Tuesday, July 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትዓለም አቀፍ ውድድሮችን እንዳያስተናግድ የታገደው የባህር ዳር ስታዲየም

ዓለም አቀፍ ውድድሮችን እንዳያስተናግድ የታገደው የባህር ዳር ስታዲየም

ቀን:

ካፍ ለጋናው የመልስ ጨዋታ አማራጭ ፈልጉ ብሏል

 

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ላለፉት ዓመታት የብሔራዊ ቡድኖችንና የክለቦችን አኅጉራዊና ዓለም አቀፍ ውድድሮችን በብቸኝነት ሲያስተናግድ የቆየው፣ የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየምን አግዷል፡፡

በኢትዮጵያ የባህር ዳሩን ስታዲየም ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች በርካታ ስታዲየሞች ቢገነቡም፣ ካፍ አንድ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ሊኖሩት ከሚገቡ ዝቅተኛ መሥፈርት ጋር በማያያዝ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ መቆየቱ ይታወቃል፡፡

የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ዝግጅት ጋር ተያይዞ፣ በየክልሉ ከ40 እስከ 60 ሺሕና ከዚያም በላይ ተመልካቾችን ማስተናገድ የሚችሉ ስታዲየሞች-የጥራታቸው ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ-መገንባታቸው ይታወቃል፡፡

ከነዚህ ስታዲየሞች መካከል የባህር ዳሩ አንደኛው የነበረ ቢሆንም፣ ካፍ ከሌሎቹ አኳያ በገደብ ውድድሮችን እያስተናገደ ጎን ለጎን ያላሟላቸውን ግንባታዎች እንዲያሟላ በማስጠንቀቂያ ማቆየቱ ይታወቃል፡፡ እስካሁን ባለው ከባህር ዳሩ ሌላ የሁሉም ስታዲየሞች ግንባታቸው የሚገኝበት ደረጃ ለብሔረሰቦች ክብረ በዓል ፕሮግራም ማድመቂያ ካልሆነ ካፍ፣ ‹‹ዝቅተኛ መሥፈርት ብሎ ባስቀመጠው ልክ መሟላት ቀርቶ ሁሉም በነበሩበት እንደ ቆሙ ይነገራል፡፡

ከሰሞኑ የካፍ የክለብ ፈቃድ (ላይሰንሲንግ) ማናጀር መሐመድ ሲዳት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት፣ ውድድሮችን እያስተናገዱ የሚገኙ የተለያዩ ስታዲየሞችን የገመገሙ ሲሆን፣ በዋናነትም በገደብ ላይ የነበረውን የባህር ዳር ስታዲየምን ገምግመው ውጤቱን ሳይገልጹ፣ ለተመሳሳይ ምልከታ ወደ ኬንያ ናይሮቢ ማቅናታቸው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቆ ነበር፡፡

ይሁንና በካፍ ባለሙያው ግምገማ የተደረገበት የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ዕጣ ፈንታ እንዳለፉት ዓመታት በገደብና በማስጠንቀቂያ ሳይታለፍ ቀርቷል፡፡ ካፍ ስታዲየሙን በሚመለከት ጥቅምት 8 ቀን 2014 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በላከው ውሳኔ መሠረት፣ ላለፉት ዓመታት የተለያዩ የብሔራዊ ቡድኖችን ጨዋታ ጨምሮ የክለብ ውድድሮች ሲያስተናግድ የቆየው የባህር ዳር ስታዲየም፣ ከዚህ በኋላ (ከጥቅምት 8 ቀ) ጀምሮ እየተከናወነ የሚገኘውን የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታና ሌሎች ውድድሮችን እንዳያስተናግድ ማገዱን አስታውቋል፡፡

ካፍ ከውሳኔው ጎን ለጎን ኢትዮጵያ ለኳታሩ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከጋና ጋር በሜዳዋ ለምታደርገው የመርሐ ግብር ማሟያ ጨዋታ፣ ከጥቅምት 10 ቀን በፊት ጨዋታውን ማድረግ የምትፈልግበትን አገርና ስታዲየም ለካፍ በአስቸኳይ እንድታሳውቅ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ፌዴሬሽኑ በተባለው ጊዜና ወቅት የማያሳውቅ ከሆነ ግን ካፍ ጨዋታውን ወደ ተጋጣሚዋ አገር ጋና እንደሚወስድ ማሳወቁም ተነግሯል፡፡

ለስታዲየሙ መታገድ ምክንያት የሆኑት የካፍ መሥፈርቶች

የጨዋታ ሜዳውና ለጨዋታ ሜዳው አስፈላጊ የሚባሉ ግብዓቶችን ባለማሟላቱ፣ በተለይም የመጫወቻ ሜዳው ሳር ደረጃውን የጠበቀ አለመሆኑ፣ የምሽት ጨዋታዎችን ለማካሄድ መብራት ያልተገጠመለት መሆኑ፣ የሜዳ አስተዳደር በተለይም ሳሩን የሚከታተል ባለሙያ (ካምፓኒ) የሌለው መሆኑ፣ ቀደም ሲል የተተከለው የሳር ጥራት ደረጃውን ያልጠበቀ መሆኑ (ወቅቱን የሚመጥን የተፈጥሮ ሳር ሙሉ በሙሉ መቀየር ያለበት መሆኑ)፣ ተቀያሪ ተጨዋቾች የሚቀመጡበት ወንበር ደረጃውን ያልጠበቀ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

የቡድኖችና የጨዋታ አመራሮች ማረፊያን በሚመለከትም የመልበሻ ክፍሎቹና መቀመጫዎቹ ደረጃቸውን ያሟሉ አለመሆናቸው፣ በመልበሻ ቤቶቹ የሚገኙ መታጠቢያ ክፍሎች ብዛት በዓለም አቀፍ ልኬት (ስታንዳርድ) በተቀመጠው ቁጥር ልክ ሊኖር አለመቻሉ፣ በመልበሻ ክፍሉ የሚገኙ ማሟሟቂያ ቦታዎች ሰው ሠራሽ ንጣፍ ሊነጠፍባቸው አለመቻሉ፣ የዳኞች ማረፊያ ክፍሎች ደረጃቸውን ያሟሉ አለመሆናቸው በዝርዝር ተቀምጧል፡፡

የሕክምና ክፍሎችን በተመለከተም አስፈላጊ የሚባሉ ማለትም፣ አውቶማቲክ ቬንትሌተር፣ ቀላል ቀዶ ሕክምና መሥሪያ መሣሪያዎች፣ ካርዲያክ ሞኒተር፣ ዓለም አቀፍ ልኬቱን የጠበቀ አበረታች ንጥረ ነገሮች (ዶፒንግ) መቆጣጠሪያ ክፍሎች የሌሉት ከመሆኑ ባሻገር፣ የተመልካቾች መቀመጫ የለውም፡፡

ለተመልካቾች መገልገያ የሚሆን ካፍቴሪያ እንዲሁም፣ ለስታዲየሙ እሳት አደጋና የደኅንነት ብቃት የሚገልጽ ሰርተፍኬት ያለው አለመሆኑም ተነግሯል፡፡

እንግዶችና የመስተንግዶ ማቅረቢያ አገልግሎትን በተመለከተ ለክብር እንግዶች የሚሆኑ ቋሚ ከወለሉ ጋር የታሰሩ ወንበሮች፣ የክብር እንግዶች የሚቀመጡበት ቦታ፣ የኢንተርኔት አገልግሎት (ዋይፋይ)፣ ቴሌቪዥንና ሳውንድ ሲስተም፣ እንዲሁም የክብር እንግዶች መቀመጫ በመስታወት የተለየ አለመሆኑ፣ የቪአይቪና የሚዲያ መውጫው አንድ መሆን፣ እንዲሁም ለቪአይፒ ተሽከርካሪዎች ማቆሚያ ተለይቶ አለመቀመጡም ተጠቅሷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በስታዲየሙ ደረጃውን የጠበቀ የሚዲያ ማዕከል አለመኖር፣ በምሽት ልምምድ ሊያሠራ የሚችል መብራት፣ የተቀያሪ ተጨዋቾች መቀመጫ ወንበርና የመልበሻ ክፍሎች የሌለው መሆኑ፣ ሻወርና መፀዳጃ ቤት ስታዲየሙ ሊያሟላቸው ከሚገቡ ዝርዝር ውስጥ ተካትቷል፡፡

እንደ ፌዴሬሽኑ መግለጫ የካፍ ክለብ ደረጃ ማናጀሩ መሐመድ ሲዳት በኢትዮጵያ በነበራቸው የምልከታ ጊዜ ከባህር ዳር ስታዲየም በተጨማሪ የአበበ ቢቂላና የጅማ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየምን ገምግመዋል፡፡

 በግምገማው መሠረት የጅማ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ከመሥፈርቱ አንፃር፣ በርካታ መሟላት ያለባቸው ነገሮች እንዳሉት በመግለጽ፣ ወደፊት እንዲያሟላ ካፍም ወደፊት ሌላ ገምጋሚ ቡድን ልኮ የሚያረጋግጥ ስለመሆኑ ጭምር መግለጹ ተነግሯል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን በኢትዮጵያ ምንም ዓይነት ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ማድረግ የሚያስችል ሁኔታ አለመኖሩን ጭምር ካፍ አሳውቋል፡፡

በአንፃሩ ካፍ የአበበ ቢቂላ ስታዲየምን በተመለከተ ግን በዕድሜ ደረጃ የሚዘጋጁ ውድድሮችንና የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎችን በጊዜያዊነት ማስተናገድ እንደሚችል፣ ለዚህም በቅርብ ቀን ማረጋገጫ እልካለሁ ማለቱ ታውቋል፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከካፍ ውሳኔ አስቀድሞ ከኃላፊዎች ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶችን ሲያደርግ ከመቆየቱም በላይ ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ ከዚህ በፊት ‹‹ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተነጋግሬ የተጓደሉ ግንባታቸው እንዲሟሉ አደርጋለሁ፤›› ብላችሁ ነበር በሚል ብቻ፣ ብሔራዊ ተቋሙ እስከ አራት ሺሕ ዶላር ቅጣት በመክፈል ጭምር ዕገዳውን ለማዘግየት ሙከራ ሲያደርግ መቆየቱ ይናገራል፡፡

የባህር ዳር ስታዲየምን ብቻ ሳይሆን፣ ከሌሎችም  በስታዲየም መሠረተ ልማትና ግንባታ ጉዳይ በተያያዘ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መሥፈርቱ በሚሟላበት ሁኔታ ላይ ተደጋጋሚ ውይይቶችን ሲያደርግ መቆየቱን የጽሕፈት ቤት ኃላፊው አቶ ባህሩ ጥላሁን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡              

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...