Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አዲሱ የከተማ አስተዳደር ቃል የገባውን በተግባር ያሳይ!

አዲሱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ በአዲስ አበባ ከተማ ተፈጸሙ በተባሉ ሕገወጥ የመሬት ወረራና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ደረስኩበት ያለውን መረጃ ሰሞኑን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ዘርፉና ከመሬት ማኔጅመንት ጋር የተያያዙ ችግሮች አስተዳደሩ ከገለጸው በላይ ስለመሆናቸው ባይጠረጠርም አሁን ባለው ደረጃ ችግሩን እንዲህ ባለ መልኩ ማቅረቡ በመልካም ሊወሰድ ይችላል፡፡

በመሬት ዝርፊያና ሕገወጥ ተግባራት ውስጥ እጃቸውን ያስገቡ የመንግሥት ተሿሚዎችም ሆኑ ግለሰቦች ለሕግ የሚቀርቡ ስለመሆኑም ይህ ሰሞናዊው የአስተዳደሩ መግለጫ አመልክቷል፡፡ ከመረጃው መገንዘብ እንደሚቻለውም የአስተዳደሩ የመሬት ማኔጅመንት የሥራ ኃላፊዎችና በየደረጃው ያሉ ሹማምንት፣ እንዲሁም ከእነሱ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ተጠርጣሪዎች መካከል በቁጥጥር ሥር የዋሉም መኖራቸውም ተጠቁሟል፡፡ በዚህ ወንጀል የተሳተፉ ጥቂቶች አለመሆናቸውን ግን ልብ ይሏል፡፡ ለማንኛውም በአዲሱ መንግሥት ምሥረታ ማግሥት የሰማነው ዜና ለአዲሱ የከተማ አስተዳደር ይህንን መረጃ ከማቅረብ ባሻገር ለራሱም የመጀመርያ ሊባል የሚችል የቤት ሥራ ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡ ለዓመታት የከተማዋ መሬት ሲዘረፍ፣ በሕገወጥ መንገድ እየተከለለ ሲቸበቸብ፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ደላሎችና አልጠግብ ባዮች ለመሬት ዋጋ እየተመኑ ምዝበራውን ሲያጧጡፉ ነበርና የሰሞኑ የአስተዳደሩ መረጃም ከቀደመው የተለየ መሆኑን የምንመሰክረው ወንጀለኞችን ለሕግ ሲያቀርብ ነው፡፡ ዋናው መፈተኛውም መሆን ያለበት ይህ ነው፡፡ ይህንን ለማለት የሚያስደፍረው ከዚህ ቀደም የከተማዋን መሬት እንደ ግል ዕቃ ሲቸበችቡ፣ ሲያስቸበችቡና ሲደልሉ የነበሩ የወንጀሉ ተሳታፊዎች ‹‹ዕርምጃ ተወሰደባቸው›› ሲባል ባለመሰማቱ ነው፡፡ ስለዚህ የዘረፋውን መረጃ ብቻ ሳይሆን፣ የዘረፋው ተዋንያኖችን ለሕግ ማቅረብና ለሌሎች ትምህርት እንዲሆን ማድረግ ካልተቸለ የመሬት ዘረፋውን ብቻ መናገር ግብ አይሆንም፡፡ ያላግባብ በሕገወጥ መንገድ የተወሰደ መሬት ሕጋዊ እንዲሆን ያደረጉ፣ ማንነቱ በማይታወቅ ሰው ስም ካርታ የሰጡ፣ ካርታ አዘጋጅው መሬት ያደሉ፣ በካርታ ላይ ካርታ እንዲሰጥ ያደረጉ፣ ሁሉ ተጠያቂዎች ናቸው ከተባለ ሕግ ፊት መቅረብ አለባቸው፡፡ እንደ ከዚህ ቀደሙ ‹‹በመሬት ዘረፋው የባለሥልጣናት እጅ አለበት፣ እጃቸውን ያስገቡ አካላት ለፍርድ ይቀርባሉ››፣ ወዘተ የሚለው ዜና፣ ከዜናነት ያልዘለለ ነበርና አሁን ከዜና ባሻገር ወንጀለኞችን ለፍርድ ስለመቅረባቸው አዲሱ አስተዳደር በተግባር ማሳየት አለበት፡፡

በአዲስ አበባ በመሬት ዘረፋ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች በተደጋጋሚ በተለያዩ መንገዶች በስፋት የመገለጻቸውን ያህል ‹‹የወንጀሉ ፈጻሚዎች ለምን ለሕግ አይቀርቡም?›› የሚለው ጥያቄ በአግባቡ ሊመለስ ይገባል፡፡ እነዚህ በቡድንና በኔትወርክ ጭምር ተሳስረው ጡንቻቸውን ያፈረጠሙ ሰዎችን ወደ ሕግ ለማቅረብ፣ እዚያም አካባቢ ተመሳሳይ ችግር ኖሮ ከሆነም ተጠያቂነቱ የሕግ አካላትንም ሊመለከት ይችላል፡፡  

ከሕገወጦች ባህሪ አንፃር ደግሞ ወንጀላቸውን ለመሸፈን በሕገወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ አፍ ማስያዣ ያደርጉታልና በዚህ መንገድ ተጠቅመው ነገሩን አፍነውት ሊሆን እንደሚችል መጠርጠሩ ክፋት የለውም፡፡

ስለዚህ አዲሱ የከተማው አስተዳደር፣ ስለአዲስ አበባ የመሬት ዘረፋና ስለዘረፋው ሁኔታ፣ እንዲሁም ተዋንያኖች በነገረን ልክ የአዲስ አበባን መሬት ያላግባብ የተቀራመቱ፣ ይህንንም ሕጋዊ እንዲሆን ሁኔታዎችን ያመቻቹ፣ ሕጋዊ ይዞታ ለማስመሰል ሥልጣናቸውንና የተመደቡበትን ኃላፊነት የተጠቀሙ ሁሉ ለሕግ ቀርበው ሕጋዊ ዕርምጃ መውሰዱን ሊያረጋግጥልን ይገባል፡፡ ወንጀለኞች መቀጣጫ ሆነው ካልታዩ አሁንም ዘረፋው እንዲቀጥል መፍቀድ ይሆናልና ሕገወጦችን ለፍርድ የማቅረቡ ነገር ወሳኝ ጉዳይ ሆኖ መታየት አለበት፡፡

በወረራና በሕገወጥ መንገድ ከተያዙ መሬቶች ምን ያህሉ ወደ መሬት ባንክ እንደገባ ከሰሞኑ መረጃ በአኃዝ የተቀመጠ ነበር፡፡ አሳዛኙ ነገር ግን ባለፈው አንድ ዓመት ወደ መሬት ባንክ ከገባው ውስጥ ተመልሶ የሌቦች ሲሳይ የሆነ መሬት መኖሩ መሰማቱ ነው፡፡ ስለዚህ ሁለተኛው የአስተዳደሩ ፈተና የሚሆነው እነዚህን መሬቶች በአግባቡ ማስተዳደርና ዳግም የሌቦች ሲሳይ ላለመሆኑ ማረጋገጫ መስጠት ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም በሕጋዊ መንገድ ለልማት የሚውሉበትን አሠራር ቀርፆ ከቀድሞው የተለየና የተሻለ ሥራ እየሠራ መሆኑን ማሳየት ካልቻለ እርሱም ነገ ተረኛ ተጠቂ መሆኑ እንደማይቀር በማሰብ መሬት ተዘረፈ በሚል መረጃ ብቻ መቆየት እንደሌለበት መታወቅ ይኖርበታል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት አስተዳደር አሰጣጥና አጠቃላይ ከመሬት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ብዙውን ጊዜ ሲያወሳሰቡ የሚታዩት ግልጽ የሆነ አሠራር ስለሌለም ጭምር መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በመሆኑም የማንኛውም የመሬት ነክ ጉዳዮች አሠራራቸውን ግልጽ ማድረግ፣ ለልማት የሚሰጥ ቦታ በሕጋዊ የመንገድ የተላለፈ ስለመሆኑ በሕዝብ ማስታወቂያ ጭምር በማሳወቅ ሌብነቱ እንዲቀንስ የሚረዳ በመሆኑ ይህንንም መተግበር የአዲሱ ካቢኔ የቤት ሥራ መሆን አለበት፡፡

ሌላው መፈታት ያለበት ችግር የተጋነነ የሊዝ ዋጋን ማስቀረት ነው፡፡ ያለውን መሬት መጠን በመለካት ለምን አገልግሎት መዋል እንደሚገባ በመለየትና ለልማት የሚጠየቀው መሬት ስለመተላለፉ ማረጋገጥ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ላለንበት የዋጋ ንረት የመሬት ዋጋ አንዱ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ኢንቨስትመንትን በቀላሉ ለማሳለጥ አንዱ እንቅፋት ይኼው ከመሬት አቅርቦት ጋር የተያያዘ በመሆኑ የሊዝ ዋጋ ለልማቱ እንቅፋት እንዳይሆን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ አንድ አገር ካሬ ሜትር በሊዝ ዋጋ 300 እና 400 ሺሕ ብር የሚሰጥበት ቁማር መቅረት አለበት፡፡

በካሬ ሜርት ይህንን ያህል ዋጋ ተሰጥቶ የኢንቨስትመንቱ ወጪ ምን ሊሆን ነው? ለመሬት ይህንን ያህል ዋጋ ተከፍሎ የሚደረግ ኢንቨስትመንት ቢኖር እንኳን የኢንቨስትመንቱን ወጪ ለመመለስ ‹‹አልሚው›› አገልግሎቱን ወይም ምርቱን በከፍተኛ ዋጋ ማቅረቡ አይቀርምና ይህ ደግሞ ለዋጋ ንረት ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ማሰቡ መልካም ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ በፊት ከነበረው አሠራር የተለየ መንገድ በመከተል እንዲህ ላሉ ችግሮች መፍትሔ መስጠትም አሁንም የአዲሱ ካቢኔ የቤት ሥራ ሲሆን፣ የሊዝ ፖሊሲውንም መልሶ መፈተሽም አስፈላጊ መሆኑ መዘንጋት የሌለበት ጉዳይ ነው፡፡  

ስለዚህ አዲሱ ካቢኔ ራሱ የሚፈተንበት አጀንዳ በራሱ አቅርቧልና የእስከ ዛሬው ውንብድና እንዳይደገም እርሱ የሚሠራውንም በተጨባጭ ማሳየት አለበት፡፡ ምክንያቱም ችግሩ ይህንን ይመስላል ካለ መፍትሔውም ከእርሱ የሚጠበቅ ስለሚሆን ነው፡፡

በጉቦና በእከክልኝ ልከክልህ ወይም ሥልጣንን መከታ በማድረግ ከማስተር ፕላን ውጪ የሚካሄዱ ግንባታዎች የከተማዋን ምን ያህል እንዳበለሻሻት ይታወቃልና ይህንን ሕገወጥ ተግባር ማስቆምና እንዳይደገም ማድረግ ከአስተዳሩ ቀጣይ ሥራዎች የሚጠበቅ  ነው፡፡  

ዛሬ ጥቂት የማይባሉ ሕንፃዎች ማስተር ፕላኑ ከሚፈቅደው ውጪ ሲገነቡ፣ ለአረንጓዴ ሥፍራነት የተከለሉ ቦታዎች ጭምር ጉቦ ለሰጡ ስግብግቦች እንደ ገፀ በረከት ሲበረከት ዓይቶ እንዳላየ መሆን አሁን የማይሠራ መሆኑን በተጨባጭ ማረጋገጥ ይገባል፡፡ እንዲህ ባለው መንገድ የተሠሩ ግንባታዎች ካሉ ያለ ርኀራኄ ዕርምጃ እንዲወሰድባቸው ካልተደረገ ነገም ላለመደገሙ እርግጠኛ መሆን ስለማይቻል እንዲህ ያሉ ነገሮችን ማሰብም የመሬት ዘርፉን ለመቆጣጠር ይረዳሉ፡፡

የመሬት ጉዳይ ከተነሳ የከተማችን ነዋሪዎች ቁልፍ ችግር ከዚሁ የመሬት ማኔጅመንት ጋር ይያያዛል፡፡ ዜጎች በአቅማቸው ጎጆ እንዳይቀልሱ ትልቁ እንቅፋት ሆኖ የቆየው የግንባታ ቦታና የሊዝ ዋጋ እጅግ የተጋነነ ሆኖ መቆየቱ ነው፡፡ የሊዝ ጨዋታው 99 በመቶ የሚሆነውን ቤት ፈላጊ የማይመለከት በመሆኑ ዜጎች በአቅማቸው የቤት ባለቤት መሆን አልቻሉም፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ለጋራ መኖሪያ ቤቶች የሚሆኑ ቦታዎችን በተመጣጠነ ዋጋ እንዲቀርብ ማድረግና ዜጎች የመኖሪያ ቤት ባለቤት የሚሆኑበት ዕድል መፍጠር ግድ ነው፡፡

አሁን ባለንበት ሁኔታ ለቪላና ለቅንጡ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ሳይሆን፣ ዜጎች በጋራ ሊኖሩበት የሚያስችል ትልልቅ አፓርታማዎችን ለመገንባት የሚውሉ ቦታዎችን መለየትና ዝግጁ ማድረግም የዚሁ አዲሱ አስተዳደር ሥራ ሊሆን ይገባል፡፡ በአጭሩ የመሬት ዘርፉ አስተዳደርና አጠቃላይ ማኔጅመንቱ ግልጽ የሆነ አሠራር ይኑረው፡፡ የቀደሙ ብልሹ ታሪኮች እንዳይደገሙ ይሁን፡፡ በዚህ ረገድ የታየውን ለውጥ አዲሱ አመራር ያሳይ፡፡ ካልሆነ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ እርሱም ተጠያቂ ይሆናል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት