– የኢትዮጵያና የጋና ጨዋታ በደቡብ አፍሪካ ይደረጋል
– ሉሲዎቹ የመልሱን ጨዋታ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ያከናውናሉ
የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) በዚህ ወር ይፋ ባደረገው የአገሮች እግር ኳስ ደረጃ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) ባለፈው ወር ከነበረበት ሦስት ደረጃዎችን አሽቆልቁሏል፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ ከወራት በኋላ በካሜሩን አስተናጋጅነት በሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ተሳታፊ መሆኑ ቢታወቅም፣ ለኳታር የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ካደረጋቸው የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች በጋናና በደቡብ አፍሪካ ያጋጠሙት ሽንፈቶች ለደረጃው ማሽቆልቆል ምክንያት ሳይሆኑ እንዳልቀረ ይታመናል፡፡
በአገሮች የእግር ኳስ ደረጃ መሠረት፣ ዋሊያዎቹ በመስከረም ወር ከነበሩበት ሦስት ደረጃዎችን አሽቆልቁለው 137ኛ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ በነዳጅ ሀብቷ በምትታወቀው ኳታር አስተናጋጅነት ከአንድ ዓመት በኋላ ለሚካሄደው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ማጣሪያ፣ በምድብ 7 ከጋና፣ ከደቡብ አፍሪካና ከዚምባቡዌ ጋር ተደልድሎ አራት የምድብ ጨዋታዎችን ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሜዳውና ከሜዳው ውጪ ባስተናገዳቸው ሽንፈቶቹ ምክንያት የዓለም ዋንጫ ተመልካች እንዲሆን ከወዲሁ ማረጋገጫ ሆነውለታል፡፡
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሲሳተፍበት ከቆየው የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ውጪ መሆኑ ቢታወቅም፣ ፊፋና ካፍ ከስታዲየም ጥራትና ደረጃ ጋር ተያይዞ ከሰሞኑ ባስተላለፉት ውሳኔ ብሔራዊ ቡድኑ በምድብ ማጣሪያው ማድረግ ከነበረበት ስድስት ጨዋታ ምንም እንኳን አራቱን የተጫወተ ቢሆንም፣ ቀሪዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ከጋና አቻው ጋር በሜዳው ሊያደርግ የነበረው ጨዋታ በገለልተኛ ሜዳ እንዲጫወት አስገዳጅ ቅጣት ተጥሎበታል፡፡
ይህንኑ ተከትሎ ካፍ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እስከ ጥቅምት 10 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ ብሔራዊ ቡድኑ በገለልተኛ ሜዳ የሚጫወትበትን አገርና ስታዲየም መርጦ እንዲያሳውቀው በጠየቀው መሠረት፣ ፌዴሬሽኑ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በደቡብ አፍሪካ ኦርላንዶ ስታዲየም እንዲሆንለት ምርጫውን አሳውቋል፡፡
ፌዴሬሽኑ የባህር ዳር ስታዲየም በካፍ መታገዱን በማስታወስ፣ ሦስት አገሮችን ማለትም ኬንያን፣ ዚምባቡዌንና ደቡብ አፍሪካን ከመረጠ በኋላ፣ ሦስቱም አገሮች ጨዋታውን ለማስተናገድ ፈቃደኝነታቸውን አሳውቀዋል ብሏል፡፡ ሆኖም ግን የዚምባቡዌ ስታዲየም የኢትዮጵያንና የዚምባቡዌን ጨዋታ ብቻ የሚያስተናድግ ከመሆኑ አኳያ ውድቅ በመደረጉ አልመረጠውም፡፡
እንደ ዚምባቡዌ ሁሉ ኬንያ ፈቃደኛ ብትሆንም፣ ነገር ግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ ዚምባቡዌ ለመጨረሻው የምድብ ማጣሪያ ጨዋታው ማቅናቱ ስለማይቀር፣ ደቡብ አፍሪካ በአንድ የአውሮፕላን ጉዞና በመጠነኛ ወጪ ጨዋታውን ለማድረግ አመቺ በመሆኑ ደቡብ አፍሪካን ምርጫው ስለማድረጉ ጭምር ፌዴሬሽኑ አሳውቋል፡፡
እንደ ፌዴሬሽኑ መግለጫ ከሆነ፣ ፊፋ በሚያወጣው ፕሮግራምና ቀን ብሔራዊ ቡድኑ በደቡብ አፍሪካ ኦርላዶ ስታዲየም መጫወት ይችላል፡፡ በአንፃሩ ለ2022 ሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ባለፈው ሳምንት ወደ ዑጋንዳ ካምፓላ አምርቶ 2 ለ 0 ተሸንፎ የተመለሰው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን (ሉሲዎቹ)፣ የመልሱን ጨዋታ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም እንደሚጫወት ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡