Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ኃላፊነቱን የማይወጣ መንግሥትን ሕዝብ አንቅሮ ይተፋዋል!

  ልማዳዊው የመንግሥት አሠራር በነበረበት መቀጠል የማይችልበት ደረጃ ላይ እየደረሰ ለመሆኑ ማሳያ ከሆኑ መሠረታዊ ጉዳዮች መካከል በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደው ጦርነት፣ በኦሮሚያ ክልል በንፁኃን ላይ እየተፈጸሙ ያሉ ግድያዎች፣ የኑሮ ውድነት፣ በተለያዩ መንገዶች የሚስተዋሉ ሌብነቶች፣ በውጭ ምንዛሪ ግብይት ላይ እየተፈጸሙ ያሉ አደገኛ ድርጊቶች፣ እንዲሁም ለብሔራዊ ደኅንነት ከፍተኛ ሥጋት የሚፈጥሩ ችግሮች ላይ የሚታዩ ቸልተኝነቶች ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ ያደራጁት መንግሥትም ሆነ የክልል መንግሥታት፣ ከዚህ ቀደም በነበረው ዓይነት ዳተኝነትና መንቀርፈፍ ለመቀጠል የማይችሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን መገንዘብ አለባቸው፡፡ እያንዳንዱ የፖለቲካ ተሿሚ የሚመራውን ተቋም ከማዘመንና የአገልግሎት አድማሱን ተደራሽ ከማድረግ በተጨማሪ፣ ለዘመናት ሕዝቡን ሲያማርሩ የኖሩ ብልሹ አሠራሮችን ከሥራቸው ነቅሎ መጣል ይጠበቅበታል፡፡ “ችግሩ ከፖሊሲ ሳይሆን ከአፈጻጸም ነው” የሚለው የሰለቸና ጊዜ ያለፈበት ሰበብ ድርደራ፣ ከዚህ በኋላ በምንም ዓይነት ሁኔታ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ በሚያማልሉ ንግግሮችና አባባሎች ማጭበርበር አይቻልም፡፡ በተለይ በማንነታቸው ምክንያት እየታደኑ የሚገደሉ ዜጎች ሰቆቃ በፍጥነት ይቁም፡፡ ሕዝብ ከማንኛውም ዓይነት ጥቃት የሚከላከለው መንግሥት እንዲኖረው ነው የሚፈልገው እንጂ፣ ደኅንነቱን ለአደጋ የሚያጋልጥ አይደለም፡፡

   

  በአሁኑ ጊዜ በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ካለው ጦርነት በተጨማሪ፣ በተለያዩ አካባቢዎች በዜጎች ላይ ከፍተኛ መከራ እየደረሰ ነው፡፡ በጭካኔ እየተገደሉ፣ አካላቸው እየጎደለ፣ እየተፈናቀሉና ንብረታቸው እየወደመባቸው ያሉ ወገኖች ከዚህ ሰቆቃ በፍጥነት ይላቀቁ ዘንድ መላ መፈለግ አለበት፡፡ በመንግሥት ቸልተኝነት ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ነው፡፡ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳትም መዘዙ የከፋ ይሆናል፡፡ ከነዳጅና ከኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃዎች በተጨማሪ በርካታ የምግብና የፍጆታ ዕቃዎችን በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የምታስገባ አገር፣ ከውጭ የምትጠብቃቸው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቶች፣ የኤክስፖርት ገቢዎች፣ የሃዋላ ገቢዎች፣ ብድሮችና ድጋፎች መጠናቸው ሲቀንስና ሊጣል በሚችል ማዕቀብ ምክንያት ፍሰታቸው ሲቆም ምን ሊያጋጥም እንደሚችል መገንዘብ ይገባል፡፡ የአገር ውስጥ ምርቶች አቅርቦት እያደገ ከመጣው ፍላጎት ጋር ሊመጣጠን እንደማይችል ይታወቃል፡፡ በእንዲህ ዓይነት አጣብቂኝ ውስጥ ተሁኖ በዜጎች ላይ የሚፈጸመው ግድያና መፈናቀል ካልቆመ፣ ሊያስከትል የሚችለው ጦስ ለማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ በቅርቡ የተደራጀው የአዲሱ መንግሥት አመራሮች ቁርጠኝነት በግልጽ መታወቅ አለበት፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ፈጽሞ መቀጠል አይቻልም፡፡ 

  ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ በጣም አደገኛ በመሆኑ የመንግሥት ተቀዳሚ ተግባሩ፣ የአገርንና የሕዝብን ደኅንነት ማስጠበቅ መሆን አለበት፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ማንነትን መሠረት በማድረግ የሚፈጸሙ ግድያዎችን ማስቆምና ተጠያቂዎችን ለሕግ ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ወለጋ ዞን ውስጥ በተደጋጋሚ እየተፈጸሙ ያሉ የጅምላ ግድያዎች በአስቸኳይ መቆም አለባቸው፡፡ በሰብዓዊ መብት ተቋማትና በበርካታ ኢትዮጵያዊያን አማካይነት፣ ለፌዴራል መንግሥትና ለክልሉ መንግሥት በተደጋጋሚ አቤቱታዎች ቢቀርቡም ሰሚ ሊገኝ አልቻለም፡፡ ከምሥራቅ ወለጋ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ባሉ ግለሰቦች ድጋፍ ጭምር ነው ግድያዎች የሚፈጸሙት፡፡ መንግሥት ይህንን ዓይነቱን ነውረኛ ድርጊት ማስቆም አቅቶት ንፁኃን ያለ ጥፋታቸው መጨፍጨፋቸው ከቀጠለ፣ ሕዝብ በማን ላይ ሊተማመን ይችላል? አቅሙ ተዳክሞ በቀቢፀ ተስፋ እንደሚንቀሳቀስ በክልሉ መንግሥት አመራሮች ጭምር ሲነገርለት የነበረው ኦነግ-ሸኔ፣ እንዴት ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ ሊሆን እንደቻለ መገለጽ አለበት፡፡ በተለይ በምሥራቅ ወለጋ ዞን እየፈጸመ ያለው አገር አፍራሽ ድርጊት በፍጥነት መቆም ካልቻለ፣ ኢትዮጵያን ወደ ለየለት የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የሚከት ቀውስ ሊፈጠር እንደሚችል ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ሕዝብ የመንግሥት ያለህ እያለ ነው፡፡

  ኢትዮጵያ ውስጥ የመንግሥት አገልግሎቶችን ለማግኘት ጉቦ መክፈል የተለመደ ከመሆኑ የተነሳ፣ በዚህ ብልሹ ድርጊት ውስጥ የተዘፈቁ የመንግሥት ሹማምንትና ሠራተኞች ደረሰኝ አምጡ ቢባሉ ከመስጠት የሚመለሱ አይመስሉም፡፡ ተገልጋይን ማክበርና ሥራን በአግባቡ በአጭር ጊዜ ማጠናቀቅ አይሞከርም፡፡ ትጉኃን ሠራተኞች ቢኖሩ እንኳ በተደራጀ ግብረ ኃይል አማካይነት አንገታቸውን እንዲደፉ ይደረጋሉ፡፡ ብዙዎቹ ተቋማት ሥነ ምግባር በሌላቸውና ሞራላቸው በላሸቀ ግለሰቦች ተጠፍንገው ስለተያዙ፣ አገልግሎት ፈላጊው ሕዝብ የሥርዓተ አልበኞች መፈንጫ ሆኗል፡፡ ወንጀል የተፈጸመበት ሰው ለፖሊስ አቤቱታ ሲያቀርብ ሥነ ምግባር የሌላቸው መርማሪዎች፣ ከሳሽን የወንጀል ተጠርጣሪ ይመስል እንግልት እየፈጸሙበት ተስፋ ያስቆርጡታል፡፡ የወንጀሉን ፍሬ ነገር ተረድቶ ፍትሕ እንዲሰፍን ኃላፊነትን ከመወጣት ይልቅ፣ ከወንጀሉ የሚገኘው ጥቅም ላይ መደራደር በመለመዱ ንፁኃን በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ እምነት እንዲያጡ እያደረገ ነው፡፡ መንግሥታዊ ተቋማትን የጥቅም ተጋሪዎች መሰባሰቢያ በማድረግ ባለሙያዎችን ተስፋ ማስቆረጥ የተለመደ በመሆኑ፣ ብዙዎቹ ተቋማት በሕግ ከተቋቋሙበት ዓላማ አፈንግጠው የሕዝብ መማረሪያ ከሆኑ ቆይተዋል፡፡ አዲሱ መንግሥት ሕዝቡን ከእንዲህ ዓይነቱ ሥርዓተ አልበኝነት የመከላከል ኃላፊነት አለበት፡፡ ቃል መግባት ብቻ ሳይሆን በተግባር ማሳየት የመንግሥት ግዴታ ነው፡፡ ካልሆነ ግን አደገኛ ቀውስ ይከተላል፡፡

  ከኢኮኖሚው ምስቅልቅል መገለጫዎች አንደኛው የሆነው በባንኮች አካባቢ የሚስተዋለው አደገኛ ሁኔታ ፈር ካልያዘ፣ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚያስከትለው አደጋ ከባድ ነው የሚሆነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በተለያዩ የፖሊሲ ማዕቀፎች ባንኮች ጤናማ ሆነው ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ለዓመታት ዕገዛ አድርጓል፡፡ በቅርቡም የተለያዩ መመርያዎች በማውጣት የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠርና ኢኮኖሚያዊ አሻጥሮችን ለመከላከል ጥረት እያደረገ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በሒደት አንዳንድ ማነቆዎችን በማንሳት ለባንኮች ትርፋማ ሆኖ መቀጠል የሚረዱ ዕርምጃዎችን እንደሚወስድ ይጠበቃል፡፡ ከዚህ ውጪ ግን በባንኮች ውስጥ የሚፈጸሙ ሥርዓተ አልበኝነቶችን ችላ ያለ ይመስላል፡፡ በተለይ በውጭ ምንዛሪ ላይ የሚስተዋለው መረን የተለቀቀው ሥርዓተ አልበኝነት ፈር ካልያዘ፣ ባንኮቹ ባለአክሲዮኖቻቸውንና ደንበኞቻቸውን ብቻ ሳይሆን የአገሪቱንም ኢኮኖሚ ይዘው እንጦረጦስ መግባታቸው አይቀርም፡፡ ከአዲስ አበባ ከተማ ጀምሮ እስከ ቶጎ ጫሌ ድረስ የዘረጉት የውጭ ምንዛሪ አደን መረብ፣ ከጥቁር ገበያ ጋር እየተሸራረበ አገሪቱን ራቁቷን እያስቀራት ነው፡፡ በዚህ ሕገወጥ ድርጊት የሚሳተፉ ባንኮችን፣ አመራሮችንና ሠራተኞችን እንዳላዩ ማለፍ ተባባሪ እንደ መሆን ይቆጠራል፡፡ የፋይናንስ ዘርፉ ጤና ሲያጣ ኢኮኖሚው በአፍጢሙ እንደሚደፋ መገንዘብ ይገባል፡፡ መንግሥት ይህንን ሥርዓተ አልበኝነት ያስቁም፡፡ ሕዝብ አገሩ የወረበሎች መጫወቻ ስትሆን ቆሞ አይመለከትም፡፡

  በዚህ አጋጣሚ የመንግሥትን ትልቅ ኃላፊነት የተረከቡ ሦስት የተፎካካሪ ፓርቲዎች አመራሮች፣ ለገዥው ፓርቲ ሹማምንት ኃላፊነትን እንዴት በብቃት መወጣት እንደሚቻል አርዓያነት ያለው ተግባር ቢያሳዩ መልካም ነው፡፡ “ከበሮ በሰው እጅ ሲያዩት…” የሚለውን ዕድሜ ጠገብ ምሳሌ የሚሽር ብቃት በማሳየት፣ “ከልብ ካለቀሱ ዕንባ…” የሚለውን ምሳሌ በገቢር ማሳየት የሚያኮራ ተግባር ይሆንላቸዋል፡፡ በተደጋጋሚ ለማየት እንደተቻለው ብዙዎቹ የመንግሥት ሹማምንትም ሆኑ ተከታዮቻቸው ተነሳሽነታቸው ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው፡፡ ለዚህ ትልቅ ምክንያት ብዙዎቹ ለሹመት የሚታጩት በዕውቀታቸው፣ በልምዳቸውና በሥነ ምግባራቸው ሳይሆን ለፓርቲያቸው ባላቸው ታማኝነት ብቻ በመሆኑ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ ሹማምንትና ቢጤዎቻቸው አድርባይነትንና አስመሳይነትን የተካኑ ስለሆኑ፣ ለጠንካራ ተቋማት ግንባታና ለብቁ የሰው ኃይል ሥምሪት ደንታ የላቸውም፡፡ የበላዮቻቸውን ዓይንና ግንባር እንደ መጽሐፍ እያነበቡ ስለሚንቀሳቀሱ ለሞራላዊና ሥነ ምግባራዊ እሴቶች ቦታ የላቸውም፡፡ መፈክር ለማስተጋባትና ጭብጨባ ለማድመቅ ሲሆን አንደኛ ናቸው፡፡ ሕዝብ በሕገወጦች ሲጨፈጨፍ ግን ድምፃቸው አይሰማም፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ካለፈው ስህተቶች በመማር አገር በሥርዓት ይምራ፡፡ በቃል የተነገረው በተግባር ይታይ፡፡ ሕዝብ ለመንግሥት ድጋፍ የሚሰጠው ሲናገር ሳይሆን ሲሠራ ብቻ ነው፡፡ ካልሆነ ግን የሰቀለውን ማውረድ ይችልበታል፡፡ ሥልጣን ማገልገያ እንጂ ሕዝብ ላይ መፈንጪያ አይደለም፡፡ መንግሥት ኃላፊነቱን ሲዘነጋ ሕዝብም አንቅሮ እንደሚተፋው ይታወቅ!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  በዕድሳት ምክንያት የተዘጋው የአዲስ አበባ ስታዲየም በቅርቡ ለአገልግሎት ክፍት ይሆናል

  የአደይ አበባ ስታዲየም ግንባታ በሚፈለገው ልክ እየተከናወነ እንዳልሆነ ተገልጿል ከስፖርታዊ...

  የንብረት ታክስ ጉዳይ በሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ጉባዔ ቀዳሚ አጀንዳ ይሆናል ተባለ

  መስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም. በሚጀምረው የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን...

  የኢትዮጵያ ባንኮችን የማዋሃድ አስፈላጊነት ፍንትው ያደረገው ዓመታዊው የአፍሪካ ባንኮች የደረጃ ምዘና ሪፖርት

  የአፍሪካ ባንኮችን በየዓመቱ በመመዘንና ደረጃ በመስጠት የሚታወቀው አፍሪካ ቢዝነስ...

  መንግሥት ለሶማሊያ የፀጥታ ኃይሎችና የመንግሥት ሠራተኞች ሥልጠና ለመስጠት ቃል ገባ

  የኢትዮጵያ መንግሥት ለጎረቤት አገር ሶማሊያ የመንግሥት ሠራተኞችና የፀጥታ አካላት...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች