Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለኢንዱስትሪ ግብዓት ተመራጭ የሆነ የበቆሎ ምርት በሦስት ክልሎች እየለማ እንደሚገኝ ተጠቆመ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት ተመራጭ የሆነ የበቆሎ ምርት በአማራ፣ ኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች እየለማ እንደሚገኝ ተነገረ፡፡

በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ የግብርና ኮሜርሻላይዜሽን ክላስተር ዳይሬክተር አቶ ተጫነ አዱኛ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በኤጀንሲው ከተመረጡ የሰብል ምርቶች ውስጥ በቆሎ አንደኛው ነው፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ በኤጀንሲው አማካይነት በተመረጡ የሰብል ምርቶች ላይ የሚሠሩ 76 ሺሕ የግብርና ክላስተሮች እንደተደራጁ ያሉት ኃላፊው፣ ከዚህ ውስጥ 30 ሺሕ የሚሆኑት የበቆሎ ምርት ክላስተሮች እንደሆኑና እነዚህም በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች የተዋቀሩ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

ከ30 ሺሕ ክላስተሮች ውስጥ 24 ሺሕ የሚሆኑት በኦሮሚያ ከልል ውስጥ ሲገኙ፣ 3,300 በአማራ ክልል፣ እንዲሁም 2,500 በደቡብ ክልል እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

የአብዛኛው አርሶ አደር የእርሻ መሬት ከሔክታር በታች ስለሆነ፣ መሬታቸው ኩታ ገጠም የሆኑትን አንድ ላይ በማምጣት አንድ ዓይነት ዝርያን በአንድ ዓይነት የአስተራረስ ዘዴ የሚያመርቱ ከ30 እስከ 60 የሚደርሱ አርሶ አደሮች በትንሹ 15 ሔክታር የሚደርስ መሬት ላይ የሰብል ልማቱን እንዲያከናውኑ ይደረጋል ያሉት አቶ ተጫነ፣ ይህ መሆኑም ለአርሶ አደሩ የሚሰጠውን የሜካናይዜሽን አቅርቦትና  ሥልጠናዎችን አንድ ላይ ለመስጠት ያስቻለ የአርሶ አደር ምርት ክላስተር (Farming Production Cluster) እንዲቋቋም እንዳስቻለ ተናግረዋል፡፡

ብዙውን ጊዜ አርሶ አደሩ በተናጠል ሲያመርት በሔክታር የሚገኘው ከ20 ኩንታል በቆሎ ፈቅ እንደማይል ያስረዱት ዳይሬክተሩ፣ በሔክታር የሚገኘው 40 ኩንታል ነው ተብሎ ቢወሰድ፣ ክላስተሪንግ በሚባለው አሠራር በአማካይ በሔክታር ከ60 ኩንታል በላይ እንደተገኘ ጠቁመዋል፡፡

በክላስተሪንግ አማካይነት የሚመረተው የበቆሎ ምርት ጥራቱ የተሻሻለ ስለሚሆን ለኢንዱስትሪዎች ግብዓትነት ተመራጭ መሆኑን የተናገሩት አቶ ተጫነ፣  በዚህ ወቅትም ይህን ምርት በስፋት የማምረቱ ሒደት እንደቀጠለ ገልጸዋል፡፡

ለአብነት በአማራ ክልል በመጪው ታኅሳስ ወር መጀመርያ ከሚሰበሰበው የበቆሎ ምርት 15.8 ሚሊዮን ኩንታል ምርት የሚጠበቅ ሲሆን፣ ይህም በ25 ወረዳዎች፣ በ541 ቀበሌዎችና በ3,332 ክላስተሮች በተደራጁ 570,995 አርሶ አደሮች የለማ ነው ተብሏል፡፡

የበቆሎ እርሻ ምርቱ 263,380 ሔክታር መሬት የሚሸፍን እንደሆነ ያስታወቀው ኤጀንሲው፣ ይህም ምርት በሚሰበሰብበት ወቅት ሰፊ የአገር ውስጥ ገበያ ድርሻ እንደሚኖረው ገልጿል፡፡

ሸጦ ማምረት (Contract Farming) የሚባለው ምርቱ ሳይመረት የማስማማት ሥራ ሌላው በኤጀንሲው የማከናወን ተግባር እንደሆነ የገለጹት አቶ ተጫነ፣ ‹‹Value Chain Alliance›› የሚባል መድረክ እንዳለና በየሦስት ወሩ የግብርና ሥራውን የተመለከተ ሁሉን አካታች ውይይት እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡ ኮንትራቱ ምርት ሳይሰበሰብም ሆነ በሚሰበሰብበት ወቅት ሊደረግ እንደሚችል አስታውቀዋል፡፡

ኤጀንሲው በክላስተር ለተያዙት አርሶ አደሮች ከሚሰጠው ድጋፍና ሥልጠና ውጪ አርሶ አደሮች ሁልጊዜ እርፍ እየተከተሉ ከሚሄዱ ይልቅ፣ ሜካናይዝድ የሆነ አገልግሎት ሊያገኙ ይገባቸዋል የሚለውን በመያዝ በሦስቱ ክልሎች ዘጠኝ የሜካናይዜሽን አገልግሎት ማዕከላትን ከዩኒየኖችና ከግለሰቦች ጋር በመሆን እየተቋቋሙ እንደሚገኙና የአብዛኞቹም ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ አውስተዋል፡፡ የማዕከላቱ መቋቋም ዋነኛ ዓላማ በአካባቢው ላሉ አርሶ አደሮች የሜካናይዜሽን አገልግሎት እንዲያቀርቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች