Sunday, November 27, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዓለምየአፍሪካን ተጠቃሚነት እንዲያጎላ የሚጠበቀው የኮፕ 26 ጉባዔ

  የአፍሪካን ተጠቃሚነት እንዲያጎላ የሚጠበቀው የኮፕ 26 ጉባዔ

  ቀን:

  በእንግሊዝ ግላስኮው በወሩ ማብቂያ የሚጀመረውና ለ12 ቀናት የሚዘልቀው የኮፕ 26 የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ፣ አፍሪካ እየገጠማት ያለውን ፈተና እንድትወጣ ማስቻል እንደሚጠበቅበት የዘርፉ ወትዋቾች ከወዲሁ እየገለጹ ነው፡፡

  አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ምክንያት ከፍተኛውን ፈተና የተሸከመች አኅጉር ስትሆን፣ ለአየር ንብረት ለውጡ ያላት አስተዋጽኦ ደግሞ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡

  የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ማዕቀፍ (ኮፕ 26) ዓለም ከፍተኛ ሙቀት ባስመዘገበችበት ወቅት የሚካሄድ ቢሆንም፣ የዚህ ተጠቂ የሆኑትን የአፍሪካ አገሮች መታደግ የጉባዔው አቅጣጫ ሊሆን ይገባል ሲልም ዳውንቱ ኧርዝ በድረ ገጹ አስፍሯል፡፡

  በ2020 የተመዘገበው 1.02 ዲግሪ ሴልሺየስ የሙቀት መጠን ሙቀት ከሚባለው የበለጠ ሲሆን፣ እንዲህ ዓይነቱ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የተከሰተ ሙቀት ደግሞ ተፅዕኖውን አብዝቶ ያሳረፈው አፍሪካ ውስጥ ነው፡፡

  እንደ ካርበን ኦክሳይድና ሚቴን ያሉ የግሪን ሐውስ ጋዞች ለአየር ንብረት ለውጥ መከሰት ዋና ምክንያቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ጋዞች ደግሞ ከበለፀጉ አገሮች ኢንዱስትሪዎች በብዛት የሚመነጩ ቢሆንም በነዚህ ጋዞች ምክንያት ለተለያዩ ችግሮች ከተጋለጡት አኅጉሮች መካከል አፍሪካ አንዷ ስትሆን፣ የእነዚህ ጋዝ ልቀት መጠኗ ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲሰላ ከአምስት በመቶ ያነሰ ነው፡፡

  የአፍሪካን ተጠቃሚነት እንዲያጎላ የሚጠበቀው የኮፕ 26 ጉባዔ

   

  ቻይና፣ አሜሪካ፣ ህንድ፣ ሩሲያና ጃፓን የግሪን ሐውስ ጋዝ በተለይም ካርበን ዳይኦክሳይድ በመልቀቅ ቀዳሚዎቹ ሲሆኑ፣ በአየር ንብረት ለውጡ የመጎዳታቸው ምጣኔ ግን እንደ አፍሪካና ሌሎች በማደግ ላይ ያሉ አገሮች የጎላ አይደለም፡፡

  በአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጡን ለመቋቋም የገንዘብና የቴክኖሎጂ አቅም አለመኖሩና በዝናብ ላይ ከተመረኮዘ ግብርና አለመላቀቋም በአየር ንብረት ለውጡ የሚመጣውን ፈተና እንዳትመክት አድርጓታል፡፡

  በአፍሪካ የሙቀት ማየል ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ዝናብና ጎርፍ መከሰቱም የዚሁ የአየር ንብረት ለውጡ አሉታዊ ተፅዕኖ አካል ነው፡፡ በምሥራቅ አፍሪካ የተከሰተው ድርቅም የአየር ንብረት ለውጡ የፈጠረው ነው፡፡

  የዓለም ገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ከሰሃራ በታች የሚገኙ  የአፍሪካ አገሮች በአየር ንብረት ለውጡ ሳቢያ ቀጥታ ከኢኮኖሚያቸው ላይ በየዓመቱ 520 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያጡም አስታውቋል፡፡

  አኅጉሪቷ እየገጠማት ላለው ችግር ምላሽ ለመስጠት ደግሞ በየዓመቱ ከሰባት ቢሊዮን እስከ 15 ቢሊዮን ዶላር ያስወጣል፡፡

  ወጪው በ2050 በዓመት 35 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል ያለው አይኤምኤፍ፣ ይህም በ2050 አፍሪካ ከዓመታዊ አጠቃላይ ምርቷ 4.7 በመቶ እንድታጣ ያደርጋል፡፡ ሰሜን አሜሪካ በ2050 የምታጣው 1.1 በመቶ ነው፡፡

  የዘርፉ ወትዋቾችም ‹‹አፍሪካ መደመጥ አለባት፣ ጆሮ ዳባ ልበስ ልትባል አይገባም›› የሚሉትም አፍሪካ ይበልጡኑ ተጎጂ በመሆኗ ነው፡፡

  የኮፕ 26 ጉባዔ፣ የፓሪስ ስምምነትንና የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ኮንቬንሽን ማዕቀፍ ተግባራዊ እንዲሆን የሚወተውት ይሆናል ተብሎም ተጠብቋል፡፡

  እ.ኤ.አ. በ2015 የተደረሰው የፓሪስ ስምምነት የዓለም የሙቀት መጠንን ከሁለት ዲግሪ ሴልሽየስ በታች ከተቻለ ደግሞ 1.5 ዲግሪ ሴልሽየስ ለማድረግ ያለመ ነው፡፡ ስምምንቱ የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ ለሚፈልጉትም ማድረግ የሚያስችል ማዕቀፍ አለው፡፡ ያደጉ አገሮች በማደግ ላይ ላሉት አገሮች ችግሩን ተቋቁመው እንዲጓዙ መደገፍ እንዳለባቸውም ያሳያል፡፡

  ያደጉ አገሮችም በአየር ንብረት ለውጡ ተጋላጭ ለሆኑና ለተጎዱ አገሮች 100 ቢሊዮን ዶላር ለመለገስ ቃል ገብተው ነበር፡፡ ነገር ግን እስከ 2018 ድረስ ቃል ከተገባው የ20 ቢሊዮን ዶላር ክፍተት ታይቷል፡፡ ሀብታም አገሮች ይህ ክፍተት እንዴት እንደሚሞላ ያስቀመጡት አሠራር ባለመኖሩ፣ ይህ አጀንዳ አሁን ላይ መነሳትና የሀብታም አገሮች ተጠያቂነት መጉላት አለበት ሲሉም ምልከታቸውን በዳውንቱ ኧርዝ ያሰፈሩ ገልጸዋል፡፡

  የኮፕ 26 ጉባዔ የፓሪስ ስምምነት ግብ ይሳካ ዘንድ ስትራቴጂ ያስቀምጣል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የአፍሪካ አገሮች ተወካዮች አጀንዳውን ለማስቀመጥ ዕድላቸውን መጠቀም ይጠበቅባቸዋል፡፡

  የአሜሪካ የአየር ንብረት ልዑክ ጆን ኬሪ እንደሚሉትም፣ በግላስኮ የሚካሄደው ኮፕ 26 የአየር ንብረት ጉባዔን ‹‹ዓለም በጋራ ዕርምጃ ለመውሰድ የመጨረሻው ተስፋ ነው›› ብለውታል፡፡

  ቢቢሲ ሚስተር ኬሪን ጠቅሶ እንዳሰፈረው፣ አደገኛ የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥን ለመገደብ ቁልፍ አገሮች የአየር ንብረት ለውጥ የሚመክት ፖሊሲ መከተል አለባቸው፡፡

  በቀጣዮቹ ዘጠኝ ዓመታት የግሪን ሐውስ ጋዝ ትነት ካልቀነሰ የረዥም ጊዜ ዕቅዶችን ማሳካት እንደማይቻልም ገልጸዋል፡፡

  የፓሪሱ ስምምነት የዓለም የሙቀት መጠንን 1.5 ዲግሪ ሴልሽየስ ላይ ማቆም ሲሆን፣ ሳይንቲስቶች እዚህ ለመድረስ በዓለም እየተለቀቀ ያለውን የካርበን መጠን በ2010 ከነበረው በቀጣይ አሥር ዓመት ውስጥ 45 በመቶ መቀነስ አለበት ይላሉ፡፡ ሆኖም የካርበን ልቀቱ አሁንም እየጨመረና በተለይም የአፍሪካ አገሮችን እየጎዳ ይገኛል፡፡

  በኮፕ 26 ጉባዔ አገሮች በ2030 የጋዝ ልቀታቸውን ለመቀነስ የሚያስችል ዕቅድ ይዘው እንዲቀርቡም ተጠይቋል፡፡ አንዳንድ አገሮች ደግሞ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀልበስ የኤሌክትሪክ መኪና መጠቀም ጀምረዋል፡፡ የደን ጭፍጨፋና የከሰል ኃይልን የቀነሱም ይገኛሉ፡፡

  መሪዎችን ጨምሮ 25 ሺሕ ያህል በሚታደሙበት የግላስኮው ኮፕ 26 ጉባዔ፣ ተቃውሞ አድራጊዎችም ቅሬታቸውን ያሰማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...