የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) በጋራ በመሆን በትግራይ ክልል ተፈጽሟል ስለተባለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት በጥምረት የሚደረገው ምርመራ፣ በተያዘለት ጊዜ ይፋ እንደሚደረግ ተገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)፣ ምርመራው ከጅምሩ በታቀደው መሠረት እየተከናወነ መሆኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በቅርቡ መንግሥት በተመድ የተለያዩ ተቋማት ውስጥ በከፍተኛ ኃላፊነት ላይ የሚሠሩ ሰባት ሠራተኞች በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብተዋል በማለት፣ በ72 ሰዓታት ውስጥ አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ መወሰኑ ይታወሳል፡፡
ይህንን ተከትሎ ከአገር እንዲወጡ ከታዘዙት ውስጥ በትግራይ ክልል የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምርመራ ወቅት ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ ተብለው የሚታሰቡት የድርጅቱ ኃላፊዎች እንደሚገኙበት በመጥቀስ፣ ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ መንግሥት ውሳኔውን እንዲቀይር ሲጠየቅ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ኢሰመኮና ተመድ በጥምረት በሚያካሂዱት ምርመራ ላይ የተመድ ሠራተኞች ከአገር እንዲወጡ መደረጋቸው በምርመራው ላይ ሊፈጥር ስለሚችለው ጫና፣ እንዲሁም ምርመራው ላይ ምን ዓይነት ተፅዕኖ ሊያደረስ ይችላል በሚል ሪፖርተር ጥያቄ ያቀረበላቸው የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር፣ የኃላፊዎቹ ከአገር መባረር በምርመራ ሒደቱ ላይ ምንም ዓይነት ጫና እንደማይፈጥርና ምርመራውን በታሰበለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ምርመራውን እያካሄዱት ያሉት ሁለቱ የሰብዓዊ መብት ድርጀቶች በመስከረም መጀመርያ ላይ በጋራ ባወጡት መግለጫ፣ በትግራይ ክልል የተጀመረው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምርመራ በጥቅምት 2014 ዓ.ም. መጨረሻ አካባቢ ለሕዝብ ይፋ እንደሚሆን ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡
በሌላ በኩል የአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ መስከረም 26 ቀን 2014 ዓ.ም. የትግራይ ክልል ሰብዓዊ ቀውስን የተመለከተ የውሳኔ ሐሳብ ያሳለፈ ሲሆን፣ በክልሉ ደረሰ የተባለው ሰብዓዊ ቀውስ ትርጉም ባለው መንገድ የተያዘው ወር መጨረሻ ድረስ መሻሻል ካልታየበት በተቀሰቀሰው ግጭት ተሳታፊዎች ላይ ማዕቀብ ለመጣል የጊዜ ገደብ አስቀምጧል፡፡
በተመሳሳይ የአሜሪካ መንግሥት እ.ኤ.አ ኅዳር 1 ቀን 2021 ኢትዮጵያ የአፍሪካ ግሮውዝ ኤንድ ኦፖርቹኒቲ አክት (አጎዋ) በመባል የሚታወቀውን ከታሪፍና ከኮታ ነፃ የንግድ ተጠቃሚነቷ ትቆይ አትቆይ በሚለው ጉዳይ ላይ ይወስናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የኢሰመኮና የተመድ የትግራይ ክልል የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሪፖርት በዚህ ወር መጨረሻ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የአውሮፓ ኅብረት ማዕቀብና የአሜሪካ የአጎዋ ዕድል የተጠቃሚነት ውሳኔ አንድ አካባቢ መሆናቸው ብዙዎችን እያነጋገረ ነው፡፡