ትውልደ ኢትዮጵያውያን አትሌቶችና ሌሎችም ባለሙያዎች በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሆነው ለመመረጥ እንዲችሉ በሥራ ላይ ያለውና ለመመረጥ ዋነኛው መመዘኛ ‹‹በዜግነት ኢትዮጵያዊ ብቻ›› የሚለው መመርያ እንዲሻሻል የኢትዮጵያ ፕሮፌሽናል ፉትቦለር አሶሴሽን ዳግመኛ ጠየቀ፡፡
ፕሮፌሽናል እግር ኳሰኞችን ያሰባሰበው ማኅበር፣ በተለያዩ ምክንያቶች ከኢትዮጵያ ወጥተው የነበሩ በዕውቀታቸው፣ በሙያቸውና በሀብታቸው ወደ አገራቸው ገብተው እንዲያገለግሉ ያመቻቸው፣ በ1994 ዓ.ም. የወጣው የዳያስፖራ አዋጅ በስፖርቱ ቤትም እንዲተገበር ያሳሰበው፣ በፌዴሬሽኑ ጠቅላላ ጉባዔ የሥራ አስፈጻሚ ምርጫ ላይ ‹‹ትውልደ ኢትዮጵያዊ መካተት ይችላል›› በሚል እንዲስተካከል በመጠየቅ ነው፡፡
ማኅበሩ ጥቅምት 8 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫው፣ የትውልደ ኢትዮጵያውያንን ጉዳይ በሚመለከት በዳያስፖራ አዋጅ የተካተተውን በመጥቀስ ዓምና (ኅዳር 14 ቀን 2013 ዓ.ም.) ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ደብዳቤ መጻፉን አስታውሶ፣ ይሁንና እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት ማስተካከያ እንዳልተደረገ ገልጿል፡፡
እንደ አሶሴሽኑ አቤቱታ ከሆነ፣ የቀድሞ ወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ይህን ጉዳይ በሚመለከት ተሻሽሎ በተዘጋጀውና መስከረም 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ፀድቆ በሥራ ላይ የዋለው የስፖርት ማኅበራት ስለሚቋቋሙበት ለመወሰን የወጣው መመርያ በእያንዳንዱ አንቀጾች ላይ ትውልደ ኢትዮጵያዊ በሚል ተስተካክሏል፡፡ ይህ መመርያ እግር ኳስ ፌዴሬሽኑን ጨምሮ ለሁሉም ባለድርሻ አካላት እንዲደርስ ተደርጓል፡፡ ይሁንና ይህን መመርያ ሌሎች የስፖርት ማኅበራት ተግባራዊ ሲያደርጉት፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ግን ከመመርያው በተቃራኒ ቀጥሎበታል ብሏል፡፡
አሶሴሽኑ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ እንዲያውም ‹‹በመተዳሪያ ደንቡ አንቀጽ 30 የሥራ አስፈጻሚ መምረጫ መመዘኛ (ሀ) በዜግነት ኢትዮጵያዊ በሚል ገልጾታል፤›› ብሎ ይህ ተገቢ ባለመሆኑና ይህንኑ ከፊት ለፊታችን በሚደረገው የፌዴሬሽኑ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ጉዳዩን በማቅረብ ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሚለውን እንዲያካትት ጠይቋል፡፡
በሌላ በኩል አሶሴሽኑ ጥቅምት 5 ቀን 2014 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በጻፈው ደብዳቤ፣ ፊፋ እ.ኤ.አ. ኦክቶበር 29 ቀን 2007 ባደረገው ጠቅላላ ጉባዔ፣ ካሳለፋቸው ውሳኔዎች መካከል ከስፖርት ግጭቶች ጋር ተያይዞ ለሚፈጠሩ አለመግባባቶች አገሮች ብሔራዊ የስፖርት ግጭት መፍቻ ሸንጎ (National Dispute Resolution Chamber) ማቋቋም እንዳለባቸው መወሰኑና ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ይህንኑ በዚህ የውድድር ዓመት ተግባራዊ እንዲያደርግ ጠይቋል፡፡
ፊፋ ይህን ውሳኔ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጨምሮ ለአባል አገሮች ያሠራጨው እ.ኤ.አ. ዲሴምበር 28 ቀን 2007 ጀምሮ መሆኑን ጭምር አሶሴሽኑ ይገልጻል፡፡ ፊፋ አገሮች እንዲያቋቁሙት የጠየቀው የስፖርት ግጭት መፍቻ ሸንጎ ገለልተኛ ሆኖ 50 በመቶ ከተጫዋቾች እንዲሁም ከክለቦች 50 በመቶ የሚካተቱ ተወካዮች የሚኖሩት ተቋም ስለመሆኑ ጭምር አሶሴሽኑ በደብዳቤው አካቷል፡፡
ፊፋ ይህን ዘዋሪ ደብዳቤ (ሰርኩላር) ለአገሮች ያስተላለፈው ከ15 ዓመት በፊት ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ተግባራዊ ሳያደርገው ቆይቷል፡፡ አሁንም ወቅቱ የውድድር እንደመሆኑ ፌዴሬሽኑ መመርያውን በውድድር ዓመቱ ተግባራዊ ሊያደረግ እንደሚገባው ጭምር አሶሴሽኑ ጠይቋል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በበኩሉ ከአሶሴሽኑ ጋር ተቀራርቦ እንደሚሠራ ተናግሯል፡፡