በመታሰቢያ መላከ ሕይወት
አዲስ አበባ እንደ ዋና ከተማነት የተቆረቆረችው በ1878 ዓ.ም. በእቴጌ ጣይቱ አማካይነት እንደሆነ ይታመናል፡፡ በዚህ ወቅት አፄ ምኒልክ ለሐረር ዘመቻ ዘምተው የነበረ በመሆኑ፣ ከዘመቻው ሲመለሱ ወደ እንጦጦ መጓዛቸውን ትትው እዚህ አዲስ አበባ መኖር ጀመሩ፡፡
በዚህ ጽሑፍ የግድ መነሳት ያለበት ጉዳይ አለ፡፡ ይህም ጉዳይ አፄ ምኒልክ ለምን ወደ ሐረር ዘመቱ የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ አንደኛ በወቅቱ በዚያ አካባቢ ግዛት ለማግኘት ብዙ አገሮች ጥረት ያደርጉ ነበር፡፡ እንግሊዞች፣ ጣሊያኖች፣ ቱርኮችና ግብፆች በሰሜኑ የኢትዮጵያ ግዛት ዘልቀው ዓባይን ለመቆጣጠር ያደረጉት ተደጋጋሚ ሙከራ አልሳካ ስላላቸው፣ ግብፆች በሐረር በኩል በመግባት ኢትዮጵያን የመያዝ ህልም ነበራቸው፡፡
በተጨማሪ የአውሮፓ ኃያል አገሮች እ.ኤ.አ. በ1885 በርሊን ላይ ተሰብስበው አፍሪካን ለመቀራመት ስምምነት ላይ የደረሱበት ወቅት የነበረ በመሆኑ፣ አፄ ምኒልክ ይህንን አካሄድ የግድ ማስቆም ስለነበረባቸው የክተት አዋጁ ታውጆ ዘመቻው ተካሂዷል፡፡ ሁለተኛው ከላይ እንደተጠቀሰው አውሮፓውያን አፍሪካን የመቀራመታቸው ጉዳይ ዕውን እየሆነ ሲመጣ፣ አፄ ምኒልክ ተጨማሪ ገንዘብ (ገቢ) የሚያስገኝላቸው ግዛት ያስፈልጋቸው ስለነበረ፣ ሐረር ደግሞ በጅማ (እናሪያ) ግዛትና በዘይላ (ጂቡቲ) ግዛት መካከል ያለች ወሳኝ የንግድ መተላለፊያ መስመር በመሆኗ አፄ ምኒልክ ሐረርን ያዙ ማለት ተጨማሪ የታክስ ገንዘብ እንደሚያስገኝላቸው በማመናቸው ዘመቻውን ለማካሄድ እንደ አንድ ምክንያት ወስደውት ነበር፡፡
ሦስተኛ አፄ ምኒልክ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ማስፋፋትና ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት የመመሥረት ዓላማ የምንጊዜውም ዓላማቸው የነበረ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያን እስከ ሐረር ድረስ ለማስፋት ሠርተዋል፡፡ በመቀጠልም ራስ መኮንን ከሐረር ባሻገር አብዛኛውን የሶማሌ ቆላማ መሬት በመውረር አሁን የተሰመረው የኢትዮጵያ ደቡብ ምዕራብ ወሰን እንዲፈጠር አስችለዋል፡፡
ጳውሎስ ኞኞ በ1984 ዓ.ም. ‹‹አፄ ምኒልክ›› በሚል ርዕስ ባሳተመው መጽሐፍ ውስጥ በዚህ ጉዳይ ላይ በስፋት ተዘግቧል፡፡ ወደ ተነሳሁበት ርዕስ ልመለስና የአዲስ አበባ ከተማ መመሥረት ከእንጦጦ ወደ ታችኛው ረባዳ መሬት የተዛወረበት ምክንያት በሦስት ከፍለን ልናየው እንችላለን፡፡ በመጀመርያ እንጦጦ ለመናገሻ ከተማነት የተመረጠችው ተራራማ ስለሆነችና ጠላትን ለመከላከል አመቺ ስለነበረች ነው፡፡ ነገር ግን ቦታው እጅግ ቀዝቃዛ በመሆኑ እንኳን ለንጉሥ ለሌላ ሰውም አመቺ ባለመሆኑ ወደ ታች መውረዱ ተገቢ ነው ተብሎ ታምኖበታል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ የአፄ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥትነት (በተለይ ከአፄ ዮሐንስ ሕልፈት በኋላ) ግልጽ እየሆነ በመምጣቱ የግድ ሰፊ ከተማ ያስፈልግ የነበረ በመሆኑ፣ ሜዳማ ወደ ሆነው ከእንጦጦ ግርጌ ወዳለው መሬት መዛወር አስፈላጊነቱ የግድ ሆኗል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የአፄ ምኒልክ ቤተ መንግሥት የተሠራበት ቦታ ፍልውኃ ያለው በመሆኑና ለነገሥታት የሚመች ስለሆነ፣ ይህ ቦታ ለቤተ መንግሥትነት እንዲመረጥ አንዱ ምክንያት አድርጎ መውሰድ ይቻላል፡፡
አዲስ አበባ ከተማ ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች ቦታው ተመርጣ ተመሠረተች፡፡ ከዚያ በኋላ እንዴት ልታድግ ቻለች የሚለውን ደግሞ እንመልከት፡፡ እንደሚታወቀው ንጉሥ አንድ ቦታ ቤተ መንግሥቱን ሲመሠርት ከፍተኛ ወታደራዊ ሥልጣን ያላቸው የንጉሡ ባለሥልጣናት የራሳቸውን መኖሪያ እየገነቡ፣ በዙሪያቸው ደግሞ አሽከሮቻቸውንና ሌሎች ባለሟሎችን እንዲሠፍሩ በማድረግ የራሳቸው ስም የያዘ ሠፈር ይመሠርቱ ነበር፡፡
ከዚያም በመቀጠል በንጉሠ ነገሥቱ ግዛት ውስጥ ያሉ ንጉሦች አዲስ አበባ ቤተ መንግሥት ይገነቡ ነበር፡፡ ለምሳሌ አሁን የሆላንድ ኤምባሲ ሆኖ የሚያገለግለው ግቢ የአባ ጃፋር ቤተ መንግሥት ነበር፡፡ ጉለሌ ደግሞ የሐጂ ሸጎሌ ቤተ መንግሥት ተገንብቷል፡፡ አሁን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሆነው ግቢ ደግሞ የራስ መኮንን ቤተ መንግሥት ነበር፡፡
ሌሎችም ራሶችና ንጉሦች በየቦታው የራሳቸው ቤተ መንግሥት ነበራቸው፡፡ ይህ ግንባታና በዙሪያው የሚካሄደው የሰዎች ሠፈራ ለከተማዋ ዕድገት እንደ እርሾ ሆኖ አገልግሏል፡፡
በኋላ ግን የከተማው ሕዝብ ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ ከፍተኛ የሚባል የማገዶ እጥረት ተፈጠረ፡፡ የማገዶ እጥረት ከመደበኛው ሕዝብ አልፎ ቤተ መንግሥት መድረስ ጀመረ፡፡ በዚህ ጊዜ አፄ ምኒልክ ከተማዋን ወደ አዲስ ዓለም ለማዛወር አስበው የነበረ ሲሆን፣ አዲስ አበባ ይኖሩ የነበሩ የውጭ አገር ዜጎችና ዲፕሎማቶች ይህ ሐሳብ አልተመቻቸውም ነበር፡፡ ምክንያቱም እዚህ አዲስ አበባ በርካታ ቤቶች ገንብተው ስለነበር ይህንን ማጣት ስላልፈለጉ ለአፄ ምኒልክ ሐሳብ አቀረቡላቸው፡፡
‹‹እኛ ራሱን ቶሎ ቶሎ የሚተካ ዛፍ ከአውስትራሊያ እናመጣልዎታለን›› ብለው ባህር ዛፍ በማምጣታቸው ዛፉ ተተክሎ እንደተባለው አንድ ዛፍ በአንድ ዓመት ውስጥ (ዕድገቱን ከጨረሰ በኋላ) በመቶ ሺሕ የሚቆጠር ዘር ይሰጥ ስለነበር፣ በአጭር ጊዜ ከተማውን አጥለቀለቀው፡፡ በዚህ ምክንያት የከተማው የማገዶና የቤት መሥሪያ እንጨት ችግር ቢቀረፍም ሌላ ችግር ተከሰተ፡፡ ይህ ችግር ባህር ዛፍ ከፍተኛ የውኃ ፍጆታ ስላለው በርካታ ምንጮች መድረቅ ጀመሩ፡፡
ባህር ዛፍ እስካሁን እየተጠቀምንበት ያለ በኢትዮጵያ ታሪክ እጅግ ወሳኝ ግብዓት የሆነ የዛፍ ዓይነት ቢሆንም፣ የተፈጥሮ ሚዛንን በማዛባት እጅግ አሉታዊ ባህርይ ያለው ዛፍ ነው፡፡
ይህ ዛፍ የከርሰ ምድር ውኃን በማድረግ ትልቅ አበርክቶ ያለው ሲሆን፣ በተጨማሪ ሥሮቹ ውኃ ፍለጋ ረዥም ርቀት በመጓዝ መሬት እንዲሰነጠቅ ያደርጉና በተሰነጠው መሬት ውስጥ ውኃ (ዝናብ እየገባ) ከፍተኛ የመሬት መሸርሸር እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ ለዚህ ነው ከእንጦጦ የሚነሱ ሁሉም ወንዞች በክረምት ወቅት ድፍርስ የሚሆኑት፡፡
ባህር ዛፍ መተከል ያለበት ሜዳማ በሆነ ቦታ ብቻ ነው፡፡ በተጨማሪ ከዛፉ ላይ የሚወድቁት ቅጠሎች አሲዳማ በመሆናቸው ከዛፉ ሥር ያለው መሬት ላይ ሳር እንዳይበቅል ስለሚያደርጉ፣ ሳር የሌለው መሬት ደግሞ ለመሸርሸር የተጋለጠ በመሆኑ ይህም ሌላኛው የባህር ዛፍ አሉታዊ ባህርይ ነው፡፡
በሌላ አነጋገር አዲስ አበባ እንደ ከተማ እንድትቀጥል ባህር ዛፍ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡
ከዓድዋ ጦርነት በኋላ የአዲስ አበባ ፈጣን ዕድገት
አይቀሬው የዓድዋ ጦርነት ከተካሄደ በኋላ በአፄ ምኒልክ ድል አድራጊነት ሲጠናቀቅ፣ ወታደራዊው ድል ብቻ ሳይሆን በርካታ ድሎችንም ይዞ ነው የመጣው፡፡ ከጦርነቱ በኋላ ከአፄ ምኒልክ ጋር ሊደረጉ የታሰቡ ግንኙነቶች ሁሉ ደብዳቤ በመጻጻፍና በዲፕሎማሲ እንዲሆን መደረጉ ይህ አንዱ ትልቅ ድል ነበር፡፡
አዲስ አበባ የተካሄዱት የኤምባሲዎች ግንባታ ለአዲስ አበባ ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ አፄ ምኒልክ ለኤምባሲዎች ቦታ ይሰጡ የነበረው ወንዝ አሻግረው በመሆኑ በርካታ ኤምባሲዎች ድልድይ ገንብተዋል፡፡
በተጨማሪም በርካታ የሚሲዮን ሰዎች ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የተለያዩ የእምነት ተቋማትንና ትምህርት ቤቶች ገንብተዋል፡፡ ከጦርነቱ በኋላ አፄ ምኒልክ በርካታ ጓደኞች በማፍራታቸው በርካታ አውሮፓውን ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በርካታ ግንባታዎችን አካሂደዋል፡፡ ከእነዚህም በዋናነት የሚጠቀሰው አልፍሬድ ኢልግ የተባለው የስዊስ ዜጋ ነው፡፡
ከዓድዋ ድል በኋላ በብዛት ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ ስብስቦች ውስጥ አርመኖች፣ ህንዶች፣ ግሪኮችና ዓረቦች ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ነጋዴዎች በርካታ ምርቶች በማምረትና በመሸጥ ለከተማው ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡
ከዓድዋ ጦርነት ማግሥት ተማርከው ወደ አዲስ አበባ የመጡ ምርኮኞችም ባላቸው ግንባታ ዕውቀት ለከተማው ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ አሁን ድረስ በከተማው መሀል ያሉ የአንዳንድ ሠፈሮች መጠሪያ ለዚህ ምስክር ነው፡፡ ጣሊያን ሠፈር፣ አደሬ ሠፈር እያልን የብሔር ስም የያዙ ሠፈሮች ማግኘት ብዙም አይከብድም፡፡
ከአፄ ምኒልክ ሕልፈት በኋላ የነገሡት ነገሥታትም የከተማዋን ዕድገት የሚያፋጥኑ በርካታ ተግባራትን አከናውነዋል፡፡ ንግሥት ዘውዲቱ አጥባቂ ክርስቲያን ስለነበሩ በርካታ የእምነት ተቋማት በመገንባት ሀብት አባክነዋል፡፡ በልጅ ኢያሱ የሥልጣነ ዘመን ይህ ነው የሚባል ግንባታ መኖሩን አላውቅም፡፡ አፄ ኃይለ ሥላሴ ግን አልጋ ወራሽ በነበሩበት ጊዜም ሆነ ንጉሠ ነገሥት በነበሩበት ጊዜ፣ በአመዛኙ ለንጉሣውያን ቤተሰቦች አገልግሎት የሚሰጡ በርካታ ግንባታዎች አከናውነዋል፡፡
አፄ ኃይለ ሥላሴ ‹ትምህርት ለአገር ዕድገት ይጠቅማል› የሚል የፀና እምነት የነበራቸው በመሆኑ፣ ለትምህርት ቤት ግንባታ ብዙ ሥራ ሠርተዋል፡፡ ነገር ግን ትምህርት ብቻውን ምንም ፋይዳ የለውም፡፡ የተማረውን የሚቀጥር የተጠናከረ የኢንዱስትሪ ልማት ከትምህርት ጎን ለጎን መሄድ ነበረበት፡፡
ከዓድዋ ድል በኋላ እስከ 1928 ዓ.ም. የማይጨው ጦርነት ጊዜ በአዲስ አበባ አንፃራዊ ሰላም ነበረ በመሆኑ፣ ከተማዋ ከፍተኛ የሚባል ዕድገት አስመዝግባለች፡፡ ከጦርነቱ በኋላ ጣሊያኖች አዲስ አበባን ከተቆጣጠሩ በኋላ ሕዝቡን በማሳተፍ፣ በአዲስ አበባና በመላው አገሪቱ በመንገድ ግንባታ፣ በሕንፃ ግንባታና በሌሎችም ተግባሮች እጅግ የሚያስደንቅ ሥራ ሠርተዋል፡፡
የገነቧቸው አሁን ድረስ አሉ፡፡ እየተገለገልንባቸው ነው፡፡ በእኔ ምልከታ አፄ ኃይለ ሥላሴ 13 ዓመታት በአልጋ ወራሽነት፣ 43 ዓመታት በንጉሠ ነገሥትነት ቢያሳልፉም የሠሩት የልማት ሥራ ጣሊያን በአምስት ዓመት ከገነባው ግንባታ የሚያንስ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡
ጣሊያን ኢትዮጵያን ለቆ ከወጣ በኋላ የነበረው የአዲስ አበባ ዕድገት
ጣሊያን ኢትዮጵያ ለቆ ወጥቶ አፄ ኃይለ ሥላሴ ተመልሰው ንጉሠ ነገሥት ከሆኑ በኋላ፣ ንጉሡ በስደት ዘመን በርካታ ነገሮችን በመመልከት የተማሩ በመሆናቸውና በዕድሜያቸውም ወጣት ስለነበሩ ብዙ ሥራ ሠርተዋል ማለት ይቻላል፡፡
በዋናነት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በማዋቀር፣ መንግሥታዊ መዋቅር እንዲኖር በማድረግና በርካታ የንግድ መሣሪያ ቤቶች (እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ) ያሉ መሥሪያ ቤቶችን በመፍጠር፣ የአገሪቱን መዋቅር የሥልጣኔ ሥርዓት እንዲይዝ በርካታ ሥራ ሠርተዋል፡፡
የኋላ ኋላ ግን የመሰላቸትና የዕድሜ መግፋት እየተጫናቸው ሲሄዱ በኢትዮጵያ ከንጉሡ በታች ባሉ ባለሥልጣናት በሕዝቡ ላይ ከፍተኛ በደል ይደርስ ስለነበር፣ በተጨማሪም አፄ ኃይለ ሥላሴ ያስተማሩት ትውልድ ወደ ሥራ ዓለም መሰማራት አለመቻሉና ሥራ ቢያገኝም የተመኘውን ኑሮ መኖር ባለመቻሉ፣ በተጨማሪ እ.ኤ.አ. በ1973 ዓረቦች ‹‹ነዳጆቻችንን በርካሽ ዋጋ አንሸጥም ብለው›› የነዳጅ ማውጫዎችን በመዝጋታቸቸውና ኢትዮጵያ ውስጥ የነዳጅ ዋጋ በመጨመሩ፣ እንዲሁም ሠራዊቱ ደመወዝ ይጨመርልን የሚል ጥያቄ በማንሳቱና ሌሎችም በርካታ ተከድነው የነበሩ ነገሮች በመገንፈላቸው የንጉሡ መጨረሻ ሊያምር አልቻለም፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ ዕድሜያቸው እንኳን አገር ለመምራት ራሳቸውን እንኳን መምራት በማይችሉበት የዕድሜ ክልል ውስጥ ሆነው በፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን ማስረከብ ባለመፈለጋቸው፣ ተዋርደው ከቤተ መንግሥት ተባረሩ፡፡ አስከሬናቸው እንኳን ራሳቸው ካሠሩት ቤተ መንግሥት መውጣት አልቻለም፡፡
ጣሊያኖች ኢትዮጵያን ለቀው ከወጡ በኋላ ጠመንጃቸውን አስቀምጠው ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የተለያየ የግንባታ ተቋማት ገንብተው፣ ኮንትራክተር ሆነው እጅግ በርካታ ተግባራትን አከናውነዋል፡፡ ኤርትራውያን ደግሞ ከጣሊያን አስተዳደር በኋላ ለአሥር ዓመት በእንግሊዞች ቢያዙም፣ በኋላ ከኢትዮጵያ ጋር በመቀላቀላቸው፣ ጣሊያኖች እስከ አራተኛ ክፍል ኤርትራውያንን እያስተማሩ፣ ከዚያ የሙያ ትምህርት ያስተምሯቸው የነበረ በመሆኑ፣ ያንን ጣሊያን ያስተማራቸውን ዕውቀት እዚህ አዲስ አበባ ሥራ ላይ በማዋላቸው ለከተማዋ ዕድገት የበኩላቸውን አበርክተዋል፡፡
ከኃይለ ሥላሴ በኋላ ወደ ሥልጣን የመጣው ደርግ በዋናነት የጦርነት እንጂ የልማት ዘመን ለማለት የሚያስደፍር ባይሆንም፣ በርካታ ባለሀብቶች በስፋት ይዘው ያለ ሥራ ያስቀመጡትን መሬት ደርግ በማኅበር ለተደራጁ ማኅበራት በማደል፣ ዜጎች ካላቸው ዝቅተኛ ገቢ በመቆጠብ ቤቶችን በመሥራት የማኅበር ቤቶች ለከተማው ዕድገት ትልቅ አበርክቶ ነበራቸው፡፡
የኪራይ ቤቶች አስተዳደርም መሥራት በሚገባው ልክ ያልሠራ ሲሆን፣ ነገር ግን በመጠኑም ቢሆን ግንባታዎች ተካሂደዋል፡፡
የአዲስ አበባ አስገራሚ ዕድገት በኢሕአዴግ ዘመን
በአንድ ወቅት አስገራሚ የሚባል ጥናት ተካሂዶ ነበር፡፡ ይህ ጥናት የተካሄደው በዓለማችን ባሉ አገሮች ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ትልቁ ከተማና ሁለተኛው ትልቅ ከተማ ያለውን ልዩነት ለማየት የተሞከረበት ጥናት ነው፡፡
በዚህ ጥናት ከኢትዮጵያ ውጭ ባሉ አገሮች በመጀመርያው ትልቅ ከተማና በሁለተኛው ትልቅ ከተማ ያለው ልዩነት ትልቁ ሁለት እጥፍ ሆኖ ሲገኝ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን በአዲስ አበባና በናዝሬት (አዳማ) መካከል ያለው ልዩነት የሃያ እጥፍ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
ይህ የሆነው አሁን ተግባር ላይ ባለው ሕገ መንግሥት መሠረት ላለፉት 30 ዓመታት የብሔር ፖለቲካ እየገነነ በመምጣቱ፣ ባለሀብቶች ከአዲስ አበባ ውጪ ኢንቨስት ማድረግ ፍላጎት በማጣታቸው፣ በክልሎች የብሔር ቡድን የበላይነት በመግነኑና የዚያ ብሔር አባል ያሆኑ ሰዎች በዚህ ክልል እንኳን ሀብታቸውን ሊያፈሱ ይቅርና መኖር እንኳን አስቸጋሪ እየሆነ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመምጣቱ፣ ከላይ በተጠቀሰው ጥናት መሠረት በአዲስ አበባና በሁለተኛዋ ትልቅ ከተማ አዳማ መካከል ይህን ያህል የዕድገት ልዩነት ለሚዘገብ ችሏል፡፡
በሌላ አነጋገር ክልሎች ኢትዮጵያ አካል ናቸው፡፡ ነገር ግን ላለፉት 30 ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚደረገው ልማት ተገቢ ድርሻቸውን ማግኘት አልቻሉም፡፡ የገጠር መሬት መሸጥ አለመቻል፣ ገበሬው ከፍተኛ የባለቤትነት ስሜት ተሰምቶት ጉልበቱንና ገንዘቡን መሬቱ ላይ እያፈሰሰ ለራሱም ለአገሩም እሴት መፍጠር አለመቻሉ፣ በተቃራኒው ደግሞ አዲስ አበባ መሬት እንደ ልብ መሸጥ መቻሉ ለአዲስ አበባ ዕድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡
የሚገርመው ለውጥ መጣ ከተባለ ይኼው ሦስት ዓመት ተኩል ቢሞላውም፣ ይህንን ሁኔታ ከመሠረቱ ሊቀየር የሚችል ምንም ተግባር አልተከናወነም፡፡ በኢሕአዴግ ዘመን ሸገር በዚህ ፍጥነት ማደግ የቻለችው መንግሥት ፈልጎ ሳይሆን፣ በሕገ መንግሥቱና በኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው የዘር ፖለቲካ ነው፡፡
‹‹አቃፊ ማንነት›› በሚለው በ2012 ዓ.ም. ለንባብ በበቃው መጽሐፌ ላይ ‹‹ሕገ መንግሥቱና የአዲስ አበባ ፈጣን ዕድገት›› በሚል ርዕሰ ሰፊ ትንታኔ ያቀረብኩ ሲሆን፣ የተወሰኑትን እዚህ ላይ ልጥቀስ፡፡ አዲስ አበባ በዋናነት በኢሕአዴግ ዘመን በከፍተኛ ፍጥነት ማደግ የቻለችው ኅብረ ብሔራዊ መሆኗ ነው፡፡ የመጣውን ኢትዮጵያዊ ሁሉ ‹እንኳን ደህና መጣህ› ብላ የምትቀበል ከተማ መሆኗ፣ ማንኛውም ዜጋ ላፈራው ሀብት ከሌሎች ክፍሎች የተሻለ ጥበቃ ማግኘቱ፣ ዜጎች ያለ ፍርኃት ሀብታቸውን እንዲያፍሱ ምክንያት ሆኗል፡፡
በኢትዮጵያ ያሉ ሁሉም ባንኮች በመላው ኢትዮጵያ ቅርንጫፍ እየከፈቱ ያሰባሰቡትን ሀብት በዋናነት እዚህ አዲስ አበባ ለብድር ማቅረባቸው፣ ብሔራዊ ባንክ አገሪቱን በዞን ከፋፍሎ የዚህ ዞን ገንዘብ ከዚህ ዞን እንዳይወጣ፣ እዚሁ ለብድር ይቅረብ አለማለቱ በአገሪቱ በባንኮች አማካይነት ከፍተኛ የካፒታል ማሸሽ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡ አዲስ አበባ የሁሉም ነገር ማዕከል መሆኗ ለዕድገቷ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ የገንዘብ፣ የንግድ፣ የሕክምና፣ የአየርና የምድር መጓጓዣ ማዕከል ከመሆኗ በተጨማሪም ወደ የትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል የሚጓዝ ሰውም፣ ዕቃም አዲስ አበባን አቋርጦ ለማለፍ ስለሚያስገደድ ለከተማዋ ተጨማሪ ገቢ መፍጠር ተችሏል፡፡ በተጨማሪም ሕገወጥ ንግድ ወይም የገንዘብ ዝውውር በአጠቃላይ ከገንዘብ ጋር የተገናኙ ወንጀሎች ሁሉ ማዕከላቸው አዲስ አበባ ነው፡፡ ለከተማዋ ዕድገት ሌላ ትልቅ አበርክቶ ያላቸው በዋናነት ከተማዋ ውስጥ ተወልደው ያደጉ ዜጎች ሳይሆኑ ከገጠር የመጡ ዜጎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ማኅበረሰቡን ስለማያውቁት ያለ ፍርኃትና ያለ ኃፍረት ኔትወርክ እየዘረጉ ከፍተኛ ሀብት ማግበስበስ ችለዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በከተማው ውስጥ ያሉ ባለሀብት የተባሉት ሁሉ የገጠር ሰዎቸ ናቸው፡፡
በኢሕአዴግ ዘመን በተለይ ከምርጫ 97 በኋላ ኢሕአዴግ ታይቶ የማይታወቅ ሕዝባዊ ማዕበል ያስተናገደ በመሆኑ፣ በዚህ ተቃውሞ የደነገጠው ኢሕአዴግ የከተማውን ሕዝብ ዝም ለማሰኘት እጀግ በሚገርም ሁኔታ የግንባታ ማዕበል ተካሂዷል፡፡ በዚያው ልክ ሌብነቱም ሙስናውም በሚያስፈራ ሁኔታ በመባባሱና ሌብነትን የሚፀየፍ ሥርዓት በመጥፋቱ፣ ከዚህ በተገኘ ሀብት ከተማዋ እንኳን ከውጭ ለመጣ ዜጋ እዚህ ለምንኖረው ዜጎች እንኳን በሚገርም ሁኔታ ዕድገት አሳይታለች፡፡
በኢትዮጵያ ያሉ የሪል ስቴት ኩባንያዎች 99 በመቶ እዚህ አዲስ አበባ በመገኘታቸው፣ እነሱም የዳያስፖራውን ገንዘብ እየሰበሰቡ አስደናቂ ልማት አካሂደዋል፡፡
በከተማው ውስጥ የሚደረገው የልማት እንቅስቃሴ ያለ ማቋረጥ እየጨመረ በመምጣቱ ማዘጋጃ ቤታዊ ገቢም ጨምሯል፡፡ ይህንን የማዘጋጃ ቤት ገቢ ዕድገትን በተመለከተ ከ2009 ዓ.ም. እስከ 2013 ዓ.ም. ያለውን የገቢ ዕድገት ብንመለከት አዲስ አበባ በ2009 ዓ.ም. 31 ቢሊዮን ብር በጀት የተያዘላት ሲሆን፣ በ2013 ደግሞ 61 ቢሊዮን ብር ተይዞላታል፡፡ ይህ ማለት የአዲስ አበባ ገቢ በአምስት ዓመት ውስጥ በእጥፍ አድጓል፡፡ በዚህ የተነሳ የተዋቡ የክፍለ ከተማ ሕንፃዎች፣ መንገዶች፣ ማሳለጫዎችና ለቁጥር የሚታክቱ የልማት ሥራዎች ተካሂደዋል፡፡
በጣም የሚገርመው የማዘጋጃ ቤት ገቢ በዚህ መጠን ሲጨምር፣ በተጨማሪም የከተማዋ የንግድ እንቅስቀቃሴ በከፍተኛ ደረጃ በመጨመሩ በከተማው ኗሪ ላይ እጅግ የሚያስፈራ የኖሮ ውድነት ተፈጥሯል፡፡ ማዘጋጃ ቤት በዚህ ደረጃ ገቢ ሲጨምር የመንግሥት ሠራተኛው ገቢ መጨመር አለመቻሉ፣ ሠራተኛው ኑሮውን ለማሸነፍ ወደ ሕገወጥ ተግባር በመሰማራቱ በአሁኑ ጊዜ በአገራችን የሙስና ደረጃ እጅግ የሚያስፈራ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡
በአጠቃላይ የአዲስ አበባን ዕድገት ስንገመግመው በኢሕአዴግ ብልፅግና ዘመን ጤነኛ በሆነ መንገድ የተገኘ ዕድገት ብለን ልንጠራው አንችልም፡፡ በሕወሓት/ኢሕአዴግ ዘመን በከተማው ዳር ዳር ሰፊ የቤት ግንባታ የተካሄደበት ምክንያት መሀል የሚኖረውን የከተማው ነዋሪ ወደ ዳር በመውሰድ፣ መሀሉን ለትግርኛ ተናጋሪዎች እንዲሆን ታስቦ የተደረገ ልማት ነው፡፡ ይህንን መረጃ ያገኘሁት በጊዜው ከራሳቸው ከፍተኛ የሕወሓት አመራር ከነበሩ ሰዎች ነው፡፡
ቻይና ውስጥ ማንኛውም ሰው የፈለገውን ሀብት ማፍራት ይችላል፡፡ ነገር ግን ላፈራው ሀብት ግብር የከፈለበትን ደረሰኝ በማንኛውም ጊዜ ሲጠየቅ ማሳየት መቻል አለበት፡፡ ቻይና ውስጥ ማንኛውም ሰው ምንጩ ያልታወቀ ሀብት ይዞ በተዓምር መገኘት አይችልም፡፡ ይዞ ከተገኘ በፈጣን ፍርድ ሀብቱ ይወረሳል፡፡
እኛ አገር ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም ባለሀብቶች ተጠርተው ‹‹ካፈራችሁት ሀብት ጋር የሚቀራረብ ግብር የከፈላችሁበትና ሌሎችን ሰነዶች አሳዩ ተብለው ቢጠየቁ አንዳቸውም ጤነኛ ሆነው አይገኙም፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የሌለ፣ በሌሎች አገሮች ውስጥ በስፋት እየተሠራበት ያለ አሠራር የንብረት ግብር (Property Tax) ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ከ50 ሺሕ እስከ 100 ሺሕ ብር የሚያወጣ ቤት ውስጥ እየኖሩ፣ የሚኖሩበት ቤት ለከተማው ዕድገት ምንም አስተዋጽኦ እያበረከተ አይደለም፡፡ ወይም ደግሞ አንዳንድ ሰዎች ያለ በቂ ጥናት ሕንፃ ገንብተው ቤቱ ካልተከራየ ለማዘጋጃ ቤት ምንም ገቢ አያመነጭም፡፡ ይህ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ መንግሥት የንብረት ታክስ ሰብስቦ የመንግሥት ሠራተኞችን ሕይወት መለወጥ አለበት፡፡ በአሁኑ ጊዜ የብዙ የወላጆች ችግር ለልጆቻቸው ትምህርት ቤት የሚከፍሉት ገንዘብ ነው፡፡ መንግሥት መሬቱን ሁሉ እየሸጠ ገንዘብ መሰብሰቡን ትቶ በየሠፈሩ ሰፋፊ የሕዝብ ትምህርት ቤቶች እንዲገነቡ ማድረግ አለበት፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ አንዳንድ መንደሮች ውስጥ ምንም ክፍት መሬት ባለመኖሩ፣ ለትምህርት ቤት መገንቢያ የሚሆን ቦታ ፈልጎ ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡
የግል ባንኮች ከመላው ኢትዮጵያ በሰበሰቡት ገንዘብ እጅግ የሚያምሩ ሕንፃዎች ገንብተዋል፣ እየገነቡ ነው፡፡ እነዚህ ሕንፃዎች ለማዘጋጃ ቤት ትልቅ የገቢ ምንጭ ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ገንዘብ እየለመኑ እጀግ የተዋቡ ፓርኮች ገንብተዋል፡፡ ፓርኮቹን ያየ አንድ ቱሪስት ከአዲስ አበባ ወጣ ሲል የሚያየው በጭቃ የተሠራ ቤትና የኩበት ፎቅ ነው፡፡ ይህ የሚያሳየን ያልተመጣጠነ ዕድገት መኖሩን ነው፡፡
በነገራች ላይ በአንድ አገር ያልተመጣጠነ ዕድገት መኖር አዲስ ነገር አይደለም፡፡ በብዙ አገሮች ያልተመጣጠነ ዕድገት ማየት የተለመደ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን እጅግ የተለጠጠ መሆኑ ነው ሊያሳስበን የሚገባው፡፡
እንደ ሩዋንዳና ኡጋንዳ ባሉ አገሮችም ይህ ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ ሩዋንዳና ኮንጎ ውስጥ በማዕድን ሀብት ከፍተኛ ገቢ የሚያገኙ ሰዎች መኖሪያቸው ኪጋሊ ነው፡፡ ምክንያቱም ሩዋንዳ ሰላም የሰፈነባትና በሕግ ሥርዓት የምትመራ አገር ነች፡፡ ሰላም ያለበትን ቦታ እንኳን ጤነኛ ሰው ሌባም ያለ ሥጋት ገንዘቡን ሥራ ላይ ለማዋል አይሠጋም፡፡
በእኔ እምነት የአዲስ አበባ ፈጣን ዕድገት ከቀሪ የኢትዮጵያ ክፍል ጋር ሲነፃፀር ጤነኛ ያልሆነ ዕደገት እንደሆነ ማንም ሊመሰክረው የሚችለው ነው፡፡ በጊዜ መፍትሔ ካልተፈለገለት የመጨረሻው ውጤት ሕዝባዊ ቁጣንና አስከፊ የእርስ በርስ ጦርነት ሊያስነሳ ይችላል፡፡ በመሆኑም ሥልጣን በእጄ ይዣለሁ የምትሉ ሁሉ ለመፍትሔ ብትረባረቡ መልካም ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡