Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉ‹‹ክልል›› - የሥነ ልሳን ቅቡልነት የጎደለው ስሁት ስያሜ

‹‹ክልል›› – የሥነ ልሳን ቅቡልነት የጎደለው ስሁት ስያሜ

ቀን:

በሁሴን አዳል መሐመድ (/)

በአገራችን ከቋንቋ ሳይንስ መርህ ውጪ የፖለቲካ ቃላት ፍላጎት ክፍተትን ለመሙላት፣  አልባሌ ቃላትን በፖለቲካ ቢሮ ውስጥ በግብታዊነት ፈጥሮ ሥራ ላይ ማዋል  የተጠናወተን የተለመደ  አሠራር ነው፡፡ ይህ ክፉ ልማድ በቋንቋ ጤንነትና ዕድገት፣ እንዲሁም በተግባቦት ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ቀላል አይደለም፡፡ የዚህን ችግር መኖር በሥልጣን ዘመኑ የመጨረሻ ዓመታት ገደማ የተገነዘበው የደርግ መንግሥት፣ ‹‹የኢትዮጵያ ቋንቋዎች አካዳሚ››  የሚል ተቋም አቋቁሞ ይህን ችግር የሚያቃልል የሳይንስናቴክኖሎጂ መዝገበ ቃላት እንዲዘጋጅ አድርጎ ነበር፡፡

መዝገበ ቃላቱታኅሳስ 1989 ዓ.ም. በአርቲስቲክ ማተሚያ ቤት ታትሞ አገልግሎት ላይ መዋሉ አይዘነጋም፡፡ መዝገበ ቃላቱን ማዘጋጀት አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት የቴክኖሎጂ ጽንሰ ሐሳቦችን ለመግለጫ የሚያገለግሉ የአማርኛ ቃላትን ለመሰየም፣ ለአገር ዕድገት የሚደረግ ማንኛውንም ግስጋሴ በሳይንስናቴክኖሎጂ ዕውቀት ለመደገፍ፣ ራስን ከሳይንስናቴክኖሎጂ ዕውቀት ጋር ለማስተዋወቅና በዚህ ዕውቀት የተካነ የሰው ኃይል ለመፍጠር ነበር፡፡

መዝገበ ቃላቱ ሥራ ላይ ሲውል የአማርኛ ቋንቋ አጠቃቀም ሥርዓትን መልክ ለማስያዝ፣ ቋንቋውን አበልፅጎ የሳይንስናቴክኖሎጂ መተግበሪያና የከፍተኛ ትምህርት ማስተማሪያ ቋንቋ እንዲሆን የሚደረግ ጥረትን ያፋጥናል ተብሎ ተገምቶ ነበር፡፡   የደርግ መንግሥትን የተካው ትሕነግ ኢሕአዴግ ገና ከጧቱ የአማራን ሕዝብ ጠላቴ ብሎ በመነሳት፣ ቋንቋውንም የአማራ ሕዝብ ቋንቋ ብቻ ተደርጎ እንዲታይ በማድረግ ቀደም ሲል በአካዳሚው የተጠናው ጥናት አስፈላጊ የሆነበትን ዓላማ ወደ ጎን በመግፋት ብዙ የተደከመበትን ጥረት በጅምር አስቀረው፡፡

የተዘጋጀው መዝገበ ቃላት ተገቢው ዕውቅና አግኝቶ በስፋት የአገርን ዕድገት እንቅስቃሴ ለማሳለጥ ድጋፍ ሰጪ መሣሪያ እንዳይሆንብሎም በጥናቱ የቀረቡ የመፍትሔ ሐሳቦች ሥራ ላይ እንዳይውሉ አደናቀፈ፡፡ የዚህ መዝገበ ቃላት ሥራ ላይ አለመዋል ቋንቋው የአጠቃቀም ስታንዳርድ እንዳይኖረው፣ የቴክኒክ ቃላትን በዘፈቀደ የመጠቀም ችግርንና በተለያዩ የትምህርት መስኮች ሐሳቦችን በትክክል የመግለጽ አቅምና የቋንቋ ችግር ፈችነት በአስተማማኝ ሁኔታ እንዳይፈጠር አድርጓል፡፡

ኢሕአዴግ አማርኛ ቋንቋን ጠልቶ በማስጠላት፣ የቋንቋውን ዕድገትና መስፋፋት በማቀብ ተግባሩ በሁሉም ዜጋ ዘንድ ይታወቃል፡፡ የቋንቋውን አፈጣጠርና ዕድገት ካለፉ ጨቋኝ ሥርዓቶች ጋር በማዛመድ በሌሎች ብሔረሰቦች ሕዝብ እንዲጠላ ማድረግ፣ የቋንቋውን የሥርጭት አድማስ ማጥበብ፣ ቋንቋው ከትምህርት ሥርዓቱ ቀስ በቀስ እንዲወጣ ማድረግ፣ የንግግርናጽሕፈት አገልግሎት ስታንዳርድ ተዘጋጅቶለት በሥርዓት ሥራ ላይ እንዲውል ባለማድረግ ማዳከም፣ በቋንቋ ፖሊሲና ደጋፊ የሰዋሰው መመርያ አለመጠናከር  የተነሳ ተጠቃሚው ቋንቋውን እንዳሻው እንዲያደርገው፣ ወዘተ. መሰሪ ተግባር ፈጽሟል፡፡

ቋንቋው በዘዴ ቀስ በቀስ ተዳክሞ እንዲጠፋ በግልጽርምጃ ከመውሰድ በተጨማሪ ትርጉማቸው በውል ያልታወቁ የቴክኒክ ቃላትን በዘፈቀደ በመጠቀም፣ አግባብ ባለው የቴክኒክ ቃል መሰየም የሚገባቸው ስሞች በአግባቡ እንዳይሰየሙ፣ ብሎም የቋንቋ ችግር ፈቺነት ችግር እንዲከሰት ተደርጓል፡፡ የዚህን  የሥነ ልሳን ቅቡልነት ጉድለት ችግርን በክፍተትነት ለማሳየት ሌሎች በርካታ አብነቶችን መጥቀስ ቢቻልም፣  ለአሁኑክልልየሚለውን የቴክኒክ ቃል የአጠቃቀም ግድፈት እንመለከታለን፡፡

በዚህ መዝገበ ቃላት ውስጥ በጂኦግራፊ (ምድረ ፅፍ) ትምህርት የመልክዓ ምድር ጽንሰ ሐሳብን ለመግለጽ እንዲያስችል ‹‹ክል›› (‹‹›› ጫን ተደርጎ የሚነበብ) የእንግሊዝኛው (Region) አቻ ቃል ተደርጎ ተዘጋጅቷል፡፡ ሰዎች ቃሉን አውቀው እምብዛም ሳይጠቀሙበት በመቅረት በመዝገበ ቃላት የሌለ ‹‹ክልል›› የሚል ቃል የመልክዓ ምድር ጽንሰ ሐሳብን ለመግለጽ እንዳሻቸው ይጠቀማሉ፡፡ ‹‹Region›› ለሚለው ቃል ‹‹ቀጣና›› የሚል የአማርኛ አቻ ቃል መጠቀም ተጀምሮ እንደነበርም አስታውሳለሁ፡፡

ዳሩ ግን በማቲማቲክ ትምህርት ለዚሁ የእንግሊዝኛ ቃል አቻ የሆነ ቃል ‹‹ክልል›› (‹‹›› ጫን ተደርጎ የሚነበብ) አለ፡፡  በአሁኑ ወቅት ‹‹ክልል›› አንድ የአገር ክፍልን ወይም ብሔረሰብ ሕዝብ የሠፈረበትን አካባቢ ለመግለጽ መንግሥት በስፋት እየተጠቀመበት ይገኛል፡፡ በዚህ ዕሳቤ ጥቅም ላይ የዋለው ይህ ‹‹ክልል›› የሚባል ቃል የፖለቲካ መቀንጨር ያስከተለው ያለ ቦታው ጥቅም ላይ የዋለ ትርጉሙ በውል ያልተጨበጠ ነው፡፡

በዚህ ሁኔታ ባለፉት 30 ዓመታት የሙያ ኃላፊነትና ተጠያቂነት በጎደለው መንገድ የቴክኒክ ቃላትን በንግግርም ይሁን በጽሕፈት እንዳሻው በመጠቀም፣ የአማርኛ ቋንቋ ይዘት ሲድበሰበስና ሲደበዝዝ ቆይቷል፡፡ ‹‹ክልል›› የሚለው ቃል ያላግባብ በአዋጅ ሥራ ላይ የዋለው የፖለቲካ ድፍረት በፈጠረው ስህተት ስለሆነ፣ ይህን የመሰለውን የተሳሳተ የቋንቋ አጠቃቀም ጉድለት ማስተካከል አገራችን አሁን በተያያዘችው የለውጥ ጎዳና መታየት ያለበት አንድ ጉዳይ ሆኖ ይቀርባል፡፡ የማቲማቲክ ጥግ ተከትለን በሥነ ምኅዳር ጥናት መስክ እስካሁን በተለምዶ ያለ የቃሉን አጠቃቀም ስናይ ‹‹ክልል›› የተፈጥሮ ሥነ ምኅዳርን መዝጋት፣ ከእንስሳት ንክኪ ነፃ ማድረግ ወይም እንስሳትን በአጥር ውስጥ ዘግቶ መጠበቅን ይገልጻል፡፡ የሚጠበቅ ነገርን ከውጭ ዘግቶ (Ex-Closure) ወይም ዘግቶ በውስጥ (In-Closure) መጠበቅ ይቻላል፡፡ 

ከውጭ መዝጋት የሚባለው ቀደም ሲል ለሰውና ለቤት እንስሳት ጥቅም ለረዥም ጊዜ ክፍት በመደረጉ በልቅ ግጦሽና ደን ጭፍጨፋ የተጎዳ የተፈጥሮ አካባቢን፣ ‹‹በሕግ ክልከላ›› ወይም ‹‹በሽቦ አጥር ክለላ›› ከእንስሳትናሰው ንክኪ ነፃ አድርጎ እንዲያገግም ማድረግ ነው፡፡ ዘግቶ በውስጥ መጠበቅ እንስሳት አርቢ ኢንቨስተሮች እንደሚያደርጉት ሰፊ መሬትን በሽቦ አጥሮ በውስጡ እንስሳትን በመልቀቅ እንስሳቱ ወደ ውጭ እንዳይወጡ አድርጎ በመጠበቅ ማርባት ወይም ማድለብ ነው፡፡ የእንስሳቱን ቀለብ ከውጭ በሚቀርብ መኖ እየደጎሙ፣ በተፈጥሮ የበቀለውን ሳር እየመገቡ፣ የሚጠጡትን ውኃ በማጠጫ ገንዳ በማቅረብ ለሽያጭና ለዕርድ እስኪደርሱ ይጠበቃሉ፡፡ ለምርት መድረሳቸው ሲረጋገጥ ከሥር ከሥር እየተቀሉ/እየተቀነሱ ይወገዳሉ፡፡

‹‹የብሔር ፖለቲከኞች›› ሁሉንም የቀድሞ ሥሪት ለማክሰም ሲሉ የተፈጥሮ ሥነ ምኅዳርና እንስሳት ማኔጅመንት ገላጭ ቃልን፣ ለኅብረተሰብና ለአገር ገላጭነት በማይመጥን ደረጃ ያለ ዕውቀት በድፍረት ጥቅም ላይ እንዲውል ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ በመሆኑም የሥነ ምኅዳርንና የእንስሳትን ክለላ የሚገልጽ ተለዋዋጭ መሥፈርት የሕዝብ ክለላን ለመግለጽ በመጠቀም የኅብረተሰቡን ሞራልና ክብር እየጎዱ እስካሁን ድረስ መጥተዋል፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ  በብሔረሰብ እየለያዩ ለየብቻ ሲከልሉ የመከለያውንም መሥፈርት የቋንቋ አጥር አደረጉት፡፡

በአንድ በኩል የአንድ ቋንቋ መሥፈርት ያሟላ የኅብረተሰብ ክፍል በዚያው በሚናገረው የራሱ ቋንቋ አጥር ውስጥ ገብቶ እንዲታፈን (In-Closed) ሲደረግ፣ በሌላ በኩል ያንኑ አካባቢ  ቋንቋውን ለማይናገር የኅብረተሰብ ክፍል ዝግ በማድረግ ሌላው ከአካባቢው እንዲገለል (Ex-Closed) ተደረገ፡፡ በዚህ መንገድ በተደረገ ዜጎችን የመለያየት ተግባር ነባር/መጤ የሚለው ዜጎችን የማቀፍና የማግለል፣ እርስ በርሱ የሚቃረን መርህ ሕጋዊ ቅቡልነት እንዲያገኝ ሁኔታዎች ተመቻቹ፡፡

‹‹ክልል›› የሚለውን ቃል ለሕዝብ አስተዳደር መዋቅር ስያሜ መጠቀም የተጀመረው በኢሕአዴግ ዘመን ነው፡፡ ኢሕአዴግ የመንግሥት ሥልጣን በያዘ ማግሥት ኤርትራን ካስገነጠለ፣ አሰብንና አካባቢውን ጨምሮ በተንኮል ለኤርትራ አስተላልፎ ከሰጠ  በኋላ ነገሮችን በማድበስበስ የቀረውን የኢትዮጵያ ክፍል በክልል ሸነሸነ፡፡ ለመጀመርያ  ጊዜ 11 ክልሎች፣ ጥቂት ቆይቶ ደግሞ ሦስት ክልሎችን ጨፍልቆ  የደቡብ ክልል የሚል በመፍጠር ድምሩ ዘጠኝ  የብሔረሰብ ክልሎችን በመመሥረት፣ክልልምን ማለት እንደሆነ በካርታ ደግፎ ውስጥ ለውስጥ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በማስተዋወቅ አለማመደ፡፡

በወቅቱ አገር ወዳድ ዜጎችና ኢትዮጵያን የሚወዱ አንዳንድ የውጭ አገር የልማት አጋሮች ሁኔታውን በመጠራጠር ተዘጋጅቶ ለማለማመድ የተለቀቀውን ብሔረሰብን መሠረት ያደረገውን አዲስ ካርታ ለምን በማለት መጠየቅ ሲጀምሩ፣ ካርታው ለቱሪስት አገልግሎት ብቻ እንዲውል በማሰብ የተዘጋጀ እንጂ ለአገር አስተዳደር አወቃቀር ጥቅም ላይ ለማዋል እንዳልሆነ ጊዜያዊ ማስተባበያ ተሰጠ፡፡ ክልሎቹ የተቋቋሙት በቋንቋ ዋና መሥፈርት ቢሆንም ለመጀመርያ  ጊዜ አንድ፣ ሁለት፣ ሦስት… ተብሎ የቁጥር ስያሜ ተሰጣቸው፡፡

ዜጎች በዓረብ ቁጥር መጠራታቸውን በመቃወም የሞራል ጥያቄ ማቅረብ ሲጀምሩ፣ የክልሎች ስም በዓረብ ቁጥር ፈንታ በብሔረሰብ ቋንቋ ስምና በኮምፓስ አቅጣጫ ስያሜ እንዲተካ ተደርጎ ክልሎች እስካሁን ድረስ የሚጠሩበትን ስም በመስጠት፣ የሕዝብን አመለካከትና አስተሳሰብ አቅጣጫ በማስቀየር ለማረሳሳት ተሞከረ፡፡ ‹‹ብሔር/ብሔረሰብ/ሕዝቦች›› የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች፣ የሁሉም ነገር አልፋና ኦሜጋ ሲደረጉ የዜጎች መብት መከበር የሚባል ነገር ሽታው ጠፋ፡፡ ሕገ መንግሥት ከመፅደቁ በፊት የተመሠረቱ ክልሎች የኢፌዴሪ መንግሥት ህልውና ወሳኝ ዋልታዎች በመሆን፣ የሕገ መንግሥት ዕውቅና ሕጋዊ ማረጋገጫ ተሰጣቸው፡፡ የአገሪቱንም ሆነ የሕገ መንግሥቱን ዕጣ ፈንታ የአንድ ብሔረሰብ ውሳኔ ብቻ ሊያሽመደምደው፣ ወይም ሊቀይረው እንዲችል የሚያደርግ የሕገ መንግሥት ሴራ በጥንቃቄ ተሸረበ፡፡

 በክልሎች የሚኖሩ ዜጎች ነባር/መጤ በሚል መደብ ተከፍለው፣ ‹‹ነባር ብሔረሰቦች የሚባሉ ተወላጆችየክልሉ መሬት ባለቤቶችና የክልሉ መንግሥት ተዋናዮች የሚሆኑበት፣ ሌሎች መጤ ተብለው በአገራቸው ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ባይተዋሮች የሚደረጉበት የሕገ መንግሥት አሠራር ተቀይሶ በስፋት ተግባራዊ ተደረገ፡፡ መጤ ተብዬዎች በክልሉ ውስጥ የመሬት ባለቤትነት መብትም ሆነ ተግባራዊ የሕገ መንግሥት ከለላ አጡ፡፡ በዚህ መሠረት መጤ የተባሉትን ዜጎች ከውጭ ዘግቶ (Ex-Closure)፣ ነባር የተባሉትን ደግሞ ዘግቶ በውስጥ (In-Closure) ‹‹እንደ እንስሳት በማጎር›› አንዱን ባይተዋር፣ አንዱን ባለቤት በማድረግ የተገነባውን የዘመናት አብሮነት አዳክሞ በዜጎች መካከል አድልኦ በመፍጠር፣ መጤ የተባሉት ዜጎች በአገራቸው ሠርቶ የመኖርና ሀብት የማፍራት መብት ተገፈፉ፡፡

በውስጥ ተዘግቶባቸው የሚጠበቁት ዜጎች ባለመብት የክልሉ ነባር ባለቤቶች ሲደረጉ፣ ከውጭ የተዘጋባቸው መጤ የተባሉት ዜጎች ደግሞ የክልሉ መብት አልባ ባይተዋሮች ተደርገው ታዩ፡፡ መጤ ተብዬዎች የዜግነት መብታቸው ባለመከበሩ ለስደት፣ እንግልትና ሞት ተዳረጉ፡፡ በመገናኛ ብዙኃን ዘወትር እንደሚገለጸው፣ እነዚህ መብት አልባ ዜጎች በግፍ ሲገደሉ ለሰው ልጆች በሃይማኖትናባህል የተፈቀደው እንደ ሰው ልጅ የመቀበር ዕድል ተነፈጋቸው፡፡ የሥነ ልሳን ቅቡልነት የጎደለው ‹‹ክልል›› የሚባል ይህ ፖለቲከኛ ሠራሽ ቃል በፖለቲካ ጉልበት ግፊት በዜጎች አዕምሮ ውስጥ ሰርፆ የፖለቲካ ቡድን ፍላጎት ማሳኪያ ሆኖ ሲያገለግል፣ የፖለቲካ ሥርዓቱ የተዋቀረበትን መንገድ መቃወም ቀርቶ የቃሉን አጠቃቀም ግድፈት የሚጠቁም ሰው አልነበረም፡፡

ክልሎች የቋንቋ መሥፈርትን በመከተል ስለመቋቋማቸው  እንጂ፣ ‹‹ክልል›› የሚለውን የቴክኒክ ቃል ትክክል አለመሆንና የወደፊት መዘዙ ከባድ መሆኑን ያስተዋለ ጥቂት ሰው ነው፡፡ ‹‹ክልል›› ለወቅቱ ገዥ መደቦች የፖለቲካ ሥልጣን ማደላደያና ማከፋፈያ፣ አሀዳዊነትን ከአዲስ አበባ ፈልቅቆ አውጥቶ ወደ ክልል ማዕከላት ከተሞች ማዛወሪያ ጥሩ መሣሪያ በመሆን አገለገለ፡፡ የየክልሉ የአስተዳደር እርከን  አንዳንዴ ‹‹መንግሥት››፣ አንዳንዴ ‹‹መስተዳድር››፣ ከፍተኛው ባለሥልጣን ደግሞ አንዳንዴ ‹‹ፕሬዚዳንት››፣ አንዳንዴ ‹‹ርዕሰ መስተዳድር›› የሚል የክብር ሥልጣን ስም እንዳሻው እየቀያየረ ዓለሙን ሲቀጭ፣ ኢትዮጵያ በበርካታ ንዑስ መንግሥታት ተከፋፍላ የሁሉም ዜጎች ያልሆነች አገር ሆና እንደ ገና ተሠራች፡፡

የክልል መንግሥት የሁሉም ዜጎች መንግሥት ሳይሆን፣ ‹‹የነባር ብሔረሰብ ተወላጆች›› መንግሥት ተደርጎ በመወሰዱ በክልል መንግሥቱ ውስጥ ተሳትፎ ያላቸውና መብታቸው የሚከበር የእነዚህ ብሔረሰቦች አባላት ብቻ ሆኑ፡፡ የነባር ብሔረሰብ አባላት በክልላቸው መንግሥት ውስጥ የሚኖራቸውን ተሳትፎና የተጠቃሚነት ዕድል ለማስፋት፣ መጤ የሚሏቸውን ዜጎች ከሁሉም ነገር እያገለሉ ማሳደድ የክልል መንግሥት የህልውና ስትራቴጂ  ተደርጎ ተወሰደ፡፡ የተቋቋመው የክልል መንግሥት መዋቅር ለክልል ባለሥልጣናት የቅንጡነት ኑሮ ማብሰያ መሣሪያ ሆኖ ሲያገለግል፣ በፌዴራል መንግሥት መዋቅር ላይ ለሚገኙት ፖለቲከኞች ደግሞ በማዕከል ላይ የመፈናጠጫ አስተማማኝ የስበት ኃይል መጠበቂያና መቀመጫ ኮርቻ ሆኖ አገለገለ፡፡

በብሔር ፖለቲካ ሥርዓቱክልልየማዕከል ኮርቻ፣ ማዕከል ደግሞ  የክልል ዣንጥላ በመሆን ከላይ እስከ ታች በቡድን መረብ ትስስር የተደራጀ ጠንካራ የጭቆና ቀንበር በሕዝቡ ጫንቃ ላይ ወደቀ፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ቀድሞ በአማራ ብሔረሰብ ሕዝብ ስም እንደተነገደው በብሔረሰቡ ሕዝብ ስም በከንቱ ተነገደ እንጂ፣ ለሕዝቡ የተረፈው ስም ብቻ ነው፡፡ የክልል መንግሥት መዋቅር ላይ መሾም የሚያስገኘው ጥቅም በፌዴራል መንግሥት መዋቅር ላይ በመሾም ከሚገኘው እምብዛም ስለማይተናነስ፣ ክልል ላይ የተሾመ ሰው ለፌዴራል ሥልጣን እምብዛም ጠብ እርግፍ ማለት አያስፈልገውም፡፡ እንዲያውም በአንድ ዙር በማዕከል ላይ፣ በሌላ ዙር ደግሞ በክልል መዋቅር ላይ እየተገለባበጡ መመዳደቡ መንሸራሸሪያና አማራጭ ምቹ የመንሸራተቻ ስጋጃ ሆኖ አገለገለ፡፡

ለማዕከላዊ መንግሥት ሥልጣን ፍለጋ ከመላላጥ ይልቅ፣ የየነገዱ መንግሥት መሪ ሆኖ መሾም በሥልጣን ላይ የመቆያ አማራጭ ዕድል ሆነ፡፡ በዚህ ሁኔታ የተዋቀረው መንግሥታዊ የአደረጃጀት መረብ በአንድ በኩል በፌዴራል መንግሥት የከፍተኛ ፖለቲካ ሥልጣን ላይ ጎሌነት ለተቀዳጀው መንግሥታዊ ቡድን ተላላኪና አገልጋይ መፍጠር ሲያስችል፣ በሌላ በኩል  የአዳዲስ ‹‹ክልል እንሁን›› ጥያቄ መንስዔ  ሆኖ አገለገለ፡፡ ይህ አስገራሚ የፖለቲካ ግብይት በኢትዮጵያ ስንት ክልል ላይ ሲደረስ ይቆማል ብሎ መገመት የሚያስቸግር የተጨማሪ ክልሎች ፍላጎት ጥያቄን ቀሰቀሰ፡፡

የመጀመርያዎቹን ዙር ክልሎች ለማቋቋም ወሳኝ መሥፈርት ተደርጎ የተወሰደው የብሔረሰብ ቋንቋ መሥፈርት ነበር፡፡ ቀስ በቀስ የብሔረሰብ ቋንቋ የክልል እንሁንየመነሻ ጥያቄ  ብቸኛ መሥፈርት  አለመሆኑን በመሞገት፣ ከቋንቋ  ተናጋሪነት ውጭ በሌሎች መሥፈርቶች ‹‹የክልል እንሁን›› ጥያቄ ማቅረብ እንደሚቻል ግንዛቤ እየተወሰደ መጣ፡፡ ከዚህ በመነሳት ለዘመናት የተገነባ ‹‹የጋራ ሥነ ልቦና እሴት ባለቤት›› መሆናቸውን በማስታወስ፣ በዚህ መሥፈርት መሠረት ‹‹የክልል እንሁን›› መብት እንዲከበርላቸው የሚጠይቁ የኅብረተሰብ ክፍሎች  ጥያቄ እያደር ገፍቶ መጥቷል፡፡

ለማንነታችን ዕውቅና ይሰጠን ብሎ ለሚጠይቅ ሕዝብ ዕውቅና ሰጪው አካል ‹‹ማንነትህን የማውቅልህ እኔ ነኝ›› ለማለት መርህ አልባነት ስለሚሆንበት፣ ተደራጅተው ለሚቀርቡ የማንነት ጥያዌዎች መልስ ከመስጠት ውጪ ቅቡል የሆነ ሌላ የተሻለ አማራጭ ሊኖረው አይችልም፡፡ ቀደም ሲል የጋራ ማንነት አለን ብለው ለጠየቁ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተፈቀደ ዕድልን ዘግይቶ ለጠየቀ ሕዝብ ዝግ ማድረግ መርህ አልባ ያሰኛል፡፡ በየጊዜው የሚቀርብን የጋራ ማንነት ጥያቄ እያጤኑ ዕውቅና መስጠትና መፍቀድ ካልሆነ በስተቀር፣ ሌላውን መንፈግ ‹‹ከልጅ ልጅ ቢለዩ በሞት ይለዩ›› ለሚለው የአገረሰብ ብሂል እጅ መስጠት ያስከትላል፡፡  

በቋንቋ ተናጋሪነት መሥፈርት በአንድ ሰፊ ክልል ውስጥ መታጨቃቸው ትርጉም ያልሰጣቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ለዘመናት ዳብሮ ከቀድሞ ትውልድ የተላለፈላቸውን ‹‹የሥነ ልቦና ተጋሪነት እሴት›› መሥፈርት የተሻለ ትርጉም በመስጠትወሎ፣ጎንደር፣ጎጃምና በሸዋ ክልል የመሆን ጥያቄ በአማራ ክልል ፈጦ እየመጣ ነው፡፡ በኦሮሚያ ክልልም ተመሳሳይ የኅብረተሰብ መሠረት ስላለ ለጊዜው የታፈነው ጥያቄ ቀስ በቀስ ገንፍሎ ወደፊት መምጣቱ የሚቀር አይመስልም፡፡ ዳሩ ግን በአሁኑ ወቅት ጥያቄው እየቀረበ ያለው ቋንቋን መሠረት አድርጎ ቀድሞ ለተዋቀረ፣ ሌላ ተፎካካሪ የጋራ ማንነት ጥያቄን ለማስተናገድ ዝግጁ ለማይመስል መንግሥት በመሆኑ አዎንታዊ ምላሽ ለማግኘት ትግል የሚጠይቅ ጉዳይ መስሎ ይታያል፡፡ ዳሩ ግን በአገራችን ከብሔረሰብ ቋንቋና ‹‹የሥነ ልቦና ተጋሪነት እሴት›› ውጪ ሌሎች በርካታ የማንነት ብዝኃነቶችም በመኖራቸው የተነሳ፣ ሌሎች አሳማኝ የማንነት መገለጫ መሥፈርቶችን እየጠቀሱ ‹‹የክልል እንሁን›› ጥያቄ ማቅረብ የሚያስችል ተለማጭ ሁኔታ መኖሩ ሊጤን ይገባዋል፡፡

ችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ካልተሰጠው በስተቀር ኢትዮጵያ ‹‹በክልል እንሁን›› ጥያቄ እየተንበሸበሸች ስትናጥ የምትኖር ታሪካዊ አገር መሆኗ ይቀጥላል፡፡ ኢትዮጵያ በእያንዳንዱ የተደራጀ ቡድን ‹‹ክልል እንሁን›› ጥያቄ ዘወትር ስትናጥ የምትኖር አገር መሆኗ መቋረጥ ቢችል፣ ለሕዝብ ሰላም ማግኘትና ለዜጎች ኑሮ የተሻለ ዕድል ይፈጠራል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ሁለት ዋና ዋና የመፍትሔ ሐሳቦች ሊሰነዘሩ ይችላሉ፡፡ አንዱ ይህ ‹‹ክልል›› የሚለው ቃል ቀድሞውንም ቢሆን ፍቺው የተዛባ፣ የሥነ ልሳን ቅቡልነት የጎደለው፣ ለሕዝብ አስተዳደር መዋቅር የማያገለግል ስሁት የቴክኒክ ቃል ስለሆነ ቃሉን ለሕዝብ አስተዳደር ያላግባብ መጠቀም ግድፈት መሆኑን በመገንዘብ፣ የተለመደውን የሕዝብ አስተዳደር መዋቅር እርከን ስያሜዎች በመጠቀም በቴክኒክ ቃላት አጠቃቀም ረገድ ያጋጠመውን ችግር መቅረፍ ይገባል፡፡

ሁለተኛው በቋንቋ ተናጋሪነት መሥፈርት የተቋቋሙ ክልሎች ሕገ መንግሥት ከመፅደቁ በፊት በሴራ ከተቋቋሙ በኋላ በማድበስበስ የሕገ መንግሥት ዕውቅና እንዲያገኙ የተደረጉ ሕዝባዊ መሠረት የጎደላቸው ጠባብ የቡድን ዓላማን ማሳኪያ መሣሪያ ሆነው ያገለገሉ የማስመሰያ  ክልሎች ስለሆኑ፣ በሕግ መሠረት ፈርሰው የኢትዮጵያን ሕዝብ ለዘመናት የተገነባ አብሮነት የሚያስቀጥል የውስጥ አስተዳደር መዋቅር በጥናት ላይ ተመሥርቶ ማስተካከያ ማድረግ ወቅቱ የሚጠይቀው የፖለቲካ ዕድገት ክስተት ነው፡፡ 

ኢትዮጵያ በክብር ለዘለዓለም ትኑር!

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በወሎ ዩኒቨርሲቲ በተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የሥነ ሕይወት ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]  ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...