Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየብልፅግና መንግሥት አካሄድ ከኢሕአዴግ ልማታዊነት አንፃር ሲፈተሽ

የብልፅግና መንግሥት አካሄድ ከኢሕአዴግ ልማታዊነት አንፃር ሲፈተሽ

ቀን:

በኢዮብ አሰለፈች ባልቻ

አገራችን ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ሁሉን አቀፍ ውጥንቅጥ በአግባቡ ለመረዳት ቆም ብለን ልናጤናቸውና ልናነሳቸው የሚገቡ ብዙ ጥያቄዎች አሉ። በዚህ አጭር ጽሑፍ የኢሕአዴግ የልማታዊነት ርዕዮተ ዓለምን ከብልፅግና መንግሥት የገበያ መር ኢኮኖሚ ምሥረታ አካሄድ ጋር በማነፃፀር፣ የኢትዮጵያን መሠረታዊ የልማት ጥያቄዎችን ከመመለስ አንፃር የተመለከትኩን ጥንካሬና ክፍተት ለማሳየት እጥራለሁ። የምላሽ ነጥቦቹ ግልጽ ይሆኑ ዘንድ ላተኩርባቸው የምፈልጋቸው ጉዳዮች የአገራችንን የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ መዋቅርና ሥርዓት፣ በልማትናፖለቲካ መካከል ያለው ጥብቅ ትስስርና ነባራዊ የፖለቲካ ሒደቶች የተቃኙበት ቀመር፣ እንዲሁም ከምዕራቡ ዓለም የሚመጡትን ርዕዮተ ዓለማዊ ጫናዎች በመተንተን ከላይ ላነሳሁት ዋና ጥያቄ መልስ ለመስጠት እሞክራለሁ።

እንደ ሌሎቹ የአፍሪካ አገሮች የኢትዮጵያ ፖለቲካል ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ችግር አስኳል የሚገኘው የአገራችን የምርትናፍጆታ ንድፍ ላይ ነው። የአገራችን ኢኮኖሚ ዋነኛ ምርት የሆኑትን ለውስጥ ፍጆታ አናውልም። በሌላ በኩል ደግሞ ዋነኛ የሆኑ የፍጆታ ሸቀጦችን ደግሞ የአገራችን ኢኮኖሚ አያመርታቸውም። በአጭር አገላለጽ የምናመርተውን አንጠቀምም፣ የምንጠቀመውን አናመርትም። ወደ ሥልጣን የሚወጡ መንግሥታት ይህንን መዋቅራዊ መዛነፍ በአጭር፣ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ ዕቅድ መፍትሔ ሊያበጁለት ይገባል። የመፍትሔ አቅጣጫው ደግሞ በእኔ አተያይ የመንግሥትን ጠንካራ ክንድና የማስፈጸም አቅም፣ በይበልጥ ደግሞ የልማታዊነት ርዕዮተ ዓለም ይጠይቃል።

በእኔ አመለካከት የኢሕአዴግ መንግሥት ተልሞት የነበረው የልማታዊ አገረ መንግሥት የመገንባት ዓላማ የራሱ ውስንነቶች ቢኖሩትም፣ ከሞላ ጎደል ትክክለኛ የልማት አቅጣጫ ነው። በተለይ በአሁኑ ለሦስት ዓመት ያህል በሪፎርም አጀንዳ ሥልጣን ላይ የነበረውና አሁን በምርጫ ሙሉ ሥልጣን የያዘው መንግሥት ከሚከተለው ገበያ መር ፖለቲካል ኢኮኖሚ አንፃር ብናወዳድረው፣ የልማታዊ አገረ መንግሥት ሥርዓት የኢትዮጵያን መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ችግሮች የመፍታት አቅም አለው ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም የልማታዊነትን አጀንዳ ማዕከሉ ያደረገ ሥርዓት ከብዙ መገለጫዎቹ አንዱ የመንግሥትን ሀብት የመያዝ፣ የማመንጨት፣ የማከፋፈልና፣ የመቆጣጠር አቅምን የአጭር ጊዜ ገበያ ተኮር ትርፋማነትን ባማከለ ሳይሆን ፍትሐዊነትን፣ የአብዛኛው ሕዝብ ተጠቃሚነትን፣ ዘላቂነትን፣ እንዲሁም አገራዊ አቅም ማጎልበትን ታሳቢ በማድረግ ለመጠቀም መቻሉ ነው። ለምሳሌ በልማታዊ መንግሥት ሰፊ የልማት ራዕይ ውስጥ የተከናወኑ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን (መንገድ፣ የጤና የትምህርት ማዕከላት፣ ግድቦች፣ የማምረቻ መንደሮች፣ የከተማ የጋራ መኖሪያ ቤቶችና ግብርና ተኮር ሥራዎች) በሙሉ ብናያቸው ከልማታዊ አገረ መንግሥት አጀንዳ ውስጥ የፈለቁ ናቸው።

እነዚህ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ሙሉ በሙሉ በስኬት የታጀቡ ከዕቅድ፣ አፈጻጸምና ውጤት አንፃር እንከን የለሽ ናቸው የሚል መከራከሪያ አላቀርብም። ነገር ግን ቆም ብለን ማየት ከቻልን መንግሥት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎችን በተመለከተ የነበረው ቁርጠኛ አቋም በብዙ ሚሊዮን ለሚቆጠሩ የአገራችን ዜጎች ሕይወት በዘላቂነት መቀየርም ሆነ፣ የአገራችን ኢኮኖሚ ላይ ያሳረፈው በጎ ተፅዕኖ እንዲሁ የሚታለፍ አይደለም።

በተለይ ደግሞ ይህን ዓይነት አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ያማከለ የልማት ራዕይ በማስፈጸም ሒደት ውስጥ፣ ከምዕራባውያን መንግሥታትና አጋሮቻቸው (በተለይም የዓለም ባንክና የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት) በመንግሥት ላይ ይደረግ የነበረው ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ ጫና በጣም ሊተኮርበት የሚገባው ነው። የህዳሴ ግድብ ለዚህ አንድ ማሳያ ነው። በልማታዊነት አገርን በትልቁ ከማሰብና ትልቅ ራዕይ ከመሰነቅ ውጪ ሊታሰብ የማይችለውን የህዳሴ ግድብ፣ ዛሬም ድረስ እንዲህ የሁላችን ዓይን ማረፊያና የልብ ትርታ ሊሆን የቻለው ሁለት በልማታዊ አገረ መንግሥት የመገንባት ማዕቀፍ ውስጥ ስለተጀመረ ነው። አሁን ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት እንዲህ ዓይነት የኢትዮጵያን አጠቃላይ የምርታማነትና የፍጆታ ሥርዓት ላይ መሠረታዊ ለውጥ የሚያመጡ የልማት ሥራዎችን ለመከወን ርዕዮተ ዓለማዊ ውስንነት ስላለበት ቢያስበውም፣ የገበያውን መልካም ፈቃድ ባማከለ መንገድ እንጂ መንግሥታዊ አቅሙን ተማምኖና ለልማቱ አስፈላጊነት ቁርጠኝነት ኖሮት አይሆንም። ለዚህ ማስረጃ ከተፈለገ ላለፉት ሦስት ዓመታት የመንግሥት ከፍተኛ ትኩረት፣ የሰው ኃይልና የመዋዕለ ንዋይ ማሰባሰብ ሒደቶች ምን ዓይነት ጉዳዮች ላይ እንዳተኮሩ ማየት ተገቢ ነው። በተለይ በአዲስ አበባ የተከናወኑ አዳዲስ ሥራዎች የራሳቸው የሆነ መልካም ጎን ቢኖራቸውም (መናፈሻ ፓርኮችና የወንዝ ዳር ማልማት ሥራዎች በተለይ)፣ አገራችን ካለባት አንገብጋቢ ፈተናዎችና የልማት ጥያቄዎች አንፃር ቅድሚያ ማግኘት የሚገባቸው ናቸው የሚል እምነት የለኝም።

የኢሕአዴግ ልማታዊነትና ውስጣዊ ተቃርኖዎች

የኢሕአዴግ የልማታዊነት ርዕዮተ ዓለም እንዲያነክስና እንዲወድቅ መሠረታዊ ምክንያት የሆነው 1983 ወዲህ ያለው አገረ መንግሥት በውስጡ የማይታረቁ ቅራኔዎችን ስለያዘ ነው። የቅራኔዎቹ አንደኛው መስመር አጠቃላይ የአገሪቱ የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ መዋቅርና ሥርዓት እንዲሁም የገዥው ፓርቲ አወቃቀርና አሠራር ብሔርን መሠረት ባደረገና የጎንዮሽ መበላለጥና እኩልነትን (Horizontal Inequality) መሠረት ባደረገ መንገድ መቋቋሙ ነው። ይህ መዋቅርና ሥርዓት ውስን የሆነ ራስ ገዝነትን ለክልሎች አንዳንዴም ሲያስፈልግ እንደ ፖለቲካዊ አዋጪነቱ ከማዕከላዊ መንግሥት ብሔርን ሽፋን አድርጎ ማፈንገጥን የሚያበረታታ ሥርዓት ነው። አንድ ከሞላ ጎደል የሚያስማማ አገራዊ የልማትና ዕድገት አቅጣጫ እንዳይኖርና ቢኖር እንኳ፣ በየብሔሩ ባሉ ልሂቃን መልካም ፈቃድ ሥር የወደቀ እንዲሆን ምናልባትም በፖለቲካው መድረክ ሥልጣንን መካፈል ሲያቅታቸው ወደ የብሔራቸው እየሄዱ ልዩነቶችን እያጦዙ የታሪክ ጠባሳዎችን እያጎሉ ፖለቲካዊ ፉክክርና ንትርክ፣ ከዚያም አለፍ ሲል ወደ ግጭት እንዲያዘነብሉ የሚያመቻች ነው። እዚህ ላይ የሕወሓት ልሂቃን የፖለቲካ ሽንፈታቸውን ለማካካስ የትግራዋይ ብሔርተኝነትን እንዴት እንዳጦዙትና ለጦርነቱ መቀስቀስና እየደረሰ ላለው አሳዛኝ ዕልቂት የተጫወቱትን ጉልህ ሚና እንደ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል።

 የቅራኔዎቹ ሁለተኛው መስመር ደግሞ የኢሕአዴግ ልማታዊ አስተሳሰብ ውስን የሆነውን ሀብት በግልጽ በተቀመጠ የልማታዊነት አጀንዳ መሠረት በማዕከላዊነት ተቆጣጥሮ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትንንና ልማትን ሊያመጣ በሚችል መንገድ መቆጣጠር፣ ማምረት፣ ማከፋፈልና በባለቤትነት መያዝን ግድ ይላል። ለዚህም እንዲረዳ የአገሪቱ የፖለቲካ መዋቅርና መደበኛ ሥርዓታት ውስን የሆነ ራስ ገዝነትን ለክልሎች የሚያጎናጽፉ ቢሆኑም፣ ለልማታዊነት ሲባል የማዕከላዊው መንግሥት ይህንን ሕገ መንግሥታዊ አካሄድ በኢመደበኛ ሥርዓታት በመቀልበስ የኢኮኖሚ ዕድገትንና ልማትን በሚያሳልጥ ሁኔታ እንዲተገበር ማድረግ ግድ ብሎት ነበር። ለምሳሌ በኢሕአዴግ ውስጥ ይተገበር የነበረው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ የልማታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም አተገባበር ከፌደራል መንግሥት ወደ ክልሎች የተዋረድ አሠራር፣ አንዳንዴም የክልሎችን የሀብት አጠቃቀምና ክፍፍል የፌደራል መንግሥት ይወስንበት የነበረው አካሄድን መጥቀስ ይቻላል። በአተገባበሩ ላይ የነበረው ድክመትን በማስቀረት ነገር ግን ይህን መሰል እርስ በርሱ የተናበበ የልማታዊነት አካሄድ ውሱን የሆነ ሀብትን በብቃትና በቅልጥፍና ለመጠቀም ያስችላል።

ከላይ የተጠቀሱት ሁለቱ የተቃርኖ መስመሮች የኢሕአዴግን የልማታዊነት ራዕይ በተደላደለ መሠረት ላይ እንዳይቋቋም አድርገውታል። ባለፉት ስድስት ዓመታት እንደታዘብነውም የሕወሓት መሪዎችን ከመንግሥትም ሆነ ከፓርቲ ሥልጣን ማስወገድ የቻሉት፣ የኦሕዴድና የብአዴን አመራሮች ለፖለቲካዊ የበላይነት ያጦዙት ለእነሱ እዲመቻቸው ተደርጎ የተቀመጠውን የብሔርን መስመር ነው። በሚገባ ዓይነት መንገድ ከፈጣን ዕድገቱ አልተጠቀምንም የሚለው አስተሳሰብ በሕወሓቶች የበላይነት ከተያዘው አፋኝ፣ በዝባዥና ሙሰኛ ሥርዓት ጋር ተደምሮ የሕወሓትን ከማዕከላዊ መንግሥት መገፋት ዕውን አደረገው።

ሥር ነቀል ለውጥ ወይስ ማስተካከያ?

 በእንግሊዝኛ ቋንቋ “Throwing The Baby Out With The Bathwater” የሚል አባባል አለ። በግርድፉ ወደ አማርኛ ስንመልሰው መወገድ ያለበትን ቆሻሻና የማይፈለግ ነገር ከእነ ዋናውና አስፈላጊው ነገር ጋር ደባልቀን ማስወገድ ወይም መጣል እንደ ማለት ነው። ላለፉትስት ዓመታት በሥልጣን ላይ የነበረው መንግሥት በተግባር ያዋለው የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የሚባለው ዕቅድ በኢሕአዴግ የልማታዊነት አጀንዳ ላይ የታዩትን ድክመቶች አሻሽሎ ጠንካራ ጎኖቹን ይዞ ከመቀጠል ይልቅ፣ በሪፎርም ሽፋን ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ያለመ ነው። የሥር ነቀል አካሄዱ በይበልጥ ጎልቶ የሚታየው በአገራችን የልማት ሒደቶች ውስጥ በመንግሥትና በግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ (የአገር ውስጥና ዓለም ዓቀፍ የግል ባለሀብቶችና ኮርፖሬሽኖች) መካከል የሚኖረውን የወሳኝነት ድርሻ መወሰን ላይ ነው። በእኔ እይታ የኢትዮጵያን ፖለቲካኢኮኖሚ አመራር ለግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ የበላይነት አሳልፎ መስጠት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍትሕ እንዲኖር ከማድረግ አንፃር፣ የአገራችንን መዋቅራዊ ተግዳሮቶች ከመፍታት አኳያና በይበልጥም ደግሞ በአገራችን ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ዜጎች የሚኖረንን ወሳኝ ሚና ከማረጋገጥ አንፃር ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍል የተሳሳተ የፖሊሲ አማራጭ ነው።

የኢሕአዴግ የልማታዊነት አጀንዳ ኢትዮጵያም ሆነች ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ካለባቸው ሥር የሰደደ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ተግዳሮቶች አንፃር አስፈላጊ ብቻም ሳይሆን እጅግ በጣም ተገቢም ነው። እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች አንደኛው መዋቅራዊ ተግዳሮት የሚያመርቱትን ምርት አብዛኛውን ለአገር ውስጥ ፍጆታ አለመጠቀማቸው፣ ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚጠቀሙት ደግሞ አብዛኛው ያላመረቱትን መሆኑ ነው። ኢኮኖሚያችን አሁንም ቢሆን በቂ እሴት ያልተጨመረባቸው የግብርናና የማዕድን ምርቶችን ወደ ውጪ በመላክ ላይ ጥገኛ ሲሆን፣ ወደ አገር ውስጥ የሚገባው ደግሞ የፋብሪካ ምርት የሆኑ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው ምርቶች ናቸው። ስለዚህም ገቢያችን ሁልጊዜ ለማለት በሚያስደፍር መልኩ ከወጪያችን በእጅጉ ያነሰ ነው።

ስለዚህም ሁልጊዜ የንግድ ሚዛን ጉድለትና የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንደገጠመን እንገኛለን። ለዚህ ችግር የመፍትሔ አማራጮች በአጭር መካከለኛና በረዥም ጊዜ የሚተገበሩ ሲሆኑ፣ እነሱም የኢኮኖሚያችንን የምርትና የፍጆታ ቀመር መቀየር (ከፍተኛ እሴት ያላቸውን ምርቶች ማምረት፣ አብዛኛውን ፍጆታችንን በአገር ውስጥ ምርት መተካት) ለመዋቅራዊ ሽግግር የሚያግዙ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን ከተቋማትና ሥርዓታት ግንባታ፣ ከሰው ኃይል አቅም፣ ከቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ከመንግሥት የማስፈጸም አቅም፣ ከመሠረተ ልማት ግንባታና ተደራሽነት አቅጣጫና በመሳሰሉት ዙሪያ ሰፊ ሥራን የሚጠይቅ ተልዕኮ ነው። እነዚህን ፖሊሲዎች መተለምና መፈጸም ጠንካራና ባለራዕይ መንግሥታዊ አመራር ግድ ይላል።

የዓለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ድርጅትን የመሳሰሉ ተቋማት ግን እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች የሚስተዋሉት የንግድ ሚዛን ጉድለትና የውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግሮች የሚፈቱት፣ መንግሥትን ከጨዋታው ገለል በማድረግና ገበያው የሚስማማውን የሚመቸውን እንዲያደርግ በመፍቀድ ነው ብለው ያምናሉ። የመንግሥት ሚናም የገበያውን ፍሰት ከማሳለጥና ለግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ቦታ ከመልቀቅ ጋር ብቻ ያያይዙታል። የኢሕአዴግ የልማታዊነት አስተሳሰብ ግን ይህንን አንድ ወጥና ታሪካዊና ነባራዊ ሁኔታን ያላገናዘበ የፖለቲካል ኢኮኖሚ አስተሳሰብ ገሸሽ በማድረግ መንግሥታዊ አቅምን ለልማት የመጠቀምን አካሄድ ተግብሯል። በዓይን የሚታይ ሁሉም ተመልካችም ሆነ ታዛቢ የመሰከረለት ተጨባጭ ለውጥም አምጥቷል። ለምሳሌ ለመጥቀስ ያህል የዜጎች በሕይወት የመኖር የዕድሜ ጣሪያ መጨመር፣ የአገሪቱ ተፈጥሮአዊ አደጋዎችን የመቋቋም ብቃት፣ መለኪያው ውስንነት ቢኖረውም ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ ዜጎች ቁጥር መቀነስ፣ በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡ ግዙፍ መሠረተ ልማቶች (የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ግድቦች፣ ፋብሪካዎች መንገዶች) ወዘተ ቋሚ ማስረጃዎች ናቸው። በሌላ አቅጣጫ ደግሞ ዜጎች በሕገ መንግሥት የተደነገጉ መብቶቻቸውን ሙሉ በሙሉ እንዳይጎናፀፉ የነበረውን አምባገነናዊ አገዛዝ መዘንጋት የለብንም። ነገር ግን ይህን ጉዳይ ለሌላ ጊዜ በይደር እናቆየው። በልማታዊነትና በዴሞክራሲያዊ አስተዳደር መካከል ያለውን ቁርኝትና ተቃርኖ በሌላ ጽሑፍ ለብቻው ማየት የተሻለ ነው ብዬ አምናለሁ።

የገበያ መር ኢኮኖሚ ግንባታ ውስንነት ሦስት ማሳያዎች

የለውጡ ኃይል የተባለው ቡድንም ይሁን ሥልጣን የያዘው የብልፅግና መንግሥት የማይክዱት ነገር ቢኖር፣ የኢሕአዴግ የልማታዊ አገረ መንግሥት የመገንባት አጀንዳ ተጨባጭ ለውጥ እንዳመጣ ነው። የተገኘው መልካም ውጤት ላይ አስፈላጊ ማሻሻያዎችን በማድረግ ፍትሐዊነትን ያማከለ የልማትና የዕድገት አቅጣጫ መያዝ ሲገባ፣ የብልፅግናው መንግሥት የያዘው አካሄድ ግን የነበሩ ስኬቶችን በዜሮ የሚያባዛ ነው። ለዚህ ማሳያ የሚሆኑ ሦስት ጉዳዮችን ላንሳ።

የመጀመርያው ጉዳይ በልማት አጀንዳው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍትሕንና ተደራሽነትን የማሳካት ጉዳይ ነው። ለምሳሌ በኢሕአዴግ መንግሥት ላይ ተቃውሞ በተቀጣጠለበት ወቅት እ.ኤ.አ. 2016 የወጣውን የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሁኔታ የሚገልጸው በአፍሪካ የልማት ባንክ የሚታተም ዓመታዊ ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ 73 በመቶ የሚሆነው የመንግሥት ወጪ ያተኮረው በአብዛኛው ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያለውን ኢትዮጵያዊ በቀጥታ የሚመለከቱ ወጪዎች ላይ ነበር። ይህ ማለት ትምህርት፣ ጤና፣ ንፁህመጠጥ ውኃ፣ ግብርና፣ መንገድና የምግብ ዋስትና ላይ ያተኮሩ ወጪዎች ናቸው ይላል። በተቃራኒው ሪፎርም አደርጋለሁ የሚለው መንግሥት ሥልጣን ላይ ከወጣ በኋላ ለመንግሥት ከፍተኛ የዕርዳታ ገንዘብ የፈቀደው የዓለም የገንዘብ ድርጅት ባወጣው ኢትዮጵያን የተመለከት ሪፖርት ደሃ ተኮር የሆኑ ድጎማዎች ቀስ በቀስ ሊቀሩ ስለሚችሉበት ሁኔታ ለመንግሥት ምክሩን ይለግሳል። ይህ ማለት የተፈቀደው ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ ካዝና የሚገባው ይህን መሰል የተቋሙ ምክረ ሐሳቦች ተግባር ላይ ሲውሉ ነው ማለት ነው። ለምሳሌም የኤሌክትሪክ ፍጆታን የተመለከተ የታሪፍ ማሻሻያን በቅርቡ ለማድረግ መንግሥት ቃል መግባቱን ያትታል።

በተመሳሳይ ‹‹የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ ገበያመር የኢኮኖሚ ሥርዓት መገንባት›› ዓላማው ያደረገው የአሥር ዓመት የልማት ዕቅድ እንደሚያትተው፣ በዕቅድ ዘመኑ ማጠቃለያ ላይ ከበጀት ውጪ በሚመቻቸው የብድር አቅርቦት ለግሉ ዘርፍ 87.2 በመቶ የሚሆነውንበመንግሥት ለሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ደግሞ ቀሪውን ማለትም 12.8 በመቶ ለማድረግ አቅዷል። ይህም አካሄድ የመንግሥትን አቅም ከማዳከምና በኢኮኖሚው ላይ የሚኖረውን የወሳኝነት ሚና ከማኮሰስ ጋር የሚያያዝ አካሄድ ነው። በዚህ ሁኔታ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸውን ዜጎች ታሳቢ አድርገው ይሠሩ የነበሩ የልማት ክንውኖች ለግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ትርፍ በሚያስገኝ መንገድ በሚተገበሩ ፕሮጀክቶች ይቀየራሉ ማለት ነው። በዚህ ሒደት ውስጥም ዋነኞቹን መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ተግዳሮቶች መፍታት ሳይሆን፣ የትርፋማነትና የወጪ ቆጣቢነት አመክንዮ የኢኮኖሚ ፖሊሲያችን መርህ ይሆናል ማለት ነው። ከደሃ ተኮር የልማት አቅጣጫ ወደ ገበያ መርና ትርፍተኮር እንሸጋገራለን ወይም እየተሸጋገርን ነው ማለት ነው። በእርግጥ በዚህ ሒደት ውስጥ በገበያው ውስጥ ተፎካክረው የገንዘብና ገንዘብነክ ያልሆኑ ሀብት ያላቸው የተወሰኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ይበለፅጋሉ። በአንፃሩ አብዛኛው መዋቅራዊ መገለል የሚደርስባቸውና የኢኮኖሚና የፖለቲካ እኩልነት ሰለባ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ግን የበለጠ ለከፍተኛ ድህነትና ተበዝባዥነት ይጋለጣሉ።

ሁለተኛው ጉዳይ በሕዝብና በመንግሥት ይዞታ ሥር ያሉ ተቋማትን ወደ ግል የማዘዋወር ሒደት ነው። የዚህ ሒደት ዋነኛ ተጎጂ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሲሆን፣ እነዚህ ለዘመናት በሕዝብ ሀብት የካበት ልምድና ተቋማዊ አቅም ያካበቱ ድርጅቶች ለግል በሚዘዋወሩበት ጊዜ ከስኬታቸው የሚገኘውን ትርፍ ማረፊያው ወይ የመንግሥት ካዝና አልያም መልሶ የድርጅቶቹን አቅም ወደ ማጎልበት ሳይሆን ወደ ገዟቸው ግለሰቦችና ድርጅቶች ኪስ ነው። ይህ ደግሞ ከአገራችን ሕጋዊም ሆነ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የሚወጣውን ሀብት በማብዛት፣ ከትርፉ ቀጥተኛም ሆነ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ በመካፈል የሚኖርን ተጠቃሚነት በመገደብ ከዚያም ባለፈ ትርፍን ብቻ በሚያሰላ አካሄድ የሚዘወር ኢኮኖሚ ውስጥ የሚኖር ኢኩልነት፣ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍትሕ ማጣት የሚፈጥሩት ቀውስ ከባድ ይሆናል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥታቸው ወደ ሥልጣን በመጣ ማግሥት ልሸጣቸው ነው በማለት ለዓለም ቁንጮ ከበርቴዎች በመሰባሰቢያ መድረክ የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ዳቮስ ስዊዘርላንድ ድረስ ሄደው ንግግር ማድረጋቸው ይህ ከፍተኛ መዘዝ የሚያመጣ የፖሊሲ ውሳኔ ምን ያህል ታስቦብት ይወሰን ወይም የርዕዮተ ዓለማዊ ግብን ለማሳካት ብቻ ይተግበር ብዙ ጥያቄ ያስነሳል። የንግድ መርከብ ድርጅትንና የኢትዮጵያ አየር መንገድን የተመለከቱት በከፊልም ሆነ በሙሉ የመሸጥ ውሳኔዎች የታጠፉ ቢሆንም፣ በብልፅግና መንግሥት ውስጥ ያለው የገበያ አምላኪነትና መንግሥት ጠልነት ብዙ ችግር የሚያመጣ መሆኑ የሌሎች አፍሪካ አገሮች ልምድ በግልጽ ያሳየናል።

ሦስተኛው ጉዳይ በዚህ የገበያ መር ኢኮኖሚ የማቋቋም ሒደት ውስጥ መንግሥት የሚኖረው የፖሊሲ ነፃነት ነው። በኢሕአዴግ የሥልጣን ዘመን የልማታዊ መንግሥት የልማት አካሄድን በመቃወም ሲተቹ የነበሩት የዓለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ድርጅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን በመጡ በስድስት ወራት ውስጥ ያመቻቹት ከፍተኛ የሆነ የብድር መጠን እንዲሁ የመጣ አይደለም። ይልቁንም የድርጅቶቹ ዋና ጉዳይ የሆነው ለምዕራባውያን ድንበር የለሽ ካፒታል የገበያ ዕድሎችን ማመቻቸትና እንቅፋቶችን ለማንሳት የተደረገ ክፍያ ነው። ለዚህም ይረዳ ዘንድ ገንዘባቸውን ብቻ ሳይሆን፣ የሙያ ዕገዛ ይሰጣሉ የሚባሉ የእነሱን ሥልጡን ባለሙያዎችም በከፍተኛ ክፍያ በተለያዩ ቁልፍ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ በዕርዳታ፣ አቅም ግንባታና ትብብር ስም ያስቀምጣሉ። በገንዘብና በሰው ኃይል የታገዘውን በመንግሥት መዋቅርና አሠራር ውስጥ ያላቸውን መገኘት ተጠቅመውና ኢትዮጵያን የመሰሉ አገሮች ሁሌም የሚጋፈጡትን መዋቅራዊ ተግዳሮትና የኢኮኖሚ ቀውስ እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅመው የፖሊሲ፣ የሕግና የአሠራር ውሳኔዎች ላይ ጉልህ ተፅዕኖ ያሳድራሉ። ወሳኝ የሚባሉ አብዛኛውን ሕዝብ የሚመመለከቱ ውሳኔዎችም በእነዚህ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና መሪዎች አስተሳሰብና ፍላጎት ላይ ተመሥርተው እንዲወሰኑ ከፍተኛ ጫና ያሳድራሉ። በብዙ የአፍሪካ አገሮች ይኼ ተሳክቶላቸዋል፣ በኢትዮጵያም እየተሳካላቸው ይገኛል። ለምሳሌ በኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፍ ለውጭ ባለሀብቶች የመክፈት ሒደት ውስጥ በመገናኛ ብዙኃን የሚነገሩ የገበያ ውድድርን የሚያበረታቱና በበጎ የሚሣሉ ማስታወቂያዎች ሳይቀሩ፣ የእነዚህን ተቋማት ባርኮት ሳይቀበሉ ወደ ሕዝቡ አይደርሱም ነበር። ስለዚህም አገር በቀል የሚል ስም ቢሰጠውም አሁን የምንገኝበት የፖለቲካኢኮኖሚ የፖሊሲና የውሳኔ መስጫው ምኅዳር በሕዝብ ከተመረጠው መንግሥት እኩል ወይም በሚበልጥ መልኩ የሌሎች አካላት ፍላጎት ማስፈጸሚያ መሆኑ ልብ ማለት ግድ ይላል።

ማጠቃለያ

 የልማታዊ መንግሥት መሠረታዊ ጽንሰ ሐሳብ ለኢትዮጵያ አስፈላጊ የልማት አቅጣጫ ነው። በኢሕአዴግ የሥልጣን ዘመን የነበረውን የልማታዊነት አካሄድ ያሰናከሉትን ውስጣዊ ተቃርኖዎች ምላሽ በመስጠትና በማስተካከል መቀጠል ተገቢ ነው ብዬ አምናለው። ለዚህም የመጀመርያው መፍትሔ የሚሆነው የፖለቲካ ቡድኖችን፣ መሰባሰብናና ፉክክርን የጎንዮሽ ባለ ልዩነት (በተለይ ብሔር፣ ቋንቋና ባህልን) ዋነኛ መሠረት ያደረገው የአገሪቱ የፌደራል መዋቅርና ሥርዓታት መቀየር አለባቸው። ይህ ሲደረግ ግን በታሪክ ሒደት ውስጥ የደረሱ መድልኦና መገለሎችን ኢፍትሐዊ ግንኙነቶችን የምናቀርብበትና የምናስተካልበት ሥርዓት ሊኖረን እንደሚገባ በአጽንኦት በማሳሰብ ነው።

በመቀጠል በተለይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነጋገር ውስጥ በጉልህ የሚስተዋለው የመንግሥትን በልማት ውስጥ ያለውን የማይተካ ሚና የማናናቅና የማሳነስ አመለካከት መገራት አለበት። በየትኛው ዘመን ባለ የአገራችን የኢኮኖሚ ልማት ሒደት ውስጥ መንግሥት የአንበሳውን ድርሻ ሳይወጣ የቀረበት ዘመን የለም። በአሁኑ ዘመን የኒዮሊበራል ርዕዮተ ዓለም መፍለቂያ የሆኑት ምዕራባውያንም ቢሆኑ የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ከልክ ያለፈ ሚና ወደ ቀውስ ውስጥ ሲከታቸው ኢኮኖሚውን የሚታደገው መንግሥት ነው። ስለዚህም በእውነታው ዓለም የሌለና ተጨባጭ ያልሆነውን ዕይታ በመረጃና በዕውቀት በተደገፈ መንገድ ማረቅ ያስፈልጋል።

በመጨረሻም ኢትዮጵያን እንደ ግዙፍና ሰፊ የገበያ ዕድል ብቻ ከሚያስቧት ዓለም አቀፍ ከበርቴዎች ጋር የሚኖረንን መስተጋብር፣ እኛም ልክ እንደ እነሱ የገበያ ሒደት ቅልጥፍናንና ትርፍን ብቻ በሚያሰላ አመለካከት ልንቃኘው አይገባም። በአገራችን ውስጥ መዋቅራዊና ታሪካዊ በሆነ ሒደት የተገለሉ፣ ለኢኮኖሚያዊ ብዝበዛ በቀላሉ የተጋለጡና የሚጋለጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች እንዳሉ አውቀን ፖሊሲዎቻችን ማኅበራዊ ፍትሕንና ፍትሐዊነትን ያማከሉ መሆናቸው ልናረጋግጥ ይገባል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...