በንጉሥ ወዳጅነው
የዚህ ጽሑፍ ርዕስ መግቢያ የሆነውን አባባል ከጋሞ አባቶች ተውሰው ሰሞኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ አባባሉንም የተጠቀሙት መደመርና መተባበር ያለውን ፋይዳ ለማስረዳት ብቻ ሳይሆን፣ ከጎረቤት አገሮችም ሆነ ከዓባይ ተፋሰስ አገሮችም ጋር ቢሆን ተደጋግፎና በጋራ ከመጠቀም ውጪ የተሻለ ዕድል አለመኖሩን ለማስረገጥ ነበር፡፡ መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የተከፈተበት ዕለት ነው፡፡
አገራችን በተለያዩ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ ፈተናዎች እየተዋከበች በነበረችበት ጊዜ በአንፃሩ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና አሳታፊ ምርጫ የተካሄደበት መሆኑ ነው ይህን የሚያስብለው፡፡ የሕዝቡ የቅድመና የድኅረ ምርጫ ተሳትፎም የሚጣጣል አልነበረም፡፡ ሒደቱን የተለያዩ ተገዳዳሪ ኃይሎችና የትጥቅ ተፋላሚዎች ለማደናቀፍ ቢሞክሩም፣ በርከት ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶችም ተሳትፈው፣ አሸናፊው የብልፅግና ፓርቲ መሪ በጠቅላይ ሚኒስትርነት የተሰየሙበት ምርጫ ዕውን ሆኗል፡፡ ይህ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ የተለያዩ የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎችም ካቢኔውን የተቀላቀሉበትና በርከት ያሉ ቴክኖክራቶች መዋቅሩን የያዙበት መሆኑ በታሪክ የሚመዘገብ ነው፡፡ የበዓለ ሲመት ሥነ ሥርዓቱም ደማቅና ታሪካዊ የሚባል ነበር፡፡
በዚህ ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ካደረጉት ሰፊ ንግግር መሀል ታዲያ፣ ለጎረቤቶቻችንም ሆነ ለዓባይ ተፋሰስ አገሮች እስከተስማማን ድረስ በዓባይ ውኃ በጋራ ከመጠቀም ውጪ አማራጭ የለንም የሚለው የተስፋ ቃላቸው የዚህ ጽሑፍ ጭብጥ ሆኗል፡፡ በእርግጥም አፍሪካዊያን በተለይም የምሥራቅ አፍሪካ ደሃ ሕዝቦች መደጋገፍና መተባበር ብቻ ሳይሆን፣ በመተሳሰብ የጋራ ሀብታቸውን ከመጠቀም የተሻለ ምን ዕድል ሊኖራቸው ይችላል፡፡
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የኡጋንዳ፣ የሶማሊያ፣ የኬንያ፣ የጂቡቲ፣ የደቡብ ሱዳንና መሰል ጎረቤት አገሮች ፕሬዚዳንቶች እንዲሁም እንደ ናይጄሪያና ሴኔጋል ያሉ የሩቅ አገሮች መሪዎች በተገኙበት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በጉዳዩ ላይ እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያ አዲሲቷ የተስፋ አድማስ ምድር ነች፡፡ በቀጣናችንም ቢሆን ከሚያጋጩን ይልቅ የሚያስታርቁን፣ ከሚያለያዩን ይልቅ የሚያስተባብሩን ነገሮች ብዙ ናቸው።
የጋሞ አባቶች ‹‹ከሰው ጋር አንድ ዓመት ያላረሰ፣ ለብቻው ሰባት ዓመት ያርሳል፤›› እንዲሉ፣ ዕጣ ፈንታችን የተሳሰረ ስለሆነ፣ በቀጣናችን ያለውን የተበታተነ አቅም ሰብሰብ አድርገን ብንተባበር ያሉብን ችግሮች ‹‹በንስር ፊት እንደ ቆመች ድንቢጥ ይኮሰምናሉ›› ያሉት ዶ/ር ዓብይ፣ የህዳሴ ግድብ እንደ አገር ከሚያስገኝልን ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጠቀሜዎች ባሻገር፣ ቀጣናዊ ትስስርና መልካም ጉርብትናን የሚያጠናክር ግዙፍ ፕሮጀክት መሆኑን ዳግም አውስተዋል።
‹‹ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን የዓባይ ወንዝ ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳነቱ ባለፈ ተምሳሌታዊ ትርጉሙ ግዙፍ ነው። ዓባይ ማለት የመነሳታችን ምሳሌ፣ በራሳችን አቅም የመቆማችን ማሳያና የኅብረታችን ገመድ ነው። ዓባይ በማይታይ ምትኃቱ ስላስተሳሰረን፣ በማይዳሰስ ኃይሉ ስላበረታንና በራስ መተማመናችንን ስለጨመረ፣ ከሕፃናት እስከ አረጋውያን፣ ከከተማ እስከ ገጠር፣ ከቆላ እስከ ደጋ፣ ከደቡብ እስከ ሰሜን፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከዕለት ጉርሱና ከመንፈቅ ልብሱ ቀንሶ ግድቡን ለማጠናቀቅ ቆርጧል፤›› ነበር ያሉት፡፡
‹‹ጎረቤቶቻችንና የዓባይ ልጆች ይኼንን ሀቃችንን እስከ ተረዳችሁልን ድረስ፣ በዓባይ ወንዝ የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ፣ ቀጣናዊ ትስስርን በሚያጠናክርና ሁሉንም አሸናፊ በሚያደርግ መንገድ ለመሥራት ሁሌም ዝግጁ ነን፤›› ሲሉም የአገራችንን የዘወትር ጠንካራ አቋም አንፀባርቀዋል። በተግባርም አገራችን ከዚህ መርህ ለበስ ንግግር ዝንፍ እንደማትል ጥርጥር እንደሌለው ሕዝቡ ብቻ ሳይሆን፣ በበዓሉ ሲመቱ ላይ የተጋበዙ አገሮች መሪዎች ሳይቀሩ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ይበሉ እንጂ ከብዙዎቹ ጎረቤቶቻችን የጋራ ተጠቃሚነት አንፃር ሱዳናዊያን ፖለቲከኞች ከአገራችን ጋር የገቡበት ፍጥጫ ያልተገባ ሆኖ ይታያል፡፡ የቀጣናው ሕዝቦች ከተዘረጋለን የጋራ የተፈጥሮ ማዕድ (ለጊዜውም ቢሆን) ዘወር ማለታቸው ግን የሚያስቆጭ ነው፡፡ አገራችን እንኳን ዛሬ ትናንትም ቢሆን ለሱዳናዊያን ክፉ አልነበረችም፡፡
ኢትዮጵያ በዓባይ የጋራ ተጠቃሚነት ዙሪያ ይቅርና በካርቱም የውስጥ ጉዳይ እየገባች ግጭቶቻቸው እንዲቆሙ፣ አለመግባባታቸው እንዲታረቅ፣ ብሎም ሰላም እንዲያገኙ ሳታሳልስ ሠርታለች፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ፣ ‹‹ኢትዮጵያን እናምናታለን ለደኅንነታችንም ሆነ ለድርድሩ ብቻዋን ትበቃናለች፤›› እስከሚሉ ድረስ፡፡
በእርግጥም ሱዳን አደጋ ላይ ስትወድቅ ኢትዮጵያ የጀግኖች ልጆቿን ሕይወት ገብራ የካርቱምን ህልውና ለማፅናት ብዙ ዋጋ መክፈሏን የሩቅ ዘመኑ ቀርቶ የቅርቡ ትውልድም አይዘነጋውም። ታዲያ የቀደመው ብቻ ሳይሆን፣ የቅርቡ ጊዜ ክስተትስ ቢሆን ዕጣ ፈንታችንን በጋራ ከመወሰን ውጪ ሌላ አማራጭ እንዳልነበር የሚያሳይ አልነበረም፡፡ ደግነቱ ይህን የረሳው የሱዳን ፖለቲካ ረጅም ርቀት ስለመቀጠሉ የሚሰጥ ዋስትና የለም እንጂ፡፡
የሱዳን ፖለቲከኞች ይህን እውነት ያበላሹት ግን አገራችን ወደ ለውጥ ከገባች ካለፉት ቅርብ ዓመታት ወዲህ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በተለይ ወላዋይ ከሆነው የግብፃዊያንን ፖለቲከኞች የዓባይ ውኃ አጠቃቀም አቋም ጋር ተያይዞ የተከተሉት መንገድ አገራችንን ማስከፋቱ ተደጋግሞ የታየ ነው፡፡
ከዚያም አልፈው የካርቱም ያልተግባቡ ፖለቲከኞችና ወታደራዊው ክንፍ፣ በአንድ በኩል በአገራችን በሕጋዊ መንገድ የተቋቋመውን መንግሥት ለማፍረስ የሚዋጉ ኃይሎችን በመደገፍ፣ በሌላ በኩል በመነጋገርና በሠለጠነ መንገድ ሊፈታ የሚችልን የድንበር አጀንዳ ጠምዝዞ የአገራችንን ሉዓላዊ መሬት በመውረር የጋራ ገበታውን ለመድፋት ሞክረዋል፡፡ አያዛልቃቸውም እንጂ እስካሁንም ወደ ቀልባቸው ላለመመለሳቸውም ከሌሎች ጎረቤት አገሮች ጋር ለመመሳሰል ሲሉ እንኳን በበዓለ ሲመቱ ከመታደም ታቅበዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለዘመናት ለሱዳን ሰላም ያላትን ፅኑ እምነት የሚያመላክት ትልቅ ፖለቲካዊ ዕርምጃ ስትወስድ ብትቆይም፣ በዓባይ ውኃ የጋራ ተጠቃሚነት መንፈስም ቢሆን፣ ፕሬዚዳንት አልበሽር ከሥልጣን እስከ ወረዱበት ጊዜ ድረስ ብቻ ሳይሆን፣ ከዚያም ወዲህ መልካም ትብብር የነበረ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ የውስጥ ችግር ሱዳን ከሸማቂው የሕወሓት ሠራዊት ጎን መቆሟ ነው ብዙዎችን ያሳዘነው፡፡ ኢትዮጵያዊያንንም ቅሬታ ውስጥ የከተተው፡፡
በተለይ በስደተኞች መጠለያ ስም የሸማቂው ኃይል ከ30 ሺሕ በላይ ታጣቂዎች ሠልጥነው አንድ ጊዜ ሳይሆን ሁለትና ሦስት ጊዜ ወደ አገራችን አጥቅተው ለመግባት መሞከራቸው ግልጽ ፀብ አጫሪነት ነው፡፡ ሌላ ባላንጣ እጁ እንዳለበት ቢታመን፣ የዚህን ኃይል ትጥቅና ስንቅ እያቀረበ በእጅ አዙር ግጭት እንዲባባስ እያደረገ ያለው የሱዳን ጊዜያዊ መንግሥት፣ በሁሉም ጎረቤት አገሮች መወገዝ ያለበት ተግባር እየፈጸመ መሆኑን ሊደብቅ አይችልም፡፡ ለሁለቱ አገሮች ብቻ ሳይሆን፣ ለቀጣናው ደኅንነት ሲባልም በአፋጣኝ መቆም ያለበት ነው፡፡
ከዚህ ተነጥሎ የማይታየው የጋራ ማዕድን የመድፋቱ ተግባር ‘ሱዳን በዚህ ጊዜ ለምን የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግራ ወረራ ፈጸመች?’ ብሎ መጠየቅ ሲቻል የሚገኘው መልስ ነው፡፡ በቅድሚያ ግን የሱዳን ጦር የኢትዮጵያን ምዕራባዊ ክፍል መሬት መውረሩ መነሻው ሕዝባዊ አለመሆኑን መረዳት፣ ለችግሩ መፍትሔ ለማበጀት ዕድል ይሰጣል። ሱዳን በተረጋጋ የፖለቲካ ሒደትና በዴሞክራሲያዊ የትብብር መንፈስ ላይ ስትቆም፣ ችግሩ ሊፈታ ይችላል ብሎ ተስፋ ማድረግም አይከፋም፡፡
ሱዳን አሁን ከአገራችን ጋር ለጀመረችው ፍጥጫም ሆነ ለቀጣናው መቃወስ መንስዔ ሊሆን ለሚችል ውዝግብ ዋነኛው ፀብ አጫሪ ማነው ካልን ግን፣ የሱዳን ሕዝብን የዳቦ ጥያቄ ከመመለስ ይልቅ ኪሳቸውን በሙስና ያደለቡ የቀድሞ ሥርዓት ተዋናዮችና ነጋዴ የጦር አዛዦች መሆናቸውን ለማወቅ ነብይ መሆን አይጠይቅም፡፡ እነዚህ የፊውዳል ባህሪ ያላቸው ጥገኛ ኃይሎች በአንድ በኩል የካይሮ ጋሻ ጃግሪዎቻቸውን አይዞህ ባይነት በመቀበል፣ በሌላ በኩል የአገራችንን ድንበር ጥሰው ለመጠቅለል በሚመኙት ሰፊ መሬት በመጎምዠት ነው የተደፋፈሩት ብሎ መደምደም ይቻላል፡፡
ይህ ወቅት የተመረጠበት ዋናው ምክንያትም የሕወሓት ኃይል የአገር መከላከያ ሠራዊቱን የሰሜን ዕዝ ወቅቱ ያዳከመው ስለመሰላቸው፣ በመላው አገሪቱ ሲታመስ የከረመው ቀውስ ሕዝቡን የከፋፈለውና መንግሥትንም ያዳከመው እንደሆነ በመገመታቸው፣ ብሎም በሚወስዱት ሕገወጥ ዕርምጃ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሥራ ስለሚቋረጥ የግብፅ ሙሉ ድጋፍም እንደማይለያቸው በማመናቸው ነበር፡፡ ከዚህም አልፎ የሩቅ አገሮች ባላንጣዎችን የሴራና የፖለቲካ ፍላጎትንም ማከል ይቻል ይሆናል፡፡
እውነት ለመናገር ግን እውነትና ፍትሕ እስካሉ ድረስ የሱዳን ፖለቲከኞች መጋፋት ሊሳካላችው አይችልም ብቻ ሳይሆን፣ አገራችንም ልትናወጥላቸው አትችልም፡፡ እንዲህ ያለውን ዕኩይ ድርጊት ዝም ብሎ የሚመለከት ሕዝብና መንግሥት ብቻ ሳይሆኑ ወዳጅ አገሮችም እንደሌሉ መታወቅ አለበት፡፡ ‹‹ከሰው ጋር አንድ ዓመት ያላረሰ ለብቻው ሰባት ዓመት ያርሳል›› እንዲሉ፣ ተነጠሉ ሲላቸው እንጂ የሚያገኙት ውጤትም ሊኖር አይችልም፡፡
እነ ጄኔራል ቡርሃን ድከሙ ሲላቸው እንጂ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለሱዳን ሕዝብ ጥቅም እንጂ ምንም ዓይነት ጉዳት የሚያስከትል አልነበረም፡፡ ይህን ደግሞ ከማንም በላይ የካርቱም ፖለቲከኞችና የውኃ ሙያተኞች ጠንቅቀው ይገነዘቡታል፡፡ ግን የሱዳና አንዳንድ ገዥዎችና ጨርቅ መጣል የሚምራቸው ፖለቲከኞች፣ ከወላዋይ አቋም የማይወጡና የግብፅን ተፅዕኖ መቋቋም የማይችሉ ሆነው በመቸገራቸው እውነቱን የሚክዱ ሆነዋል፡፡
በእርግጥ ሱዳናዊን የግብፅን ያህል ባይሆንም፣ ከሌሎቹ የናይል ተፋሰስ አገሮች በላይ በውኃ ሲጠቀሙ እንደኖሩ የታወቀ ነው፡፡ በዚያው ልክ የዓባይ ውኃ በጎርፍና በደለል ሲያጠቃቸው እንደኖረም በመረጃ ላይ የተደገፈ ሀቅ የሚያስረዳው ነው፡፡ የግድቡ መገንባት ግን በአንድ በኩል ሲያጠቃቸው የነበረውን ጎርፍና ደለል የሚገታ፣ በሌላ በኩል በፍትሐዊና በምክንያታዊ ውኃ አጠቃቀም መርህ የውኃ ፍላጎታቸውን የማይከለክላቸው ነው፡፡
እውነተኛና ለሕዝብ ጥቅም የቆመ የሱዳን መንግሥት ቢኖር ግን፣ በፍጥነት የውኃ አጠቃቀም ስምምነቱንም ሆነ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት መቀበል በቻለ ነበር፡፡ ያ ባለመሆኑ ከኢትዮጵያ ጋር ብቻ ሳይሆን፣ ከጎረቤቶቻችን ጂቡቲ፣ ደቡብ ሱዳንም ሆነ ከኬንያና ከኤርትራ ጋር ሊያቃቅራቸው የሚችለውን የግጭትና የውዝግብ አቋም ማራመድ ፈልገዋል፡፡ የቅደም ተከተል ጉዳይ ሆኖ እንጂ የነገው የአገራችን አጀንዳም ይኼ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡
ለዚህ አብነት የሚሆነው የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ከቀናት በፊት ግብፅ ሄደው ለሱዳንም ሆነ ለግብፅ የሚበጀው ከኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በጋራ መሥራት ነው ማለታቸው ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም የኤርትራ መንግሥትም በተደጋጋሚ የሱዳን ፖለቲከኞችና ወታደራዊው ክንፍ አካሄዳቸውን እንዲያጠኑ መክሯል፡፡ የሌሎቹ ጎረቤቶቻችንን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ኅብረት አቋምም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡
መላው አፍሪካዊያን በተለይም የቀንዱ ሕዝቦች ተረጋግተውና ተጋግዘው ከድህነት ይወጡ ዘንድ፣ ኢትዮጵያና ሱዳን በምንም መሥፈርት ወደ ጦርነት መግባት ያለባቸው አገሮች አይደሉም፡፡ ይህን ሀቅ ደግሞ የሁለቱም አገሮች ሕዝቦች በፅናት የሚቀበሉት ነው፡፡ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በካርቱምና ሌሎች የሱዳን አካባቢዎች እየተንቀለቀለ ያለው የለውጥ ፍላጎትም ሆነ የሕዝብ እንቢተኝነት ምንም እንኳን በኑሮ ውድነትና በአገሪቱ ባለው የፖለቲካ አለመረጋጋት ላይ የተመሠረተ ቢሆንም፣ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር አለመስማማቷን ክፉኛ የሚያወግዝ ነው፡፡
እንዲህ ያሉ የሕዝብ ሐሳቦች በአንድም በሌላም እየተነሱ ያሉት ደግሞ፣ ኢትዮጵያና ሱዳን መለስተኛ ውዝግብና ግጭቶችን በየመሀሉ ቢያስተናግዱም በታሪክ ሚዛን ሲታዩ ሕዝቦቻቸው ከልዩነታቸው ይልቅ አንድነታቸውን ለማጠናከር ሲሠሩ የኖሩ መሆናቸውን በማስታወስ ነው። ሁለቱ አገሮች በእምነት፣ በባህልና በኢኮኖሚ ያላቸው ትስስር ብዙ ተስፋ የተጣለበት መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ የማይበጠስ መሆኑ ስለሚታወቅ ነው። የናይል/ዓባይ ውኃንም ሆነ የጋራ ድንበሩን በእኔ እበልጥ/አንተ ትበልጥ እንደሚፈታ እምነት ስላላቸው ነው፡፡
ለሱዳንና ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ብቻ ሳይሆን ለመላው የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የሚበጀው ብቸኛ መፍትሔ ግን መደማመጥ፣ በጋራ መንፈስ መሥራትና መተሳሰብ መሆኑን በማጠቃለያው ላይ ማስታወስ እወዳለሁ፡፡ ‹‹ከሰው ጋር አንድ ዓመት ያላረሰ ለብቻው ሰባት ዓመት ያርሳል፤›› የሚለውን የጋሞ አባቶች ምክር ዳግም በመለገስ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡