ኢትዮጵያ የገዛ አገራቸውን በውጭ ኃይሎች እንድትጠቃ፣ እንድትዋረድና ከዚያም አልፎ እንድትበታተን ሌት ተቀን የሚሠሩ ጠላቶችን አፍርታለች፡፡ አገርን ያህል ነገር እንድትበተን የሚመኙቱ እነዚህ ቡድኖች ይህ ምኞታቸው ተሳክቶ በዓይናቸው ለማየት መሻታቸውን ጭምር ሲናገሩ ሰምተናል፡፡ ይህ ምኞታቸው ባይሳካላቸውም ኢትዮጵያን ባሰቡት ልክ ለማሰናከል እያደረጉ ያሉት ኃይሎች በአገር ውስጥ እያደረሱ ያሉት ጥፋት ሳያንስ ኢትዮጵያን ለመጫን ከቆረጡ የውጭ ኃይሎች ጋር በማበር እየሠሩ ያሉት ሸፍጥ የአገር ጠላትነታቸው ልክ የሌለው መሆኑን በተጨባጭ ያሳያል፡፡
ዛሬ ማዕቀብ ለመጣል ቀን ከሌት እየዛቱብን ያሉ ምዕራባውያን እዚህ ደረጃ ለመድረሳቸውም ዋናው ምክንያት ይኼው ኢትዮጵያ ጠል የሆነው ቡድን በሐሰት ትርክት የሸረበው ሴራ ነው፡፡ የምዕራባውያን አካሄድና ዛቻ በተግባር የሚለወጥ ከሆነም ይብዛም ይነስም አገርን ይጎዳል፡፡
በዚህ ላይ በሸፍጥና የተወሰኑ ቡድኖችን ለመጥቀም ወይም ለዘረፋ የተመቻቸው የንግድ እንቅስቃሴ ዛሬም ሰንኮፉ ያልተነቀለ መሆኑ ሲታሰብ ጦርነቱ የተከፈተው በኢኮኖሚያችን ላይ ጭምር መሆኑን በግልጽ ያመላክተናል፡፡
እንደሚታወቀውም ጦርነት የኢኮኖሚ አቅምን የሚጎዳ ነው፡፡ ከውጭም ከውስጥም ኢትዮጵያ የገጠማት ፈተና የሚያስከፍለው ዋጋ የእያንዳንዳችንን በራፍ ሊያንኳኳ የሚችል ይሆናል፡፡ በተለይ ደግሞ የምዕራባውያን ዛቻ እንደተባለው የሚተገበር ከሆነ ጉዳቱ የቱንም ያህል ቢሆን እንደ አገር አማራጮችን መፈለግ ግድ ይለናል፡፡
እየተሰማ እንዳለውም አሜሪካ ከሰሃራ በታች ላሉ የአፍሪካ አገሮች ከታሪፍና ከኮታ ነፃ (አጎዋ) የሰጠችውን የገበያ ዕድል ኢትዮጵያ ተጠቃሚ እንዳትሆንት ለማድረግ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ በተግባር ከተለወጠ መጎዳታችን አይቅርም፡፡ በአጎዋ ዕድል በየዓመቱ ከ40 ሚሊዮን እስከ 50 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ የምናገኝበት ነው፡፡
ይህንን ዕድል እንዳናጣ መታገሉ ተገቢ ይሆናል፡፡ ጎን ለጎንም አጋጣሚውን ሌላ የገበያ ዕድል የምናይበት እንዲሆን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡
ዛሬ ፍርደ ገምድል ሆነው ኢትዮጵያን ለመጉዳት እየተሸረበ ያለው ሴራና እስካሁንም እየደረሰብን ያለው በደል እንደ ኢትዮጵያዊ ቆም ብለን ቆራጥ ውሳኔ እንድንወስን የሚያደርግ ነው፡፡ ፈተናዎች እንደ መልካም አጋጣሚ የምንጠቀምባቸው በመሆኑ ማዕቀቡ ከፀና አማራጭ ገበያዎችን ማፈላለግ አለብን፡፡
አውቀውም ሆነ ሳያውቁ ወይም እውነታውን እያወቁ ኢትዮጵያን ለመጉዳት የተነሱ ጠላቶች የሚወስዱት ዕርምጃ ምንም ይሁን ምን የአገር ሉዓላዊነትን እያስጠበቁ ጎን ለጎን ኢኮኖሚውን መታደግን ይጠይቃል፡፡
አገር ሁሌም ከድህነት እንዳትወጣ እንቅፋት ከሆኑ ምክንያቶች አንዱ የሆነውን እዚሁ ማምረት በሚቻሉ ምርቶች ላይ ኢንቨስት ከማድረግ ይልቅ ከውጭ በማስመጣት ብቻ የተጠናወተንን ሀብት የማካበት ሱስ ማስወገድ ያስፈልጋል፡፡
ራሳችንን እንችል ዘንድ ምርታማ መሆን ብቻ ያሻናል፡፡ የዋጋ ንረት ፈተናችን ከዚህም በላይ እንዳይብስ የእያንዳንዳችንን ጥረትና ከፍ ሲልም በጋራ ሆኖ የግብርናውን ዘርፍን እንደ ህልውና ጉዳያችን መያዝ ይፈልጋል፡፡
በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ዛሬ ያለው የኑሮ ውድነት ካለንበት ጦርነትና ጫናዎች ጋር የተያያዘ በመሆኑ ይህን ተቋቁመን የምናልፈው እስከዛሬ ከተጓዝንበት መንገድ በተለየ ስንንቀሳቀስና እዚሁ ስናመርት ብቻ ነው፡፡
ለዘለቄታውም ቢሆን ግብርናው ጠንከር ብሎ መሠራት አለበት፡፡ ከዚህ አንፃር መሠራት ካለባቸውና ከዚህ በኋላ ሊተኮርባቸው ከሚገቡ ጉዳዮች አንዱ ግብርና ነው የምንልበት ምክንያት ራስን ከመመገብና በተመጣጣኝ ዋጋ ዜጎች መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶችን እንዲያገኙ ብቻ ሳይሆን፣ በሌሎች ተፅዕኖ ሥር እንድንወድቅ ያደረገን በበቂ አለማምረታችን በመሆኑ ነው፡፡ የተረጂነት ታሪካችንን ለመቀየርም ቀዳሚ ተግባራችን መሆን ስለሚገባው ነው፡፡
ሌሎች እጃችንን ለመጠምዘዝ የደፈሩትና ማዕቀብ ካደረግንባቸው የትም አይደርሱም ያሉትም ይኼው በቀላሉ አምርተን ራሳችንን የምንችልበትን ፀጋ ባለመጠቀማችን ነው፡፡ ይህንን አውቆ ትውልዱን ግብርና ‹‹ህልውና›› እና ‹‹ክብር›› ነው ብሎ ማስተማር ያስፈልጋል፡፡
ተፈጥሮ የሰጠችንን መልካም ዕድል ተጠቅመን በአገር ውስጥ ሊመረቱ የሚችሉ ማንኛውም የግብርና ምርቶችን ማምረት ቀዳሚ አጀንዳችን ማድረግ ለዘለቄታውም ቢሆን የግድ አስፈላጊ ነው፡፡ ግብርና ህልውናችን መሆኑን በመረዳት ዜጎች ወደዚህ ዘርፍ እንዲገቡ ማበረታታትም የሚኖርብን በቀላሉ ማድረግ የምንችለው በመሆኑ ነው፡፡
አገርን መውደድ መገለጫው ለገጠሬው ብቻ የተሰጠ እስኪመስል ድረስ የራቅነውን ግን የምናውቀውን የግብርና ሥራ መሥራትና ለዚህ የተመቻቸ ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ዘርፍ ጉልበትንና ሀብት ማፍሰስም ጀግንነት ተደርጎ መወሰድ አለበት፡፡
በየዓመቱ ሁለትና ሦስት በመቶ እያደገ የመጣውን ሕዝብ መቀለብ የሚቻለውና የኑሮ ውድነቱ ከዚህም የባሰ እንዳይሆንና የተረጋጋ ገበያ ለመፍጠር ብቸኛው አማራጭ ይኼው በመሆኑ አሁን የገጠመንን ችግር እንደ መልካም ዕድል ልንጠቀምበት ይገባል፡፡
መንግሥትም ዜጎች በዚህ ዘርፍ ተሳትፏቸው እንዲጎለብት ምቹ ፖሊሲዎችን መቅረፅና ለግብርና ቦታዎችን በመለየት ሁሉም በአቅሙ እንዲሠራ ማድረግ አለበት፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎን በአገር ደረጃ ሊመረቱ የሚችሉ ምርቶችን ደፍሮ ከውጭ እንዳይመጡ መከልከል ለግብርናችን ዕድገት ወሳኝ መሆኑን በማወቅ ዕርምጃዎችን መውሰድ ይገባል፡፡ ቢያንስ ከውጭ የሚገባውን ስንዴንና ዘይት ማስቀረት የሚችል ቆራጥ ፖሊሲና ይህንን ለመተግበር የሚችል አዲስ ትውልድ ማፍራት ጊዜው የሚጠይቀው ጉዳይ ነው፡፡ ዱቄት፣ ፓስታንና መኮሮኒን የመሳሰሉት ሁሉ እዚሁ የሚመረቱ እንዲሆኑና እነዚህን ምርቶች ከውጭ የሚያስገቡ አስመጪዎችን ፊታቸውን ወደ አገር ውስጥ እንዲያዞሩ መምከርና መደገፍ ያስፈልጋል፡፡
ሽንኩርትና ብርቱካን ከሱዳን የሚያስመጡ ባለሀብቶች ሳይሆን፣ የሚያመርት ዜጋ ማፍራት አለብን፡፡ እንዲህ ላሉ ምርቶች የሚውልን የውጭ ምንዛሪ መከልከል ሁሉ ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያን የሚያህል አገር፣ በቂ ሽንኩርት ማምረት አቅቷት ከውጭ ታስገባለች የሚለው ዜና ሊያሳፍረን ይገባል፡፡
ለሌሎች የሚተርፍ ስንዴ ሊያመርት የሚችል መሬት ያላት፡፡ አገር በስንዴ እጥረት የጠላቶች እጅ መጠምዘዣ ከምትሆን ወሳኝ የሚባሉ የግብርና ምርቶች ላይ አጥብቀን መሥራት አለብን፡፡ ከዚህ የሚገኘው ውጤት እንደ አገር የምንፈተንባቸውን ብዙ ነገሮች ይለውጣል፡፡ ዳይ ወደ ግብርና!