- ኦብነግ ሁለቱ የካቢኔ አባላት እንደማይወክሉት ገለጸ
ላለፉት ሦስት ዓመታት በምክትል ርዕሰ መስተዳድርነት ማዕረግ ሲመሩ የቆዩትና በአዲሱ የሶማሌ ክልል ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሆነው በተሰየሙት አቶ ሙስጠፋ መሐመድ፣ የተመሠረተው ካቢኔ፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) አባላት ናቸው ለተባሉ ሁለት ግለሰቦች በአመራርነት ሾመ፡፡ ኦብነግ በበኩሉ ግለሰቦቹ ፓርቲውን እንደማይወክሉ ገልጿል፡፡
አቶ ሙስጠፋ 27 አባላት ያሉት ካቢኔ አደረጃጀት አቅርበው በምክር ቤቱ ሲያፀድቁ፣ ሁለቱ ኃላፊነት የተሰጣቸው ግለሰቦች ‹‹የኦብነግ አመራር አባል›› መሆናቸው ተገልጿል፡፡ በአዲሱ ካቢኔ ዘጠኝ አመራሮች በአዳዲስ ተሿሚዎች እንዲተኩ ተደርጓል፡፡
አቶ ሙስጠፋ ሶማሌ ክልልን ለረዥም ዓመታት በርዕሰ መስተዳድርነት ሲያስተዳድሩ የነበሩትንና አሁን በእስር ላይ የሚገኙትን አቶ አብዲ ሙሐመድ ዑመርን (አብዲ ኢሌ) በመተካት፣ ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ዓመታት ያክል የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ሲያገለግሉ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡
መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም. በተካሄደው የሕዝብ ተወካዮችና የክልል ምክር ቤት ምርጫ፣ የክልሉ ምክር ቤት ካሉት 273 መቀመጫዎች ውስጥ፣ 272 ያህሉን ያገኘው የሶማሌ ክልል ብልፅግና ፓርቲ የሚመራው የመንግሥት ምሥረታ መርሐ ግብር ሰኞ ጥቅምት 8 ቀን 2014 ዓ.ም. ተካሂዷል፡፡
በክልሉ ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት አዳራሽ በተካሄደው ምክር ቤት የመጀመሪያ ውሎ የሶማሌላንድ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት፣ እንዲሁም የሶማሌ ክልል ነባር ፕሬዚዳንቶችና የፌደራል መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
አቶ ሙስጠፋ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ባለፉት ዓመታት ሲሾሙ የነበሩ የክልሉ መንግሥት ኃላፊዎች፣ በሕወሓት ቡድን ሴራ በራሳቸው መቆም እንዳይችሉ ተደርገው መቀመጫቸውን በሐረር ከተማ ባደረጉ የጦር ጄኔራሎች ይዘወሩ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ይሁን እንጂ ከመንግሥት ለውጡ በኋላ ባለፉት ሦስት ዓመታት የሶማሌ ሕዝብ በፌደራል መንግሥት ያለው ውክልና ተጠብቆ፣ በኢሕአዴግ ዘመን አጋር ሲባል የነበረውን ስያሜ የሻረ የክልል አስተዳዳሪ ድርጅት መመሥረቱን አስታውቀዋል፡፡
በሥነ ሥርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት አቶ ሙስጠፋ የሶማሌ ክልልን ፖለቲካ ከጅግጅጋ ወደ አዲስ አበባ በመውሰድ ትልቅ ለውጥ ማምጣታቸውን፣ ዛሬ አገሪቱን የሚመራው የብልፅግና ፓርቲ የሶማሌ ክልል ልጅ በሆኑት በአቶ አደም ፋራህ እየተመራ መሆኑን አውስተዋል፡፡
እንደ አዲስ የተዋቀረው የክልሉ አደረጃጀት በመጪዎቹ በቀጣይ አምስት ዓመታት በሶማሌና በአፋር ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በአስተዳደር ወሰን አለመግባባት ሳቢያ በየጊዜው ለሚከሰቱ ግጭቶች የመጨረሻ መፍትሔ እንዲያገኝ እንደሚሠራ፣ የክልሉ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን የኅትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ክፍል ኃላፊ አቶ አብዶ ሂሎው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ለዘመናት አብሮ ይኖር የነበረውን የሶማሌና የአፋር ሕዝብ በአንዳንድ ፖለቲከኞችና ተልካሻ ምክንያታቸው ደሙ እንዲፈስ የተደረገበትን ችግር፣ አዲሱ ሥራ አስፈጻሚ ከፌደራል የፀጥታ መዋቅርና ከአፋር ክልል ካቤኔ ጋር በመሆን ለመፍታት የመጀመሪያው የቤት ሥራው እንደሚሆን ስምምነት ላይ መደረሱን አቶ አብዶ አክለው ተናግረዋል፡፡
ከጥቂት ዓመታት በፊት በነበረው ሥርዓት ምንም እንኳ በሥራ ላይ ያለው የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ለሁሉም ዜጎች እኩል መብት የሚሰጥ ቢሆንም፣ የሶማሌ ሕዝብ እንደ ሁለተኛ ዜጋ ይቆጠር እንደነበርና በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥስቶች ሲፈጸሙበት መቆየቱን፣ እንዲሁም በባህል አብሮ ከተሳሰረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር አብሮ እንዳይኖር ተደርጎ የኖረውን ሕዝብ በቀጣይ ከሁሉም ኢትዮጵያዊ ጋር ተዋዶና ተሳስቦ እንዲኖር ይደረጋል ሲሉ ኃላፊው አስረድተዋል፡፡
በሶማሌ ክልል አዲሱ ካቢኔ ውስጥ ‹‹የኦብነግ አባላት ናቸው›› ተብለው ሹመት የተሰጣቸውን ሁለት ግለሰቦች አስመልክቶ ያነጋገርናቸው የፓርቲው የአዲስ አበባ ቢሮ ዳይሬክተር አቶ አህመድ አብዱላሂ ‹‹ተሾሙ የተባሉት ሁለት ግለሰቦች ኦብነግን አይወክሉም›› ብለዋል፡፡
ሁለቱ ግለሰቦች ከዓመት በፊት ከፓርቲ አባልነታቸው እንደተባረሩ አቶ አህመድ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡