Saturday, July 13, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከ1.1 ቢሊዮን ብር በላይ የኢንቨስትመንት ካፒታል ያላቸው ሁለት ኩባንያዎች ሥራ ሊጀምሩ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከ1.1 ቢሊዮን ብር በላይ የኢንቨስትመንት ካፒታል ካላቸው ሁለት ኩባንያዎች ጋር፣ በድሬዳዋና በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ሥራ እንዲጀምሩ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረመ፡፡

 

ስምምነቱ ኤል አውቶ ኢንጂነሪንግና ትሬዲንግ ከተባለ የአገር ውስጥ መኪና መገጣጠሚያ ድርጅትና ዲሚትሪዮስ ካምፑሪስ ከተባለ የግሪክ ልብስ አምራች ድርጀት ጋር፣ በኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ መሥሪያ ቤት ሐሙስ ጥቅምት 11 ቀን 2014 ዓ.ም. ተደርጓል፡፡

ኤል አውቶ ኢንጂነሪንግና ትሬዲንግ የተባለው ድርጀት በኢስተርን ኢንዱስትሪ ፓርክ መኪና በመገጣጠም ለአገር ውስጥ ገበያ የሚያቀርብ ድርጅት እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ ባለፈው ዓመት ተጠናቆ ወደ ሥራ በገባው የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ 700 ሚሊዮን ብር የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ አቋቁሞ ወደ ሥራ ይገባል ተብሏል፡፡ ኤል አውቶ በድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ 11 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ የሚይዝ ሼድ ለመከራየት የሚያስችለውን ስምምነት ከኮርፖሬሽኑ ጋር ፈጽሟል፡፡ መገጣጠሚያ ድርጅቱ በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር 400 ዜጎች ጊዜያዊና ቋሚ የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ በዓመት 9,000 መኪኖች ለአገር ውስጥና ለምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ገበያ እንደሚያቀርብ ተገልጿል

ኮርፖሬሽኑ ሁለተኛውን ስምምነት በግሪካዊው ባለሀብት ስያሜ ከተቋቋመው የዲሚትሪዮስ ካምፑሪስ (ካምቦቴክስ) ከተባለው የልብስ አምራች ድርጅት ጋር የፈጸመ ሲሆን፣ ድርጅቱ በቦሌ ለሚ የኢንዱስትሪ ፓርክ 18,600 ካሬ ሜትር የለማ መሬት ላይ በ486.5 ሚሊዮን ብር (11 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር) የልብስ አምራች ድርጅት እንደሚያቋቁም ተገልጿል፡፡

ዲሚትሪዮስ ከ15 ወራት በኋላ ሙሉ ለሙሉ ገንብቶ ያጠቃልዋል ተብሎ የሚጠበቀው የማምረቻ ፋብሪካ ሼድ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባ አንድ ሺሕ በላይ ቋሚና ጊዚያዊ ሠራተኞችን ለመቅጠር ዕቅድ የተቀመጠ ሲሆን፣ ምርቱንም  በአውሮፓ በሚገኙ 24 ሱቆቹና አዳዲስ በሚከፍታቸው ሱቆች ለደንበኞች እንደሚያከፋፍል በስምምነቱ ወቅት ተገልጿል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ ከሁለቱ ድርጅቶች ጋር በተደረገው ስምምነት ወቅት እንደተናገሩት፣ ከአንድ ወር እስከ ዓመት ባለ ጊዜ ውስጥ የድርጅቶቹ ሰነድ በኮርፖሬሽኑ ሲፈተሽ ቆይቷል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ካለፈው በጀት ዓመት ጀምሮ የአገር ውስጥና የውጭ ድርጅቶችን ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለማስገባት ጠንከር ያሉ ሥራዎች እንደተከናወኑ የገለጹት አቶ ሳንዶካን፣ የውል ስምምነቶቹም የዚህ ጥረት አካል ውጤት ናቸው ብለዋል፡፡

በድሬዳዋና በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ሥራ የሚጀምሩት ሁለቱ ኢንቨስትመንቶች አጠቃላይ ካፒታላቸው 1.18 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ የቂሊንጦን ጨምሮ በሌሎቹ የመንግሥት የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚያለሙ ኢንቨስተሮች ስምምነት በቀጣይ ሳምንታት እንደሚፈጸም በስምምነቱ ወቅት ተጠቁሟል፡፡

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የትራንስፎርሜሽንና የዋና ሥራ አስፈጻሚ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ ማሞ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ በተያዘው ሳምንት ከተደረጉት ስምምነቶች በተጨማሪ በቀጣዩ ሳምንት ውስጥ በፋርማሲዩቲካልስ ዘርፍ ለመስማማት ከሚፈልጉ ድርጅቶች ጋር ስምምነቶች ይደረጋሉ፡፡

በተለይ በመንግሥት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ኢንቨስት ለማድረግ የሚንቀሳቀሱ የውጭና የአገር ውስጥ ባላሀብቶች እንቅስቃሴ ተቀዛቅዟል የሚባል እንዳልሆነ ገልጸው፣ ሆኖም ባለፉት ሁለት ዓመታት ከኮቪድ-19 ወረርሺኝ ጋር ተያይዞ የፕሮሞሽና ተያያዥ ሥራዎች እንቅስቃሴ እንደተገደበ አስታውቀዋል፡፡

በመደበኛ አሠራር አንድ ኢንቨስተር ለማልማት በሚያደርገው እንቅስቃሴ ከመሬት ጥያቄ አንስቶ እስከ ማምረት ባለው ሒደት ውስጥ የሚያጋጥሙ ቢሮክራሲዎች የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን ረዥም ጊዜ እንዲወስድ ያደርጋል ያሉት አቶ አዲሱ፣ ሆኖም  በመንግሥት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ከተዘጋጁት የተጠናቀቁ ሼዶች አንስቶ የመሠረተ ልማት ችግሮች የተስተካከሉ በመሆናቸው ኩባንያዎች በራሳቸው ማሟላት የሚጠበቅባቸውን በማከናወን በቀጥታ እንዲሠሩ የሚያስችል ዕድል እንደተመቻቸ ተናግረዋል፡፡

እንደ ኤል አውቶና ዲሚትሪስ ካምቡሪስ ያሉ ኩባንያዎች እስከ 15 ዓመታት በሚደርስ የኪራይ ስምምነት ከኮርፖሬሽኑ ጋር የሚፈራረሙበት ዕድል እንዳለ ያስታወቁት የጽሕፈት ቤት ኃላፊው፣ ይህም መንግሥት ድጎማ ታክሎበት  በአንድ ካሬ ሜትር ከሦስት ዶላር በላይ ያልሆነ ዋጋ እንደሚከፈል ገልጸዋል፡፡ የሚቀርበው ዋጋ በፓርኮቹ ላይ የወጣውን የኢንቨስትመንት ወጪ ይመልሳል በሚል ሳይሆን፣ መንግሥት አምራች ኢንዱስትሪውን ለማበረታትና ምኅዳሩን ከማስፋት አኳያ የተደረገ እንደሆነ አቶ አዲሱ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የትኛውም የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ኢንቨስተር በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ገብቶ ለማልማት ፍላጎት ሲያሳይ በኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጥያቄው ከተፈተሸ በኋላ ለኮርፖሬሽኑ እንደሚቀርብ፣ ኮርፖሬሽኑም ጥያቄውንና የአልሚዎቹን ማንነት በሚገባ በመለየት ፈቃዱን ወይም ስምምነቱን እንደሚያደርግ የተገለጸ ሲሆን፣ ሁለቱም የኢንቨስትመንት ኩባንያዎች በዚህ ሒደት ውስጥ አልፈው ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አቶ አዲሱ ለሪፖርተር አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች