Wednesday, February 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ረቂቅ ሕገ መንግሥት የክልል መቀመጫን ሳይጠቅስ ማለፉ...

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ረቂቅ ሕገ መንግሥት የክልል መቀመጫን ሳይጠቅስ ማለፉ አወዛገበ

ቀን:

መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም. የተከናወነውን ሕዝበ ውሳኔ ተከትሎ በክልልነት ለመደራጀት የሚያስችለውን ድምፅ ያገኘው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ረቂቅ ሕገ መንግሥት፣ በተለያዩ ዞኖች ውይይት እየተደረገበት ቢሆንም፣ የክልል ከተማን በግልጽ ባለማስቀመጡ ውዝግብ እያስነሳ ነው፡፡

የክልሉ ረቂቅ ሕገ መንግሥት የክልል መቀመጫ አንድ ብቻ እንደማይሆንና በርካታ ከተሞች እንደሚኖሩ የሚደነግግና በስብሰባዎቹ የተገኙ ታዳሚዎች፣ የክልል ከተሞች በርካታ ቢሆኑም፣ የርዕሰ መስተዳድር መቀመጫ የሚሆነው የት ነው የሚለው ጥያቄ እያወዛገበ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ረቂቅ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ ስድስት ላይ ርዕሰ ከተማን የሚመለከት ድንጋጌ የያዘ ሲሆን፣ ‹‹የክልሉ መንግሥት ከአንድ በላይ ከተሞች ይኖሩታል፡፡ ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል፤›› ሲል ይደነግጋል፡፡

የደቡብ ምዕራብ ክልልን ለመመሥረት በሕዝበ ውሳኔ የመረጡ ዞኖችና አንድ ልዩ ወረዳ በረቂቅ ሕገ መንግሥቱ ላይ ሕዝባዊ ውይይቶች ሲከናወኑ የነበሩ ሲሆን፣ እነዚህ ውይይቶች አካታች ስላልሆኑና ግልጽነት እንደሚጎድላቸው የሚገልጹ ትችቶች እየቀረበባቸው ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የክልልነት ጥያቄዎቹ ሲነሱና ሕዝበ ውሳኔው ሲደረግ የነበረው አሳታፊነት አሁን ቀንሷል ያሉ ወጣቶች ስብሰባዎቹ በግድ እንዲፈቀዱላቸው በማድረግ እየተሳተፉ እንደሚገኙም፣ ምንጮች ለሪፖርተር አስታውቀዋል፡፡

የደቡብ ክልል የክልልነት ጥያቄዎችን ያጠኑ ባለሙያዎችና ሌሎች የክልል መቀመጫዎች በርከት ማለታቸው መልካም ጅማሮ እንደሆነ፣ የደቡብ ክልል በሐዋሳ ማዕከልነት ዕድገትን ሳያሠራጭ የቀረበትን ድክመት ላለመድገም እንደሚያግዝ የሚያስረዱ ሲሆን፣ የክልል መቀመጫዎች በርከት ሲሉ ግን የትኛው ማዕከል ለምን አገልግሎት የት ቦታ ይመሥረት የሚሉ ውሳኔዎች በውይይት አለበለዚያም በምርጫ ይከናወኑ ይላሉ፡፡

ሆኖም የተለያዩ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ተጠቃሚዎች ጉዳዩን በማጉላት የክርክር መንፈስ እንዲላበስ አድርገዋል፡፡ በተለይም የቤንች ሸኮ፣ የካፋና የሸካ ዞን ተጠቃሚዎች የጦፈ ክርክር ሲያደርጉ ይታያሉ፡፡ በእነዚህ ክርክሮችም የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር መቀመጫ ቦንጋ፣ ሚዛን አማን፣ ቴፒ አልያም ማሻ ይሆናሉ በማለት እየተወዛገቡ ነው፡፡

የሞቻ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ከአሁን ቀደም በክልልነት ለመደራጀት በሚደረገው ሕዝበ ውሳኔ አዲስ ክልል ከመመሥረትና በነባሩ የደቡብ ክልል ከመቅረት ውጪ በኦሮሚያ ክልል መካተት የሚል ተጨማሪ ጥያቄ አቅርቦ እንደነበረ የሚታወስ ሲሆን፣ የርዕሰ መስተዳድሩ መቀመጫ ክርክርም ይኼንን ያካተተ ሆኖ ይታያል፡፡

በደቡብ ክልል ባለፉት ሦስት ዓመታት ከ13 በላይ ከሚሆኑ ዞኖች የክልልነት ጥያቄን ሲያስተናግድ የከረመ ሲሆን፣ ከእነዚህ ጥያቄዎች መካከል ሲዳማ ራሱን ችሎ አንድ ክልል ሆኖ በመቋቋም ቀዳሚው ሲሆን፣ የደቡብ ምዕራብ ዞኖች ደግሞ ጥያቄያቸውን ለየብቻ ያቀረቡ ቢሆንም በጋራ ክልል ለመመሥረት ተስማምተው ከክልሉ ለመገንጠል ሁለተኛ ይሆናሉ፡፡

የክልልነት ጥያቄዎቹ እየበረከቱ ሲመጡ የክልሉ መንግሥትና የቀድሞው የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) 20 አባላት ያለው የባለሙያዎች ቡድን አቋቁመው የጥያቄዎቹን መነሻዎች፣ ጥያቄዎቹ ሊመለሱ የሚፈለጉባቸውን አግባቦችና ሊፈቱ የሚችሉባቸውን መንገዶች ያመላከተ ጥናት አስጠንተው ነበር፡፡ ይህም ጥናት ሦስት ምክረ ሐሳቦችን አቅርቦ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ እነሱም የደቡብ ክልልን በነበረው ቅርፅ ማስቀጠል፣ በአንድ አካባቢ ያሉ ዞኖችን በማሰባሰብ ክልሉን ከአምስት ባልበለጡ ክልሎች ማደራጀት፣ አልያም የክልልነት ጥያቄዎችን መልስ ሳይሰጡ ማቆየት የሚሉ ነበሩ፡፡

የዚህ ጥያቄ አንገብጋቢነት ያሳሰባቸው የአዲሱ ክልል አመራሮች በተደጋጋሚ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች የክልል ማዕከል ተመርጧል እየተባለ የሚናፈሰውን ወሬ ያጣጣሉ ሲሆን፣ በሕግ አግባብ መሥፈርቶችን በማስቀመጥ የሚወሰን እንደሆነም እያስታወቁ ናቸው፡፡

ከዚህ ባለፈም በጉዳዩ ላይ ከመግባባት መድረስ ካልተቻለ የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባና መፍትሔ እንዲሻ ጥሪ ሊደረግለት እንደሚችልም ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ኮንታ ልዩ ወረዳ፣ በምዕራብ ኦሞ ዞን፣ ቤንች ሸኮ ዞን፣ ዳውሮ ዞን፣ ካፋ ዞንና ሸካ ዞን በጋራ በክልልነት የመደራጀት ጥያቄ በሕዝበ ውሳኔ እንዲወሰን ድምፅ መስጠታቸው የሚታወስ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በወቅታዊ ፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች ላይ የቀረበላቸውን ምክረ ሐሳብ እያደመጡ ነው]

ችግሩ ምን እንደሆነ በትክልል ለይተነዋል ግን ግን ምን? በይፋ መናገር አልነበረብንም። ለምን? ችግሩን...

የ12ኛ ክፍል የብሔራዊ ፈተና ውጤትና እንደምታው

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) የትምህርትን...

ንግድ ባንክ ከቪዛና ማስተር ካርድ ጋር ተደራድሮ ያስጀመረው የገንዘብ ማስተላለፊያ ቴክኖሎጂና ፋይዳው

ከውጭ ወደ አገር በሕጋዊ መንገድ የሚላክ ገንዘብ (ሬሚታንስ) መጠን...

ይኼ አመላችን የት ያደርሰን ይሆን?

እነሆ ከፒያሳ ወደ ካዛንቺስ። ‹‹አዳም ሆይ በግንባር ወዝ ትበላለህ››...