Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹በስሜት መንገድ ላይ ወጥቶ የሚወራጭና የሚፎክር ዲፕሎማት አንፈልግም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

‹‹በስሜት መንገድ ላይ ወጥቶ የሚወራጭና የሚፎክር ዲፕሎማት አንፈልግም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

ቀን:

ኢትዮጵያ ወደ ሌላ አገር ለሥራ የምትልከው ዲፕሎማት ፊት ለፊት ስለአገሩ ጥቅም የሚከራካር፣ ከስሜት ወጣ ያለ ችሎታ ያለውና መነጋገር የሚችል እንጂ፣ መንገድ ላይ ወጥቶ የሚወራጭና የሚፎክር ዲፕሎማት እንዳልሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

‹‹ምንም እንኳ አገራዊ ፍቅሩን በተለያዩ መንገዶች እንዲገልጽ ቢጠበቅበትም በተቋሙ ባሉ የተልዕኮ የሥልጣን ደረጃዎች ያለ አንድ ሠራተኛ፣ በተመሳሳይ ደረጃ ላይ ካለ አሜሪካዊ ወይም ኬንያዊ ዲፕሎማት ጋር እኩል ቆሞ መከራከር የሚችል መሆን ይኖርበታል፤›› ሲሉ የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ (አምባሳደር) ባለፈው ሳምንት በሰጡት ሳምንታዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል፡፡

ቃል አቀባዩ አክለውም ወደ ሌላ አገር የሚላክ ዲፕሎማት አቅም ያለውና የሚጠበቅበትን የሚሠራ መሆን እንደሚገባው፣ በየግብዣዎች እየተገኘ ተቃቅፎ የሚያወራ፣ በቋንቋና በዕውቀት ማነስ ወይም ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታን ባለማወቅ የሚሸማቀቅ መሆን እንደሌለበት፣ ዲፕሎማሲውም ከእንዲህ ዓይነት ልምድ መውጣት እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ታዳጊ አገር ስለሆነችና የውጭ ምንዛሪ ስለሚያስፈልጋት የአገሩን ጉዳይ በሚገባ ተረድቶ መወሰን፣ መነጋገርና ማሳመን የሚችል ዲፕሎማት እንጂ ወደኋላ ለማፈግፈግ  የሚዳዳው መሆን እንደሌለበት አስታውቀዋል፡፡

ኢትዮጵያን በውጭ አገሮች ከወከሉ ለዓመታዊ ስብሰባና ለአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና ከተጠሩ ዲፕሎማቶች ውስጥ አብዛኞቹ ቢመለሱም፣ የተወሰኑት በዚያው መቅረታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡

ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ለሪፖርተር ቅርብ የሆኑ ምንጮች እንደ ጠቆሙት፣ በሁለት ዙሮች በተካሄደው ሥልጠና ወደ አገር ቤት መምጣት ከነበረባቸው በተለያየ የሥራ ኃላፊነት ላይ ከነበሩ ዲፕሎማቶች ውስጥ 100 ያህሉ ጥሪ ተደርጎላቸው አስካሁን አልተመለሱም፡፡

ከሥልጠናው በኋላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቅርቡ ዲፕሎማቶችን እንደገና የመመደብ ሥራ እንደሚከናወን የሚጠበቅ ሲሆን፣ እሰካሁን 31 ያህል ኤምባሲዎችና የቆንስላ ጽሕፈት ቤቶች እንዲዘጉና ወደ ሌላ አገር እንዲዛወሩ አድርጓል፡፡

በዚህ መሠረት እንዲዘጉ ከተወሰነባቸው ሚሲዮኖች ውስጥ በኦማን መስካት የሚገኘው ወደ አቡዳቢ፣ በኔዘርላንድስ ዘ ሄግ የሚገኘው ወደ ቤልጂየም ብራሰልስ፣ በአየርላንድ ደብሊን የሚገኘው ወደ እንግሊዝ ለንደንና በኩዬት የሚገኘው ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ሪያድ ይዛወራሉ ተብሏል፡፡

በኢንዶኔዥያ ጃካርታ የሚገኘው ወደ ቻይና ቤጂንግ፣ በአውስትራሊያ ካንቤራ የሚገኘው  ወደ ጃፓን ቶኪዮ፣ በኩባ ሃቫና የሚኘው ወደ ፈረንሣይ ፓሪስ፣ በብራዚል ብራዚሊያ የሚገኘው ወደ ዋሽንግተን ዲሲ፣ በሲኦል ደቡብ ኮሪያ የሚገኘው ወደ ጃፓን ቶኪዮ፣ በስዊዲን ስቶኮልም የሚገኘው ወደ ጀርመን በርሊን፣ በኳታር ዶሃ የሚገኘው ወደ ሪያድ ሳዑዲ ዓረቢያ መዛወራቸው ታውቋል፡፡  

ከባህሬን ወደ ሊባኖስ ቤይሩት፣ ከታንዛኒያ ወደ ኬንያ፣ ከኮንጎ ኪንሻሳ ወደ ኡጋንዳ፣ በኮቲዲቯር፣ ከሞሮኮ፣ ከአልጄሪያ፣ ከሴኔጋልና ከጋና ወደ ናይጄሪያ አቡጃ በሚገኘው የኢትዮጵያ ሚሲዮን ሥር ይሆናሉ ተብሏል፡፡

በአሜሪካ ሎስአንጀለስ፣ ሚኒሶታና ኦቶዋ ካናዳ የነበሩትን ቆንስላ ጽሕፈት ቤቶች ወደ ዋሽንግተን ዲሲ፣ እንዲሁም በቻይና ሹዋንሹ የሚገኘው ወደ ቤጂንግ፣ በህንድ ኮችን የሚገኘው ወደ ቤጂንግ፣ በጀርመን ፍራንክፈርት የሚገኘው ወደ በርሊን፣ በቱርክ ኢስታንቡል የሚገኘው ወደ አንካራ፣ በህንድ ሙምባይ የሚገኘው ወደ ኒውደልሂ፣ በዚምባቡዌ ሐራሬ የሚገኘው ወደ ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ፣ እንዲሁም በግብፅ ካይሮ የሚገኘው ወደ ሱዳን ካርቱም መዛወራቸውን ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ዲና (አምባሳደር) በጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ የአውሮፓ ኅብረትና የአሜሪካ መንግሥት ማዕቀብ ሊጥሉ ነው ተብሎ የሚነገረውን በተመለከተ፣ ‹‹ለእኛ አገር ትልቅ ጉዳይ አይደለም፤›› በማለት፣ የእነዚህ አካላት ፉከራ በመሬት ላይ ያለውን ሁኔታ በግልጽ እያወቁ ነገር ግን ካላቸው ጥቅም የተገናኘ በመሆኑ፣ ለዚህም መልሱ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንቢ፣ አይሆንም ማለት ነው ያለበት ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...