Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትኢትዮጵያ በሕግ አምላክ እንጂ በጉልበታችሁ አምላክ አትልም!

ኢትዮጵያ በሕግ አምላክ እንጂ በጉልበታችሁ አምላክ አትልም!

ቀን:

በገነት ዓለሙ

 

ዓለም አቀፋዊው ማኅበረሰብ የሚባለው አቦዳደንና ‹‹አደረጃጀት›› ሁሉ የአሜሪካና የምዕራባውያን፣ የእነዚህም ኮርፖሬት ሚዲያዎች መጫወቻ ሆኖ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የመላውን ዓለም ሕግና ሥርዓት ከተስቦው/ከኮቪዱ በላይ እያጠቃና እየጎዳ ነው፡፡ ተከታታይ ትውልዶችን ከጦርነት መርገምት ለማዳን፣ በ‹‹እኛ ዕድሜ›› እንኳን ከሁለት ጦርነቶች፣ እንዲሁም ከከሸፈው የዓለም ማኅበር/ሊግ ኦፍ ኔሽንስ ትምህርት አግኝተናል ብሎ የተቋቋመው የመንግሥታቱ ድርጅት በሰላም ላይ ሊደርስ የሚችል ሥጋትና ጠንቅን ለመከላከልና ለማስወገድ የነደፈውና የዘረጋው መላና ሥልት የጋራና የወል ዕርምጃ ነው፡፡ ‹‹Collective Measures›› ይባላል፡፡ ይህ ራሱ በፀጥታው ምክር ቤት ትክልና ያጋደለ፣ ሚዛን ያጣ አወቃቀርና አሠራር ምክንያት በዓለም ላይ የተከተለው ፍዳና መከራ ገና ተተርኮ አላበቃም፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በዚህ በያዝነው የአውሮፓውያን ዓመት የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት ብቻ የተመለከቱ አሥር ስብሰባዎች ጠርቷል፡፡ የታላቁን የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ አያለሁ ብሎ የጠራቸው ስብሰባዎች ሳይቆጠሩ፡፡ በእነዚህ ስብሰባዎች ግን የፀጥታው ምክር ቤት፣ ራሳቸው የጉዳዩ አነቃናቂ፣ ከሳሽና ባለጉዳይ ሆነው ወዲያውም ፈራጅነትን በቋሚነት የተጎናፀፉትም ሆነ፣ በአጋጣሚ በጊዜያዊነት የተቆናጠጡት አባላት ኢትዮጵያን ‹‹እንብላት›› ብለው ደግመው ደጋግመው ጎምዥትው ቢነሱም ምክር ቤቱ የተባበረ ድምፅ ሊያገኝ ባለመቻሉ ድምፅ መስጠት ደረጃ ላይ እንኳን የደረሰ የረባ ነገር ሳይመዘገብ ቀርቷል፡፡

‹‹ዓለም አቀፋዊው ማኅበረሰብ›› ግን በዋናው፣ ሕጋዊና የተለመደ የጨዋታ ሜዳ፣ የትግል መድረክ፣ የዓለም የዳኝነት አደባባይና ሸንጎ ያጣን ድል፣ ወይም ያጋጠመውን ሽንፈት ለመቀልበስ ሌላ የፍልሚያ ቡድድን እየፈጠረ ነው፡፡ ለምሳሌ በቀደም ጥቅምት 2 ቀን 2014 ዓ.ም. ማክሰኞ የአሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ የፈረንሣይ፣ የጀርመንና የታላቋ ብሪታንያ ‹‹ቡድን›› የተለመደ የጭቃ ጅራፉንና ማስፈራሪያውን የሚያውለበልብ ‹‹ውሳኔ›› ማሳለፋቸውን፣ ይህንን ስብሰባ ‹‹High Level Meetings on Ethiopia›› እንዳለው፣ የአሜሪካ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ነግሮናል፡፡ የአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ በመስከረም ወር መጨረሻ ሳምንት ውስጥ ያሳለፈው ውሳኔ/የውሳኔ ሐሳብም ይህንኑ በሕግና በዓለም አቀፋዊ ሥርዓት ውስጥ የፈለጉትን ማድረግ ሲያቅትና እንዳሻው ማድረግ ሳይቻል ሲቀር፣ መድረክ ለመፍጠር የሚደረገውን ተራ ወስላታነትና የከበደ ሸፍጥ የሚሳይ ነው፡፡

የአውሮፓ ፓርላማ የመስከረም 27 ቀን 2014 ዓ.ም. ውሳኔ ወይም ረዘሉሽን ከማሳለፉ በፊት የዚህ ውሳኔ መነሻ ሆኖ የቀረበለት ሞሽን (ማለትም በዚህ ጉዳይ ላይ ተወያይቶ/ውይይት አካሂዶ ውሳኔ እንዲያስተላለፍበት የቀረበለት ሐሳብ) ነበር፡፡ ፓርላማው በዜና እንደሰማነው/እንዳነበብነው፣ ለምሳሌ ወዲያውኑና በአስቸኳይ የግጭት አቁም ዕርምጃ እንዲወሰድ ጠየቀ፣ የጦር መሣሪያን ጨምሮ መጠነ ሰፊ ማዕቀብ እንዲደረግ ወሰነ፣ እንደተባለው የውሳኔው ይዘትና ምንነት (ምንድንነት) ያው ራሱ ፓርላማውን የሚመስለው ነው፡፡

የአውሮፓ ፓርላማ፣ ከየአባል አገሮች ለእያንዳንዱ አገር በተወሰነው መቀመጫ መሠረት በቀጥታ በሕዝብ የተመረጡ 705 እንደራሴዎች ያሉት የአውሮፓ ኅብረት የሥልጣን አካል ነው፡፡ በዚህ ረገድ ፓርላማው የሕዝብ ድምፅ ሊባል ይችላል፡፡ አውሮፓ ግን አንድ አገር ባለመሆኑ፣ ከተለያዩ የየብቻ አገሮች የሕዝብ ድምፅ በላይ የሆነ የሥልጣን አካል አለው አውሮፓ ኅብረት፡፡ እና ከፓርላማው ከየአገሮቹ የሕዝብ ድምፅ በላይ የየአባል አገሮቹ ድምፅ ያይላል፡፡ ይህንን የሚወክለው ደግሞ የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት (The Council of the European Union) የሚባለው ነው፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደ ማለት ነው፡፡ ስያሜውም እንደዚያ ነበር፡፡ ከዚህም በላይ ሌላ የሥልጣን አካል አለ፡፡ አውሮፓ ኅብረት ‹‹ስም ማውጣት ያውቃሉ›› ተብሎ የሚዘፈንለትና የሚቀናበት አይደለምና ቅድም ከተጠቀሰው ካውንስል/ምክር ቤት ሌላ ምክር ቤት አለ፡፡ ‹‹The European Council›› ይባላል፡፡ ይህ የእያንዳንዱ አባል አገር ርዕሰ ብሔር/መስተዳድርና የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት የሚገኙበት የሥልጣን አካል ነው፡፡ ኮሚሽን የሚባለው የኅብረቱ የአስፈጻሚ አካል ነው፡፡

እና የአውሮፓ ፓርላማ ዞሮ ዞሮ የወሰነው፣

በኦክቶበር ወር 2021 መጨረሻ ላይ፣ በተለይም አዲሱ መንግሥት ከተመሠረተ በኋላ፣ የሰብዓዊነት ሁኔታው በቅጡ/በሚገባ ካልተሻሻለ በኢትዮጵያና በኤርትራ መንግሥት፣ በሕወሓት አባላትና በሌሎችም ግጭቱን በሚያራዝሙት ላይ… ኮሚሽኑ የዕቀባ ዕርምጃ እንዲወስድ ‹‹Suggest›› ያደርጋል ይላል፡፡ በ27/1/2014 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. 7 ኦክቶበር 2021) ውሳኔ በተራ ቁጥር 24 የተዘረዘረው ይኼው ነው፡፡

በዚህና መነሻዬ ላይ በጠቀስኩት መንደርደሪያ ምክንያት ይህ ሁሉ ዋጋ ቢስ ነው፣ ‹‹ተልባ ቢንጫጫ… ›› ነው፣ ‹‹ቢከፍቱት ተልባ ነው›› እልኩ አይደለም፡፡ ይህ ‹‹ውሳኔ›› ወይም የውሳኔ ሐሳብ ወይም ‹‹ምክር›› ነገ ከነገ ወዲያ ኢትዮጵያን፣ ሕዝቧን፣ ነፃነቷን፣ የግዛት አንድነቷን፣ የፖለቲካ የሠራ አካላቷን ወደ የሚተናነቅ አደጋና ግፍ ስላለመለወጡ ዋስትና የለንም፡፡ የዓለም ማኅበር ለዘለዓለም ይኑር፣ ለሰላም ለፍቅር እያልን መዘመር የጀመርነው ብዙዎቹ ገና አገር ሳይሆኑ፣ አገር ሳይኖራቸው፣ ሰብዓዊ መብቶች የሁሉም ሰዎች ባልነበሩበት ጊዜ አንስቶ ነው፡፡ የዓለም ማኅበርን የተካው የእሱንም የክሽፈት መራራ ትምህርት የወሰደው የመንግሥታቱ ድርጅት እነሆ የጉልበተኞች መሣሪያ ሆኗል፡፡ የአውሮፓ አገሮችና አሜሪካ ሽብርን፣ የሰብዓዊ መብት ረገጣን፣ የሰብዓዊነቱ ቀውስን መታገልን ሽፋንና ሰበብ አድርገው የሚያካሂዱት የኢኮኖሚ ጦርነታቸውን ነው፡፡

ስለሕግ ሲያወሩ እንሰማለን፡፡ ጥሩ ነው፡፡ ተገቢ ነው፡፡ በማን ዕድላችን ብለን የምንመኘውና የምንሳልለት ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለገዛ አገር ሕጓ፣ ለዓለም አቀፋዊ ሕጎች ለገባችው ግዴታ ተገዥነቷ የስም ጌጥ ጉዳይ አይደለም፡፡ የለውጡ መነሻ፣ ሕግ የማስከበር የመንግሥት ተግባር ከመንግሥት ሕግ የማክበር፣ ከሕግ በታች የመሆን ግዴታ ተለይቶ መታየት የለበትም ከሚል እምነትና የሕዝብ ንቅናቄ የመነጨ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የሕዝቦቿን መብትና ነፃነት እንዲሁም እኩልነት የማስጠበቅ፣ ደኅንነታቸውንና ሰላማቸውን የማረጋጥ ግዴታ አለባት፡፡ ሳይጠየቁ መቅረትን የመዋጋት፣ ተጠያቂነትን የማስፈን ግዴታ አለባት፡፡

ኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠረው የተለያዩ አቦዳደኖች ዘመቻ ግን ሕግ ማስከበርን ጉዳዬ ያለ አይደለም፡፡ በረሃብ አደጋና በጅምላ ጭፍጨፋ ውንጀላ አመካኝቶ የምዕራባውያንን የጦር ጣልቃ ገብነት ልጥራ የሚል ግርግር ነው፡፡ ይህንን ለማሳየት የአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ የውሳኔና ለውሳኔው መነሻ የሆነውን የሞሽን ሰነዶች ብቻ እንመልከት፡፡

ለምሳሌ የመስከረም 24 ቀን የሞሽን ሰነድ ከበርካታ መንደርደሪያና መግቢያ በኋላ ሀ ብሎ የሚጀምረው ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. (ወይም 4 November 2020) ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ በትግራይ ላይ በማወጃቸውና በሰሜናዊው የትግራይ ክልል መንግሥት ላይ ወታደራዊ ዘመቻ በማዘዛቸው፣ ከዚያ ጀምሮ እነሆ አገር ጦርነት ላይ ናት ይላል፡፡ የሥር የመሠረቱ የዓለም ኅብረተሰብ ‹‹ኃጢያት›› እና ወንጀል ይህ ነው፡፡

ይህንን የጥቅምት 24 ቀን 2013 ጉዳይ በኋላ እንድመለስበት ፍቀዱልኝና በፓርላማው ውሳኔ ላይ ያልተካተተውንና መጀመርያ ግን ለፓርላው ቀርቦ በነበረው ሞሽን ላይ የነበረውን አንድ ነገር ላንሳ፡፡ የአውሮፓ ኅብረት ውይይት እንዲያካሂድበት፣ ተወያይቶም ውሳኔ እንዲያስተላልፍበት ከቀረቡለት ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ ‹‹የኖርዌጂያን የኖቤል ኮሚቴ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ዓሊ እ.ኤ.አ. በ2019 የሰጠውን የኖቤል የሰላም ሽልማት እንዲሠረዝ ጥሪ እናደርጋለን፤›› ያለውን ነው፡፡

በተራ ሰዎች አዲስ አበባ መንገድ ላይ ወይም ፌስቡክ ጫካ ውስጥ፣ ወይም በሆነ ሰላማዊ ሠልፍ መድረክ እንዲህ ያለ ነገር ቢነሳ አይገርምም፡፡ ኖርዌይ የአውሮፓ ኅብረት አባል ባትሆንም አውሮፓዊ አገር ነች፡፡ ኖርዌይን የመሰለ አኅጉሩ ውስጥ የምትገኝ አገር የምታስተዳደረውን በአንድ ግለሰብ ኑዛዜ ላይ የተመሠረተና በራሱ መተዳደሪያ ደንብ ላይ የተመሠረተ ሽልማትን ግፈፍና ውጤቱን ንገረኝ ማለት ግን አውሮፓ ውስጥ፣ አውሮፓ ኅብረት ፓርላማ ላይ ይሰማል ብሎ የሚገምት ማንም የለም፡፡ የአገሬ ሰው ይህንን እዚህ አገሬ ውስጥ ቢሰማ እንዲህ ያለውን ጥያቄና ጠያቂ፣ ‹‹እግዜር ጅልነትን በሁለት እጁ ያስታቀፈው ግትቻ›› ይለው ነበር፡፡ ለማንኛውም የኖቤል ኑዛዜም፣ የሽልማቱ መተዳደሪያ ደንቡም እንዲህ ያለ ሥራ አይፈቅድም፡፡ አንዴ የተሰጠ ሽልማት አይገፈፍም፣ ለምን ተሰጠ ተብሎም ይግባኝ አይቀርብበትም፡፡

ወደ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓም. አደጋ እንመለስ፡፡ ጥቅምት 24 ቀን ባለፈው ዓመት ምን ሆነ? በዚያው ዕለት በውድቅት ሌሊት ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ እንደገለጹት የኢትዮጵያ ሠራዊት እንዲዋጋ ትዕዛዝ የተሰጠው መሆኑ እውነት ነው፡፡ ይህ ግን የሆነው ዝም ብሎ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ‹‹ጦር አምጣ›› ስላለ አይደለም፡፡ ጦርነቱን የቀሰቀሰው፣ የኢትዮጵያን መንግሥት አስገድዶ ጦርነት ውስጥ የከተተው፣ ትግራይ ላይ ከ20 ዓመታት በላይ ከእነ ስንቅና ትጥቁ፣ ከእነ ሁለመናው የሠፈረውን በፌዴራሉ መንግሥት ሥልጣን ውስጥ የሚገኘውን ወታደራዊ ዕዝ በማጥቃቱ ነው፡፡

ይህን ሌላው ቢቀር የኢትዮጵያን መከራከሪያና መልስ አልሰማም ማለት ምንም ያህል ቢከፋና ቢጠነዛ፣ የራሱ ‹‹የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ›› አካል የሆነውን የ‹‹UNDP››ን ምስክርነት ሰምቶና መርምሮ አጣርቶ መረዳት ይቻላል፡፡ ይህን የመሰከረው (ሐሰተኛ ቃልም ከሆነ ተጣርቶ መወገዝና መኮነን ያለበት) የ‹‹UNDP›› ዋና ኃላፊ ለመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ የጻፉት ማስታወሻ ነው፡፡ የካቲት 9 ቀን 2013 ዓ.ም. የተጻፈውን ይህንን ለዋና ጸሐፊ የተጻፈ ማስታወሻ፣ የካቲት 30 ቀን 2013 ዓ.ም. የወጣው ፎሬይን ፖሊሲ እሱም እንደ አቅሚቲ ጎራርዶና አንጋዶ የወጣውን ከማየታችን በስተቀር ባለአድራሻው ዋና ጸሐፊውም ሆኑ ተመድ ራሱ ላጣራው ያላለው፣ አሁንም ድረስ ተድበስብሶ የኖረ ሰነድ ነው፡፡ በጣም አስፈላጊ ስለሆነ ያነሳቸውን ነጥቦች ላቅርብ፡፡

የፌዴራል መንግሥቱን የማጥቃት ሥራ የቆሰቆሰውና የቀሰቀሰው የትግራይ ክልል አመራር ነው፣ ጥፋተኛም እሱ ነው፡፡

የመፈናቀሉም፣ የጥቃቱም መነሻ ይኼው ነው፡፡ የፌዴራሉን መንግሥት ‹‹Offensive›› ፕሮቮክ ያደረገው ቲፒኤልኤፍ ነው፡፡ ትግራይ ውስጥ ያለውን የኢትዮጵያ የሰሜን ዕዝ ጠቅላይ መምርያ ያጠቃውና የተቆጣጠረው የቲፒኤልኤፍ ዕርምጃ ነው፡፡

ይህ በየትኛው የዓለም ክፍል ‹‹An act of war anywhere in the world, and one that typical triggers military response in defense of any nation!››

የዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ያለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ የቲፒኤልኤፍ ፀብ ጫሪነት/ጦር ጥራ ተግባር የመንግሥትን የለውጥ/የሪፎርም ዕርምጃ መቃወምንና ከመንግሥት ጋር ፖለቲካዊ ንግግር/ውይይትን አሻፈረኝ ማለትን ጨምሮ ጆሮ ዳባ ልበስ በማለቱ ኃላፊነቱን አልተወጣም፡፡

ለጋሽ አገሮች የኢትዮጵያን መንግሥት በሰብዓዊ መብቶች ሪኮርዱ፣ በተለይም በግጭቱ ወቅት ስለተፈጸሙት ‹‹Excesses›› ከማተኮር ይልቅ፣ ይበልጡኑ በልማትና የሰብዓዊነት ዓላማዎች (Humanitarian Goals) ላይ እንዲያተኩሩ ያሳስባል፡፡

  • የሰብዓዊ መብት ጥቃትና ጥሰት የትኛውም ምርመራም መመራት ያለበት በራሱ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ምናልባትም/አስፈላጊ ከሆነም ከዓለም አቀፉ ተሳትፎ ጋር መሆን አለበት ሲል አደራ አለ፡፡
  • የተያዘውን የፍጥጫ ዓይነት መንገድ አስመልክቶም በኢትዮጵያ ነባራዊና ተጨባጭ ሁኔታ ውስጥ ተፈላጊውን ውጤት አለማስከተል ብቻ ሳይሆን ተቃራኒውን ሊያመጣ ይችላል፡፡
  • የትግራይን ፖለቲካ አመራር ይኮንናል፣ የመንግሥትን የሪፎርም አጀንዳ እንቅፋት ነው ይላል፡፡ የውጭ አገር መንግሥታትንም የቲፒኤልኤፍ አመራር ባለፉት ሁለት ዓመታት በተግባራቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድን አመራር/አስተዳደር ሲጠናወቱ ዝም በማለታቸው/ባለመናገራቸው ጥፋተኛ ያደርጋል፡፡
  • ዓብይ ደካማ ነህ/ደካማ ነው/ሕግ የማስከበር አቅም የለውም እየተባለ እንኳን፣ መጀመርያ ላይ ኃይል የመጠቀቀም ፍላጎት አልነበረውም (Reluctant) ነበር፡፡ ከመላው አገሪቱ ተለይተው ምርጫ ቢያካዱም ‹‹Financial Support›› ነፈገ እንጂ የትግራይ ‹‹ወታደሮች›› (Troops) ግን የሰሜንን ዕዝ ‹‹Armory Facilities›› በማጥቃት አስገደዱት፡፡
  • ጦርነቱም ከተጀመረ በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት ሁኔታውን ለመግታት ለምሳሌ ለመንግሥት ሠራተኞች የከፈለውን የሁለት ወራት ውዝፍ ደመወዝ፣ እንዲሁም ቁልፍ የኤሌክትሪክና የባንክ የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግቶችን መልሶ ማቋቋሙን የመሳሰለሉ ዕርምጃዎች እንኳን ምሥጋና ቢስ ሆኗል፡፡
  • የትግራይ ኃይሎች ከአላማጣ ከተማ 10 ሺሕ እስረኞች ፈትተው መልቀቃቸውን ይህም ባለመረጋጋቱ ላይ ተጨማሪ ችግር መፍጠሩን፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግሥት ባቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ሥራ ላይ ውስብስብ ችግር መፍጠሩን ይናገራል፡፡ የመንግሥታቱ ድርጅት የሕግ መጽሐፍ የሚነግረን ከኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ጋር መግጠምን ነው፡፡ ስኬታማ ለመሆንም የኢንተርናሽናል ኮሙዩኒቲውን ወቅታዊውን ‹Hard Talk› እና ‹Posture› እንደገና መገምገም ያስፈልጋል፡፡
  • የዓለም አቀፋዊው ማኅበረሰብ የተለያየ መሥፈሪያ ቁና አለው ማለት፣ የተቋቋመ እምነት መሆኑን በኢትዮጵያ ‹Body Politic› ላይ የበቀለውን የሁለት ዓመት ዕድሜ ያለው ካንሰር ተብሎ የታወቀውን ችግር አለመግታት የወሰደው ዕርምጃ ስለመኖሩ ማስረጃ የለም፡፡  

ይህንን ከላይ የሠፈረ ምስክርት የሚሰጠው የራሱ መንግሥታቱ ድርጅት አንድ ዋነኛ ክፋይ አካልና አምሳል የሆነ ተቋም ዋና ኃላፊ ነው፡፡ ማንም ከቁብ የቆጠረው፣ ከእነ መኖሩም ያወቀው ‹‹ዓለም አቀፋዊ ማኅበረሰብ›› የለም፡፡ ውሸት መሆኑን አረጋጠናል ማለትን የመሰለ ‹‹ክብር›› እንኳን አላገኘም፡፡

እዚህ ምስክርነት ውስጥ በተነሱ አንዳንድ ጉዳዮች ላይ ምናልባትም በዋነኛው አንድ ከንካኝ ጉዳይ ላይ አንድ ነገር ማለት ያለብኝ ይመስለኛል፡፡ የዩኤንዲፒ፣

‹‹Everything within the UN rule book tells us it is a moment to engage with the government and people of Ethiopian.

‹‹It is an opportunity to put the humanitarian, development and peace nexus into action. To succeed will require a re-assessment of the international community’s current hard talk and posture›› ይላል፡፡

ተመድ፣ አውሮፓ ኅብረት፣ ሌሎች G6፣ ወዘተ አቦዳደኖች ሆነም የትኛውም ‹High level Meeting on Ethiopia› በመጽሐፈ ሕግጋቱ (Rule Book) አይሠራም፡፡

ሕፃናት እንኳን በዚያ በጨቅላ ዕድሜያቸው ‹‹ጨዋታ ፈረስ ዳቦ ተቆረሰ›› እስኪባል ደረስ፣ ወይም እፍርታም መባልን የመሰለ ሳንክሽን ወይም ጭቆና መከናነብን ወደው ካልመረጡ በስተቀር የጨዋታውን ሕግ ያከብራሉ፡፡ አፈረ መባልን ይፈራሉ፡፡ እፍርታም ሰው/ልጅ በጨዋታ የሚያፍር ልጅ እንደገና መጫወት እንደማይችል ያውቃሉ፡፡ ይህ ወግና ማዕረግ ግን ዓለም አቀፋዊ ኅብረተሰብ ውስጥ ተፈልጎ ሲጠፋ እየመሰከርን ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...