ኳታር በሚቀጥለው ዓመት በምታስተናግደው የዓለም ዋንጫ አፍሪካን ከሚወክሉ አንዱ ለመሆን፣ በምድብ ሰባት ማጣርያ የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) ሁለት ጨዋታዎች እየቀሩት ከወዲሁ ተሰናብቷል፡፡
ከደቡብ አፍሪካ፣ ከጋና እና ከዚምባቡዌ ጋር ተደልድሎ የምድብ ማጣሪያውን እያከናወነ ያለው ብሔራዊ ቡድኑ፣ ዚምባቡዌን በሜዳው በጠባብ ውጤት (1 ለ 0) ሲያሸንፍ በጋና ከሜዳው ውጪ፣ በደቡብ አፍሪካ ደግሞ በደርሶ መልሱ ሁለቴ ሽንፈትን አስተናግዷል፡፡
ይህ የዋሊያዎቹ ተደጋጋሚ ሽንፈት ሰሞነኛ መነጋገሪም ሆኗል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ዋሊያዎቹ ከጋናው የምድብ ጨዋታ ጀምሮ፣ ከኳታሩ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ውጪ መሆኑን ባረጋገጡበት የደቡብ አፍሪካ ሽንፈት ድረስ፣ ከተጋጣሚዎቻቸው እንቅስቃሴ አኳያ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ቢኖራቸውም በስኬት አላጀቡትም፡፡ በጨዋታው ሒደት ተጫዋቾቹ በፈጠሯቸው ተደጋጋሚ ስህተቶች ለውጤቱ መታጣት አንዱ ምክንያት ሆኗል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ሽንፈትን በፀጋ ተቀብሎ ለመሻሻል መሥራት እንጂ፣ ምክንያታዊነት የጎደለው ቁጭት የትም እንደማያደርስ የሚያንፀባርቁ አስተያየቶች እየተደመጡ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ ቡድን በደቡብ አፍሪካ አቻው በሜዳውና ከሜዳው ውጪ ሽንፈትን ቢያስተናግድም በኳስ ቁጥጥሩ በኩል የተሻለ እንደነበር የሚናገሩት አስተያየት ሰጪዎች፣ ለሽንፈቱ ምክንያት የሚሉት ተከላካዮችና በረኞች ከሚፈጽሙት ስህተት በተጨማሪ አሠልጣኝ ውበቱ አባተ በመረጡት የጨዋታ ታክቲክና የተጫዋቾች የቦታ አጠቃቀም ጭምር ከፍተኛ ክፍተት የነበረበት መሆኑ ሲናገሩ ይደመጣል፡፡
በዚህ ጉዳይ ሪፖርተር ያነጋገራቸውና ‹‹የኳስ ቁጥጥር ብልጫ›› በሚለው በምልዓት የማይስማሙ አሠልጣኞችና የቀድሞ ተጫዋቾች በበኩላቸው እንደሚሉት፣ የቡድኑ አጨዋወት ሜዳ ላይ ብልጭ ብሎ የሚጠፋ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የነበረው መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ይሁንና ለዚህ ድክመት አሠልጣኞችን፣ ተጫዋቾችንና ሌሎች የቡድኑ አባላት ብቻቸውን ተጠያቂ ሊደረጉ እንደማይገባም ያስረዳሉ፡፡ ምክንያት የሚሉት ደግሞ ለብሔራዊ ቡድን ዋነኛ ግብዓት ተብለው የሚጠቀሱትና በአኅጉራዊ ውድድሮች ላይ አገሪቱን በመወከል ከሚሳተፉ ክለቦች ውስጥ ለአፍሪካ የክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግና ለአፍሪካ ክለቦች ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የቀረቡት ፋሲል ከተማና ኢትዮጵያ ቡና ከፉክክሩ ውጪ የሆኑት በተመሳሳይ ገጽታ ነው፡፡ ክለቦቹ ብልጫ የተወሰደባቸው፣ ከደካማው የምሥራቅ አፍሪካውያኑ ሱዳንና ዑጋንዳ ክለቦች መሆኑ ሲታይ ስህተቱ ዘርፈ ብዙ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
ከዘጠኝ ዓመት በፊት ዋሊያዎቹን ከ31 ዓመታት በኋላ ለአኅጉራዊ መድረክ ያበቁት ኢንስታራክተር ሰውነት ቢሻውና የኦሊምፒክና የዓለም ሻምፒዮናው ኃይሌ ገብረሥላሴ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወቅታዊ ብቃት ዙሪያ አስተያየት ከሰጡ ሙያተኞች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ የሁለቱ ሙያተኞች አስተያየት ዋነኛ ትኩረቱን ያደረገው፣ ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት በተለይ በእግር ኳሱ ዙሪያ የሚገኘው ሙያተኛ በአጠቃላይ አንዱ በሌላው ላይ ጣት ከመጠቋቆም ተላቆ ተቀራርቦ መሥራቱ ላይ ነው፡፡
ከሰሞኑ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን (ካፍ) ከአራት ወራት በኋላ በካሜሩን የሚከናውነውን አኅጉራዊ ሻምፒዮና ምክንያት በማድረግ የአፍሪካን ዋንጫ በየአገሩ እያስተዋወቀ ይገኛል፡፡ አዲስ አበባ የደረሰው ዋንጫው ሐሙስ ጥቅምት 4 ቀን 2014 ዓ.ም. በሐያት ሬጀንሲ ሆቴል ለዕይታ ሲበቃ ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴን ጨምሮ ታዋቂ ሰዎችና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አባላት ተገኝተዋል፡፡
‹‹እግር ኳሱ ከሚፈልገው መሠረታዊ ግብዓቶች አንዱ የሆነው ሩጫ የእኛ ኢትዮጵያውያን ነው፤›› በማለት የተናገረው ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ ኢትዮጵያውያን ተጨዋቾች በእግር ኳስ ስኬታማ ለመሆን ጠንክረው መሥራት እንደሚጠበቅባቸው መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡
ሌሎች ታዳሚዎችም ዋሊያዎቹ ከፊት ለፊታቸው ለሚጠብቃቸው የአፍሪካ ዋንጫ በዓለም ዋንጫ ማጣርያ የታየባቸው ክፍተቶች ላይ ሠርተው በአኅጉራዊው መድረክ ቢያንስ የተሻለ ተፎካካሪ ለመሆን በትጋት መሥራት አለባቸው ብለዋል፡፡
ከዚህ ውጪ ጠንካራውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን ጨምሮ ክለቦችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በጥናት ላይ በመመሥረት ለአገሪቱ እግር ኳስ ወጥ የሆነ የሥልጠና ልኬት ማዘጋጀት ብቻ ሳይሆን፣ ከታዳጊዎች ጀምሮ ተመጋጋቢነት ያለው ብሔራዊ ቡድን መገንባት እንደሚያስፈልግ ጭምር የሚናገሩ አልጠፉም፡፡
ዋሊያዎቹ በቁጥራዊ ሥሌት አሁን ላይ ከኳታሩ የዓለም ዋንጫ ውጪ መሆናቸው ቢታወቅም፣ በሜዳቸው ከጋና እንዲሁም ከሜዳቸው ውጪ ከዚምባቡዌ ጋር ቀሪ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ፡፡
ምድቡን ደቡብ አፍሪካ በ10 ነጥብና በ4 ግብ ክፍያ ስትመራ፣ ምዕራብ ጋና በ9 ነጥብና በ3 ግብ ክፍያ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ ኢትዮጵያ በ3 ነጥብና በ3 የግብ ዕዳ፣ ሁለተኛዋ ተሰናባች ዚምባቡዌ በ1 ነጥብና በ4 የግብ ዕዳ ከግርጌ ተቀምጣለች፡፡ ከምድቡ የመጨረሻ ኃላፊ ለመሆን ደቡብ አፍሪካና ጋና የሚያደርጉት ግጥሚያ ወሳኝ ይሆናል፡፡
የኳታሩ ዓለም ዋንጫ የሚካሄደው ከኅዳር 12 ቀን እስከ ታኅሣሥ 9 ቀን 2015 ዓ.ም. መሆኑ ታውቋል፡፡