Wednesday, June 12, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች መታወቂያ ዕድሳት በመቋረጡ አስመጪዎችና ማኅበራት ቅሬታ አቀረቡ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ሲሰጥ የቆየው የድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች መታወቂያ ዕድሳት ላልተወሰነ ጊዜ በመቋረጡ፣ በወጪና በገቢ ንግድ ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩን አስመጪዎችና የድንበር ተሻጋሪ ትራንስፖርት ማኅበራት ቅሬታቸውን አሰሙ፡፡

 

በአዲሱ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ሥር የተጠቃለለው የድንበር ተሻጋሪ ትራንስፖርት የሾፌሮች የመግቢያ መታወቂያ የተቋረጠው ዕድሳት ከጥቅምት 4 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ መሆኑን፣ የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሠሪዎች ፌዴሬሽን ዋና ጸሐፊ አቶ ደረጀ ለገሰ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

አገልግሎቱ በመቋረጡ ከአንድ ሺሕ በላይ አገር አቋራጭ ተሽከርካሪዎች ጭነት ይዘው መቆማቸውን የገለጹት ዋና ጸሐፊው፣ ለባለሥልጣኑ ጥያቄ ቢቀርብም ተገቢው ምላሽ እንዳልተገኘ አስታውቀዋል፡፡

የቅባት እህሎች አስመጪና ላኪ የሆነው አልባር ትሬዲንግ ባለቤት አቶ ተስፋዬ ጌታቸው ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ አስመጪና ላኪ ሥራ ፋታ የሚሰጥ አለመሆኑንና በጂቡቲ መግቢያ መታወቂያ ዕድሳት ምክንያት ለአሥር ቀናት ምንም ዓይነት ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ አገልግሎቱ ተቋርጧል፡፡

 አሽከርካሪዎች የጂቡቲ መግቢያ መታወቂያቸው የአገልግሎት ዘመኑ ከማለቁ በፊት ሪፖርት ቢያደርጉም ቀኑ ካለቀ በኋላ እንደሚሰጥ የገለጹት አቶ ተስፋዬ፣  ለአስመጪዎችም ሆነ ለተሽከርካሪዎች ማኅበራት ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ አገልግሎቱ መቋረጡ ቅር እንዳሰኛቸው ገልጸዋል፡፡

ከመንግሥት በኩል የተሰጣቸው ምላሽ ማኅተም ተቀርፆ ሊቀየር ስለሆነ፣ በዚህም ምክንያት ለአሥር ቀናት አገልግሎት እንደማይሰጥ መናገሩን ጠቁመዋል፡፡ በኢትዮጵያ ዋናው የወጪና የገቢ የንግድ አንቀሳቃሹ የጭነት የትራንስፖርት መሆኑን ያስረዱት አቶ ተስፋዬ፣ ተሽከርካሪዎች የወጪ ንግድ ዕቃዎችን ጭነው በመቆማቸው የውጭ ምንዛሪና ሌሎችም ኪሳራዎች እየደረሰባቸው እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል ከጂቡቲ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ዕቃዎች የሚመጡበት ቀን ሲራዘም፣ ለመጋዘን የሚከፈለው የውጭ ምንዛሪ አገርን ሊያከስር እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

የድንበር ተሻጋሪ ትራንስፖርት ማኅበራት፣ አስመጪና ላኪዎች ያለ ሥራ መቀመጣቸውን፣ ለዚህ ችግር ምላሽ የሚሰጥ አካልም መጥፋቱን አክለው ገልጸዋል፡፡

የዩኒቲ ድንበር ተሻጋሪ ትራንስፖርት ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ደረጀ ጌታቸው፣ የጂቡቲ መግቢያ መታወቂያ ከዚህ ቀደም አሽከርካሪዎች ሲቀየሩና የአገልግሎት ጊዜው ሲያበቃ በየዓመቱ እንደሚታደስ ገልጸዋል፡፡

በቅርቡ የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን በትራንስፖርትና ሎጂስቲክም ሚኒስቴር ሥር እንዲጠቃለል ከተደረገ በኋላ አዲስ የማኅተም ለውጥ እየተደረገ በመሆኑ፣ አገልግሎቱ ላልተወሰነ ጊዜ ተቋርጧል መባላቸውን ሥራ አስኪያጁ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

መታወቂያ ባለመሰጠቱ ምክንያት ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ማስወጣት እንደማይቻል አቶ ደረጀ ገልጸው፣ በጂቡቲ ወደብ ያላግባብ የተከማቹ ኮንቴይነሮችን የሚያነሱ ተሽከርካሪዎች በወቅቱ ካልደረሱ ለአገር ትልቅ ኪሳራ ሊያመጡ ይችላሉ ብለዋል፡፡

የገቢና ወጪ የንግድ እንቅስቃሴውን የሚያሳልጠውን የትራንስፖርት አገልግሎት የሚገድበው የመግቢያ መታወቂያ ዕድሳት መዘግየት፣ አፋጣኝ መፍትሔ እንደሚያስፈልገው አቶ ደረጀ ይገልጻሉ፡፡

የድንበር ተሻጋሪ የትራንስፖርት አሽከርካሪዎችና የረዳቶች የመግቢያ መታወቂያ ዕድሳት አገልግሎት በመቋረጡ፣ ከአንድ ሺሕ በላይ ተሽከርካሪዎች ጭነት ይዘው መቆማቸው ተጠቁሟል፡፡

የድንበር ተሸከርካሪዎች የትራንስፖርት ማኅበራት 70 ያህል ሲሆኑ፣ በአንድ ማኅበር ብቻ እስከ ስድስት አሽከርካሪዎች በመታወቂያ ዕድሳት አገልግሎት መቋረጥ ምክንያት ሥራ መፍታታቸውን የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ ተናግረዋል፡፡ ማኅበራቱ ከ14‚000 በላይ ተሽከርካሪዎች እንዳላቸው ተገልጿል፡፡

ማኅበራቱና አስመጪዎች ስለጉዳዩ በተደጋጋሚ ለመንግሥት ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ ትክክለኛውን ምላሽ እንዳላገኙ ተናግረዋል፡፡ የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን የደረቅ ጭነት ትራንስፖርት የቀድሞ ዳይሬክተር አቶ ዓለማየሁ ወልዴ በበኩላቸው፣ መሥሪያ ቤቱ ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ጋር ስለተዋሀደ ሒደቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ በጊዜያዊነት የመታወቂያ ዕድሳት ተቋርጧል ብለዋል፡፡

እስከ ዓርብ ጥቅምት 12 ቀን 2014 ዓ.ም. ለድንበር ተሻጋሪ ትራንስፖርት የመታወቂያ ዕድሳት መፍትሔ ይሰጠዋል የሚል እምነት እንዳላቸው ግን አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች