪካ በአፍጋኒስታን ለዓመታት የፈጸመቻቸውን ኢሰብዓዊ ሰቆቃዎችና ግድያዎችን በአኃዝ በመዘርዘር ካጋለጡ በኋላ፣ ‹‹አሜሪካ በደም የተጨማለቀ እጇን በጥቂት ጠርሙሶች ውኃ ሁሉንም ኃጢያቶች ታጥባ መሄድ ያምራታል እንዴ?›› ሲሉ አጥብቀው ይሞግታሉ፡፡
ሰውየው በዚህ ሳያበቁ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እያለች የምትነዛውን ዲስኩር እንድታቆም፣ ዓለም ከእንግዲህ የሰብዓዊ መብት የአሜሪካን ወሬ እንደማይገዛውና አስመሳይነትም እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ቃል አቀባዩ፣ ‹‹ከዚህ ወዲያ አሜሪካ የሰብዓዊ መብት እያለች የምትጠቀምበትን የአስመሳይ የፖለቲካ ቋንቋዋን እንድታቆም ያስፈልጋል…›› ይላሉ፡፡
በዚህ በአፍጋናውያን ሰቆቃና በዚያን ዓይነት የሰው ልጅ ከአውሮፕላን ላይ ከሰማይ እየተቆራረጠ ሲወድቅ በታየበት ኩነት፣ አሜሪካ የዓለም ወራዳ አገር ለመሆን ቁልቁለቷን ማጋመሷን የሚያሳይ ነበር፡፡ ይህ በሆነ በቀናት ውስጥ ግን አሜሪካንን አንገት የሚያስደፋ አጸፋውን እንደምትመልስ ዛቻ ጭምር የሰጠችበት ፍንዳታ በካቡል አውሮፕላን ማረፊያ አካባቢ በጥቃት መልክ ተከስቶ በ133 ሰዎች ላይ ጉዳት ሲከሰት፣ 13 የአሜሪካ ጦር አባላት ሲሞቱ በሞትና 18 ወታደሮች ደግሞ መጎዳታቸውን ሰማን፡፡
ይህ ጉዳይ በመጀመሪያ በአገሮች ሉዓላዊ መብት ቀልደው አገር እናረጋጋለን በሚል ሰበብ የራሳቸውን ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ሲያጣድፉ በከረሙ አሜሪካውያን ላይ ዋጋ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ሲሆን፣ በታሊባን ለደረሰባት እጅግ አሳፋሪ ሽንፈት አንዱ መገለጫ ተደርጎም ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሁነት የሰው ልጆችን ከምንም ያለመቁጠር ተግባርና ሰውን የትንሽ ዕቃ ያህል እንኳን አለመቁጠር ሰብዓዊና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራው በዕለት ሊመለስ የሚችል እንደሆነ ማሳያ ነው፡፡
የሰው ልጆች የማይገፈፉና የማይቆረሱ መብቶች ሊከበር የሚችለው በተቀመጠው ዓለም አቀፋዊ ሕግ እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን፣ አሜሪካ እቆምለታለሁ ያለችውን ይኼንን በወሬ እንጂ በተግባር ልዩ የሆነውን የሰብዓዊ መብት ጉዳይ አፍጋናውያንን በእንዲህ ዓይነት ታሪክ ይቅር በማይለው የበደሎች በደል በሆነው ግፏ ለዓለም ሕዝብ አሳይታለች፡፡
በአንድ አካባቢ ያለን ሌባ ከሌብነቱ መቆጣጠር የሚችለው ሰው በመጀመሪያ ራሱን ከዚያ ዓይነት የሌብነት ተግባር በማራቅ እንጂ፣ ራሱ ሌባ የሆነ ሰው ሌባን እከታተላለሁ ቢለን የስርቆቱ ተካፋይ ለመሆን እያሯሯጠ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ የተሰረቀውን ዕቃ ለማስመለስ መሥራት የሚያስችል የሞራል ልዕልና ሊኖረው እንደሚችል መተማመኛ ሊሰጠን አይችልም፡፡
ስለሰብዓዊ መብት (Human Right)፣ ስለሰው ልጆች በሰላም የመንቀሳቀስና የመኖር መብቶች ስናወራ ራሳችን በጉዳዩ ጥልቅ ዕውቀት ከመያዛችን ባለፈ ሚዛናዊና ለአንድ ወገን የማያደላ አቋም ከመያዝ ጀምሮ የምንሰጣቸው ሰብዓዊ፣ ቁሳዊና ወታደራዊ ድጋፎች ሁሉ ችግሩን በማባባስ ረገድ ሚና ያላቸው ሊሆኑ እንዳይችሉ አልሞ መሥራትን ይጠይቃሉ፡፡
በአገራችን አሁን የሚታየው ሁኔታም ይህንን እንድናስብ ያደርገናል፡፡ ከአፍጋናውያን ብዙ እንማራለን፡፡ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ የውጭ ኃይሎች መሳተፍ ካለባቸው እንኳ ኢትዮጵያ ችግሩን ለመፍታት የምታደርገውን ጥረት ሊያግዝ በሚችል መንገድ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት መሆን ይጠበቅበታል እንጂ፣ ከዚያ ባለፈ የሚንቀሳቀሱ እጃቸውን እንዲሰበስቡ መደረግ አለበት፡፡ የእኛ ችግር በእኛ እንጂ በሌሎች ጣልቃ ገብነት እንደማይፈታልን ጠንቅቀን እናውቃለን፡፡
የአንድን አገር የእርስ በእርስ ግጭት ለማስወገድና ችግሩን ለማርገብ የገባ የሰላም አስከባሪ ኃይል ለአንደኛው ወገን ስንቅና ትጥቅ የማቀበል ሥራዎችን እየሠራ፣ በሌላ ህሊናው ደግሞ ለሰላማቸው እየሠራ እንደሆነ ቢያወራ የአገርን ማፍረስ የማፋጠን ሚና ከሚኖረው በስተቀረ ጉልህ አስተዋጽኦ ለጋራ አገር ግንባታ አይሆንም፡፡
የኢሳቱ ጋዜጠኛ መሳይ፣ ‹‹የአሜሪካን የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪነት ከምላስ ካራቴ ማለፍ አልቻለም። ፍትሕና ርትዕ መጻሕፍት ላይ የቀሩ ጌጦች ሆነዋል። ነፃነትና ዴሞክራሲ የሕገ መንግሥት ማጣፈጫ ቃላት እንጂ ከዚያ የዘለለ በመሬት ላይ የሚመነዘሩ ሊሆኑ አልተቻላቸውም፤›› ሲል የአሜሪካን የሰብዓዊ መብት አፈጻጸም ሁኔታ ምልከታውን ያስቀምጣል። ሲቀጥልም ‹‹….አሜሪካ በጭፍን እያሳየች ያለችው ሁኔታ ስለብቸኛዋ ልዕለ ኃያልነቷ ለዘመናት ውስጣችን የታተሙትን መልካም እሴቶች ፍቀን እንድናስወጣ እያስገደደን ነው…›› ይለናል። እውነትም ትናንት ለአሜሪካ የነበረን መልካም ዕይታና ጉጉት እንዲወጣልን እያደረግን እንደሆነ እረዳለሁ፡፡
የአሜሪካን በኢትዮጵያ ላይ ያላትን አስተሳሰብ ከሌሎች አገሮች እንደፈረሱትና እንደተበጣበጡት አገሮች አድርጋ እንድትወስደን አንሻም፡፡ ‹‹እኛ እናውቅላችኋለን›› የሚለውን ብሂሏን እናወግዛለን፡፡ ድሮም ኢትዮጵያውያን የነበርን አሁንም ያለን፣ ወደፊትም ኢትጵያውያን ሆነን የምንኖር ነን፡፡ እኛ እንደተባለውም ‹‹ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞትም ኢትዮጵያ›› የምንሆን ሕዝቦቸ ነን፡፡ እኛ መንግሥት የሚያደርገውን ጥረት ከመደገፍ ባሻገር በማውገዝና ሆን ብሎ በሰብዓዊ ድጋፍ ስም ሌላ ተልዕኮን የሚፈጽሙትን የማንወድ ነን፡፡ አገራችንን፣ ሉዓላዊነታችንንና መንግሥታችንን ሊደግፍ በሚችል መንገድ የሚሠራን ማንኛውንም አካል የምንተባበር፣ የምናግዝና መሆን የሌለበትንና መሆን የሚገባውን ለይተን የምናውቅ በአቋማችን የፀናን ሕዝቦች እንደሆንን የማያውቁን ካሉ እንዲያውቁን ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡
አንድ ነገር ለማየት ያህል በበርካታ ምክንያቶች በአገራችን በሰው ሠራሽና በተፈጥሮዓዊ ምክንያቶች ችግሮችና በተለያዩ ክልሎች መፈናቀሎች እንደነበሩ የምናስታውስ ሲሆን፣ ይህ የአሁኑ የአገራችን የጦርነት ክተት ከመታወጁ በፊትም ብዙ መፈናቀሎችና የረሃብ ችግሮች እንደነበሩ ይታወሳል፡፡
ሆኖም የአሜሪካ ዕርዳታና ድጋፍ እንዴት ለትግራይ ሕዝብ ብቻ ሊሆን ቻለ…? በዚህ ወቅትስ ትግራይን ብቻ ትኩረት አድርጎ ለመሥራት ማሰብ ሌሎችን የአገሪቱን ሕዝቦች እንደምን ከማየት ይመነጫል? በዕርዳታ አቅርቦታቸው ወቅትስ እነዚያን ያህል በመቶዎች የሚቆጠሩ ተሽከርካሪዎች በትግራይ ውስጥ ላለ ለተራበና በመጠለያ ውስጥ ላለ የማኅበረሰብ ክፍል ብቻ የሚደርስ በሚል ተደርድረው ለበርካታ ሳምንታት የቆዩት መኪኖችን ጉዳይ በእውነት ሰብዓዊነት ካላቸው ያስቆማቸው ችግር እስኪፈታ ድረስ፣ በሌሎች አካባቢዎች ጦርነቱ ላፈናቀላቸው ማኅበረሰቦች መድረስ የሚችሉበት ሁኔታ ሊኖር አይችልም ነበር ወይ? የሚሉትን ሐሳቦች በየመልካቸው ደርድረን ስናስባቸው የአሜሪካን ውስጠ ወይራ ሐሳብ ይገለጽልናል፡፡
ኢትዮጵያውያን እንደ ሌሎች አይደሉም፡፡ በቀላሉ የመፈራስና የመበታተን አደጋ ሊያስተናግዱ እንዳይችሉ የትውልድ ሐረግ ተብትቧቸዋል፡፡ ክፉ አሳቢዎች ቆም ብለው ማየት የሚገባቸው እኛ በተለያዩ አስተሳሰቦች መንደርተኛ የሆንን ቢመስላቸውም በአገራችን ጉዳይ አንድ ነንና አይድከሙ፡፡
ግፈኛዋ አሜሪካ ሆይ እኛና ወንድሞቻችን ሥራ መኖሩንና በሥራ ገንዘብ እንደሚገኝ አውቀን ወደ አገርሽ እየገባን በፋብሪካዎችሽ ከ16 ሰዓት ያላነሰ በቀን እየሠራን፣ አረጋውያኖችሽን እያፀዳዳን፣ እየተንከባከብንና እየጦርን፣ ሕንፃዎችሽን የተሽከርካሪዎችሽ ፓርኪንግና ዘበኝነት ተቀጥረን ሕንፃዎችሽንና መንገዶችሽን እየጠበቅን፣ መፀዳጃ ቤቶችሽን ሳይቀር እያጠብንና እያፀዳን፣ ሞኞችሽን ሳይቀር እያጫወትንና እየተንከባከብን፣ ወዘተ. በምድርሽ ሠርተን ጥሪት ለመቋጠር ባሪያዎችሽ ሆንን እንጂ የሐሳብ ድሆች እንዳንመስልሽ፡፡ ለእኛ ተርፎ ለሌሎችም እንሆናለን፡፡
ለመኖር ብለን ብዙ ሆንን በሆንነውም አገራችንን ለመጥቀም አንችም ረድተሸናል፣ ውለታሽን ለሰከንድም አንረሳም፡፡ እኛም ጉልበታችንን ገብረንልሻል፣ የእኛንም ውለታ ባትረሽ መልካም ነበር፡፡ ይህ ይቅርና ‹‹እኔ አውቅላችኋላሁ›› የምትይው ቀልባችን ስለማይወደው የመጣው ይምጣ፣ያደረግሽውን አድርጊ እንጂ በአገራችን ጉዳይ ካንቺ ጋር አንደራደርምና ሰላም ስጪን፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡