መስከረም ‹‹ከረመ›› ከሚለው ግስ የተገኘ ሲሆን ትርጓሜውም ቀዳማይ፣ ለዓለም ሁሉ መጀመሪያ፣ ርእሰ ክራማት፣ መቅድመ አውራኅ ማለት ነው፡፡ መስከረም፣ ዐውደ ዓመት፣ የክረምት ጫፍ መካተቻ፣ የመፀው መባቻ ማለትም ይሆናል፡፡ መስከረም ከጥንት ጊዜ ጀምሮ ለዓለም ሁሉ የመጀመሪያ ወር እንደሆነ ይታመንበታል፡፡
መስከረም በክረምት ውስጥ የሚካተት ቢሆንም የጨለማው ጊዜ አልፎ ብርሃን የሚታይበት፣ ዕፀዋትና አዝርዕት የሚያብቡበትና የሚያፈሩበት፣ እንስሳት የጠራ ውኃ እየጠጡ፣ ለምለም ሣር እየነጩ የሚቦርቁበት፣ በአጠቃላይ ምድር በአበቦች የምታጌጥበት፣ ሰማይ የደመና ቡሉኮውን (ጋቢውን) ጥሎ ቀን ብቻ ሳይሆን ሌሊት በከዋክብት ማጌጥ የሚጀምርበት ወቅት በመሆኑ ልዩ ወር ናት፡፡ ለዚህም ነው በሰኔ መጨረሻ፡-
‹‹ነው ወይ ልንለያይ ልንበታተን
ዳግመኛ ለመምጣት ተስፋ ሳይኖረን፤››
እያለ በእንባ የተለያየው ተማሪ በመስከረም ወር ተመልሶ ትምህርት ቤት ሲገናኝ፡-
‹‹መስከረም መስከረም መስከረም ለምለም
ከወራቱ ሁሉ እንደ አንቺ የለም
ደመናውም ሸሸ እያጉረመረመ
በመስከረም ማማር እየተገረመ፤››
በማለት የሚዘምረው፡፡
– ካሕሣይ ገ/እግዚአብሔር ‹‹ኅብረ–ብዕር›› (1998)