Saturday, June 10, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሰሜኑ ጦርነትና የፖለቲካ አለመረጋጋት የኢንሹራንስ ዘርፉ ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል የሚካሄደው ጦርነትና ከዚሁ ጋር ተያይዞ እየተፈጠሩ ያሉ ቀውሶች ጉዳት እያደረሰባቸው ከሚገኙ የንግድ ዘርፎች አንዱ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ነው፡፡ በአንድ አገር ጦርነት በሚካሄድበት ወቅት አጠቃላይ የሚታየው ኢኮኖሚዊ ቀውስ የኩባንያዎችን ጉዞ የሚያስተጓጉልበት፣ ሊያገኙ ይችሉ የነበረውን ገቢ የሚያሳጣቸው መሆኑም ይታመናል፡፡

ከኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪውም የዚህ ሰለባ እየሆነ መሆኑ በተለያየ መንገድ እየተገለጸ ነው፡፡ በተለይ ጦርነቱ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ያሉ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ቅርንጫፎች ከሥራ ውጪ ሆነው በመቆየታቸው፣ አጠቃላይ የኢንሹራንስ አገልግሎት እንዲቋረጥ በማድረጉ የኩባንያዎቹን ገቢ አሳጥቷል፡፡ ደንበኞቻቸውንም ማገልገል እንዳይችሉ አድርጓቸዋል፡፡

የኢንሹራንስ ባለሙያው አቶ ኢብሳ መሐመድ እንደገለጹትም፣ በጦርነት ወቅት ሁሉም ቢዝነሶች የሚጎዱበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ተነጥሎ ሲታይ ጉዳቱ በተለያየ መንገድ የሚገለጽ እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡ እንደ እሳቸው ምልከታ ከወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ አንፃር በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ያሉ የኢንሹራንስ  የኩባንያዎች ቅርንጫፎች መዘጋት በእነዚያ ቅርንጫፎች በኩል የመድን ሽፋን ያገኙ የነበሩ ኩባንያዎችና ግለሰቦች ውል እንዳያድሱ ማድረጉንና ከዚህ ሊገኝ የሚችለውን ዓረቦን ማሳጣቱን ገልጸዋል፡፡ ይህ አንዱና ትልቁ ጉዳታቸው እንደሆነ የገለጹት አቶ ኢብሳ አዳዲስ ደንበኞችንም ለማፍራት ስለማይችሉ ጦርነት ባለባቸው አካባቢዎች የኢንሹራንስ ኩባንያዎች አገልግሎት ሰጥተው ገቢ የሚያገኙበትን ዕድል ያሳጣቸዋል፡፡

ሌላው የኢንሹራንስ ባለሙያ አቶ አሰግድ ገብረ መድህን ደግሞ፣ በጦርነቱ ተጎጂ ከሆኑ ቢዝነሶች ውስጥ አንዱ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው መሆኑን ተስማምተው፣ በተለይ ጦርነቱ የሚካሄድበት ቦታ እየሠፋ በሄደ ቁጥር ደግሞ ጉዳቱም እየጨመረ የሚመጣ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ በትግራይ አካባቢ ሥራቸው የተቋረጠባቸው የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ጦርነቱ ወደ አማራ ክልል በመስፋፋቱ ያሉ ቅርንጫፎችም በአካባቢው የመድን ሽፋን አገልግታቸውን እንዲያቋርጡ ማስገደዱን ተናግረዋል፡፡ በዚያ አካባቢ ያሉ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ሥራ መስተጓጎል ደግሞ አዳዲስ ደንበኞችን እንዲያፍሩና ያሉትንም ደንበኞች ነባር ውል አሳድሶ ማስቀጠል ዓረቦን መሰብሰብ እንዳይችሉ ማድረጉን አቶ አሰግድ ገልጸዋል፡፡  

የአዋሽ ኢንሹራንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጉዲሳ ለገሰ በበኩላቸው፣ በጦርነቱ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ያሉ ቅርንጫፎች መዘጋት፣ በዚያ ያለ ቢዝነሳቸውን የሚያሳጣ ከመሆኑም በላይ በቀጣይ አገልግሎቱን ለማስቀጠልም የሚያስቸግር መሆኑን ተናግረዋል፡፡   

አንዳንድ የኢንሹራንስ ኩባንዎች በትግራይ ክልል ውስጥ የራሳቸው ሕንፃ ገንብተው፣ ራሳቸው አገልግሎት ከሚጠቀሙበት የሕንፃው ክፍል ውጪ ያለውን የሚያከራዩ በመሆኑ፣ ከዚህም የሚያገኙትን ገቢ ማጣታቸው ሲታከልበት ጉዳቱን ከፍ ያደርገዋል የሚል እምነት እንዳላቸው ከእነዚሁ የኢንሹራንስ ባለሙያዎች ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ችግሩ ከአገልግሎት ውጪ በሆኑ ቅርንጫፎች ምክንያት የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዚያ አካባቢ ያሉ ደንበኞቻቸውን ቢያንስ ነባር ውላቸውን አድሰው ውል ያገኙ የነበረውን ገቢ ማሳጣት ብቻ ሳይሆን አዳዲስ ደንበኞችን በማፍራት ገቢያቸውን ለማሳደግ የያዙትን ዕቅድ የሚያሰናክል መሆኑንም ተጠቅሷል፡፡ ይህ በጦርነቱ አካባቢ ካለ ችግር ጋር በቀጥታ የሚያያዝ ጉዳት ሲሆን፣ ከዚህ ውጪ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ለኩባንያዎቹ ዓረቦን መቀነስ ምክንያት የሚሆኑ ተጨባጭ ሁኔታዎች እየታዩ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

ከዚህ አንፃር አቶ ጉዲሳ፣ ‹‹ካለፈው ዓመት ጀምሮ በነበረው ጦርነት ምክንያት ወደ አገር የሚገቡ ኩባንያዎች ያለመግባታቸው፣ ለእነሱ ከሚሰጥ የኢንሹራንስ ሽፋን ይገኝ የነበረው ዓረቦን ገቢ መቅረቱም ተጠቃሽ ጉዳት ነው፤›› ብለዋል፡፡ ስለዚህ የአዳዲስ ኩባንያዎቹ ሥራ አለመጀመርም የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ላይ ተፅዕኖ ማሳረፉንም ገልጸዋል፡፡

ሁሌም የኢንሹራንስ ዕቅድ የአገሪቱን ዕድገት የኢኮኖሚ ዕቅድ ተከትሎ የሚቀረፅ በመሆኑ፣ የአገሪቱ የልማት እንቅስቃሴ በጦርነት ሲስተጓጎል የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪውም አብሮ እንደሚጎዳ አቶ አሰግድ ገልጸዋል፡፡ ጉዳቱ በጦርነቱ አካባቢ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው አገልግሎቶች ላይ መሆኑን ያመለከቱት አቶ አሰግድ፣ ለዚህም አንድ ማሳያ ይሆናል ብለው የጠቀሱት ወቅታዊውና አገራዊ ሁኔታ አንፃር በቅርቡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንዲተገበር ትዕዛዝ የተሰጠበት የብድር ገደብ መመርያን ነው፡፡

ይህ መመርያ ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ የወጣ ስለመሆኑ በማመልከት መመርያው ከባንኮችና ከተበዳሪ ደንበኞች ባልተናነሰ ኢንሹራንስ ኩባንያዎችን ጎድቷል ይላሉ፡፡

ይህ ገደብ ከወቅቱ ጦርነት ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ ችግሮችን ለማቅለል የወጣ ቢሆንም፣ የብድር ገደቡ ኢንሹራንስ ኩባንያዎችን የሚጎዳው ባንኮች ለሚሰጡት ለእያንዳንዱ ብድር በማስያዣነት የሚቀርብ ንብረት የግዴታ ዋስትና የሚጠይቁ በመሆኑና ለንብረቱ ዋስትና የሚሰጡት ደግሞ ኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ በመሆናቸው ነው፡፡ ባንኮች ለሚሰጧቸው ብድሮች የሚይዙት የዋስትና ንብረት የኢንሹራንስ ሽፋን የሚጠይቁ በመሆኑ የብድር ገደቡ በተዘዋዋሪ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ለብድር መያዣነት ለሚቀርብ ንብረት የሚሰጡት የመድን ሽፋን ገቢ እንደሚቋረጥ ገልጸዋል፡፡

አቶ ጉዲሳም የአቶ አሰግድን ሐሳብ ተጋርተው፣ ‹‹ደንበኞች ብድር ቢፈቀድላቸውና ወደ ሥራቸው ቢሄዱ ደግሞ ለዚያ የቢዝነስ ሊገቡ ይችሉ የነበረውን የመድን ሸፋን ስለማይገቡ የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ ከዚህም አንፃር ገቢያቸው ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራል፤›› ብለዋል፡፡

ከብድር ገደቡ ጋር በተያያዘ የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ ገቢ ያጡበታል ተብሎ በዝርዝር የተጠቀሰው ሌላው ጉዳይ ኩባንያዎች ለሚያስመጡት ጥሬ ዕቃ የሚገቡት የመርከብ ትራንስፖርት ኢንሹራንስ ስለማይኖር ዘርፉ እንደሚጎዳ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ይህንኑ ዕቃ ከወደብ ወደ ማምረቻ ሥፍራ ለማድረስ ተሽከርካሪ መጠቀም ግድ ነውና እንዲህ ላሉ ጉዳዮችም ዋስትና መግባት ስለሚያስፈልግ የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ የጉዳቱ ሁኔታ ተያያዥ እንደሆነ ያመለክታል ብለዋል፡፡ በአብዛኛው የቢዝነስ እንቅስቃሴዎች ከብድር ጋር የተያያዘ ከመሆኑ አንፃር ሲታይና የብድር አሰጣጡ ደግሞ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪውን የሚመለከት በመሆኑ የብድር ገደቡ ለኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ላይም ጫና መፍጠሩን ያመለክታል፡፡  

የአቶ አሰግድ ገለጻ በዚህ ጉዳይ ላይ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ ደግሞ፣ ‹‹ባንኮች ሲያበድሩ ላበደሩት ገንዘብ ንብረት ይይዛሉ፡፡ ንብረቱ ኢንሹራንስ ሽፋን እንዲኖረው ማስገደዳቸው ብቻ ሳይሆን አሁን ባለው በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የፖለቲካ ቀውስና ቴረሪዝም ሪስክም (ሥጋት) እንዲገባ ያስገድዳል፤›› ይላሉ፡፡

ስለዚህ ጦርነት ባለበት ወቅት ይገኝ የነበረ ገቢ መታጣት ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ኢንሹራንስ ያሉ ዘርፎች ላይ ጫና የሚፈጥሩ ሁኔታዎች ይከሰታሉ፡፡ ባንኮች ከፖለቲካ ቫዮለንስ ቴረሪዝም ኢንሹራንስ ሽፋን እንዲገቡ የሚያስገድዱበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ይህንን የሚያደርጉት በጦርነት ወቅት የሚቃጠልን አንድ ንብረት በተራ የእሳት ቃጠሎ የኢንሹራንስ መሸፈን ስለማይችል ነው፡፡ በጦርነት ወቅት የሚፈጠሩ ቀውሶች እንዲህ ያሉ ጫናዎችን ሊያሳድሩ የሚችሉ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በጦርነት ወቅት የኢንሹራንስ ኩበንያዎች ከሚደርስባቸው የገቢ ተፅዕኖ ባሻገር ደንበኞቻቸውም ይጎዳሉ ያሉት አቶ ኢብሳ ደግሞ፣ በጦርነት አካባቢዎች ያሉ ደንበኞች ጉዳት ቢደርስባቸው የሚካሱበት ዕድል የሌለ መሆኑን ነው፡፡ ይህም የሚሆነው የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ጉዳቱን ዓይተው ካሳውን ለመክፈል ዕድል የሌላቸው በመሆኑ አንዱ ምክንያት ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ በጦርነት ወቅት ለሚወድሙ ንብረቶች ይኖራሉ ተብሎ ታስቦ ኢንሹራንስ የማይገባ በመሆኑ በጦርነቱ ወቅት የሚደርሱ ውድመቶች ሳይሳኩ የመቅረት ሌላ አደጋ እንደሚገጥማቸው ገልጸዋል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በጦርነት አካባቢዎች ባሉና ሽፋን ያላቸውን ንብረቶች ጉዳት ለደረሰባቸው ንብረቶች ካሳ ለመስጠት የማይቻልበት ሁኔታ መኖሩን የገለጹት አቶ አሰግድም፣ አብዛኛው ወይም ሁሉም በሚባል ደረጃ በጦርነት ወቅት ለሚከሰት ጉዳት ለብቻ የሚገዛውን ኢንሹራንስ ሽፋን ስለማይጠቀሙ የሚካሱበት ዕድል የጠበበ መሆኑንም አክለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት አብዛኛዎቹ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች የፖለቲካ አለመረጋጋትና የጦርነት ጉዳት የመድን ሽፋን እየሰጠ ቢሆንም፣ ይህንን የመድን ሽፋን የኢንሹራንስ ደንበኞች ስለማይጠቀሙት የእሳት አደጋ ኢንሹራንስ ቢኖራቸው እንኳን ንብረቱ የወደመው ከጦርነት ጋር የተያያዘ መሆኑ ከታወቀ ካሳ አይከፈልም፡፡ ስለዚህ ከጦርነቱ መከሰት ጋር በተያያዘ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪውም ሆነ ተገልጋዩ የሚጎዳባቸው ዘርፎች በርካታ ከተሰጠው ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ከጦርነት፣ ከአመፅና ከሽብርተኝነት ጋር በተያያዘ ለሚከሰት አደጋ ስለሚሰጥ የመድን ሽፋን ኢትዮጵያ ውስጥ ያልተለመደ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ባለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት ያልታወቀ ባህል ማስተናገድ ጀመረች ያሉት አቶ አሰግድ፣ በየቦታው መኪና፣ ቤትና ፋብሪካ ማቃጠል፣ ንብረት ማቃጠልና የመሳሰሉት ነገር መታየት መጀመሩ ይህ ኢንሹራንስ ሽፋን እንዲጀምር አስገድዷል፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች እንዲህ ባለው ሁኔታ የሚደርሰውን ውድመት መልሶ ለመተካት የፖለቲካ ግጭት የመድን ፖሊሲ አስፈላጊ ቢሆንም፣ ይህንን የኢንሹራንስ ዓይነት የሚገዙ በብዛት ባለመኖራቸው ንብረቱ ሳይካካስ ይቀራል፡፡ በአሁኑ ወቅት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በሚካሄደው ጦርነት የወደሙ ንብረቶች ኢንሹራንስ ሽፋን የሌላቸው መሆን ትልቅ ጉዳት ስለመሆኑም ከአቶ አሰግድ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

አሁን ያለው የጦርነትና ተያያዥ ቀውሶች ኢንዱስትሪው ላይ የደረሰው ጉዳት በተለያየ መንገድ የተገለጸ ቢሆንም፣ አብዛኞቹ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ግን ገቢያቸው ጨምሯል፡፡ አቶ ጉዲሳ እንደገለጹት ከሆነ እሳቸው የሚመሩት የአዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ በ2014 የሒሳብ ዓመት አፈጻጸሙ ሲታይ አለ ከተባለው ችግር ጋር የማይገናኝ ነው፡፡

ኢንዱስትሪው ያለበትን ተፅዕኖ ተቋቁሞ በ2014 ዓ.ም. የመጀመርያ ሦስት ወራት ውስጥ ያገኘው የዓረቦን ገቢ በ25 በመቶ መጨመሩን ገልጸዋል፡፡ ይህ የሆነው በሌሎች የአገልግሎቶች የተገኘውን ገቢ ማሳደግ በመቻሉ እንደሆነም ይጠቁማሉ፡፡ ‹‹ይህ የሚያሳየው ሰላም ብንሆን ኖሮ ምን ያህል እንሠራና ገቢያችንንም በምን ያህል መጠን ይጨምር እንደነበር ነው፤›› በማለት ተናግው ሰላም የሁሉም መሠረት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች