Sunday, February 25, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኤቲኤም ካርድ ኅትመት በመዘግየቱ ደንበኞች በንግድ ባንክ ላይ ቅሬታ አቀረቡ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለደንበኞቹ የሚያቀርበውን የገንዘብ መክፈያ ኤቲኤም ካርድ በወቅቱ አትሞ ማድረስ ባለመቻሉ ደንበኞች ቅሬታ እያቀረቡ መሆኑ ታወቀ፡፡

በርካታ ቁጥር ያላቸው የባንኩ ደንበኞች ለሪፖርተር በተደጋጋሚ እንደገለጹት፣ ካርዱን ለማግኘት አንዳንዶቹ ከሦስት እስከ አራት ወራት ጊዜ እየወሰደባቸው ነው፡፡

በኔትወርክ መጨናነቅና በደንበኞች መብዛት የባንኩን አገልግሎት ለማግኘት ኤቲኤም ካርድ መያዝን የሚመርጡና በባንኩ ሠራተኞች አማካይነት ካርድ እንዲወስዱ በግፊት ፎርም ሞልተው ከአካውንታቸው ገንዘብ የተቆረጠባቸውን በርካታ ደንበኞች ሪፖርተር በቦሌ፣ በስድስት ኪሎ፣ በአራት ኪሎና በመገናኛ አካባቢ አግኝቶ አነጋግሯል፡፡

የባንኩ ደንበኛ የሆኑና ስማቸው ሳይጠቀስ አስተያየታቸውን የሰጡ አንድ ግለሰብ፣  ‹‹ስድስት ኪሎ በሚገኘው ቅርንጫፍ ደመወዝ ለማውጣት በሄድኩበት ወቅት ያስተናገደኝ ሠራተኛ፣ ኤቲኤም ከሞላሁ በሁለት ሳምንት እንደሚደርስልኝ ነግሮኝ ብሞላም፣ አራት ወራት ተቆጥረው ካርዱን አላገኘሁም፤›› ብለዋል፡፡

ባንኩ ደንበኞችን ኤቲኤም ካርድ እንዲሠራላቸው የሚገቡትን ውል እንዲፈርሙ ካደረገ በኋላ፣ ውል ከፈጸሙ ደንበኞች በተለይም ለጠፋባቸው፣ ለተበላሸባቸው ወይም የመጠቀሚያ ጊዜው ካለፈባቸው የካርድ ደንበኞች አካውንት ላይ የካርድ ዋጋ 50 ብር ይቀንሳል፡፡

ሮማን የተባለች አንድ የባንኩ ደንበኛ ካርዱን ለመውሰድ ውል የገባችው ከወራት በፊት በመስኮት ባስተናገዷት የባንኩ ሠራተኞች እንደነበር፣ በ15 ቀናት ውስጥ ይደርሳል በሚል ተስፋ የተመዘገበች ቢሆንም ካርዱ ሳይደርሳት ሦስት ወራት አልፈዋል ብላለች፡፡

በቦሌ አካባቢ በድለላ ሥራ የሚተዳደር የባንኩ ደንበኛ፣ ‹‹ሥራዬ ሩጫ በመሆኑ ቁጭ ብሎ ወረፋ ጠብቆ ከመስተናገድ በካርድ የሚያስፈልገኝን አገልግሎት አገኛለሁ ብዬ ካርድ ለማውጣት የተመዘገብኩት በሐምሌ ወር 2013 ዓ.ም. ነበር፣ ነገር ግን እስካሁን አልደረሰኝም፤›› ብሏል፡፡

የንግድ ባንክ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ የአብሥራ ከበደ የደንበኞችን ቅሬታ አስመልክቶ ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ለደንበኞቻችን የምንሰጠው የካርድ ዓይነት፣ የባንካችንን ተቋማዊ ቀለማት ይዘት የሚገልጽ፣ በተለይም ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለሚጠቀሙ ደንበኞች የሃይማኖት አስተምህሮ ታሳቢ የሚያደርግ እንደ አዲስ ተዘጋጅቶ በሥርጭት ላይ ይገኛል፤›› ብለዋል፡፡

የካርዱ ግዥም የአገሪቱን የግዥ መመርያ ተከትሎ በጨረታ የሚከናወን እንደሆነ፣ በአሁኑ ወቅትም ኤቲኤም ካርድ ለዘገየባቸው ቅድሚያ በመስጠት እየተሠራጨ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ነገር ግን ሪፖርተር በተለያዩ የባንኩ ቅርንጫፎች ተንቀሳቅሶ ለማረጋገጥ እንደቻለው፣ በርካታ ደንበኞች ለወራት እየጠበቁ እንደሆነና ባንኩ አሁንም በትዕዛዝ ሁሉንም ደንበኞች ፎርም እያስሞላ የኤቲኤም ካርድ እንዲይዙ እየጠየቀ ነው፡፡ ከተባለው ጊዜ እንደማይደርስ ግን ስድስት ኪሎ አካባቢ በሚገኝ ቅርንጫፍ ስማቸው ሳይጠቀስ መናገር የፈለጉ የባንኩ ሠራተኛ አስረድተዋል፡፡

ምንም እንኳ የደንበኞች የዕለት ተዕለት ጥያቄና ምልልስ ቢበዛም፣ ምዝገባው አለመቆሙን፣ ነገር ግን ለባንኩ ፕሪሚየም (ልዩ) ደንበኞች በቀናት ወይም በአንድ ሳምንት ውስጥ ካርድ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል፡፡

የባንኩ የአራት ኪሎ ቅርንጫፍ አንድ ሠራተኛ እንደሚሉት ባንኩ የካርድና የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዳለበት ከበላይ ኃላፊዎች ሲነሳ መስማታቸውን፣ ደንበኞች በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም አሁን ይኼ ነው የሚል መልስ ለመስጠት አያስችልም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች