Friday, September 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የግብርናን ንግድ ዘርፍ ይደግፋል የተባለ የንግድ ትርዒት ተካሄደ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያን የግብርና ንግድ ዘርፍ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግና የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚነትን ለማጎልበት ያስችላል የተባለ ዓለም አቀፍ ንግድ ትርዒት  ተካሄደ፡፡

 

ከጥቅምት 4 እስከ 6 ቀን 2014 ዓ.ም. በስካይ ላይት ሆቴል በተከናወነው ንግድ ትርዒት ላይ ከ11 በላይ አገሮች የተሳተፉ ሲሆን፣ ከ2,000 በላይ የዘርፉ ባለሙያዎችና ባለሀብቶች ታድመውበታል፡፡

የንግድ ትርዒቱ የተዘጋጀው ፌር ትሬድ በተባለ ድርጅት አማካይነት ሲሆን፣ የድርጅቱ መሥራችና ማኔጂንግ ፓርትነር ማርቲን ማሬዝ የንግድ ትርዒቱ መከፈቱን አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር፣ የንግድ ትርዒቱ ከተለያዩ አገሮች የተውጣጡ ባለሙያዎች የተሳተፉበት መሆኑን ተናግረው፣ በተለይም የአፍሪካ አገሮች ከአውሮፓ አገሮች ጋር እንዲሠሩ ትኩረት እንደሚሰጡ አብራርተዋል፡፡

 ፌር ትሬድ ባለፉት አሥር ዓመታት በተለያዩ አገሮች ላይ የንግድ ትርዒት ማድረጉን ያስታወሱት ማሬዝ፣ ከ36 ሺሕ በላይ ተሳታፊዎችና ከ1.5 ሚሊዮን በላይ የንግድ ጎብኒዎች ተሳትፎ ማድረጋቸውንና የልምድ ልውውጥ መካሄዱንም አስረድተዋል፡፡

የግብርና ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ የሚደረገውን ርብርብ አጠናክሮ ለመቀጠል የንግድ ትርዒቱ ትልቅ ሚና እንደሚጫወትና መንግሥት በዘርፉ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑንም የፕራና ኢቨንትስ መሥራች አቶ ነብዩ ለማ ተናግረዋል፡፡

የንግድ ትርዒቱ በግብርናም ሆነ በተለያዩ ዘርፎች ላይ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በቀላሉ ለማግኘት የሚረዳ ሲሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃም በንግድ ሰንሰለቱ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካበረከቱ ተቋማት ጋር የልምድ ልውውጥ የሚደረግበት መሆኑን አቶ ነብዩ ጠቁመዋል፡፡

ከ11 በላይ አገሮች የተሳተፉበትና ከ2,000 በላይ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች የታደሙበት ንግድ ትርዒት፣ ኢንቨስትመንቱ ላይ ከፍተኛ ለውጥ እንደሚያመጣም አክለዋል፡፡

የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ አግሪ ቢዝነስና ማርኬቲንግ ዳይሬክተር አቶ ሔኖክ መስፍን በበኩላቸው፣ አርሶ አደሩ የሚያመርተውን ምርት በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግና ባለሀብቶችም በዘርፉ ላይ ተሳትፏቸው የጎላ እንዲሆን የንግድ ትርዒቱ የበለጠ አጋዥ ይሆናል ብለዋል፡፡

ኢኮኖሚያዊም ሆነ ማኅበራዊ ፋይዳዎችን ለመፍታት የግብርና ዘርፉ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

ከጥቅምት 4 እስከ 6 ቀን 2014 ዓ.ም. በተካሄደው የንግድ ትርዒት ላይ ከተሳተፉት አገሮች መካከል ፈረንሣይ፣ ጀርመን፣ ቱርክ፣ ህንድ፣ ጣሊያን፣ ናይጄሪያና ሩሲያ ይገኙበታል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች