Friday, December 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አስተዳደሩ የሸገር ዳቦ አቅርቦት እጥረትን በፍጥነት እንዲፈታላቸው ሸማቾች ጠየቁ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በሙሉቀን ካሳ

አዲስ አበባ ከተማ የሸገር ዳቦ አቅርቦት ከተጠቃሚው አንፃር በበቂ እየቀረበ ባለመሆኑ በቀላሉ ተሠልፈን ማግኘት አልቻልንም ሲሉ ሸማቾች ገለጹ፡፡ ሪፖርተር በተለያዩ የሸገር ዳቦ መሸጫ ሱቆች ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው ዳቦ ሸማቾችና በአነስተና ጥቃቅን ተደራጅተው ሱቅ ተሰጥቷቸው ዳቦ እየሸጡ ያሉ ወጣቶች እንደገለጹት፣ ጠዋት 12 ሰዓት መጥቶ ለሚሸጥ ዳቦ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት፣ ማታ ከ11 ሰዓት በኋላ ለሚሸጥ ዳቦ ከቀኑ ሰባት ሰዓት በፊት ሸማቾች ተሠልፈው እየጠበቁ እንደሚቆዩ ገልጸዋል፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች ባሉ ዳቦ መሸጫ ሱቆች ዘጋቢው ተዘዋውሮ እንዳረጋገጠው፣ በአንድ የዳቦ መሸጫ ሱቅ ከንጋቱ 11 ሰዓት ተሠልፈው ተመልክቷል፡፡ አቶ አያሌው ንጉሡ የተባሉ ዳቦ ሸማች ሸገር ዳቦ በተለይ በገቢ ዝቅተኛ ለሆነው ማኅበረሰብ ያለውን ፋይዳ ገልጸው፣ የአቅርቦት እጥረት ስላለ፣ ለማግኘት ሲሉ ከአሥር ሰዓት በፊት በመምጣት ተሠልፈው እየተጠባበቁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ‹‹አሁን ላይ ከዳቦ እጥረት በተጨማሪ ዳቦ የሚያቀርበው መኪና አርፍዶ እየመጣ ስለሆነ፣ የዕለት ጉርስ ለመሸፈን ለሥራ የምናደርግውን ሩጫ እየተሻማብን ነው፤›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡ እዚያው አካባቢ ባለ ሌላ ዳቦ መሸጫ ሱቅ ተሠልፈው ያገኘናቸውና ‹‹ስሜ አይጠቀስ›› ያሉ እናት፣ ስድስት ቤተሰብ አባል እንዳላቸው ጠቁመው ‹‹ከረፈደ ሸገር ዳቦ ለማግኘት መጥተን ብዙ ቀን አጥተን እየተመለስን በመሆኑ፣ ከጓደኞቼ ጋር ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ ተሠልፈን እየጠበቅን ነው፡፡ መንግሥት ይኼንን እጥረት ሊያቃልልን ይገባል›› በማለት ገልጸዋል፡፡  

ዳቦ ለመሸጥ በአነስተኛና ጥቃቅን ተደራጅተው ሱቅ ተረክበው ሸገር ዳቦ ለመሸጥ ከተሰማሩ ወጣቶች አንዱ የሆነው ወጣት ያሲን እንደገለጸው፣ ‹‹የሸገር ዳቦ የተጠቃሚው ፍላጎት የተመጣጠነ ባለመሆኑ፣ ለአንድ ሰው ከስምንት እና ከ16 ዳቦ በላይ እንዳይወስድ አድርገን ብንሸጥም፣ ሠልፉ ግማሽ እንዳለ እያለቀ እንዲበተኑ የምንነግርበት ጊዜ በርካታ ነው›› ሲል ገልጿል፡፡

የሸገር ዳቦ የአቅርቦት እጥረትን አስመልክቶ ሪፖርተር ያነጋገርራቸው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ የመሠረታዊ ሸቀጣ ሸቀጥ ትስስርና ሥርዓት ኃላፊ አቶ ደበሬ ደንሳ እንደገለጹት፣ የነዋሪውን የዳቦ እጥረት ለመቅረፍ በከተማ አስተዳደሩ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው፡፡ እንዲሁም አዲስ አበባ በወር ከተፈቀደላት 165,657 ኩንታል የስንዴ ኮታ ውስጥ 60 ሺሕ ኩንታል ሆራይዘን ፕላንቴሽንስ ወይም ሸገር ዳቦና ዱቄት ፋብሪካ ከፍተኛ ድጎማ ተደርጎበት እንዲወስድ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ነገር ግን የኢትዮጵያ ንግድና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወ/ሮ እቴነሽ ገብረ ሚካኤል እንደተናገሩት፣ ሸገር ዳቦ ፋብሪካ ባለፉት ሁለት የመጨረሻ ወራት በነሐሴ ወር 15 ሺሕ ኩንታልና በመስከረም ደግሞ 15 ሺሕ ኩንታል ስንዴ ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ሸገር ዳቦና ዱቄት ፋብሪካ ኮታውን በትክክል እየተጠቀመ አለመሆኑን ገልጸው፣ የድርጅቱ ኃላፊዎች የሚያቀርቡት ምክንያት የፋይናንስ እጥረት እንዳለባቸው እንደሆነና ስንዴው ተወደደብን የሚል እንደሆነ ያብራራሉ፡፡

ወ/ሮ እቴነሽ አያይዘው እንዳብራሩት፣ መንግሥት በአሁኑ ሰዓት ከውጭ ስንዴ ገዝቶ እያስገባ ያለው በ450 ዶላር ወይም 18,900 ብር ሲሆን ‹‹እኛ እዚህ ሁለት በመቶ የመጋዘን ኪራይ ብቻ በመጨመር አንድ ኩንታል ስንዴ 1,927.80 ብር እያቀረብን ነው፤›› ብለዋል

የሸገር ዳቦ ፋብሪካው መከፈት በተበሰረበት ጊዜ በቀን ከሁለት ሚሊዮን ያላነሰ ዳቦ እያመረተ ለነዋሪው ያደርሳል ቢባልም፣ አሁን ላይ ግን በአማካይ 1.2 ሚሊዮን ያልበለጠ ዳቦ በቀን እያቀረበ እንደሆነ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ከሰኔ 24 እስከ ሐምሌ 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ካሠራጨው ሪፖርት የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡

የሸገር ዳቦ አቅርቦትና ምርት ለምን እንደቀነሰ ፋብሪካው ድረስ በመሄድ ሪፖርተር ለማናገር ጥረት ቢያደርግም በጥበቃ ክፍል ሠራተኞች በመከልከሉ ማብራሪያ ለማግኘት አልተቻለም፡፡ የሸገር ዳቦ ፋብሪካ ኃላፊ ከሆኑት አቶ ኃይሉ ቡልቡላንም በስልክ ለማናገር ሞክረን ‹‹በሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በኩል ባሉ ሰዎች እንጂ እኛ መረጃ አንሰጥም›› በማለት ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡ የሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊን ለማናገር ብንሞክርም፣ በሥራ ምክንያት ከአዲስ አበባ ውጪ መሆናቸውን ገልጸው ሲመለሱ መረጃውን እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡

መሠረታዊ ፍላጎት የሆነውን የዳቦ አቅርቦት ከማሻሻል አንፃር ሪፖርተር ያናገራቸው የምጣኔ ሀብት መምህር አቶ አሸናፊ አዕምሮ እንዳሉት፣ መንግሥት በተለይ ከማንኛውም የንግድ ዘርፍ ዳቦ ሸምተው ለመመገብ ኢኮኖሚው የሚገዳደራቸውን ማኅበረሰብ ክፍሎች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት አለበት፡፡ ቃል በገባው መሠረት ለማኅበረሰቡ የዳቦ ጥያቄ አስተዳደራዊ ውሳኔ በማስተላለፍ ችግሩን ለማስተካከል ክትትል ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ መንግሥት አሁን ላይ የሚታየው የዳቦ አቅርቦት የማይፈታ ከሆነ፣ መልሱ ግልጽ እንደሆነና የዳቦ ጥያቄ መሠረታዊ ጥያቄ በመሆኑ የፖለቲካም፣ ቀውስ መፈጠሩ እንደማይቀር አስገንዝበዋል፡፡

ሸገር ዳቦ በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በሆነው ሆራይዘን ፕላንቲሸን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በ900 ሚሊዮን ብር በከተማው አስተዳደር ልዩ ድጋፍና ክትትል ተገንብቶና በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ተመርቆ ሰኔ 19 ቀን 2012 ዓ.ም. አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች