Tuesday, May 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየነፀብራቅ ሐሳብ

የነፀብራቅ ሐሳብ

ቀን:

ጥበብ ከዕይታና ሐሳብ የሚመነጭ ነው፡፡ ገጣሚዎችም ካላቸው ዕይታ፣ ከማኅበረሰብ ክንውኖች፣ ከዕለት ተዕለት ተግባሮችና ሌሎችንም አጋጣሚዎች በመጠቀም ስንኛቸውን ይደረድራሉ፡፡

ሠዓሊዎች ደግሞ በመስመሮች ሐሳባቸውንና ዕይታቸውን ለተመልካች ያጋራሉ፡፡

የሥዕል ዕይታ እንደሚያየው ሰው የተለያየ ትርጓሜ ቢኖረውም ብዙ ጊዜ ሠዓሊው ከሚነሳበት ሐሳብ ብዙም የራቀ ሆኖ አይገኝም፡፡

      ‹‹ነፀብራቅ›› የሚል መጠርያ የሰጠውን የሥዕል ዓውደ ርዕይ ያዘጋጀው ሠዓሊ ኑር አበጋዝ መስከረም 29 ቀን 2014 ዓ.ም. በላፍቶ ኮንቴምፖራሪ አርት ጋለሪ ሥራዎቹን አቅርቧል፡፡ በዓውደ ርዕይ ያቀረባቸው 24ቱ ሥዕሎች ስያሜም ነፀብራቅ ነው፡፡

ሠዓሊው እንደተናገረው፣ ‹‹አልጋዬ ላይ ተኝቼ የሐሳብ ዥዋዥዌ ከዚህ ወደ እዚያ እያገላበጠኝ የጠዋት ፀሐይ በመስኮት ገብታ ፊቴን ታሞቃለች፡፡ ሸረሪት ድሯን ያደራችበትን አምፑል ንፋስ ያወዛውዘዋል፡፡ አምፑሉ ለረዥም ጊዜ ባለመፅዳቱ ክፍሌን ድንግዝግዝ አድርጋ ነው የምታሳየኝ፡፡ በመስኮት የገባችው የፀሐይ ብርሃን በአምፑል ውስጥ ሲያልፍ የአምፑል ነፀብራቅና የሸረሪቷ ድርና ጥላ በግድግዳው ላይ የተለያዩ የመስመር ስብጥሮችን ፈጥረዋል፡፡ የመስመሩ ስብጥሮች እንደ ንፋሱ ፍጥነትና ዕርጋታ ቅርፃቸው እየተለዋወጡ የውዝዋዜ ድግስ ይደግሳሉ፡፡››  

ሠዓሊ ኑር አበጋዝ

የነፀብራቅ ሥዕሎችና መነሻዎች ከላይ የተጠቀሱት መሆናቸውን፣ የመጨረሻው ሐሳብ የሆነው ደግሞ ሠዓሊው ከእንቅልፉ ተነስቶ ትኩረቱ የነበረው የአምፖሉን ነፀብራቅ ከሸረሪት ድር ጋር ያላቸውን መስተጋብር መመልከቱ ነው፡፡

‹‹ድንገት ከአልጋዬ ላይ ተስፈንጥሬ ራቁት ገላዬን በሸረሪት ድርና ጥላ በአምፖል ነፀብራቅ ውስጥ አዋሀድኩት፤›› የሚለው ሠዓሊው፣ የዛኔ ከነበረው የሰውነት እንቅስቃሴ ጋር ሲዋሀድ የሣላቸው 24ቱም ሥዕሎች፣ አንድን ሐሳብ ከብዙ እንቅስቃሴዎች ጋር ለማጋራት ያለመው መሆኑን ገልጿል፡፡ ሥዕሎቹ የተዋቀሩበት ሐሳብ ተፈጥሮአዊ የሰው ልጆች የሰውነት ቅርፅ፣ የሸረሪት ድር መስመሮች፣ የአምፖልና ሌሎችም የታከሉበት ነው፡፡

ሥዕሎች እንደ ሥነ ጽሑፍ ለመስበክ አለመሆኑን፣ ነገር ግን አንዳንዴ በመስታወት ራሱን የሚመለከት ሰው ፈገግ ሲል በሐሳቡ ከመስታወት ውስጥ ያለው ደግሞ ኮስተር ብሎ ቢመለከት የሚስማውን ሌላኛው ነፀብራቅ ለማሳየት ያለመ መሆኑንም ይናገራል፡፡

አንዳንድ ጊዜ ነፀብራቅ ከነፀብራቅ ጋር ግጭት ይፈጥራል የሚለው ሠዓሊው፣ ብዙ ጊዜ በሁለት ሐሳብ ውስጥ የሚመጡ የሐሳብ ምልልሶች ቢኖሩም ሰዎች የሚገልጹት የተወሰኑትን ነው፡፡ እነዚያን የማይገልጹት ነገሮች ደግሞ በሥዕል ይገለጻሉ ይላል፡፡

አንዳንዴ በቃላት መግለጽ የሚያቅቱ (የሚያስቸግሩ) ወይም ሐሳቡ ትክክለኛ አገላለጽ ሲታጣለት በሥዕል የሚገልጹት አሉ የሚለው ሠዓሊ ኑር፣ ሥዕልን መረዳት አይወዱም የሚባሉ ሰዎች እንኳን በቃላት መግለጽ ያቃታቸውን ሥዕል ውስጥ ሐሳባቸውን ሲያዩት ይረዱታል ሲል ያሰምርበታል፡፡

 የነፀብራቅ የሥዕል ዓውደ ርዕይ የመዘጋጀቱ መንስዔ በጽሑፍ ወይም በቃል መግለጽ የማይቻለውን በሐሳበ ሥዕል ለማሳየት ነው፡፡

ሸረሪት ድሯን ስታደራ ብዙ ትጠበብበታለች፣ ብዙ ድግግሞሽም እንዳላት የገለጸው ሠዓሊው፣ የሥዕሎቹ መልዕክቶች ቢመሳሰሉም በተለያዩ መንገዶች መቅረባቸውን ያስረዳል፡፡

ዘርፉ ላይ ያሉ ችግሮች

ብዙ የሚያስገርም ችሎታ ያላቸው ሠዓሊያን ኢትዮጵያ ውስጥ መኖራቸውን የጠቆመው ሠዓሊው፣ 110 ሚሊዮን ለሚበልጥ ሕዝብ ከአሥር ጋለሪ ያነሰ መሆኑ ዘርፉ እንዳያድግ አድርጎታል ይላል፡፡

አብዛኛው የሥዕል ጋለሪ የሚገኘው በአዲስ አበባ መሆኑን በመጠቆም፣ ኢትዮጵያ ከሥዕል ዘርፍ ማግኘት ያለበትን ጥቅም ዘርፉ ትኩረት ባለማግኘቱ ብቻ እያጣች መሆኑንም ገልጿል፡፡

በሌላ በኩል የሥዕል ዓውደ ርዕዮች እንደ አንድ የቱሪስት መዳረሻ መሆኑ እንደሚችሉ ሠዓሊው ያምናል፡፡ ቱሪስቶቸች በቆይታቸው ጋለሪዎችን እንዲጎበኙ አስጎብኚ ድርጅቶች መትጋት እንዳለባቸውም ያሳስባል፡፡

      በሠዓሊው አገላለጽ፣ አዲስ አበባ ውስጥ ያሉትን ታሪካዊ ቦታዎች ከማስጎብኘት በተጨማሪ አስጎብኚ ድርጅቶችም ሆኑ በዘርፉ የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት ከሥዕል ማሳያ ጋር ትስስር እንዲፈጠር ቢያደርጉ፣ ዓለም አቀፋዊ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ሠዓሊያንን ማፍራት ይቻላል፡፡

እግር ኳስ በየቀኑ ትንታኔ ይሠራለታል፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ነገሮችም የሚቀርቡ ቢሆንም፣ ለሥዕል ዘርፍ የሚሰጠው የሚዲያ ሽፋን ግን አነስተኛ በመሆኑ ማኅበረሰቡ ሥዕል ያለው ቦታ አነስተኛ እንዲሆን ምክንያት መሆኑንም ገልጿል፡፡

      በሌላ በኩል ትምህርት ቤቶች ታሪካዊ ቦታዎችን ለተማሪዎች ሲያስጎበኙ እግረ መንገዳቸውን የሥዕል ጋለሪዎች ቢያሳዩ ተተኪው ትውልድ ቢያንስ ለሥዕል ጥሩ ግንዛቤ ኖሮት እንዲያድግ ማድረግ ይቻላል፡፡

      ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት ከተመረቀ 23 ዓመት እንደሆነው የገለጸው ሠዓሊ ኑር አበጋዝ፣ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ከዘጠኝ በላይ የግልና በርካታ የቡድን ዓውደ ርዕዮችን ለተመልካች ተደራሽ ማድረጉን ተናግሯል፡፡

በተጨማሪም ከ11 ዓመት በፊት ከላፍቶ ሞል ባለቤት ጋር ላፍቶ አርት ጋለሪን እንደከፈቱና ብዙ ሠዓሊያን ሥራዎቻቸውን ለተመልካች ማቅረብ እንዲችሉ የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን አስረድቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመስቀል አደባባይ የመግቢያ ክፍያ ለምን?

ወጣቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ መንፈሳቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት...

በሕገ መንግሥቱ የተዋቀረው ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› እና ‹‹ሥርዓቱ›› ያስከተለው መዘዝና መፍትሔው

(ክፍል አራት) በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ) ባለፈው ጽሑፌ (በክፍል ሦስት) አሁን ያለው...

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና የመንግሥት መሪ ምሥል

በበቀለ ሹሜ በ2015 ዓ.ም. መጋቢት ወር ውስጥ ይመስለኛል በ‹ሸገር ካፌ›...

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና...