Sunday, January 29, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

አዲሱ መንግሥት አዲስ ምዕራፍ ብሎ የሰየመው ምርጫውን ስላሸነፈ ወይስ ለአገሪቷ ዘመን ተሻጋሪ ሥራ ለመሥራት?

በበላይ ወልደየስ (ፕሮፌሰር)

አንባቢያን ምናልባት ዘግናኝ ነገር ለማንበብ ካልፈለጋችሁ፣ ይኼንን አንቀጽ (Paragraph) ሳታነቡ ወደሚቀጥለው እንድትሄዱ እጠይቃለሁ፡፡ ባለፈው 27 ዓመት በተተከለው የብሔር (Tribe)/የጎሳ (Clan) ፖለቲካ ወገን ተለይቶ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ላለፉት ሦስት ዓመታት የእርስ በርስ ብጥብጥና ጦርነት ተካሄደ፡፡ በወሬ እንደሰማነውና በምሥል  እንዳየነው፣ በሒደቱ ዘግናኝ የሆኑ ድርጊቶች ተፈጽመዋል፡፡ መላ ቤተሰብ በር ተዘግቶባቸው፣ ሕፃናት እያለቀሱ ከነሕይወታቸው ተቃጥለዋል፡፡ አዛውንቶች በመጦሪያቸው ጊዜ ሙሉ ዕድሜያቸውን በኖሩበት ቀዬ መጤ ተብለው ከነሕይወታቸው በእሳት ጋይተዋል፡፡ ባልና ሚስት የፊጥኝ ታስረው ተረሸነዋል፡፡ እርጉዝ ሴት፣ ያረገዝሺው የእኔ ብሔር አይደለም በማለት፣ በሳንጃ ሽሉን በመውጋት ተገድላለች፡፡ ሰውን ከነሕይወቱ የቁልቁል በመሰቀል ተስቅሏል፡፡ በጦርነቱ መሸነፋቸውን ያወቁ ወታደሮች ነብሳቸውን ሊያድኑ ሲሮጡ፣ የትነው የምትሸሹት በማለት በመትረየስ ተረፍርፈዋል፡፡ የተማረኩትን ምርኮኞች፣ ከዓለም አቀፍ ሕግ ውጪ፣ ጥይት አናጠፋም በማለት፣ በሲኖ ትራክ ተጋድመው ተደፍጥጠዋል፡፡ የሞተን አለቃቸውን ማንነቱን እንዳይታወቅ የሬሳውን አንገት በመቁረጥ፣ በተለያየ ቦታ ቀብረዋል፡፡ ተዋጊዎች ከተማ ሲገቡ፣ ሴቶችን በልጆቻቸው ፊት የብዙኃን ግንኙነት (Gang Rape) አካሂደዋል፡፡ ባልን አስረው፣ ባለቤቱን በፊት ለፊት ተገናኝተዋል/ደፍረዋል በየቤቱ እየገቡ ንብረት ዘርፈዋል፡፡ ትምህርት ቤቶችን ሐኪም ቤቶችን፣ ያስተዳድር ጽሕፈት ቤቶችን ከእነ ግለሰብ መረጃ፣ የሚዘረፈው ተዘርፎ አቃጥለዋል፡፡ ወታደር የሚሆን ሲጠፋ፣ ሕፃናትን ጦርነት ላይ በማሠለፍ አስጨርሰዋል፡፡ በአጠቃላይ ባለፉት ሦስት ዓመታት፣ ከሰው ድርጊቶቸ ውጪ፣ አረመኔነት በተሞላው፣ የ21ኛውን ክፍለ ዘመን አኗኗር በማይመጥን፣ በጋርዮሽ ዘመን እንደነበረው አካሄድ ለጆሮ የሚቀፍ ከፍተኛ ጭካኔ በአገራችን ተካሂዷል፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን እንደዚህ ነን እንዴ ብለን መልስ የሌለው ጥያቄ እንድናነሳ ተገድደናል፡፡ በሰብዓዊነታችን ላይ የኃፍረት ማቅ አጠለቅን፡፡ ለአፍሪካውያን ወንድሞቻችን፣ እኛን እንደ ተምሳሌት የሚያዩን፣ በጠበቁበት ቦታ ሳይሆን፣ አንሰን ተገኝተናል፡፡

አገራችን በፖለቲካ ችግር ምክንያት፣ ክብሯ ወድቆ፣ የዓለም የመጥፎ ነገር አጀንዳ ምሳሌ ሆና፣ እንዳትጠፋ፣ እያንዳንዳችን ኃላፊነት አለብን፡፡ ዝም ብለን ማየት የለብንም፡፡ እኔም ይኼ ነገር ዞሮ ዞሮ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ አገራችንን ይከታል ብዬ በመሥጋት፣ የማንኛውም ፖለቲካ ፓርቲ አባል ባልሆንም፣ ኃላፊነት ስለተሰማኝ፣ ከሙያዬ ውጪ መጋረጃውን ቀድጄ፣ አገሪቱ የገጠማትን ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ችግሮች በመዘርዘር፣ መፍትሔ ይሆናል ያልኩትን ሐሳብ በዚህ ጽሑፍ ላይ እንዳቀርብ የተገደድኩት፡፡ እናንተም ይኼንን ጽሑፍ የምታነቡ ምሁራን፣ ፖለቲከኞች፣ የሚዲያ ሰዎች፣ የሲቪክ ማኅበራት ወዘተ. ጽሑፉን፣ ለሌሎችም አጋርታችሁ፣ የእኔን ፈለግ በመከተል፣ በአገራችን ችግር ላይ ለመወያየት አጀንዳ እንቅረፅ፡፡ ለመወያየትም እንነሳ፡፡ የሚበጀውንም መንግሥት ሕዝቡን አወያይቶ፣ እንዲያስፈጽም ግፊት እናድርግ፡፡ ችግሩን ለመፍታት ጊዜው አሁን ነው፡፡

መግቢያ   

በመጀመርያ ኢትዮጵያ ገጠማትን ችግር ለማስወገድ፣ ሕጋዊ ሥልጣን በምርጫ ይዤ እሠራለሁ ብሎ ያለውን መንግሥት ለውጥ የማይፈልጉ ጽንፈኛ ብሔርተኞችና አንዳንድ አገሮች፣ ምርጫው እንዳይደረግና መንግሥቱ ሕጋዊ እንዳይሆን፣ ያደረጉት የሞት ሽረት ትግል ሕዝቡ ውድቅ አድርጎ በመምረጡና በማክሸፉ፣ ‹‹እንኳን ደስ አለን›› እላለሁ፡፡ ደስታዬን የምገልጸው፣ ምርጫው አንድ ምርጫ ማሟላት የሚገባውን ይዞ፣ ወደ መደበኛ ደረጃ የተጠጋ ውጤት አምጥቷል ብዬ አይደለም፡፡ ብዙም እንደሚቀሩት እገምት ነበር፡፡ ውጤቱም አሁኑ የተገለጸው እንደሚሆን እጠብቅ ነበር፡፡ ሕዝቡም ቢሆን፣ ይኼንን የምርጫ ውጤት በፀጋ የተቀበለው፣ ያሰበው ስለተሳካለት ሳይሆን፣ ጽንፈኛ ብርተኞች ‹‹ያለው መንግሥት ጊዜው አልፎበታል፡፡ ጊዜያዊ መንግሥት ይቋቋም›› ብለው በአቋራጭ ሥልጣን በመያዝ፣ የእርስ በርስ ጦርነትን ከማስፋፋታቸውና አገሪቷን ከመበተናቸው በፊት፣ መንግሥት አቋቁሜ ለአዲሱ መንግሥት አገሪቷ ከገባችበት አረንቋ እንዲያወጣ ዕድል ልስጠው ብሎ ነው፡፡

በሕዝቡ የተመረጠው መንግሥትም ይኼንን እውነት ‹‹አዲስ ምዕራፍ›› ብሎ ሰየመው፡፡ እንግዲህ ይኼን ስያሜ መንግሥት የሰጠው በአሁኑ ጊዜ የተካሄደውን ጦርነት ማዳከምና ከውጪ ያሉትን ተፅዕኖዎች ማርገብ መቻሉ ብቻ ‹‹አዲስ ምዕራፍ››  ያሰኛል ብሎ ከሆነ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሚጠብቀው ሁኔታ በቂ አይደለም፡፡ ከዚህ በፊትም አፄ ኃይለ ሥላሴ ከስደት ሲመለሱ፣ ተመሳሳይ ቃላት ‹‹ለኢትዮጵያ አዲስ ዘመን›› ብለው ነበር፡፡ ንጉሡ በኋላ እንደታየው ‹‹አዲስ ዘመን›› ያሉት ከስደት ተመልሰው ሥልጣን እንደገና መያዛቸውን እንጂ፣ የፖለቲካ ለውጥ አድርገው አገሪቷን ዘመን ተሻጋሪ ለማድረግ አልነበረም፡፡ ይኼንንም ባለማድረጋቸው ከሠላሳ ዓመታት በኋላ በፋሺስት ደርግ ተገድለው አሁን ለምንገኝበት ውጥንቅጥ ሁኔታ እርሾ ጥለውልን ሄዱ፡፡

ስለዚህ ‹‹አዲስ ምዕራፍ››ን አሁን የገጠመንን ጦርነትና የውጭ ተፅዕኖ ብቻ ለማሸነፍ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያን እስከ ወዲያኛው የሚያሻግር የፖለቲካ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ችግሮችን በመቅረፍ በየአሥር ዓመታት እንደ አዙሪት እየተሽከረከረ የሚያስቸግረንን ጦርነትና ሁከት የሚያስቆም ሥርዓት ዘርግተን አስተማማኝ ሕግ የሚከበርባት ኢትዮጵያን ለመመሥረት የምንጀምርበት ነው ብለን ብንቀበል ሊያስማማን ይችላል፡፡ አለበለዚያ አባባሉ እርባና ቢስ ሆኖ ለታሪክ ይቀራል፡፡

ከሦስት ዓመት በፊት ንቅናቄውን አስተባብረው የመንግሥቱ መሪ የሆኑት ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከመምጣታቸው በፊት በሕዝቡ አምብዛም አይታወቁም ነበር፡፡ እሳቸውን ሕዝቡ ያወቃቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ሹመታቸው ፀድቆ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ከመቀመጫ የሚያስነሳ ውብ ቃላትን ባደረጉበት ወቅት ነው፡፡ ሕዝቡም ‹‹ሆ›› ብሎ ‹‹ኢትዮጵያን ከብሔር (Tribe) ፖለቲካ አውጥቶ ያልተከፋፈለች አገር የሚያደርግ፣ ዓለም በሚጓዝበት ዜጋ ተኮር የሚያሻግር፣ ሁሉም ዜጋ እኩል በደስታ የሚኖርባት፣ አንዲት ጠንካራ አስተማማኝ ኢትዮጵያን የሚመሠርት፣ ወዘተ መሪ ሊሆን ይችላል›› በማለት ቆሞ በማክበር የተቀበላቸው፡፡ በምርጫውም ላይ እሳቸውን በማየት ድምፅ ሰጠ፡፡ በዚሁ ጋዜጣ በአንድ ወቅት ኢትዮጵያ ዘመን ተሻጋሪ መሪ አላጋጠማትም ብዬ ጽፌ ነበር፡፡  ዶ/ር ዓብይ ኢትዮጵያ ያለባትን ችግር ቀራርፈውና አስወግደው አስተማማኝ ኢትዮጵያን በመመሥረት ዘመን ተሻጋሪ ሊያደርጓት ከፈለጉ እንደሚችሉ ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል፡፡ የአገራችን ችግር ምንጩ የብሔር ፖለቲካ ስለሆነ፣ ዶ/ር ዓብይም ራሳቸውን ከብሔር አፅድተው/አውጥተው፣ በአካባቢያቸው ያሉትን የብሔር አቀንቃኞች ለውጠው/አፅድተው፣ በብሔር የፖለቲካ ሥልጣን መያዝን ካስወገዱ፣ ዘመን የምትሻገር ኢትዮጵያን መመሥረቱ ይቀላቸዋል፡፡ ይኼንን ለማድረግ ግን ዶ/ር ዓብይ በቆራጥነትና በፍጥነት መንቀሳቀስ አለባቸው፡፡ ብረት በትኩሱ ነው እንደሚባለው፣ ፖለቲካም ዛሬ ነው፣ ነገ ሊረፍድ ይችላል፡፡  

የኢትዮጵያ ችግሮች ብዙ ቢሆኑም፣ መሠረታቸው የብሔር (Tribe) የጎሳ (Clan) ፖለቲካ ሲሆን፣ ከዚህ ጋራ በቀጥታም ይሁን በሌላ ችግሮቹ እየተፈለፈሉ፣ የሕዝቡን ደም በማፋሰስ አገሪቷን ዞሮ እምቦጭ እያደረጉ ያለመረጋጋት ፈጥረዋል፡፡ በዚህ ጽሑፌ ላይ፣ በእኔ ዕይታ ዋና ዋና መቀየር የሚገባቸውን ችግሮች ለማንሳት እሞክራለሁ፡፡ እዚህ ላይ መጤን ያለበት እነዚህንም ሆነ ሌሎች ችግሮች በሙሉ ላንዴም ለመጨረሻም አሁን ቀይረን ዘመን ተሸጋሪ አስተማማኝ ኢትዮጵያን መፍጠር ካልቻልን፣ ከፊሎቹን ችግሮች ብንተዋቸው፣ ለጊዜው ዕፎይታ ይሰጠን ይሆናል እንጂ፣ ችግሮቹ ተመልሰው መምጣታቸውና ደም በማፋሰስ፣ ልማቱን በማውደም አገሪቷን  ወደ ኋላ መጎተታቸው አይቀርም፡፡

መቀየር ያለባቸው የኢትዮጵያ ችግሮች

ሕገ መንግሥት

ኢትዮጵያ የተወሰኑ ብሔሮች ፈቅደው የመሠረቱዋት የብሔር ብሔረሰብ አገር ናት በማለት፣ ሕገ መንግሥቱ የዜጋን መብት የሆነውን ኢትዮጵያዊነትን ደፍጥጦ፣ የኅብረተሰብ መብት ያረጋግጣል በሚል ብዙዎቹ ይከሳሉ፡፡ በዚህም ብቻ ሳይወሰኑ ሕገ መንግሥቱ ብሔሮች ለየብቻቸው አጥር አጥረው እንዲቀመጡ መብት ሰጥቶ፣ አገር በቅርጫ እንዲከፋፈል በር በመክፈት፣ ብሔሮች በኢትዮጵያ ውስጥ ተካተው ለመኖር ካልፈለጉ በሕዝብ ውሳኔ፣ የየራሳቸውን መንግሥት ሊመሠርቱ እንደሚችሉ በመፍቀድ ኢትዮጵያ ሁሌም ደካማ ሆና የመበታተን አደጋ እንዲጋለጥባት ያበረታታል በማለት ይከሱታል፡፡ አንዳንድ ወገኖች ሕገ መንግሥቱ የአገሪቷን መከላከያ ሠራዊት በጥቂት ብሔሮች እንዲዋቀር በማድረግ፣ አገሪቱን ከማዳከሙም በላይ፣ ወገንተኛነት የተሞላው ክልላዊ ታጣቂ እንዲቋቋም ይፈቅዳል በማለት ሕገ መንግሥቱ መሻሻል እንዳለበት ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ አሁን ለገባችበት መበታተን አረንቋ፣ ሕገ መንግሥቱ ዜጋ ተኮር ላይ በመመሥረት፣ ሰው በሰውነቱ ብቻ  ሰብዓዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መብቱ የሚያስከብር ሆኖ ሕገ መንግሥቱ እንደገና መቀረፅ መሻሻል አለበት፡፡

የብሔር ፖለቲካ

ኢትዮጵያ ከ80 በላይ ብሮችና ጎሳዎች ያሉባት አገር ስትሆን፣ ሁሉም ዜጋ ቢያንስ ከአንድ ብር ወይም ጎሳ የወጣ ነው፡፡ እነዚህም ብሮችና ጎሳዎች ተዋልደው ለዘመናት አብረው ተሳስረው ኑረዋል፡፡ በአገሪቱ የቅርብ ጊዜ ታሪክም ቢሆን አንዱ ብሔር በሌላው ብሔር ላይ ጦርነት አድርጎ፣ ንብረቱን የቀማበት ሁኔታ አልተከሰተም፡፡ ብዙ ጊዜ የነበረው በአጎራባች ጎሳዎች መካከል ለሳር ግጦሽ ፍለጋ፣ ወይም የአንዱ ጎሳ ሸፍቶች ከብት በመዝረፍ፣ ሴቶችን በመጥለፍ፣ አንዳንዴም ሕፃናትን በመውሰድ፣ ወዘተ. የሚደረጉ ጦርነቶች ነበሩ፡፡ እነዚህንም ጦርነቶች ወዲያው የየጎሳዎቹ መሪዎች ተቀምጠው በዳይን እንዲክስ በማድረግ ዕርቅ እንዲወርድ በማድረግ ያስቆሙ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ከመቶ ዓመት በፊት መሳፍንትና ባለሀብቶች ግዛታቸውን ለማስፋፋት ብቻ ከብሔር ውጪ፣ በሌላው አካባቢ ውጊያ በመክፈት ሕዝቡን ሲያጫርሱ እንደ ነበር ታሪክ የሚመዘግበው አለ፡፡

በታሪኩ ውስጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ የኖረው፣ በኢትዮጵያ ጥላ ሥር ሆኖ የወጣበትን  ብሔረሰብ  ለማሳወቅ፣ ራሱን ወሎዬ፣  ጎጃሜ፣  ጎንደሬ፣ ጆሌ አርሲ፣ ጆሌ ባሌ፣ ተንቤን፣ ዓድዋ፣ አክሱም፣ ጉራጌ፣ ሲዳማ፣ ወላይታና ጎፋ ወዘተ. ነኝ እያለ በመጥራት ነበር እንጂ በቋንቋ በማሰባሰብ በብሔር ተከልሎ አልነበረም፡፡ አሁን ፖለቲከኞች ብሔር ብለው ያካለሉት ክልል ከ27 ዓመት በኋላ የመጣ አከላለል እንጂ ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ታይቶ አይታወቅም፡፡ በምን መሥፈርት እንደከለሉት እንኳ ማስተማመኛ ማስረጂያ አያቀርቡም፡፡ የሚናገሩት በባህል/ትውፊትና በቋንቋ አንድ የሆኑትን ሕዝቦች በማሰባሰብ ነው የሚሉት፡፡ ይኼ አባባል ውኃ አይደፋም፡፡  በባህል ሊሆን አይችልም፡፡ ለምሳሌ የወለጋ፣ የባሌ፣ የቦረናና የሰላሌ ሕዝቦች የተለያየ ትውፊት እንዳላቸው በቀላሉ ማየት ይቻላል፡፡ አንድ ቋንቋ በመናገራቸውም የግድ በአንድ ክልል ይሰባሰቡ ሊባል አይቻልም፡፡ በውስጣቸው ከክልሉ ቋንቋ በላይ ሌላ ቋንቋ የሚናገሩ ሕዝቦች ሊኖሩ ከመቻሉም በላይ ብዙ አገሮች አንድ ቋንቋ በመናገራቸው በአንድ አገር ተሰባስበው አልመሠረቱም፡፡ ለምሳሌ አካባቢያችን ስዋህሊኛ ቋንቋ ከአምስት በበለጡ የተለያዩ አገሮች ይነገራል፡፡ ግን አንድ አገር አይደሉም፡፡

ስለዚህ እነዚህ አክራሪ ብሔርተኞች አከላላቸው በባህልና በቋንቋ አሰባስበው የፈጠሩት ክልል፣ ሳይሆን እነሱ ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ውጭ ሥዕል ስለው የፈጠሩት  ብሔር ነው፡፡ ለዚህ ምሳሌ እንዲሆን የ1977 ዓመቱ ድርቅ ጊዜ ደርግ በከፍተኛ ደረጃ በድርቅ የተጎዱትን ሕዝቦች በማንሳት፣ ድርቅ ባልደረሰባቸው፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ወስዶ አሠፈረ፡፡ ከዩኒቨርሲቲ የዘመትን ሁኔታውን እናውቀዋለን፡፡ ደርግ ሠፋሪዎችን በሁለት ዓይነት ቦታዎች ማለት፣ ገበሬዎች ውስጥ በሚገኝ ክፍት ቦታ ‹‹በመሠግሠግና ሰው ባልሠፈረበት/በማይኖርበት ሰፋፊ ቦታዎች ‹‹ሠፈራ›› በሚባል እንዲሠፍሩ ተደረገ፡፡ እነዚህ ሠፋሪዎች ልጆች አፍርተው የአካባቢውን ባህልና አኗኗር ተቀብለው ኖረው አልፈዋል፡፡ የእነዚህ ሠፋሪ አብዛኞቹ ልጆችም የአካባቢውን ቋንቋ የአፍ መፍቻ በማድረግ ሌላ ቋንቋና ባህል ሳይኖራቸው፣ ከአካባቢው ኅብረተሰብ ተጋብተው፣ የሚኖሩበትን ቦታ የትውልድ አገሬ ብለው የሚኖሩ ናቸው፡፡ ከእነዚህም በምሳሌነት አንዱ ሠፋሪዎችን በመሠግሰግ ከተካሄደባቸው ቦታዎች አንደኛው ወለጋ ነበር፡፡ እነዚህም ሠፋሪዎች አክራሪ ብሔርተኞች ያወጡትን ሁለቱንም መሥፈርቶች ያሟላሉ፡፡ የዚያው አካባቢ የሚኖሩ የብሔሩ ተወላጅ መባል ነበረባቸው፡፡ አክራሪ ብሔረተኞች ግን እነዚህን የሠፋሪዎች ልጆችና ጎልማሶች መጤ ናችሁ፣ ወደ መጣችሁበት ተመለሱ ብለው አፈናቀሉ፣ አንዳንዶችንም ሕፃናትንና ሴቶችን ጭምር በጭካኔ ገደሉዋቸው፡፡ እዚህ ላይ መጤን ያለበት፣ እነዚህ ተፈናቃዮች፣ አያቶቻቸውና አባቶቻቸው ከዚያ መጣን ብለው ከነገሩዋቸው በስተቀር ሂዱ የተባለበት ቦታ የት እንደሆነና ቋንቋው ምን እንደሆን አያውቁትም፡፡ በቴሌቪዥን ቀርበው በአካባቢው ቋንቋ ያስረዱትም ይኼንኑ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ነው በሁሉም የኢትዮጵያ ግዛት በብሔር ክልል የተሸነሸነው፡፡  የሚገርመውም ራሳቸው አክራሪ ብሔርተኞቹም ቢሆኑ ቅም አያታቸው አዚያ አካባቢ እንዳልኖረ በታሪክ ያውቁታል፣ ምክንያቱም ቢባል ከክፍለ ዘመናት በፊት፣ በየቦታው በኢትዮጵያ የነገዶች ፍልሰት ተካሂዶ ነበር፡፡                        

እንግዲህ እነዚህ አክራሪ ብሔርተኞቹ ሁኔታው እንደዚህ ባለበት ሁኔታ የግል ጥቅማቸውን ለማካበት አንድ የሆነውን ሕዝብ፣ ከላይ ባየነው በተዛባ ሁኔታ ባህልና ቋንቋን መሠረት በማድረግ በብሔር ስም የተደራጀ የአካባቢ መንግሥታት ፈጠሩ፡፡ እነዚህም መንግሥታት በአንድ አካባቢ አብሮ ተዋልዶ የነበረውን ማኅበረሰብ፣  የእኔና መጤ በማለት፣ አንዱ በይ ሌላው ተመልካች ሆኖ የተዛባ ኢኮኖሚ በመፍጠርና አድሏዊ አስተዳደር (አፓርታይድ) በመመሥረት በልዩነት እንዲኖር አደረጉ፡፡ በዚህም አገሪቷን በዓለም ላይ የጠፋውን የብሔር አገዛዝ አስተዳደር የምታራምድ ብቸኛ አገር ሆና እንድትሠለፍ አደረጓት፡፡ በብሔር ላይ የተመሠረተ አስተዳደርም ውጤት የሆነው በዋነኝነት በአንድ በኩል በክልሉ የሚኖሩትን የብሔሩ ተወላጅ አይደላችሁም የሚሏቸውን መጤ በማለት ያፈሩትን ገንዘብ መውሰድ ሲሆን፣ በሌላ በኩል አጎራባች ክልሎችን መሬት ፍለጋ ጦርነት መለኮሰ ነው፡፡ በአጠቃላይ በብሔር ክልል መሥርቶ መተዳደር ትርፉ አገሪቷ ታምሳ፣ መረጋጋት ማጣትና የዕድገት ጭላንጭል ስታይ መልሳ እያወደመችው አዙሪት ውስጥ መሽከርከር ነው፡፡ ስለዚህ እኛ ኢትዮጵያውያን በብሔር መደራጀት ያመጣውን ጣጣ በደንብ የተመለከትን ስለሆነ፣ ወደፊት በሰላም ለመኖር በብሔር ፓርቲ መሥርቶ ሥልጣን መያዝን በሕግ እንዲቀር መወትወትና መታገል አለብን፡፡ እዚህ ላይ አስረግጦ መናገር የሚገባው ማንኛውም ዜጋ በብሔሩም ሆነ በጎሳው ተደራጅቶ ባህሉን ማክበር፣ በአፍ ቋንቋው መማር፣ ቋንቋውን ማስፋፋት ወዘተ. የማይገረሰስ መብቱ ሲሆን፣ በብሔር ተደራጅቶ ሥልጣን መያዝ ግን፣ እኩልነትንና ፍትሕነትን ስለሚያሳጣ መከልከል አለበት፡፡ በብሔር አካባቢ የተሰበሰቡት የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሁሉንም በሚያቅፍ የኢትዮጵያ ፓርቲ ገብተው፣ ለሥልጣን መፎካከር አለባቸው፡፡ ይኼንን እንደ መርሕ በመውሰድ፣ የብሔር ፖለቲካ/ፓርቲ ከኢትዮጵያ እንዲጠፋ በሕግ መከልከል አለበት፡፡

አስተዳደራዊ  አወቃቀር

አሁን በብሔር ከፋፍሎ የተዘረጋው አስተዳደር ሀብትን ለጥቂት ቡድኖች ከመስጠት የተለየ መዋዕለ ንዋያቸውን አፍስሰው ልማት ለሚተክሉ አስቸጋሪ ነው የሆነው፡፡ በአካባቢው የተወለደ ብሔርህ ነው የተባለ ተወላጅ የእኔ መሬት ነውና በእኔ ቦታ ነው አንተ ንጥረ ነገር የምታወጣው ወዘተ. በማለት ምንም ሳይሠራ ገንዘብ ለማግኘት አምባ ጓሮ ሲፈጥር ካመረረም ሲገድል ታይቷል፡፡ ይህም አስተዳደር እንግዲህ ነዋሪዎችን በሁለት በመክፈል በኢኮኖሚ የመጠቀም ፍትሐዊነትን አጉድሏል፡፡ በተጨማሪም በሰፋፊ ክልል አስተዳደር መመሥረቱ፣ ኅብረተሰቡ ግልጋሎትን ለማግኘት፣ በመቶዎች ኪሎ ሜትር መጓዝ ግድ ከመሆኑም በላይ መሠረተ ልማቶችን ለማስፋፋት ከፍተኛ ወጪን በመጠየቁ ብዙ አካባቢዎች እንዳይለሙ ሆነዋል፡፡ የአስተዳደር ማዕከሉ ራቅ በማለቱ፣ ሽፍታ፣ ቀማኛና የጎበዝ አለቃ በማንአለብኝነት በሕዝቡ ላይ እየጨፈሩ ነው ያሉት፡፡ ስለዚህ አሁን ያለው የክልል አስተዳደር ለልማት አመቺ ስላይደል አዲስ ለልማት አመቺ የሆነ አስተዳደራዊ  አወቃቀር መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡

በብሔራዊ ቋንቋ ላይ የተነሳው ጭቅጭቅ

ሁሉም በአፍ ቋንቋው መማር፣ ባህሉንና ሃይማኖቱን ማክበር ፍትሕ ማግኘት ወዘተ. ብሎም አካባቢውን ማስተዳደር፣ ማንም የሚቸግረው አይደለም፡፡ ሰብዓዊ መብቱ ነው፡፡ ችግር ያለው ኢትዮጵያ ብዙ ቋንቋ የሚናገሩ ሕዝቦች አገር ስትሆን፣ ይኼም ጌጧ ነው እንዴት ሁሉንም አስተዳደደር የሚያገናኝ ብሔራዊ ቋንቋ ይኑር ነው፡፡ እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት፣ ከእኛ የበለጡ ብዙ አገሮች የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪ አገሮች እንዳሉ ነው፡፡ እነዚህም አገሮች የተለያዩ ቋንቋዎችና ክልላዊ አስተዳደሮች ዘርግተው በማዕከላዊ መንግሥት ይተዳደራሉ፡፡ ብሔራዊ ቋንቋ ያደረጉት ሁሉንም የሚያማክል ቋንቋ ፈልገው በውይይት ነው፡፡ ለምሳሌ ሕንድ በእንግሊዝ ስለተዳደሩ፣ ዋናው ሁሉንም የሚያማክለው እንግሊዝኛ በመሆኑ፣ ዋናው ብሔራዊ ቋንቋቸው እንግሊዝኛ ሆነ፡፡ በተመሳሳይ ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጄሪያ እንግሊዝኛን ዋና ብሔራዊ ቋንቋ አድርገዋል፡፡ እኛ አገርም በሁሉም ሕገ መንግሥት አማርኛን ብሔራዊ ቋንቋ አድርጎ ተቀብሎት በአሁኑ ጊዜ በሁሉም ክልሎች፣ ከክልልና ከፌዴራል መንግሥት ጋራ የሥራ ቋንቋ ሆኖ እየተሠራበት ነው፡፡ እዚህ ላይ የአማርኛ ስም ከብሔረ አማራ ጋራ ምንም የሚያገኛኘው ነገር የለም፡፡ የአማርኛ ቋንቋ መጠቀም የተጀመረው ከ600 ዓመታት በፊት፣ ከነበሩት የዛጉዌና ሰለሞናዊ ሥርወ መንግሥት ውስጥ የነበሩ ሠራዊቶች፣ ለሚስጥር መገልገያ የሚሆን ከየነገዱ ደባልቀው የፈጠሩት ቋንቋ በመገልገል ነው፡፡ ይኼም ቋንቋ፣ በአጋጣሚም ሆነ፣ ሆን ተብሎ፣ አማርኛ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የመንግሥት ቋንቋ በመሆን፣ ሁሉም በኢትዮጵያ ክልል ለመስፋፋት ተሞክሯል፡፡ በቅርቡም እንኳ በአፄ ዮሐንስ ዘመን፣ አፄ ዮሐንስ መቀሌ ላይ ሆነው ኢትዮጵያን ሲያስተዳድሩ የሚጠቀሙት የሥራ ቋንቋ አማርኛ ነበር፡፡

በአሁኑ ጊዜ በተለይ የኦሮሞ ብሔርተኞች፣ በተሳሳተ ትርክት አማርኛን ከአማራ ብሔር ጋራ በማያያዝ፣ ቋንቋውን ላለመጠቀም እያንገራገሩ ከመሆንም በላይ በትምህርት ቤት ተማሪዎች አማርኛ እንዳይማሩ፣ ትውልድን እያበላሹ ነው፡፡ አንድ ምሳሌ እኔ ያጋጠመኝን ብናገር፣ ከኦሮሚያ የመጣ የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪየ፣ በትምህርቱ በዩኒቨርሲቲው ለመቀጠል እንዲችል ማመልከቻ አስገባ አልኩት፡፡ የዩኒቨርሲቲው የሥራ ቋንቋ እንግሊዝኛ ስለሆነ፣ እንዲጽፍ የጠየቅኩት በዚሁ ነበር፡፡ ይኼንን እንደማይችል ሲገልጽልኝ፣ እንግዲያውስ በአማርኛ አስገባ አልኩት፡፡ ‹‹አሱ ይብሳል›› ነበር መልሱ፡፡ ይኼ በየቀኑ የሚታይ ክስተት ነው፡፡ እንግዲህ ወንድሞቻችን የኦሮሞ ተወላጆች፣ በኦሮሚያ ትምህርት ቤት ከኦሮምኛ ቋንቋ ጎን ለጎን ተማሪዎች አማርኛን እንዲማሩ ካልፈቀዱ፣ በሌላው የኢትዮጵያ ክልል እንዴት ሊግባቡና ሥራ ሊሠሩ ይችላሉ፡፡ ይኼ አሠራር የኦሮሞን ወጣት ጥቅም ማሳጣት ብቻ ሳይሆን ትውልድንም መበደል ነው፡፡

አንዳንድ ጽንፈኛ ብሔርተኞች የሚታገሉት ‹‹ቋንቋቸውን ብሔራዊ ቋንቋ ለማድረግ፣ አማርኛን ለማዳከም ወይም ለማጥፋት›› ነው፡፡ ሁሉም ቋንቋውን ለማሳደግ መጣሩ ጥሩ ነው የሚደገፍም ነው፡፡ መታወቅ ያለበት ቋንቋ በቀላሉ የሚስፋፋው ጥቅምን እንደሚሰጥ ታውቆ ፍላጎት ሲያድግ ነው፣ እንጂ አንዱን ቋንቋ አዳክሜ፣ የራሴን በግድ እጭናለሁ በማለት አይደለም፡፡ ይኼ በፍፁም አይሠራም፡፡ ስለዚህ በብሔራዊ ቋንቋ ላይ ጭቅጭቅ የተነሳው ከነባራዊው ሁኔታ ውጪ ስለሆነ፣ አማርኛ ቋንቋን ብቸኛው ሁሉንም ክልሎች የሚያስማማ መሆኑን ተቀብለን፣ በሁሉም ክልል ከትምህርት ቤት ጀምሮ የሚስፋፋበትን ዕቅድ፣ በመጪው መንግሥት መኖሩን በዘላቂ ሕግ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡

ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማና የሕዝብ መዝሙር የተነሳው ጭቅጭቅ

የኢትዮጵያ መንግሥት የአገሪቱ መለያ አድርጎ የሚጠቀምበት ሰንደቅ ዓላማ/ባንዲራ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለም ማውለብለብ ከተጀመረ በሺዎች ዓመታት እንደሚበልጥ ይነገራል፡፡ ምኒልክ ያመጡት እንዳልሆነ፣ ማረጋገጫው ከምኒልክ በፊት የነበሩት አፄ ዮሐንስ በመቀለ ቤተ መንግሥታቸው፣ ይኼንኑ ባንዲራ ያውለበልቡ ነበር፡፡ በተለይ በዓድዋ ጦርነትና ከፋሺስት ጦርነት ንጉሡ በድል አድራጊነት ኢትዮጵያ ተመልሰው፣ በኦሜድላና በቤተ መንግሥት ባንዲራውን አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ከተከሉ በኋላ፣ እነዚህን ቀለማት፣ ልክ እንደ ሃይማኖቱ ተመለከተ፡፡ መብቱ ሲነካበት ‹‹ወድቆ በተነሳው ባንዲራ›› በማለት መብቱን ያስከብራል፡፡ በሐዘኑም ሆነ በደስታው፣ ሕዝቡ ባንዲራውን ያነጥፋል፣ ይሰቅላል፡፡ ባንዲራው ይነካል/ይዋረዳል ብሎ ሲያስብ፣ ለሕይወቱ ሳይሳሳ፣ ባንዲራውን ይዞ ደረቱን ገልብጦ ይዋጋዋል፡፡ ዘርዓይ ደረስ፣ ፋሺስቶች በሮም አደባባይ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይን ባንዲራ መሬት አንጥፈው በሺሕዎች ሲረጋግጡ፣ ብቻውን አላስችል ብሎት የሚችለውን ቀልቶ፣ ራሱን ለመስዋዕትነት አቅርቧል፡፡ በሌላ በኩል ይኼንኑ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ባንዲራ ከዓድዋው ድል በኋላ፣ የዓለም ጭቁን ሕዝቦች በተለይ ጥቁሮች፣ የነፃነት አርማ በማድረግ ይዘውት ተዋግተዋል፡፡ በየአደባባዩ አውለብልበውታል፡፡ የሰው ልጅ መብት ተቆርቋሪዎች ከያንያን (እንደ ቦብ ማርሌ) በየመድረኩ ሲቀርቡ ባንዲራውን ሰቅለው ሕዝቡን አስጨፍረዋል፡፡ ከአርባ የበለጡ የአፍሪካ አገሮች ነፃ ሲወጡ፣ ሲታገሉበት የነበረውን በተለያዩ ዲዛይን መሠረቱን ሳይለቅ በማሰማራት ባንዲራቸው እንዲሆን አድርገዋል፡፡ ስለ ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ብዙ መጻፍ የሚቻል ቢሆንም፣ በአጠቃላይ ማለት የሚገባው ‹‹የኢትዮጵያን ሕዝብ ተነስ፣ አገርህን የሚደፍር ጠላት መጣ ብለህ ለመቀስቀስ ባንዲራውን ማሳየት ነው፡፡ በዚህን ጊዜ ለባንዲራው የማይሞት ስለሌለ፣ ቀፎ እንደተነካበት ንብ ተምሞ ይነሳል፡፡ ባንዲራው የአገሩን ወሰን ዳርቻ ተውለብልቦ ያሳያል፡፡ በዚህም ነው፣ አፋሮች ሰለ ባንዲራው ሲናገሩ፣ ‹‹እንኳን አፋር፣ ግመሉ የኢትዮጵያን ባንዲራ የት እንደተውለበለበ ያውቃል፣ ወሰኑንም ያሳያል›› የሚሉት፡፡ የኢትዮጵያ ወሰን በባንዲራ የታጠረ ነው፡፡ ለዚህ እንደ ማስረጃ ለማቅረብ እንግሊዝ ጋምቤላን ከሱዳን ጋራ ቀላቅላ ታስተዳድር ነበር፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ሱዳን ነፃ ከመውጣቷ በፊት፣ ጋምቤላን ለኢትዮጵያ እንድትመልስ እንግሊዝን እየጠየቀ እያለ፣ ተንኮለኛው የእንግሊዝ መንግሥት ጥያቄውን ወደ ጎን ጥሎ፣ ጋምቤላን ከሱዳን ጋራ ቀላቅላ፣ ለሱዳን ነፃነት እንደሚሰጥ ለኢትዮጵያ መንግሥት ዕቅዱ ደረሰው፡፡ ወዲያው የዛኔ የጦር ሚኒስትር የነበሩት ራስ አበበ፣ ለወታደሩ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ባንዲራን በመስጠት ‹‹በቶሎ እየሮጥህ፣ የአገሬውን ሕዝብ የኢትዮጵያ ድንበር እንዲያሳይህ እየጠየቅህ በወሰኑ ላይ ይኼን ባንዲራ ትከል›› ብለው መመርያ ሰጡ፡፡ ወታደሩም እንደ ታዘዘው በወሰኑ ላይ ድቅድቅ አድርጎ ባንዲራውን ተከለ፡፡ እንግሊዞቹም ባንዲራውን ሲያዩ፣ ‹‹ኢትዮጵያ አምርራለች›› ብለው ሳይወዱ በግድ፣ ጋምቤላን ለእናት አገሯ መለሱ፡፡ እንግዲህ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀዩ ባንዲራ ለኢትዮጵያውያን እንደ አምልኮት በሚታይበት አገር ውስጥ ነው፣ ኢትዮጵያን እናስተዳድራለን  በሚሉት ኃይሎች ‹‹ባንዲራው ጨርቅ ነው››፣ ይኼ የምትሉት ባንዲራ የነፍጠኛ ነው እኛ የራሳችን ባንዲራ ስላለን፣ በክልላችን የራሳችንን ባንዲራ እንተክላለን ወዘተ. ያሉ ሰው እስኪያልቅ ተደረሰ፡፡ 

በአገራችን ላይ ፖለቲከኞች አውቀውም ይሁን ሳያውቁ ዓርማንና ሰንደቅ ዓላማን ሲያምታቱ ይታያሉ፡፡ ዓርማ የአንድን ድርጅት ዓላማ ወይም መለያ የሚያሳይ ነው፡፡ ድርጅቶች ፓርቲም፣ ክፍለ አገርም፣ ክፍለ አገርን የሚመራ አስተዳደርም፣ መሥሪያ ቤትም፣ ሆቴልም፣ የተለያዩ ዓርማዎች በአንድ አገር ውስጥ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ሰንደቅ ዓላማ ግን የአንድ አገር ብቸኛው መለያ ነው፡፡ በንጉሡ ጊዜ በአረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀዩ ላይ አንበሳ ተለጥፎ፣ እሳቸው መኪና ላይ፣ መኖሪያ ቤታቸው ወዘተ. ይሰቀል ነበር፡፡ ይኼ የእሳቸው መንግሥት ዓርማ ነው፡፡ በተመሳሳይ መከላከያና ቤተ ክህነት ወዘተ. በአረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀዩ ላይ የራሳቸውን ዓርማ አድርገው በአካባቢያቸው ይጠቀሙ ነበር፣ ይጠቀማሉም፡፡ በእነዚህ ጊዜያት በየሕዝቡና በየመንግሥት መሥሪያ ቤቱ የሚሰቅለው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ግን ልሙጡ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ነው፡፡ ንጉሡም አሜድላ ላይ የሰቀሉት ሰንደቅ ዓላማ ይሄንኑ ልሙጥ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ነው፡፡ ደርግም በተመሳሳይ በአረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀዩ ላይ የራሱን ዓርማ በመለጠፍ ይጠቀም ነበር፡፡ ሕዝቡም ልክ እንደ ንጉሡ ጊዜ ባንዲራ ሳይለውጥ ይጠቀም ነበር፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀዩ ላይ ኮከብ በመለጠፍ ሲመጣ፣ ሕዝቡ እንደ በፊቱ ልሙጡን አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ይጠቀም ነበር፡፡ ውሎ አድሮ ግን ኢሕአዴግ በሕገ መንግሥቱ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ  አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀዩ ላይ ኮከብ የተለጠፈው ስለሆነ፣ ሕዝቡም በየቤቱ ይኼንን ብቻ መስቀል አለበት ብሎ አስገደደ፡፡ ክልሎቹም የየራሳቸው ሰንደቅ ዓላማና የክልሉ የሕዝብ መዝሙር እንዲኖር አደረጉ፡፡ እዚህ ላይ ነው እንግዲህ በአንድ አገር ላይ የተለያዩ ባንዲራዎች፣ መዝሙሮች መኖራቸውና እስከ ጭራሹም የኖረውን ባንዲራ በክልሌ በአደባባይ አታውለበልብም መባሉ፣ የሕዝብ አመፅ የተቀሰቀሰው፡፡ ይኼ ጉዳይ አሁኑኑ ማስተካከልና ብዥታውን በማጥፋት ነዋሪውን ሰንደቅ ዓለማ በመመለስ፣ ምንም ዓርማ መጠቀም መደንገግ አለበት፡፡ በሌላ በኩል ከንጉሣዊው አገዛዝ በኋላ የብሔራዊ መዝሙር ጉዳይ ፖለቲካውን እየቃኘ በመድረሱ፣ ብዙው ሕዝብም መዝሙሩ ሥልጣን በያዘው ተደርሷል በማለት ሊቀበለው አልቻለም፡፡ ዘላቂ የሆነ ከፖለቲካ ተፅዕኖ የተላቀቀ የኢትዮጵያን ባህሪ የሚያሳይ ብሔራዊ መዝሙር ማዘጋጀት አለብን፡፡ በአጠቃላይ በአገራችን ያለውን ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማና የሕዝብ መዝሙር አለመስማማት አስወግደን በኅብረት የምናከብራቸውን ሁኔታ መፍጠር አለብን፡፡

የምርጫውን ውጤት አለመቀበል  

ለአገራችን ዴሞክራሲ አዲስ አካሄድ መሆኑን መቀበል አለብን፡፡ ዴሞክራሲ የሚያድገው በሒደት ነው፡፡ ይኼም በአንዴ የሚደረስ አይደለም፡፡ ከ200 ዓመት በላይ ዴሞክራሲ አራምጃለሁ የምትለው አሜሪካ ገና እንደሚቀራት ባለፈው ምርጫ አይተናል፡፡ እኛም በየጊዜው እየተማርን፣ ስህተታችንን እያረምን ከሄድን ዴሞክራሲ ጥሩ ቦታ ልናደርስ እንችላለን፡፡ ዴሞክራሲ ከሚገለጽባቸው ሒደቶች አንዱ ምርጫ ነው፡፡ በዴሞክራሲ ስም ላለፉት አርባ ዓመታት ምርጫ አካሂደናል፡፡ በሁሉም በሚባል የዴሞክራሲ ስም ብቻ ነው እንጂ የተሰጣቸው ውጤታቸው አልነበረም፡፡

የሰሞኑም ምርጫ ካለፉት ምርጫዎች በብዙ የተሻለ መሆኑን፣ በዓይናችን ዓይተናል፡፡ ለዚህም አንዱ የምርጫ አስፈጻሚው ቦርድ በተቻለው መጠን፣ ገለልተኛ በመሆን ምርጫውን ፍትሐዊ ለማድረግ የተንቀሳቀሰበት ነው፡፡ ይኼም ለጅማሮ ጥሩ በመሆኑ፣ የታዩትን ስህተቶች ወደፊት ይታረማሉ በሚል ሙሉ በሙሉ ምርጫውን መቀበል ግድ ይላል፡፡ ይኼም ቢሆን፣ በዚህ ምርጫ ላይ ሁለት ዋና ችግሮች ታዝበናል፡፡ አንደኛው የምርጫውን ዴሞክራሲያዊነት የሚያኮስስ ሲሆን፣ ይኸውም እላይ ያሉት የብልፅግና አመራሮች ምርጫውን በዴሞክራሲ እንከን የለሽ እናደርገዋለን ብለው ሲታገሉ፣ ከዚህ በተቃራኒው ብዙ የብልፅግና ካድሬዎች በተቃራኒው ነበር የቆሙት፡፡  ይኼም የሆነበት ምክንያት፣ በተለይ በየገጠሩ ለምርጫ የቀረቡት የብልፅግና አመራሮች፣ ዶ/ር ዓብይ በምርጫ ካላሸነፍን ከሥልጣን ሊያንገዋልለን ይችላል በማለት ምርጫውን ለእነሱ የመኖር ያለመኖር አድርገው በመቁጠር፣ ከባለ ሀብቶች ገንዘብ በማሰባሰብ፣ በቀለም ያሸበረቁ ትልልቅ ባነሮች በመለጠፍ፣ ከሃያ የማያንሱ ትላልቅ ዘመናዊ መኪኖችን  በተርታ አሠልፈው፣ መኪኖቹም መብራት እያበሩ፣ ጥሩንባ እያስጮሁ ለገጠር ሕዝብ ልክ መንግሥት አካባቢው እንደመጣ እንዲቆጥር በማድረግ ሲርመሰምሱ፣ የገጠሩ ሕዝብ ከመንግሥት ጋራ አልጣላም በማለት በሥነ ልቦና ጫና በመውደቅ መረጣቸው፡፡ በዚህም የብልፅግና የበላይ አመራርና የምርጫ አስፈጻሚው ቦርድ ያልጠበቁት ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ አንድ ፓርቲ በማሸነፍ በምርጫው ዴሞክራሲ ላይ ጥላሸት ጣሉበት፡፡

በሁለተኛ በምርጫው ላይ የታዘብነው የምርጫው ውጤት አተረጓጎም ዴሞክራሲውን አቀጭጮታል፡፡ ዕውን ነው በማንኛውም ምርጫ መንግሥት የሚመሠረተው በድምፅ ብልጫ አብላጫ ያገኘው ነው፡፡ ይኼም ማለት በአገሪቱ የሚገኙ የተለያዩ  ፓርቲዎች ሐሳቦቻቸውን ለመራጩ አቅርበው፣ መራጩ እኔ የምፈልገውን ሐሳብ ይዟል ብሎ ይመርጣል፡፡ አብላጫ ድምፅ ያገኘው ፓርቲም መንግሥት ይመሠርታል፡፡ ይኼ ሒደት ትክክል ነው፡፡ በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ግን ይኼ ሊፈጸም አልተቻለም፡፡ ባለፈው ምርጫ ከ40 በላይ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከአንድ የብልፅግና ፓርቲ ጋራ ተወዳደሩ፡፡ ውጤቱንም ሲከፋፈሉ አብላጫው ድምፅ መና ሆነ፡፡ ይኼንን በምሳሌ ለማሳየት ባንድ ምርጫ ጣቢያ አሥር ሰዎች ሊመርጡ ቢሄዱና አምስት ፓርቲዎች እነዚህን ሰዎች ምረጡን ቢሉ፣ ድምፅ ሲቆጠር፣ ለፓርቲ ‹‹ሀ›› አራት ሰዎች፣ ለፓርቲ ‹‹ለ›› ሦስት ሰዎችና ለተቀሩት ሦስት ፓርቲዎች አንዳንድ ሰው ቢመርጣቸው፣ ባለው ምርጫ ሕግ መሠረት፣ ፓርቲ ‹‹ሀ›› ከመራጮች 40 በመቶ ድምፅ አግኝቶ፣ ወይም ከመራጮች አብላጫው ስልሳ በመቶ የሆኑት ድምፅ ተጥሎ በአሸናፊነት ይመዘገባል፡፡ በዚህም ምክንያት እንግዲህ በሚቀጥለው ምርጫ ይኼ በምርጫው ቅቡልነት ላይ ሊነሱ የሚችሉትን ጥያቄዎች አስወግደን፣ ፍትሐዊ ማድረግ አለብን፡፡

መንግሥታዊ አመሠራረት ላይ አለመስማማት

የኢትዮጵያ መንግሥት አሃዳዊ ነው ወይስ ፌዴራላዊ መሆን ያለበት የሚለው ጥያቄ መወያየትና መወሰን ተገቢ ነው፡፡ ፖለቲከኞች የብሔር ችግር ላለባት አገር ፌዴራሊዝም ነው መፍትሔው ብለው ያቀርባሉ፡፡ ይኼ ግን ሐሰት ነው፡፡ ብዙ ብሔሮች ያሉባቸው አገሮች የመንግሥታቸው አስተዳደር አሃዳዊ ነው፡፡ እንዲያውም በፌዴራላዊ መንግሥት የሚተዳደሩ በዓለም ላይ ከ20 አገሮች ብዙም አይዘልም፡፡ በአሃዳዊ የአካባቢ አስተዳደራዊ ነፃነትም በሕግ ተደንግጎ ይከበራል፡፡ አሁን ያለው ሕገ መንግሥት በብሔርተኞች በራሳቸው ዕሳቤ በመሰጠቱ በሕዝቡ የፌዴራላዊ አስተዳደር ላይ ጥያቄ እያስነሳ ስለሚገኝ፣ ብዙ አማራጮች ቀርበው ሕዝቡ ተወያይቶ ይበጀኛል የሚለውን በመንግሥታዊ አመሠራረት ላይ አለመስማማት የተነሳውን መወሰን አለበት፡፡

በመከላከያ ሠራዊት ግንባታ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች

በአንድ ወቅት በዚሁ ጋዜጣ ጽሑፌ ላይ ኢትዮጵያ የምትኖረው በመንግሥትና በመከላከያ ሠራዊት ጠንካራነት ብዬ ጽፌ ነበር፡፡ ብዙም ሳይቆይ ሁላችንም አየነው፡፡ መከላከያ ሠራዊት ስል የምድር፣ የአየርና የፀጥታ ወዘተ. ማለቴ ነው፡፡ የእነዚህ ኃይል መጠናከር ከውጪም ከውስጥም ኢትዮጵያን ለማፍረስ ለሚነሱ ኃይሎች ውድቀት ነው፡፡ እነዚህ ኃይሎች ከዚህ በፊት የተዋቀሩት ሽወዳ በተሞላበት በብሔር አስተዋጽኦ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ይልቅ ለብሔር ጥቅም እንደሚቆሙ ዓይተናል፡፡ ከሦስት ዓመት ወዲህ መንግሥት ከሠራዊቱ ለብሔር ማድላትን በማስቀረት ኢትዮጵያዊነትን ለማስረፅ እየሠራሁ ነው ቢልም፣ በቀላሉ ግን የእኔ ብሔር ብሎ ላደገ፣ በቀላሉ የሚሳካ አይደለም፡፡ በዚህ በአሥር ወራት በነበረው ሁኔታ፣ የኢትዮጵያ ሠራዊት ለመገንባት ጥሩ አጋጣሚ ተፈጥሯል፡፡ ልዩ ኃይልና ሚሊሺያ የሚባሉ ወደ ሠራዊቱ ተጠግተዋል፡፡ ከእነዚህም ሆነ ከሌሎች መልምሎ ለኢትዮጵያ በሚመጥን ቁጥር ባሉት የኢትዮጵያ ሠራዊት አዛዥ መኮንኖች ሠራዊቱ መገንባት አለበት፡፡ በተጨማሪም ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ መደበኛ ጦር ብቻ አይበቃም፡፡ ሁሉም ለአገሩ ሠራዊት መሆን አለበት፡፡ ይኼንን ለማዘጋጀት ከ18 ዓመት በላይ የሆነ ኢትዮጵያዊ ለአንድ ዓመት ወታደራዊ ሥርዓት የሚሠለጥንበት ብሔራዊ ግዳጅ መጣል አለበት፡፡ ይኼንን በማድረግም በመከላከያ ሠራዊት ግንባታ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችን ቀርፈን ሁሉን የሚያስማማ፣ ብሔሩ ኢትዮጵያዊ ብቻ የሆነ ሠራዊት መፍጠር የጊዜው አንገብጋቢ ጥያቄ ነው፡፡    

ችግሮቹን ለመፍታት መከተል ያለብን አካሄድ

እንግዲህ አገራችን ከላይ እንደተረዳነው ዘርፈ ብዙ የተደራረቡ ችግሮችና ጦርነቶች ጠፍረው ይዘዋት በሉዓላዊነቷና በዘላቂ ቀጣይነቷ ላይ አደጋ አስከትለዋል፡፡  አንዳንድ ችግሮችን በአሁን ጊዜ ፈታናቸው ወደ ሰላም አምጥተን አገሪቷን ያስቀጠልን መስሎ ቢታየን እንኳ፣ የኢትዮጵያን አስተማማኝ ሉዓላዊነት የሚፈትኑትን፣ ከላይ የተጠቀሱትን ዓይነት ችግሮች ነቅሰን ዘላቂ መፍትሔ ሰጥተን አገሪቷን ካላሻገርናት፣ በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ችግሩ ተባብሶ አገሪቷ በአንድነት ለመቀጠል የማትችልበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ዕውን ነው፡፡ ችግሩን ለመፍታት በዋናነት መንግሥት ነው ተዋናይ የሚሆነው፡፡ በዚህም አዲሱ መንግሥት ኢትዮጵያን ለማሻገር አዲስ ዕቅድ አውጥቶ መንቀሳቀስ አለበት፡፡ ከዚህ በፊት መንግሥት ያወጣው ዕቅድ ሙሉ በሙሉ እንደገና አሁን አገሪቷ ካለችበት ሁኔታ አንፃር መከለስ ግድ ይላል፡፡ አዲሱ ዕቅድ በሦስት ዓበይት ጉዳዮች ላይ መመሥረት አለበት፡፡ አንደኛው፣ በጦርነት ምክንያት የተፈናቀሉትን ሰዎች ከቀዬአቸው መመለስና የወደሙትን መሠረተ ልማቶች መልሶ መገንባት፣ ሁለተኛው፣ አገሪቱ ቅድሚያ የምትሰጣቸው ዕለታዊ የመንግሥት ሥራዎችና የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ማጠናቀቅ፣ በሦስተኛ የሚነሳው የፖለቲካ ችግሮችን ዘላቂ በሆነ ሁኔታ ፈትቶ፣ አገሪቱን ዘመን ተሻጋሪ ማድረግ ናቸው፡፡ እነዚህ ከመደበኛ ጊዜ ለየት ባለ የሚወጡ ዕቅዶች፣ ከፍተኛ ንዋይ ስለሚጠይቁ፣ ይኼም ገንዘብ ምናልባት አሁን ባለው ሁኔታ አገሪቱ ከራሷ ካዝና ብቻ ማውጣት ስለምትገደድ፣ ለተወሰኑ ዓመታት ወጪን በመቆጠብ ማለትም በአገሪቱ በሙሉ (ክልሎችንም ይጨምራል) አላስፈላጊ ግብዣዎች፣ ጉዞዎች፣ ግዥዎች፣ ስብሰባዎችና በዓሎች እንዲሁም አዳዲስ ፕሮጀክቶች ወዘተ. ማቆም ግድ ይላል፡፡ በተጨማሪም መንግሥት ኅብረተሰቡን በማስተባበር የገንዘብ መዋጮ በማድረግ ችግሩን ለመፍታት መሥራት አለበት፡፡ መንግሥት ዕቅዶቹን በመደበኛ፣ በአጭር፣ በመካከለኛና በሽግግር ከፋፍሎ ሊያዘጋጅ ይቻላል፡፡

መደበኛ ዕቅድ

የመደበኛ ዕቅድ የመንግሥትን በአብዛኛው ዋና ዋና የተባሉትን የመንግሥት መደበኛ ሥራ የሚሠራበት ነው፡፡ በዋና ዕቅድ የሚታዩት፣ የህዳሴ ግድብ ሥራን፣ በሥራ/በግንባታ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶችን፣ የኮቪድ ክንዋኔዎችን፣ አሁን የተጀመሩትን በምግብ ራስን መቻል የግብርና ፕሮጀክቶችን ወዘተ. ዕለታዊ የመንግሥት ሥራዎች ይሆናሉ፡፡ እነዚህ ምንም ሳይነኩ ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው፡፡ አዳዲስ ፕሮጀክቶችና ብዙ የልማት አዳዲስ ፕሮጀክቶች በፌዴራሉም ሆነ በክልል ታጥፈው ገንዘቡ ለሌሎች ፕሮጀክቶች ማሟያ መተላለፍ አለባቸው፡፡

የአጭር ጊዜ ዕቅድ

በዚህ አስቸኳይ ዕቅድ ጦርነቱን በሁሉም የኢትዮጵያ ክልል ማጠናቀቅ/ማስቆም ነው፡፡ ጦርነት አውዳሚ ከመሆኑም በላይ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራውም ከፍተኛ ነው፡፡ ጦርነቱ በተራዘመ ቁጥር ቀውሱ እየተስፋፋ በመሄድ የአገሪቱን ሕልውና አደጋ ላይ ይጥላል፡፡ መንግሥት ማወቅ ያለበት የሐሳብ/እምነት (Ideology) ጦርነት ለማቆም/ለማጥፋት አስቸጋሪ ነው፡፡ ማድረግ ያለበት ውይይት በመጀመር ብሔራዊ መግባባት ማምጣት ነው፡፡ በዚህ ላይ ምናልባት ለተወሰኑ ክፍሎች/ግለሰቦችም አስፈላጊ ከሆነ ሰላም ለማምጣት መንግሥት ምሕረት ማድረግ ይገባዋል፡፡ እልክ ፖለቲካ አይደለም፡፡ ዘላቂ ጥቅምን እስከ አልጎዳ ድረስ ሰጥቶ መቀበል ሁሌም የፖለቲካ ሥነ ምግባር ነው፡፡

የመካከለኛ ጊዜ ዕቅድ

ሰላም እንደመጣ ወዲያው መንግሥት የመካከለኛ ጊዜ ዕቅድ አውጥቶ የኑሮ ውድነትንና የተፈናቀሉትን ወደ አካባቢያቸው መልሶ ለማቋቋም መሥራት አለበት፡፡ የኑሮ ውድነት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ አብዛኛው በመካከለኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ነዋሪ፣ መሠረታዊ ፍላጎቶችን ለሟሟላት እየተቸገረ ነው፡፡ የኑሮ ውድነት ከዚህ በላይ እያሻቀበ ከሄደ ሰላሙን የበለጠ ሊያደፈርሰው ይችላል፡፡ ስለዚህ መንግሥት በአስቸኳይ ማውረድ አለበት፡፡ በመካከለኛ ዕቅድ ላይ ሌላው በከፍተኛ ደረጃ መካተት ያለበት ከቀያቸው የተሰደዱትን መልሶ ማቋቋም ነው፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከአሥር ሚሊዮን በላይ ሕዝብ (ትግራይንም ይጨምራል) በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በኢትዮጵያ ከሚኖሩበት አካባቢ ተፈናቀለዋል፡፡ ንብረታቸው ወድሟል፣ ተዘርፏል፡፡ የአካባቢያቸው መሠረተ ልማት እንደ ትምህርት ቤት፣ ጤና ጣቢያ፣ ሆስፒታልና ፋብሪካዎች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል፣ ተዘርፈዋል፡፡ ይኼ ከፍተኛ ንዋይና የመንግሥትና የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁርጠኝነት ይጠይቃል፡፡ ለዚህም ነው መንግሥት ሌሎች የልማት አጀንዳዎችን አቁሞ፣ በጀታቸውንም አጥፎ በመረባረብ ሌት ተቀን መሥራት ያለበት፡፡ መንግሥት ከራሱና ከረጂ አገሮች የሚያገኘውን ያለ የሌለውን ገንዘብ አሟጦ ለመጠቀም በማስላት፣ የቀረውን ከማንኛውም ዜጋ እስከ ቀረጥ በመጣል ለማሟላት መንቀሳቀስ አለበት፡፡ ሁሉም ዜጋ በችግር ቢሆንም ከሚያስፈልገው ገንዘብ ቀንሶ ለዚህ ጥሪ የመተባበር ኃላፊነት አለበት፡፡ በአጠቃላይ ይኼንን ግዙፍ ችግር መንግሥት በመደበኛ ሥራ አመርቂ ውጤት ማምጣት ስለማይችል አስቸኳይ አሠራር አደራጅቶና ከመንግሥትም ከሕዝብም በተወጣጡ ፈቃደኛ አመራሮች የሚመራ ባለሥልጣን አቋቁሞ ሥራውን ማንቀሳቀስ አለበት፡፡ በዚህ ሥራ ውስጥ በፈቃደኝነት ለመሠለፍ ብዙ ሰዎች እንገኛለን፡፡   

የሽግግር ዕቅድ

የዚህ ዕቅድ ዋና ዓላማ በአጭሩ ከሦስት ዓመት በፊት የነበረውን ኢትዮጵያን በማዳከም ብሔርን በማንገሥ ሲንቀሳቀስ የነበረውን ሥርዓት በማሰወገድ አዲስ ዜጋ ተኮር አገር ለመመሥረት ነው፡፡ ይኼንን ግብ ለማሳካት፣ ጨፍድደው የያዙንን የብሔር/የጎሳ ፖለቲካ፣ የዴሞክራሲ ዕጦት ወዘተ. ከእነዚህ ጋራ ተያይዘው ያሉ የፖለቲካና የማኅበራዊ ችግሮች መፍታት ግድ ይላል፡፡ እነዚህን ሳንፈታ ከሄድን እንደ በፊቱ፣ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ፣ አደጋ ላይ መውደቃችን አይቀርም፡፡ ስለዚህ በነዚህ አምስት ዓመታት ካሁን ጀምረን ችግሮች በሽግግር ዕቅድ ነቅሰን አውጥተን፣ ለሚቀጥለው ምርጫ፣ ሕዝብ፣ አስተማማኝ ዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያን የሚመራ መንግሥት ለመምረጥ እንዲወጣ ማስቻል አለብን፡፡

እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት እነዚህ ችግሮች ውስብስብ በመሆናቸው በውጪም በውስጥም ተፅዕኖ ኅብረተሰቡን በጥቅም ከፋፍለውታል፡፡ አንዱ ፖለቲከኛ የእኔ ወገን በአሁን አካሄድ ተጠቃሚ ነው፡፡ ሌላ አካሄድ አይጠቅመኝም ሊል ይችላል፡፡ እንደዚህ ዓይነቱን ለማስቀየር ትዕግሥትና ውይይት ያስፈልጋል፡፡ ብሔራዊ መግባባት መደረግ አለበት፡፡ ይህንን የሚመሩት በዋናነት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሲሆኑ፣ ለአስፈጻሚነት ከማንኛውም ፖለቲካ ወይም ሃይማኖት ውጪ የተውጣጡ ምሁራን መሆን አለባቸው፡፡ እነሱም እንደ ዓላማ የሚይዙት ጠንካራና ዘላቂ የሆነች ኢትዮጵያን መመሥረት፣ በዚችም አገር ሁሉም ዜጋ ሰብዓዊ መብቱ የተከበረና በሚፈልገው አካባቢ ለመኖር፣ ለመሥራት፣ ሀብት ለማፍራት፣ አካባቢውን ራሱ በዴሞክራሲያዊ የሚያስተዳድርበት መሆን አለበት፡፡  አገራችን ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!

ከአዘጋጁጸሐፊው በላይ ወልደየስ (/ር ኢንጂነር) የኬሚካል ኢንጂነሪንግ ፕሮፌሰር ሲሆኑ፣ ስፔሻላይዝድ ያደረጉት ደግሞ በፔትሮኬሚካል ኢንጂነሪንግ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ2015/16 የአስተማሪነት ልዕልና ሽልማትን (Distinguished Teaching  Award) ተቀብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚ መሥራች አባልም ናቸው፡፡  ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]  ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles