ኢሰመኮ በአቶ እስክንድር ላይ ደርሷል ስለተባለው ጉዳት ማጣራቱን አስታወቀ
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ፕሬዚዳንት አቶ እስክንድር ነጋ ላይ ጥቅምት 11 ቀን 2014 ዓ.ም. ከደረሰው ጉዳት ጋር ተያይዞ የሚመለከታቸው የፍትህ አካላት ድርጊቱን አጣርተው ፈጻሚዎቹን ለሕግ አካል እንዲያቀርቡ ጠየቀ፡፡
ጉባዔው ጥቅምት 12 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው፣ አቶ እስክንድር ነጋ ጥቅምት 11 ቀን 2014 ዓ.ም. ከጠዋቱ 12 ሰዓት አካባቢ በሕግ ጥበቃ ሥር በሚገኙበት ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ውስጥ በእስረኞች ተደብድበው ዓይናቸው አካባቢና ጉልበታቸው ላይ ጉዳት እንደደረሰባቸው ከደረሱት መረጃዎችና በዕለቱ ፍርድ ቤት ቀርበው ከነበሩት የማረሚያ ቤቱ የፈረቃ ኃላፊ ጉዳት መድረሱን ለችሎቱ ከገለጹት ቃል ለማወቅ መቻሉን አስታውቋል፡፡
በሕግ ጥበቃ ሥር ያሉ ሰዎች፣ ሰብዓዊ ክብራቸውን በሚጠብቁ ሁኔታዎች የመያዝ መብት እንዳላቸው በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 21(1) እንዲሁም በዓለም አቀፉ ሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን አንቀፅ 10 በግልፅ መስፈሩን የጠቆመው ጉባዔው፣ ከዚህ በተጨማሪም የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1174/2012 ከወጣበት ዓላማ ውስጥ አንዱ፣ እስረኞች ባላቸው የአደገኝነት ባህሪ፣ ባላቸው የጉዳት ተጋላጭነት ወይም በፆታቸው እንዲሁም ከፍርድ በፊት በማረሚያ ቤት የሚቆዩ እስረኞች ሊደረግላቸው የሚገባ አያያዝን መደንገግ አስፈላጊ በመሆኑ፣ ከአዋጁ መግቢያ ለመረዳት ይቻላል ብሏል፡፡ በዚህም መሠረት እስረኞች በማረሚያ ቤት ቆይታቸው ሰብዓዊ መብታቸውን፣ ክብራቸውንና ጤናቸውን ያከበረ አያያዝ የማግኘት መብት እንዳለቸው በአዋጁ በግልፅ መመላከቱን አስታውቋል፡፡
ማረሚያ ቤቱ የእስረኞቹንና የማረሚያ ቤቱን ደንብና ሥርዓት ለማስጠበቅ እንዲሁም ፀጥታው የተከበረ ሰላማዊ የማረሚያ ቤት አካባቢ እንዲኖር ለማድረግ አስፈላጊ የሆነ የጥበቃና ቁጥጥር ሥርዓት የመዘርጋት ኃላፊነት እንዳለበት በአዋጁ በግልፅ እንደተቀመጠ ኢሰመጉ ጨምሮ አስታውቋል፡፡
ከላይ የተጠቀሱት ሕጎች በሕግ ጥበቃ ሥር ያሉ ሰዎች አያያዝ ደኅንነታቸውንና ሰብዓዊ ክብራቸው መጠበቅን መርህ ያደረገ መሆን እንዳለበት የሚያስረዳ ነው ያለው ኢሰመጉ፣ በማንኛውም ደረጃ የሚገኙ የመንግሥት አካላትም በእያንዳንዱ ተግባራቸው፣ በሕገ መንግሥቱና አገሪቱ በተቀበለቻቸው የሰብዓዊ መብቶች ሰነዶች ዕውቅና ያገኙ መብቶችን የማክበር፣ የማስከበር እንዲሁም እንዲከበሩ ሁኔታዎችን የማሟላት ግዴታ እንዳለባቸው መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
የሚመለከታቸው የፍትህ አካላት በአቶ እስክንድር ነጋ ላይ የተፈጸመውን ድርጊት በማጣራት ፈጻሚዎቹ ለሕግ አካል ቀርበው ተጠያቂ እንዲሆኑና አስተማሪ ቅጣት እንዲያገኙ በማድረግ ሁኔታውን ለሕዝብ ይፋ እንዲያደርጉ ጉባዔው ያሳሰበ ሲሆን፣ ማረሚያ ቤቱም የደረሰውን ጉዳት አስመልክቶ ተገቢውን ማጣራት በማድረግ ኃላፊነታቸውን ባልተወጡ የማረሚያ ቤት ባልደረቦች ላይ አስተማሪና ሕጋዊ ዕርምጃ በመውሰድ ሁኔታውን ለሕዝብ ይፋ እንዲያደርግ አሳስቧል፡፡
በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጥቅምት 12 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳስታወቀው፣ አቶ እስክንድር ነጋ የሚገኙበትን ሁኔታ ለማጣራት በቂሊንጦ ጊዜያዊ ማረፊያ በመገኘት፣ አቶ እስክንድር ነጋን፣ ክስተቱ ሲፈጠር በስፍራው የነበሩትን አቶ ስንታየው ቸኮልን፣ ስማቸውን ባይጠቅስም ከአቶ እስክንድር ጋር ተጋጩ የተባሉትን እስረኛ፣ እንዲሁም የማረሚያ ቤቱን አስተዳደር አካላት አነጋግሯል።
ኮሚሽኑ እንዳስታወቀው አቶ እስክንድርና ከአቶ እስክንድር ጋር ተጋጩ የተባሉት እስረኛ መካከል ከዚህ ቀደም አለመግባባት እንደነበረና እስረኛው ከተዘዋወሩበት የቃሊቲ ማረሚያ ቤት በቅርቡ የተመለሱ መሆኑንና በመካከላቸው የተነሳው የቃላት ልውውጥ ወደ አካላዊ ግጭት እንደተሸጋገረ ባደረገው ማጣራት የተገነዘበ መሆኑን አስታውቋል።
ሁለቱ እስረኞች በተጋጩበት ወቅት በአቶ እስክንድር በግራ እግር አውራ ጣት ላይ እብጠት፣ በሁለቱም ጉልበቶቻቸው ላይ የመላላጥና በቀኝ ቅንድባቸው ላይ የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው መሆኑንና በማረሚያ ቤቱ ክሊኒክ የተመላላሽ ሕክምና እያገኙ እንደሆነ ጠቁሞ፣ በአሁኑ ጊዜ በደህና ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡ በሌላኛው እስረኛ ላይም በቀኝ እጅ ጣታቸው ላይ የመፋፋቅ ጉዳት እንደደረሰባቸው ማረጋገጡንም አክሏል፡፡ ሁለቱም እስረኞች በግጭቱ በደረሰባቸው ጉዳት ክስ ለመመሥረት ፍላጎት እንደሌላቸው ለኮሚሽኑ እንደገለጹም አስታውቋል፡፡
አቶ እስክንድር የተፈጠረው ክስተት ‹‹ተራ ጠብ ነው›› ብለው እንደማያምኑና በፍርድ ቤት የምስክር ማሰማት ሒደት እያነሷቸው ባሉ መስቀለኛ ጥያቄዎችና ሌሎች ጉዳዮች ጋር የተያያዘ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት መናገራቸውንም አስታውቋል፡፡
ኢሰመኮ ከማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር ባደረገው ውይይት፣ የታሳሪዎችን ደኅንነት ስለማረጋገጥ፣ እንዲሁም በእስረኞች መካከል የሚነሱ አለመግባባቶችና ፀቦችን መከላከልና በሚከሰቱበት ጊዜ ፈጣን ዕርምጃዎችን መውሰድ የታሳሪዎችን ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነት አንዱ አካል እንደሆነና፣ ከዚህ ጋር ተያይዞ መወሰድ ባለባቸው ዕርምጃዎች ላይ መመከሩን በመግለጫው አስታውቋል።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲም (ባልደራስ) ባወጣው መግለጫ፣ በአቶ እስክንድር ላይ ስለተፈጸመው ከባድ ድብደባ ዓቃቤ ሕግ ማብራሪያ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ አቶ እስክንድር በፖሊስ ሪፈራል ሆስፒታል ጥቅምት 12 ቀን 2014 ዓ.ም. በተደረገለት የራጅ ምርመራ የግራ አውራ ጣቱ መሰበሩ መረጋገጡን በፓርቲው ድረገጽ ላይ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡