Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልክብረ መውሊድ

ክብረ መውሊድ

ቀን:

‹‹አሏሁም መሶሌ አላሙ ሀመዴ

ሙሐመድ፣ ሙሐመድ የዓለሙ ዘውድ፣

ተቆጥሮ የማያልቀው የሱማ ገለታ፣

ለሙሐመድ ኡመት ያደረገን ጌታ፣

መሻሪያ ሰጥቶናል ከወንጀል በሽታ፣

ሰላምና ሶላት ይጉረፉ ጠዋት ማታ፣

በአህመድ በኛ ጌታ በአዘሉውድ፣

ሙሐመድ፣ ሙሐመድ የዓለሙ ዘውድ፡፡››

ይህን የመንዙማ ዝማሬ በየዓመቱ ለሕዝበ ሙስሊሙም ሆነ በጎ ፈቃዱ ላላቸው ሁሉ በነቢዩ መሐመድ የመውሊድ ዕለት ረቢ አወል 12 ቀን ላይ በቅብብሎሽ የሚያሰሙት ባለመንዙማዎች ናቸው፡፡

የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ያዘጋጀው አንድ የጥናት መድበል የመንዙማን ምንነት እንደሚከተለው ገልጾታል፡፡

‹‹መንዙማ ምስጋና (ማወደስ) ማለት ነው፡፡ መንዙማ በይዘቱ በዋነኛነት ከሃይማኖታዊ ዝማሬዎች ይመደብ እንጂ በውስጡ የተለያዩ ማኅበራዊና ፖለቲካ መልዕክቶችንም ያቀፈ ነው፡፡ ሃይማኖታዊ ይዘቱም አላህ የሚመሠገንበት፣ ነቢዩ መሐመድ የሚሞገሱበት፣ የእስልምና ትምህርት የሚሰጥበት፣ ታላላቅ ሰዎች (አወሊያዎች) እና መላዕክት የሚወደሱበት፣ ገድላቸውና ተዓምራቸው የሚነገርበት፣ ችግር (ድርቅ፣ ረሃብና በሽታ) የመሳሰሉት ሲያጋጥሙ የተማፅኖ ጸሎት የሚደረግበት ነው፡፡›› 

መንዙማ ከሚተገበርባቸው በዓላት አንዱ የነቢዩ መሐመድ ልደት በዓል መውሊድ ነው፡፡ በአብዛኛው የመንዙማ ግጥሞች የሚጀምሩት አላህና ነቢዩ መሐመድን በማወደስ ሲሆን፣ የሚጨርሱት ደግሞ አላህን ለማመስገንና ለነቢዩ መሐመድ ሰላምና እዝነትን አላህ እንዲሰጣቸው ነው፡፡ የመንዙማው አቀንቃኝ በተሳታፊዎች ፊት ሲያቀነቅን ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን የአከዋወን ስልት በመከተል የተለያዩ አካላዊ እንቅስቃሴዎችን ያሳያል፡፡ ከግራ ወደ ቀኝ ከቀኝ ወደ ግራ ሰውነቱን ያወዛውዛል፣ ታዳሚዎችም አስፈላጊውን አጸፋና ምላሽ በድምፅና በጭብጨባ ይገልጻሉ፡፡

የመንዙማ አጨፋፈር እንደ ዜማዎቹ ዓይነት ይለያያል፡፡ ዝግ ያለ የድቤ መምቻ ያላቸው መንዙማዎች የአጨፋፈር ስልት ምቱን ተከትለው እየዘለሉና እጅን ከአናት በላይ እያሳለፉ ማጨብጨብ ሲሆን፣ ፈጣን የድቤ ምት ያላቸው መንዙማዎች ደግሞ እያጨበጨቡ ከወገብ በላይ አካላቸውን ወደ ግራና ወደ ቀኝ ማወዛወዝ ናቸው፡፡

ዒድ መውሊድ

ሕዝበ ሙስሊም ዘንድሮ ዒድ መውሊድን የሚያከብረው በኢስላም ካሌንደር (ሐሳበ ሒጅራ) መሠረት በሦስተኛው ወር በረቢ አል አወል 12 ቀን 1443 ዓመተ ሒጅራ ሲሆን፣ ይህም በኢትዮጵያ የጨረቃና የፀሓይ ጥምር አቆጣጠር ጥቅምት 12 ቀን 2022 ዓ.ም. ማለት በፀሓያዊው አቆጣጠር ጥቅምት 9 ቀን 2014 ዓም (ዓመት) ይውላል፣ ይከበራል፡፡

ታሪክ

... 570 በረቢ አል አወል አሥራ ሁለተኛ ቀን መካ ውስጥ እንደተወለዱ ይታመናል፡፡ ዕለቱም ‹‹ዒድ መውሊድ›› (የልደት በዓል) በመባል ይጠራል፡፡ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪና ደራሲው አቶ ተሾመ ብርሃኑ ‹‹የመውሊድ ማኅበራዊ ፋይዳ ምንድነው?›› በሚለው መጣጥፋቸው እንደገለጹት፣ የነቢዩ ሙሐመድ የልደት ቀን በብዙ አገሮች መከበር ከመጀመሩ በፊት ሰዎች ነቢዩ ሙሐመድ ራሳቸው ወደ ተወለዱበት ቤት በመሄድ ጸሎት ያደርሱ ነበር፡፡

ይህም ነቢዩ መሐመድ የተወለዱበት ቤት የኸሊፋ ማህዲ ሚስት በነበረችውና የሐሩን አልረሺድ እናት በሆነችው፣ በአል ኸይዙራን ወደ መስጊድነት ተቀየረና ብዙ ምዕመናን ተሰብስበው ጸሎታቸውን የሚያደርሱበት ሥፍራ ሆነ፡፡ የልደት ቀናቸው መከበር የጀመረው በግለሰቦች ተነሳሽነት እንደሆነም አንዳንድ መረጃዎች ቢያመለክቱም፣ በራቢ ዓል አወል 12 ቀን ወይም ከዚያ ቀን ጀምሮ ባለው በዕለተ ሰኞ ይከበራል፡፡

በብዙ አገሮች የነቢዩ ሙሐመድ ልደት በሚከበርበት ጊዜ ‹‹ቃሲዳ አልቡርዳ›› በሚል ርዕስ 13ኛው ክፍለ ዘመን የተጻፈውን የግጥም መጽሐፍ የሚነበብ ሲሆን እንደ ኢትዮጵያና ሱዳን ያሉ አገሮች ደግሞ በራሳቸው ሊቃውንት የተገጠሙትን የውዳሴ ግጥሞች በዜማ ያቀርባሉ፡፡ በግጥሞቹም ውስጥ የነቢዩ አወላለድ፣ የእናታቸው፣ የአባታቸውና የቤተሰቦቻቸው ታሪክ፣ የነቢዩ ሙሐመድ የልጅነት፣ የወጣትነትና የአዋቂነት ዕድሜ ክንውኖች፣ ስለ ደግነታቸው፣ ስለ አርቆ አስተዋይነታቸው፣ ስለነቢይነታቸው፣ ስለመጀመርያው ራዕይ፣ በመጀመርያ ሙስሊም ስለሆኑ ተከታዮቻቸው፣ ስለገጠማቸው ፈተና ወዘተ ይካተታሉ፡፡

እንደ አቶ ተሾመ ማብራሪያ በኢትዮጵያ ውስጥ የመውሊድ በዓል ከሚከበርባቸው ሥፍራዎች ውስጥ በወሎ ዳና፣ ገታ ንጉሥ፣ በባሌ ሸኽ ሑሴን ባሌ (አናጀና) በሐረር ከተማ፣ በትግራይ ዓዲርጉድ፣ ግጀት፣ ራያ (አና) ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የመውሊድ በዓል በሚዘጋጅበት ቦታ አስቀድሞ እንግዶችን ለማስተናገድ የሚያስችል ሁኔታ ምክክር ተደርጎ ይመቻቻል፡፡ መውሊድ ወደሚዘጋጅበት ተካፋይ ሰውም አንድም ተጋብዞ ካለበለዚያም ጠይቆ በእግር፣ በግመል፣ በበቅሎና በፈረስ ዛሬ ደግሞ በመኪና ሥፍራው መምጣት ይጀምራል፡፡ ወደ መውሊዱ ሥፍራ የሚመጡት በአብዛኛው ኢስላማዊ ዕይታ፣ ራዕይ፣ ዓላማና አመለካከት ይዘው የተለያየ የዕድሜ መጠን፣ የዕውቀት ደረጃና ፍላጎት ያላቸው ሲሆኑ ኢስላምን ባይከተሉም የሚከተሉ ሰዎችን ተከትለው መንፈሳዊና ቁሳዊ ጥቅም የሚያገኙ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

«መውሊድ አልነቢ» ወይም «መውሊድ አንነቢ» በአጭሩ «መውሊድ» ማለት የነቢዩ ሙሐመድ የልደት ቀን ነው፡፡ ቱርካውያን ደግሞ «መውሊዲ ሸሪፍ» ይሉታል፡፡ ትርጉሙም «የተቀደሰው ልደት» እንደማለት ነው፡፡ ፋሪሳውያንም «ሚላድ ፓየምባረ ኢክራም» ሲሉ ይጠሩታል፡፡ የታላቁ /የቅዱሱ ነቢይ ልደት እንደማለት ነው፡፡ አልጀሪያውያን በበኩላቸው ‹‹መውሊደ ነቢ ሻሪፍ›› ሲሉት የቅዱሱ ነቢይ ልደት ቀን ማለታቸው ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ‹‹የውም አነቢ›› ማለትም የነቢዩ ቀን ብለው በየቋንቋቸው የሚጠሩት አሉ፡፡ ዞሮ ዞሮ የነቢዩ ሙሐመድ የልደት በዓል ማለት ነው፡፡

የመውሊድ ሥነ በዓል በጡርሲና

መውሊድ በልዩ ሥነ በዓል ከሚከበርባቸው ቦታዎች አንዱ የጡርሲና መስጊድ ነው፡፡ ሀገሬ ሚዲያ ኮሙዩኒኬሽን ባሳተመው ‹‹የኢትዮጵያ ፌስቲቫል ማውጫ›› ላይ እንደተገለጸው፣ የጡርሲና መስጊድ በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን (ወሎ) ከዞኑ ርዕሰ ከተማ ከከሚሴ 16 ኪሎ ሜትር በከሚሴና በወለዲ ከተሞች መካከል ሸከላ ተብላ በምትጠራ ትንሽ የገጠር ከተማ ይገኛል፡፡

የጡርሲና መስጊድ መሥራች ሼክ መሐመድ አማን ይባለሉ፡፡ የጡሩሲና መስጊድ የተሠራው በሳርና በእንጨት ሲሆን ስፋቱ 625 ሜትር ነው፡፡ መስጊዱ ከትልቅነቱ የተነሳ በትልልቅ ምሰሰዎች የተደገፈ ነው፡፡ የውጭ ምሰሶዎች 85 ሲሆኑ የውስጥ ምሰሶዎች 41 ናቸው፡፡ በመስጊዱ ለመስጊዱ ኅብረተሰብ የሚቀርበው ቡና የሚዘጋጅበት ክፍል ውስጥ ርዝመቱ ወደ ሁለት ሜትር የሚሆን ረከቦት፣ 150 የሚበልጡ ሲኒዎች ያሉ ሲሆን፣ ረከቦቱ በአንድ ጊዜ 190 ሲኒዎችን መደርደር የሚችል ነው፡፡

ጀበናዎቹ ደግሞ የእንስራ መጠን ያላቸው ከብረትና ከሸክላ የተሠሩ ናቸው፡፡ የቡና ሙቀጫዎችም በተመሳሳይ የእህል ሙቀጫ መጠን ያላቸውና ትላልቅ ናቸው፡፡ ቡና ማፍሊያዎቹና የንፍሮ መቀቀያ በርሜሎች ናቸው፡፡ ሌላው የሥጋ ቤቱ ክፍል ሲሆን የዚህ ክፍል ዋነኛ ተግባር የዕርድ ከብቶች ከታረዱ በኋላ ሥጋው የሚቀመጥበትና ተዘጋጅቶ ለመስጊዱ የሚደርስበት ቦታ ነው፡፡

በመውሊድ ጊዜ እስከ 27 ከብት ይታረዳል፡፡ በፆም ጊዜ በተለያዩ ዝግጅቶች የማር ስጦታ ለመስጊዱ ሲቀርብ ማር እየተበጠበጠ የሚዘጋጅበትና ለመስጂዱ ኅብረተሰብ የሚከፋፈልበት ክፍል ደግሞ ማር ቤት ይባላል፡፡ በጡርሲና መስጂድ በየዓመቱ የመውሊድ በዓል በተለየ ድምቀት ይከበራል፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...