Monday, September 25, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መንግሥት የእንግሊዙ ከፊ ጎልድ ኩባንያ ያቀረበውን የጊዜ ገደብ ማራዘሚያ ጥያቄ ውድቅ አደረገው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የእንግሊዙ ኩባንያ ከፊ ጎልድ በቱሉ ካፒ አካባቢ የተገኘውን የወርቅ ማዕድን ለማውጣት፣ ወደ ሙሉ የፕሮጀክት ልማት እንዲገባ የተሰጠው የጊዜ ገደብ እንዲራዘምለት ያቀረበውን ጥያቄ የማዕድን ሚኒስቴር ውድቅ አደረገው። 

 

የእንግሊዝ ኩባንያ የቱሉ ካፒ የወርቅ ማዕድን ልማትን በፀደቀው ዕቅድ መሠረት ማከናወን ባለመቻሉ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያና የጊዜ ገደቦች እየተሰጠው ለበርካታ ዓመታት የቀጠለ ሲሆን፣ በሰኔ ወር 2013 ዓ.ም. የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት ነበር። 

ነገር ግን ኩባንያው የፕሮጀክት ልማቱን ለመጀመር የሚያስፈልገውን ፋይናንስ በማግኘቱ የተሰጠው የጊዜ ገደብ ተሻሽሎ እ.ኤ.አ. እስከ ኦክቶበር 2021 መጨረሻ ቀን ድረስ ልማቱን እንዲጀምር አዲስ የጊዜ ገደብ ተቆርጦለት ነበር። 

ይሁን እንጂ ኩባንያው በመስከረም ወር 2014 ዓ.ም. ለማዕድን ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ፣ ፕሮጀክቱ በሚገኝበት ቱሉ ካፒ አካባቢ የፀጥታ ችግር መኖሩን ጠቅሶ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ የወርቅ ማዕድን ልማቱን መጀመር እንደማይችል አስታውቆ፣ የጊዜ ማራዘሚያ መጠየቁን ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

የማዕድን ሚኒስቴር በበኩሉ ጥቅምት 1 ቀን 2014 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ለተቋቋመው እህት ኩባንያ በጻፈው ደብዳቤ የተጠየቀውን የጊዜ ማራዘሚያ ከነምክንያቱ ውድቅ በመጥቀስ ጥያቄውን ውድቅ አድርጎታል።

የማዕድን ሚኒስቴር ለኩባንያው በጻፈው ደብዳቤ ቀደም ሲል በሁለቱም መካከል የተደረጉ የደብዳቤ ልውውጦችን ዋቢ አድርጓል።

ከፊ ጎልድ ወይም ቱሉ ካፒ የማዕድን ልማት አክሲዮን ማኅበር ባለፈው ሐምሌ ወር ለማዕድን ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ፣ በቱሉ ካፒ አካባቢ ያለው የፀጥታ ሁኔታ መንግሥት በሰጠው ልዩ ትኩረት የተሻሻለ በመሆኑ፣ የፕሮጀክት ልማቱን ለመጀመር ዝግጁ እንሆነ ገልጾ ሲያበቃ፣ የፕሮጀክት ልማቱን በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ተግባራዊ ያደርጋል ተብሎ በሚጠበቅበት ወቅት የጊዜ ማራዘሚያ መጠየቁ ተቀባይነት እንደሌለው የማዕድን ሚኒስቴር በደብዳቤው አስታውቋል።

ቀድሞውንም ቢሆን የማዕድን ሚኒስቴር ለኩባንያው የጊዜ ማራዘሚያ የፈቀደበት መሠረታዊ ምክንያት፣ ኩባንያው ፕሮጀክቱን ለመጀመር የሚያስችል ፋይናንስ ለማግኘት ባለመቻሉ እንጂ፣ በፀጥታ ችግር ምክንያት እንዳልሆነ ይገልጻል።

በተቀመጠው የጊዜ ገደብ የፕሮጀክት ልማቱን ለመጀመር አለመቻልን ለመሸፈን ሲባል የፀጥታ ሥጋትን አሁን ላይ ማንሳት ተቀባይነት እንደማይኖረው የሚኒስቴሩ ደብዳቤ ይገልጻል።

‹‹ኩባንያው ፕሮጀክቱን በማልማት ረገድ እጅግ ዝቅተኛ አፈጻጸም ከማሳየቱ በተጨማሪ፣ በተደጋጋሚ የፈጸማቸው በርካታ የውል ጥሰቶችን የማዕድን ሚኒስቴር እያቻቻለ ሲያልፍ ከመቆየቱ አንጻር ተጨማሪ የጊዜ ማራዘሚያ ጥያቄው ተቀባይነት አይኖረውም፤›› በማለት በሚኒስትሩ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ተፈርሞ ለኩባንያው የተላከው ደብዳቤ ይገልጻል።

የማዕድን ሚኒስቴርን ውሳኔ በተመለከተ የኩባንያውን አስተያየት ለማካተት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። ኩባንያው ከሁለት ሳምንት በፊት በድረ ገጹ ይፋ ባደረገው መረጃ ግን፣ በአካባቢው ያለውን የፀጥታ ሥጋት በመጥቀስ የፕሮጀክት ልማቱን በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ለመጀመር እንደማይችል ለሚመለከታቸው የኢትዮጵያ መንግሥት አካላት እንዳስታወቀ በመጥቀስ፣ የፕሮጀክት ትግበራው 2021 ከመጠናቀቁ በፊት ዕውን ይሆናል የሚል ተስፋ እንዳለው አስታውቋል።

ሰሞኑን በምዕራበ ወለጋ ዞን ግጭት መቀስቀሱን መነሻ በማድረግ ሪፖርተር ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የማዕድን ሚኒስትሩ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር)፣ ‹‹ፕሮጀክቱ በሚካሄድበት በቱሉ ካፒ አካባቢ ምንም ዓይነት የፀጥታ ችግር የለም፤›› ብለዋል።

የወርቅ ልማት ፕሮጀክቱ ዕውን እንዲሆን መንግሥት ባለው ቁርጠኝነት አንድ የፌዴራል ፖሊስ የጥበቃ ቡድን ከሦስት ዓመት በፊት በቱሉ ካፒ የልማት ቀጣና ማሰማራቱንና አሁንም በአካባቢው ተሰማርቶ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በቱሉ ካፒ የወርቅ ክምችት መኖሩ ከተረጋገጠ ከ70 ዓመታት በላይ ቢያልፉም፣ የወርቅ ክምችቱን ለማውጣት ለመጀመሪያ ጊዜ ሙከራ የተደረገው እ.ኤ.አ. በ1930ዎቹ ውስጥ በጣሊያን ኩባንያ አማካኝነት መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። 

ይህ ሙከራ ብዙም ውጤት ሳያስገኝ የወርቅ ክምችቱ ለበርካታ ዓመታት ሳይለማ ቆይቶ እ.ኤ.አ. በ2009 ኖዮታ ሚነራል በተባለ ኩባንያ የቱሉ ካፒ አካባቢ ላይ የማዕድን ፍለጋ ፈቃድ በመውሰድ ሰፊ የፍለጋ ሥራና የጉድጓድ ቁፋሮ በማካሄድ እ.ኤ.አ. በ2012 ሰፊ የወርቅ ክምችት መኖሩን ካረጋገጠ በኋላ ወደ ምርት የመሸጋገር ሒደት ጀምሮ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ።

ይሁን እንጂ ኩባንያው ኖዮታ ሚነራል በአካባቢው ያገኘውን የወርቅ ክምችት መጠን በማስተዋወቅ፣ በክምችቱ ላይ የነበረውን ሕጋዊ የማልማት ፈቃድ ተንተርሶ የኩባንያውን 75 በመቶ ድርሻ እ.ኤ.አ. በ2013 ከፊ ሚነራል ለተባለው ለአሁኑ ኩባንያ እንደሸጠ መረጃው ይገልጻል።

በቀጣዩ ዓመትም የቀረውን 25 በመቶ ድርሻ ለዚሁ ኩባንያ አስተላልፎ ከኢትዮጵያ የወጣ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥትም እ.ኤ.አ. በ2015 ከፊ ሚነራል ለተባለው ኩባንያ በቱሉ ካፒ የተገኘውን የወርቅ ክምችት አምርቶ ለገበያ እንዲያቀርብ ለ20 ዓመታት የሚቆይ የከፍተኛ ማዕድን ልማት ፈቃድ ሰጥቷል።

ኩባንያው ይህንን ፈቃድ ካገኘ በኋላ ወደ ምርት ለመግባት የተለያዩ ጥረቶችን ያደረገ ቢሆንም ፈቃዱን ከወሰደበት ጊዜ አንስቶ ላለፉት ስድስት ዓመታት ግን ተጨባጭ ወደ ሆነ የማምረት ሥራ አልተሸጋገረም። 

የቱሉ ካፒ የተረጋገጠ የወረቅ ክምችት 1.7 ሚሊዮን ኦንስ እንደሆነ የከፊ ሚነራል መረጃ የሚያመለክት ሲሆን፣ ይህ የወርቅ መጠን በአንድ ጊዜ ወጥቶ ጥቅም ላይ ባይውልም፣ አሁን ባለው ዓለም አቀፍ የወርቅ አማካኝ ዋጋ መሠረት ሲሰላ ግን 2.5 ቢሊዮን ዶላር ወይም በወቅቱ የብር ምንዛሪ 109 ቢሊዮን ብር እንደሚያወጣ ይገመታል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች