በክፍላተ ከተሞች 600 ቢሊዮን ብር ግምት ያላቸው ቦታዎች በመንግሥት ተይዘዋል
በፌዴራልና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር ባሉ መንግሥታዊ ተቋማት የተያዙ ክፍትና ሥራ ላይ ያልዋሉ ቦታዎች፣ ለቤቶችና ሌሎች ልማት እንዲውሉ የተቀመጠውን አቅጣጫ ተግባራዊ ማድረግ ተጀምሯል ተባለ፡፡
መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አዲስ ለተቋቋመው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የተነሱ ጥያቄዎችን ሲመልሱ እንደገለጹት፣ በመንግሥት ተቋማት የተያዙ መሬቶች ለአገልግሎት ሳይውሉ፣ በአንጻሩ ዜጎች በመኖሪያ ቤት እጥረት መሰቃየታቸው ከሀብት አስተዳደር አንጻር ያለውን ክፍተት በግልጽ ያሳያል፡፡
በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳነሱት በአዲስ አበባ፣ በቦሌና ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍላተ ከተሞች ብቻ በድምሩ 600 ቢሊዮን ብር የሚገመት መሬት በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ያለአግባብ ተይዟል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ጥራቱ በየነ እንዳስታወቁት፣ በመንግሥት የተያዙ መሬቶች ለልማት እንዲውሉ በማሰብ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በፓርላማ የተቀመጠውን አቅጣጫ መሠረት በማድረግ፣ የከተማ አስተዳደሩ በፌዴራልም ሆነ በከተማው አስተዳደር በሚገኙ ተቋማት ተይዘው የሚገኙ መሬቶች፣ በቀጣይ አሠራሩን ተከትሎ ለከተማው ነዋሪዎች የቤት ልማት አገልግሎትና ለሌሎች መሠረተ ልማቶች እንዲውሉ የማድረግ አቅጣጫን ተከትሎ እየተሠራ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
በዚህ ወቅት አቅጣጫውን ተከትለው የወጡ ሥራዎች እንደተጀመሩ የተጠቀሰ ሲሆን፣ የተጀመረው ሥራ ሲጠናቀቅ ምን ያህል መሬት በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ለልማት እንደዋለና ከመንግሥት ተቋማት ወደ ሕዝብ መጠቀሚያነት እንደተቀየረ መረጃው በቀጣይ ይፋ እንደሚደረግ አቶ ጥራቱ ገልጸዋል፡፡
በመንግሥታዊ ተቋማት ሥር ያሉ ይዞታዎችን ወደ ሕዝብ ይዞታነት የማስተላለፍ ሒደቱ በተጨባጭ በእንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ አፅንኦት ሰጥተው የተናገሩት አቶ ጥራቱ፣ በቴሌና በሌሎች መንግሥታዊ ተቋማት የተያዙና ክፍትና ሥራ ላይ ያልዋሉ ቦታዎች፣ ለከተማዋ ነዋሪ በተለይም የቤት ልማት ሥራ ላይ እንዲውሉ ታሳቢ ያደረገ ሥራ ተጀምሯል ብለዋል፡፡
በተያያዘም አዲስ የተመሠረተው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳር መዋቅሩን በአዲስ መልክ በማደራጀት፣ ከዚህ ቀደም በብልሹ አሠራር ሥር የነበሩ አመራሮችን የመለየትና ጠንካራ መዋቅር ለማደራጀት ዕድል እንዳገኘ አቶ ጥራቱ አስታውቀዋል፡፡
የከተማዋ አስተዳደር ከሕገወጥ መሬት ወረራ ጋር በተያያዘ የተደረገውን ማጣራት መነሻ በማድረግ፣ የመሬት ልማት ቢሮ አደረጃጀትን መቀየር የሚያስችል ሥራ እንደተሠራ የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ፣ ለአብነትም ከዚህ ቀደም በመሬት ልማት ማኔጅመንት ቢሮ ውስጥ ከሦስት በላይ የሚደርሱ ጽሕፈት ቤቶች (ቢሮዎች) እንደነበሩ አስታውቀዋል፡፡
የመሬት ባንክ፣ ይዞታና ማስተላለፍ እንደዚሁም ከተማ ማደስ የሚባሉ ጽሕፈት ቤቶች እንደነበሩ ያስታወቁት ሥራ አስኪያጁ፣ ጽሕፈት ቤቶቹ እርስ በርሳቸው የማይቀናጁ ይልቁንም ለብልሹ አሠራር በር የከፈተ አደረጃጀት እንደነበራቸው በተደረገው ጥናት ተረጋግጧል ብለዋል፡፡
በአዲሱ የከተማ አስተዳደር ውስጥ የመሬት ልማት ማኔጅመንት ቢሮ በአንድ የቢሮ ኃላፊና በዘርፎች እንዲመራ እንደተደረገና አደረጃጀቱ ብልሹ አሠራርንና የቁጥጥር ሥራን ለማጠናከር የሚያስችል ተደርጎ ወደ ሥራ መገባቱንም አክለዋል፡፡