Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናዓቃቤ ሕግ በእነ አቶ እስክንድር ላይ የቆጠራቸውን ምስክሮች ፈቃደኝነታቸውን ጠይቆ እንደሚያቀርብ አስታወቀ

ዓቃቤ ሕግ በእነ አቶ እስክንድር ላይ የቆጠራቸውን ምስክሮች ፈቃደኝነታቸውን ጠይቆ እንደሚያቀርብ አስታወቀ

ቀን:

የምስክሮች  ዝርዝር  በሚዲያ  እንዳይቀርብ ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ጠይቋል

 

ዓቃቤ ሕግ በእነ አቶ እስክነድር ነጋ ላይ የመሠረተው የወንጀል ክስ እውነት መሆኑን ለፍርድ ቤት ያስረዱልኛል ብሎ ከቆጠራቸው 21 ምስክሮች መካከል የዘጠኙን ስም ዝርዝር ለፍረድ ቤቱ ያቀረበ ቢሆንም፣ የቀሪዎቹን 12 ምስክሮች ስም ዝርዝር የሚያቀርበው ፈቃደኝነታቸውን ጠይቆ መሆኑን ጥቅምት 5 ቀን 2014 ዓ.ም.  ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከሰዓት በኋላ በነበረው ችሎት ቀርቦ አስታወቀ፡፡

ዓቃቤ ሕግ 12ቱ ምስክሮቹ መመስከር እንደሚፈልጉና እንደማይፈልጉ ፈቃዳቸውን ጠይቆ ከተስማሙ እንደሚያቀርባቸው የተናገረው፣ ክሱን እያየው ያለው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የሕገ መንግሥትና የሽብር ጉዳዮች የወንጀል ችሎት በዕለቱ ከሰዓት በፊት፣ ዓቃቤ ሕግ የምስክሮች ዝርዝርንና ጭብጥ  በግልጽ አለማቅረቡን ተከትሎ ማን በማን ላይና በየትኛው ክስ ላይ እንደሚመሰክር ለይቶ እንዲቀርብ በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ማቅረብ አለማቅረቡን አረጋግጦ፣ ምስክሮቹን ለመስማት በተሰየመበት ሰዓት ነው፡፡

ፍርድ ቤቱ ከሰዓት በኋላ ሲሰየም ዘግይቶና ሳይሟላ (ሁለት ዳኞች) በመሰየሙና የሚያቀርባቸው ምስክሮች ስም ዝርዝር በሚዲያ እንዳይቀርብ ትዕዛዝ እንዲሰጥለት  በማስገባቱ፣ እነ አቶ እስክንድር የቅሬታ አቤቱታ አቅርበዋል፡፡

አቶ እስክንድር ነጋ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው፣ ‹‹ምስክሮች እንዲፈሩ ሳይሆን እውነታውን ሕዝብ እንዲረዳ ስም ዝርዝራቸው በሚዲያ እንዲቀርብ እንፈልጋለን፤›› በማለት ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቋል። ጠበቆቹም አክለው፣ ዓቃቤ ሕግ 15 ወራት ሙሉ የተለያዩ ምክንያቶችን በመጠቀም መዝገቡ እንዲዘገይና በተፋጠነ ሁኔታ ዕልባት እንዳያገኝ መጓተቱን አስረድተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ በዕለቱ የጠዋት ችሎት ላይ፣ ዓቃቤ ሕግ የምስክሮች ስም ዝርዝርና ጭብጥ እንዲያቀርብ የሰጠውን ተዕዛዝ እየጣሰ መሆኑን በማስታወስ፣ትዛዙ መሠረት እንዲያስፈጽምላቸውም ጠይቀዋል።

ዓቃቤ ሕግ በበኩሉ በሰጠው ምላሽ፣ ‹‹እኛ የጠየቅነው ዳኝነት ነው፡፡ እንደኛ ፍላጎት ቢሆን ኖሮ የምስክር ስም ዝርዝር አስቀድመን አናቀርብም ነበር፡፡ ነገር ግን ስም ዝርዝራቸው በሚዲያ እንዳይገለጽ የጠየቅነው በምስክሮቻችን ላይ ሊከሰት የሚችልን  አደጋ ለመቀነስ ነው›› በማለት አስረድቷል።

የችሎቱ አንድ ዳኛ በድንገተኛ ችግር ምክንያት  ሊሰሙ እንዳልቻሉና በሌሎች ዳኞችም ተሟልቶ ለመቅረብ ተሞክሮ እንዳልተቻለ ለታዳሚው በማስረዳት፣ ችሎቱ ባለመሟላቱና በምስክር አሰማም ሒደት ላይ አቤቱታና ክርክር በመነሳቱ በዕለቱ የቀረበውን ክርክር መርምሮ ትዕዛዝ መስጠት እንደማይቻል አስረድቷል። በመሆኑም በተሟላ ችሎት ትዕዛዝ ለመስጠት ለማክሰኞ (ረቡዕ) ቀጠሮ ሰጥቷል። አቶ ስንታየው ቸኮል  ጠቅምት 4 ቀን 2014 ዓ.ም. ያለበትን  የኩላሊትየዓይንና  የጥርስ ሕመም እንዳለበት አስረድቶ ከማረሚያ ቤቱ የሕክምና አቅም በላይ ስለሆነ  በግሉ  እንዲታከም ያቀረበውን አቤቱታን በሚመለከት ማረሚያ ቤቱ በቀጠሮው ዕለት አስተያየት እንዲሰጥበት ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ዓቃቤ ሕግ አስተያየት ለመስጠት ቢፈልግም፣ ከማረሚያ ቤቱ አስተያየት በኋላ  እንደሚሰጥበት ፍርድ ቤቱ ስታውቋል።

አቶ እስክንድር ነጋ፣ አቶ ስንታየሁ ቸኮል፣ ወ/ሮ ቀለብ (አስቴር) ሥዩምና ወ/ሮ አስካለ ደምሌ፣ ከኦሮሚኛ ድምፃዊው ሃጫሉ ሁንዴሳ ሞት ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ከተማ ተፈጠሮ በነበረው ሁክትና ብጥብጥ፣ ከጠፋው የሰው ሕይወትና ከወደመው ንብረት ጋር በተያያዘ ክስ እንደተመሠረተባቸው ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹ከኦነግ ሸኔ ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት አለን›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ

መንግሥት ከ‹‹ኦነግ ሸኔ››ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት...

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...