- በመቅደላ በእንግሊዝ የተዘረፉ ንዋያተ ቅድሳት እንዲመለሱ ፓትርያርኩ ዳግመኛ ጠይቀዋል
የካሊፎርኒያ ፓልም ስፕሪንግ አርት ሙዚየም የኢትዮጵያን ቅርሶች በጨረታ መሸጡን እንዲያቆም በአስቸኳይ የተቃውሞ ድምፅ እንዲሰማ ጥሪ ቀረበ፡፡
ለጨረታ የተዘጋጁትና በሙዚየሙ ድረ ገጽ ይፋ የሆኑት በግምት በ18/19ኛ ምዕት ዓመት በብራና ላይ እንደተጻፈ የሚነገርለት የግእዝ መዝሙረ ዳዊት ከነማህደሩና ጥንታዊ መስቀል ናቸው፡፡
የተቃውሞ ድምፅ እንዲሰማ ጥሪውን በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ያስተላለፈው የኢትዮጵያ ቅርስ ባላደራ ማኅበር ነው፡፡
‹‹ቅርሶቹ በዚህ መልኩ መሸጣቸውን በአስቸኳይ ተቃውሞ በማሰማት ሙዚየሙ ጉዳዩን እንዲያጤነው ድምፃችንን እናሰማ!!!›› ሲልም ማኅበሩ አስተጋብቷል፡፡
ከኢትዮጵያ የተወሰዱት እነዚህን ቅርሶች ሙዚየሙ በውስን ጨረታ ለመሸጥ የወሰነው ለቀሪ የሙዚየሙ ስብስቦች ጥበቃ ፈንድ ለማሰባሰብ መሆኑ በገጻቸው ተጠቅሷል፡፡ ለገበያ የቀረቡት እነዚህ ቅርሶች ከ500 እስከ 700 የአሜሪካን ዶላር መገመታቸው ታውቋል፡፡
በተያያዘ ዜና የእንግሊዝ መንግሥት ባሰማራቸው ወታደሮች በ1860 ዓ.ም. ከመቅደላ የተዘረፉ ታቦታትን ጨምሮ የተለያዩ ቅርሶች እንዲመለሱ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ለሁለተኛ ጊዜ መጠየቃቸው ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብዙኃን መገናኛ እንዳስታወቀው፣ ቅዱስ ፓትርያርኩ የጻፉት ደብዳቤ በብሪቲሽ ሙዚየም ቦርድ በኩል በቀና መንገድ ታይቷል።
የቤተ ክርስቲያኒቱ የውጪ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ መምህር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል እንደገለጹት፣ በቅርቡ የተሰበሰበው በብሪቲሽ ሙዚያም ያሉ ቅርሶችን በተመለከተ ወሳኝ የሆነው ጉባዔ የቅዱስነታቸውን ጥያቄ አዳምጧል፡፡
‹‹ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ ቅርሶቹን መመለስ የሚያስችሉ የሕግ ድንጋጌዎችን ማጤን መጀመሩ ቅርሶቹ ሊመለሱ እንደሚችሉ ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች መኖራቸውን ያመለክታል፤›› ሲሉም ገልጸዋል።
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በደብዳቤያቸው ላይ ሙዚየሙ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ አምልኮ የሚፈጸምባቸውን ቅዱሳት ንዋያት፣ በተለይም የቃል ኪዳኑን ታቦት ይመለሳሉ በሚል እየጠበቁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ሙዚየሙ እነዚህን በዝርፊያ የሄዱ ታቦታት የመመለስ የሞራል ኃላፊነነት እንዳለበትም አሳስበዋል።
ታቦታቱ የምስጢራተ ቤተክርስቲያን መፈጸሚያ መሆናቸውን በማስረዳት የብሪቲሽ ሙዚየም እነዚህን ታቦታት በማይገባ ሥፍራ ማስቀመጡን አሳፋሪ መሆኑን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡
ዘ ጋርዲያን የተሰኘው የእንግሊዝ ጋዜጣ በሰሞኑ ዕትሙ ከ150 ዓመታት በላይ ከእይታ ተሰውሮ የቆየው ታቦት ወደ አገሩ ሊመለስ መሆኑን ጠቁሞ፣ ታቦት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ትልቅ መንፈሳዊ እሴት እንደሆነ በመግለጽ በኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል ጥያቄው እንደቀረበ የሙዚየሙ አስተዳደርም ለመመለስ እያሰበ እንደሆነ ፍንጭ ማግኘቱን ዘግቧል::
የ154 ዓመቱ ዘረፋ እንዴት ነበር?
‹‹የቴዎድሮስ አሟሟትና የመቅደላው ዘረፋ›› በሚል ርዕስ ጥናት ያከናወኑት ግርማ ኪዳኔ አፄ ቴዎድሮስ ራሳቸውን ሰኞ ሚያዝያ 6 ቀን 1860 ዓ.ም. ካጠፉ በኋላ የመቅደላ አምባን የወረሩት እንግሊዞች የፈጸሙትን ዝርፊያ በዝርዝር አቅርበውታል፡፡ እንዲህም አሉ፡-
‹‹እንደ እንግሊዝ ጦር አዛዦች አባባል ተልዕኮአቸው የእንግሊዝ እስረኞችን ለማስፈታት ነበረ፡፡ ከዚህ የተልዕኮ ሽፋን በስተጀርባ ግን ዓላማቸው እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ ታሪካዊና ባህላዊ ይዘት ያላቸውን ቅርሶች ለመዝረፍ ጭምር መሆኑ የሚያጠያይቅ አይሆንም፡፡ ሪቻርድ ሆምስ የተባለው የብሪትሽ ሙዚየም ተወካይ ከእንግሊዝ ጦር ጋር አብሮ እንዲመጣ መደረጉ ለዚህ የዘረፋ ተግባር መከሰት እንደነበረ፤ ግልጽ ነው፡፡
‹‹የመጀመርያው ዘረፋ ቡድን ያተኮረው በሟቹ ንጉሥ ሬሳ ላይ ነበር፡፡ የአንገት መስቀልና የጣት ቀለበታቸውን፣ ሸሚዛቸውንና ሽጉጣቸውን ከመዝረፋቸውም ባሻገር ሹሩባቸውን ሳይቀር ሸልተው የወሰዱ ለመሆኑ በታሪክ መዛግብት መረዳት ይቻላል፡፡
‹‹ሁለተኛው የዘረፋ ቡድን ያተኮረው የቤተ መንግሥት ሕንፃ በመድፈር ነበር፡፡ ንጉሡ በሕይወታቸው ሳሉ ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት ለማቋቋም የሰበሰቡአቸውን እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ መጻሕፍትን እንደዚሁም በአሁኑ ጊዜ የብሔራዊ ቤተ መዛግብት መሠረት ሊሆኑ የሚችሉ አያሌ የመንግሥት ሰነዶችንና የተለያዩ መረጃዎችን ሳይቀሩ ዘርፈዋል፡፡ ከነዚህም መካከል የአፄ ቴዎድሮስ ዘውዶችና ማኅተም፣ በተለይም ክብረ ነገሥት የተባለው ታላቁ መጽሐፍ ይገኙባቸዋል፡፡ ቀጥለውም ወደ ንጉሠ ነገሥቱ ማዕድ ቤት ውስጥ በመግባት ሃያ እንሥራ የሚሆን የተጠመቀ ጠጅና የእህል አረቄ ዘርፈው ከመጠን በላይ ሰክረው ነበር፡፡ ከዘረፉዋቸው ቅርሶች ይልቅ ጥፋት ያደረሱባቸው አመዝነው ታይተዋል፡፡ ብዙ ቅርሶች ጥለዋል፣ ሰባብረዋል፣ መጻሕፍትንም ቀዳደዋል፤ አልባሳትንም ሸካክተዋል፡፡
‹‹የሦስተኛው የዘረፋ ቡድን ከወሰዳቸው መካከል ከወርቅ የተሠራ የአቡነ ሰላማ አክሊል ወይም ዘውድ ጫማና ቀበቶ፣ ከወርቅ የተሠሩ ሁለት ጽዋዎች፣ ከወርቅ የተሠራ በአንገት ላይ የሚጠልቅ የአፄ ቴዎድሮስ የሰሎሞን ኒሻን እንደዚሁም ንጉሡ ሲነግሡ ለብሰውት የነበረው የማዕረግ ልብስ ይገኙባቸዋል፡፡
‹‹አራተኛው ቡድን ከዘረፋቸው መካከል የተለያዩ ጋሻዎች፣ ከነዚህ ውስጥ የአፄ ቴዎድሮስ ጋሻ ሳይሆን አይቀርም ተብሎ የሚገመተውና የፊታውራሪ ገብርዬ ጋሻ፣ ልዩ ልዩ ጦሮችና ጎራዴዎች፣ ያሸበረቁ የፈረስ ዕቃዎች፣ በተጨማሪም የቴዎድሮስ እስረኞች የታሰሩበት የእግር ብረት ይገኙበታል፡፡
‹‹አምስተኛውና የመጨረሻው የዘረፋ ቡድን ያተኮረው አፄ ቴዎድሮስ በየአገሩ ሲዘዋወሩ ያርፉበት በነበረው ድንኳናቸውና ይጠጡበት በነበረው ዋንጫቸው፣ የማንነቱ ባልታወቀ የፈረስ ልባብ ላይ ነበረ፡፡ ወታደሮቹ በዚህ ሳይገቱ የደረሱበትን መንደር በማሰስና እያንዳንዱ ቤት ውስጥ በመግባት ተመሳሳይ ዘረፋ ከማካሄዳቸውም ባሻገር ከተለያዩ ቤተ ክርስቲያኖች የተገኙትን መንፈሳዊ ሥዕሎችና እንደዚሁም ቁጥራቸው አሥር የሚደርሱ ታቦቶችን ሳይቀሩ ወስደዋል፡፡ በአጠቃላይ ከንጉሠ ነገሥቱ ቤተ መንግሥት ጀምሮ በአነስተኛ ጎጆ ውስጥ የሚገኙ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች ሳይቀሩ ተዘርፈዋል፡፡
‹‹አብዛኛዎቹ በዘረፋ ላይ ተሰማርተው የነበሩት ወታደሮች አስተሳሰብ ብዙ ገንዘብ ለማግኘት እንጂ ለዕቃዎቹ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርስነት እንዳልሰጧቸው መገመት አያዳግትም፡፡ ለምሳሌ ሪቻርድ ሆምስ የብሪትሽ ሙዚየም ኤክስፐርትና አርኬዎሎጂሲት ከአንድ በዘረፋ ላይ ተሰማርቶ ከነበረ ወታደር ከወርቅ የተሠራውን የአቡነ ሰላማን የዘውድ አክሊልና የወርቅ ጽዋ በላዩ ላይ በግዕዝ እንደሚከተለው የተጻፈበትን ‹‹ዝንቱ ጽዋ ዘወሀብዋ ዳግማዊ ኢያሱ ወብእሲቱ ወለተ ጊዮርጊስ ለቅድስት ቁስቋም ከመ ትኩኖሙ መድኃኒተ ሥጋ ወነፍስ›› ወደ አማርኛ ሲተረጐም- ይህም አፄ ኢያሱ ብርሃን ሰገድ ለቁስቋም ቤተ ክርስቲያን ያበረከቷቸውን ሦስት ኪሎ የሚመዝኑ የቁርባን ጽዋዎች›› ማለት ሲሆን እነዚህንም በአራት የእንግሊዝ ፓውንድ ብቻ እንደሸጠላቸው ይነገራል፡፡
እነ ጄኔራል ናፒየር ለየራሳቸው ካከማቿቸው ቅርሶች መካከል የአፄ ቴዎድሮስ ዘውዶች፣ የክብርና የማዕረግ ልብሶቻቸው፣ በሺሕ የሚቆጠሩ የብራና መጽሐፎችና የቴዎድሮስ ማኅተም፣ የአቡነ ሰላማ የወርቅ አክሊል፣ በብር ያሸበረቀ ጋሻ፣ በክብረ በዓል ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውል የቴዎድሮስ ከበሮና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡
የአቡነ ሰላማን ከወርቅ የተሠራ አክሊልና የቁርባን ጽዋ ከአንድ ጦር ሜዳ ላይ ከዋለ ወታደር የብሪትሽ ሙዚየም ተወካይ ሆልምስ በአራት የእንግሊዝ ፓውንድ ብቻ ገዝቶት እንደነበርም ተጠቅሷል፡፡