ግልጽነት በሌለበት አገር በርካታ ብሔራዊ ጉዳዮች ሚስጥር ይሆናሉ፡፡ ሚስጥራዊነት በበዛ ቁጥር እውነቱን ከሐሰት፣ ተጨባጩን ከምናባዊው መለየት ስለማይቻል መላምቶች ይበዛሉ፡፡ የመረጃ ፍሰቱ የተገደበ ስለሚሆንም ሐሜትና አሉባልታ የበላይነቱን ይይዛሉ፡፡ አሁን በኢትዮጵያ የተንሠራፋው ችግር ይህ ነው፡፡ አገር የሚያስተዳድረው ገዥው ፓርቲ ግልጽነት ስለሚጎድለው፣ በመንግሥት እጅ ያለ መረጃ ለሕዝብ ግልጽ አይደለም፡፡ በመንግሥታዊ መዋቅር ውስጥ ግልጽነት በመጥፋቱ ሳቢያ ብቻ የተጣራ መረጃ ማግኘት አይቻልም፡፡ በዚህ ምክንያት ተጠያቂነት እየጠፋ በርካታ ጉዳቶች ይደርሳሉ፡፡ የአገር ጉዳይ የሚያሳስባቸው ዜጎች የአገራቸውን ውሎና አዳር ለማወቅ ቢማስኑም፣ እውነትና ሐሰት ተደባልቀው ግራ ያጋባሉ፡፡ በዚህ ላይ ከየአቅጣጫው የሚሠራጩ የሴራ ትንተናዎች (Conspiracy Theories) አየሩን በስፋት እየቀዘፉት ነው፡፡ በሰሜን የአገሪቱ ክፍል እየተካሄደ ያለው ጦርነት አድማሱን እያሰፋ ንፁኃን ሕይወታቸውን እያጡ ነው፡፡ የደሃ ጎጆዋቸውና ማሳቸው እየወደመ፣ ሕፃናት፣ አቅመ ደካማ አዛውንት፣ ነፍሰ ጡሮችና እመጫቶች ተፈናቅለው ሜዳ ላይ እየወደቁ ነው፡፡ በጦርነቱ ምክንያት እየደረሰ ካለው ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት በተጨማሪ፣ ረሃብ ብዙዎችን ለመፍጀት አሰፍስፏል፡፡ ከየአቅጣጫው የሚሰማው የወገን ዋይታ በፍጥነት ካልቆመ፣ መሀሉ ዳር የማይሆንበት ምንም ምክንያት አይኖርም፡፡
ጦርነቱ በዜጎች ላይ እየደረሰ ካለው መከራ በተጨማሪ፣ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን በአንድ ጠባብ አካባቢ ውስጥ በተደጋጋሚ እየተፈጸመ ያለው ጭፍጨፋ አስከፊ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ የፀጥታ አካላትን እግር እየተከተለ ጭፍጨፋ እየፈጸመ ያለው ኦነግ-ሸኔ፣ ከዚህ ቀደም በተለያዩ መግለጫዎች ተደምስሶ አቅም ማጣቱ ቢነገርም ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ መሆኑን በተደጋጋሚ እያሳየ ነው፡፡ ይህ አልበቃ ብሎ ከኦነግ-ሸኔ በተጨማሪ ሌላ አካል እንዳለም እየተነገረ ነው፡፡ የፌዴራልና የኦሮሚያ ክልል መንግሥታት በግልጽ እዚያ አካባቢ ምን እየተከናወነ እንደሆነ ለሕዝብ መግለጽ ባለመቻላቸው፣ ንፁኃን ያለ ጥፋታቸው ማንነታቸው እየተለየ እየተጨፈጨፉ ነው፡፡ ሕዝብና መንግሥት ቢናበቡ ኖሮ አላስፈላጊ ድርጊቶች እየተፈጸሙ የሰው ክቡር ሕይወት አይጠፋም ነበር፡፡ የአገር ሀብትም በከንቱ አይወድምም ነበር፡፡ ነገር ግን አገሪቱን እንደ ቁራኛ የያዛት የሴራ ፖለቲካ ግን አሁንም መደበቂያ እያገኘ ችግር እየፈጠረ ነው፡፡ የመፍትሔ ያለህ ሲባል እየባሰበት የሚሄድ ግድያና መፈናቀል ሲበዛ እንዴት ዕርምጃ መውሰድ ያቅታል? የአካባቢውን ነዋሪዎች ሰቆቃ ለማስቆምና ከባድ ችግር ውስጥ የወደቁ ዜጎችን ለመታደግ ያልተቻለው ለምንድነው? በዚህ ሁኔታ እስከ መቼ ይቀጠላል? የክልሉ መንግሥት ለምን በግልጽ እየሆነ ያለውን ነገር መግለጽ አቃተው? ኦነግ-ሸኔም ሆነ ሌላ አካል ከመንግሥት አቅም በላይ የሚሆነው በምን ምክንያት ነው? የንፁኃን ሰቆቃ እንዲያበቃ ፈጣን መፍትሔ ይፈለግ፡፡
በማናቸውም ጊዜያት ከሕዝብ ለመንግሥት ጥያቄዎች ይቀርባሉ፡፡ መንግሥትም ሕግና ሥርዓቱን ጠብቆ ምላሽ የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡ የጥያቄዎቹ አቀራረብ ሕጋዊና ሰላማዊ እንዲሆን ደግሞ መንግሥት ምኅዳሩን የማመቻቸት ኃላፊነት ይኖርበታል፡፡ ሕጋዊ ዋስትና ያገኙ መሠረታዊ መብቶች በተግባር ሲረጋገጡ ለሴራ ፖለቲካ መጋለጥ አይኖርም፡፡ ላለፉት ሦስት ዓመታት በላይ በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉት ግድያዎችና ማፈናቀሎች መፍትሔ ያልተገኘላቸው፣ በሕግ ዋስትና ያገኙ መብቶች ሥራ ላይ መዋል ስላቃተቸው መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ እነዚህ መብቶች እየተጣሱ ሰው በገዛ አገሩ እንደ አውሬ እየታደነ ነው፡፡ ነገር ግን በሕጉ መሠረት መንቀሳቀስ ቢቻል ኖሮ፣ ወገኖቻችን በገዛ አገራቸው በማንነታቸው ምክንያት አይጨፈጨፉም ነበር፡፡ ጎጆዎቻቸው እየጋዩ አይፈናቀሉም ነበር፡፡ ንብረታቸው ተዘርፎ የሚቀምሱት አያጡም ነበር፡፡ ሕዝብ በመንግሥት ላይ እምነት የሚያጣው ሕገወጦች በግልጽ ሰላሙን ሲያቃውሱ ነው፡፡ ሕዝብና መንግሥት ሆድና ጀርባ ሆነው መደማመጥ ካቆሙ የአገር ህልውና ለአደጋ ይዳረጋል፡፡ የሰላማዊ ዜጎች በሰላም ወጥቶ የመግባት መብት ይደፈጠጣል፡፡ ለአገር የሚጠቅሙ የንግድ፣ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም ሥራዎች ይደናቀፋሉ፡፡ በላባቸው ያፈሩትን ሀብት ሥራ ላይ ያዋሉ ዜጎች ተስፋ ይቆርጣሉ፡፡ ከድህነት ጋር የተፋጠጠው ሕዝብ ለበለጠ መከራ ይዳረጋል፡፡ ይህ ሰቆቃ ማብቃት አለበት፡፡
ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ እንዳልነው አርቆ አስተዋዩ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንዱ በሌላው ላይ የመነሳት ታሪክ የለውም፡፡ ይህ ኩሩና ጨዋ ሕዝብ ያገኘውን ተካፍሎ ከመብላትና ከመተሳሰብ አልፎ ተጋብቶና ተዋልዶ የሚኖር ነው፡፡ ይህንን የመሰለ አርዓያነት ያለው አስተዋይ ሕዝብ ለማይረባ የፖለቲካ ትርፍ ሲባል ብቻ፣ ማተራመስና የሚወዳትን አገሩን ህልውና ለመናድ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ በግልጽ እየታየ ያለውም ኢትዮጵያውያንን እርስ በርስ በማጋደል አገር የማፍረስ ሴራ ነው፡፡ ይህ አደገኛ ድርጊት አደብ እንዲገዛ መደረግ አለበት፡፡ እስካሁን ድረስ የዘለቀውን የተበላሸ የፖለቲካ ቁማርተኝነት በማስቆም፣ ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎች በእኩልነት የሚያስተናግድ ዴሞክራሲያዊ ምዕራፍ እንዲከፈትና ለብሔራዊ መግባባት የሚረዳ ማዕቀፍ እንዲፈጠር መታገል ሲገባ፣ የሕዝብን ደኅንነት አደጋ ውስጥ መክተት ለአገር ህልውና ጠንቅ ነው፡፡ ዴሞክራሲ ከሕጋዊነትና ከሰላማዊነት ጋር እንጂ ከሕገወጥነት ጋር ዝምድና የለውም፡፡ ከዚህ ውጪ አገርና ሕዝብን እያተራመሱ የሶሪያንና የየመንን የውድመት ጎዳና መያዝ ጤንነት አይደለም፡፡ ግድያና ውድመት አገር ሲያፈርስ እንጂ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሲያመጣ ታይቶ አይታወቅም፡፡ የሴራ ፖለቲካ የንፁኃንን ሰቆቃ እያራዘመ ስለሆነ በፍጥነት መላ ይፈለግለት፡፡
ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ናት፡፡ ከ110 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ እንዳላት ይገመታል፡፡ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት ታዳጊዎችና ወጣቶች ናቸው፡፡ ከ30 ሚሊዮን በላይ በትምህርት ገበታ ላይ ናቸው፡፡ ይህ ግርድፍ መረጃ የሚያሳየው በዚህ ትውልድ አማካይነት መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ነው፡፡ ይህ ለውጥ በውይይት፣ በክርክርና በድርድር ታግዞ መሠረት እንዲይዝ የሚያዋጣው መንገድ መጀመርያ ለሕግ የበላይነት መገዛት ነው፡፡ ሁለተኛው የሕዝቡን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፍላጎቶች በፍትሐዊ መንገድ ማስተናገድ ነው፡፡ ሦስተኛው በሕግ ዋስትና ያገኙ መሠረታዊ መብቶች ያላንዳች መሸራረፍ ሥራ ላይ እንዲውሉ በማድረግ ለሐሳብ ነፃነት መደላድሉን ማመቻቸት ነው፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች ከፖለቲካ ወገንተኝነት በመላቀቅ፣ የአገር ግንባታ ትልሙ ፈር እንዲይዝ ዕገዛ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ ገዥው ፓርቲም ሆነ መንግሥት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ለአገራቸው የሚያስቡ ዜጎች፣ ወዘተ. የሴራ ፖለቲካ ተገቶ ኢትዮጵያ ቀና ጎዳና እንድትይዝ ድጋፍ ያድርጉ፡፡ የአገር ጉዳይ ሁሉንም ወገን በጋራ ማስተሳሰር መቻል አለበት፡፡ ግትርነት፣ ቂመኝነትና ራስ ወዳድነት ይብቃ፡፡ የሴራ ፖለቲካ የንፁኃንን ሰቆቃ እያራዘመ አገር ያፈርሳል፡፡
የሴራ ፖለቲካ ትርፉ አንዱን ከሌላው ጋር በማጋጨት አገርን መበታተን ነው፡፡ በዚህ የተካኑ የሴራ ፖለቲከኞችና ተንታኞች ወደ ቀልባቸው ተመልሰው የሰላም መንገድ ይያዙ፡፡ በመርዝ ምላሳቸው ያገኙትን እየሸነቆጡ በኢትዮጵያውያን መካከል መጠራጠርና መፈራራት በመፍጠር የአገርን ህልውና አይፈታተኑ፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ከመታገል ይልቅ ኢትዮጵያውያንን በዘር፣ በሃይማኖትና በመሳሰሉት በመለያየት የጠላት ዒላማ ለማድረግ እንቅልፍ አጥተው አይደሩ፡፡ በእነሱ ሴራ ምክንያት ንፁኃን ይሞታሉ፣ አካላቸው ይጎድላል፣ ከቀዬአቸው ተፈናቅለው ለመከራ ይዳረጋሉ፣ የአገር አንጡራ ሀብት ይወድማል፡፡ እንዲህ ዓይነት አሳፋሪ ድርጊት ለዚህ ዘመን ኢትዮጵያውያን አይመጥንም፡፡ ይህ ኩሩና አስተዋይ ሕዝብ በመሰሪዎችና በሴረኞች የሚደርስበት ግፍ ይበቃዋል፡፡ ይህች የአፍሪካውያንና የመላው ጥቁር ሕዝቦች ተምሳሌት አገር ከሴራ ፖለቲካ ተላቃ ፊቷን ወደ ልማትና ዕድገት ታዙር፡፡ በአገርና በሕዝብ ላይ መቀለድ ይብቃ፡፡ በሴራ ፖለቲካ አገር አይታመስ፡፡ በሴራ ፖለቲካ የኢትዮጵያዊያን ክቡር ሕይወት አይቀጠፍ፡፡ የሕዝባችን ሰቆቃ በፍጥነት እንዲያበቃ በጋራ መነሳት ያስፈልጋል!