Monday, September 25, 2023

የማይተነበየው የሱዳን ፖለቲካ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በዮናስ አማረ

 

ባለፈው ዓመት ሚያዝያ በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል የድንበር ንግድ አለመቋረጡን የሚጠቁም ዜና መውጣቱ አስገራሚ ነበር፡፡ ሱዳን በዚያው ዓመት ከወራት በፊት የኢትዮጵያን ድንበር እስከ 60 ኪሎ ሜትሮች ተሻግራ ሰፊ መሬት በኃይል መውረሯ ብዙ ሲባልበት የነበረ ጉዳይ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ በይደር እያለ ዘንድሮ በመስከረም መግቢያ ከሱዳን በኩል ተሻግሮ የገባና የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን የማውደም ዒላማ ያለው ቅጥረኛ ቡድን ተደመሰሰ የሚል መግለጫ፣ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በኩል ተደመጠ፡፡

በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ጉርብትናም ሆነ ግንኙነት ከየት፣ እንዴትና ወዴት የሚለው ጉዳይ ያልለየለት ፍፁም ጉራማይሌ መሆኑን ብዙዎች ይናገራሉ፡፡

በመስከረም ወር የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከሱዳን የገቡ 50 ቅጥረኛ አሸባሪዎችን ገድዬ ከ70 በላይ አቆሰልኩ ቢልም፣ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የሚቃጣው አደጋ ግን ገና ያበቃ አይመስልም፡፡ ከሰሞኑ በሱዳን የተፈጠረው አለመረጋጋትና ብጥብጥ ደግሞ ይህን ሥጋት የሚያሳድግ ነው ተብሎ ይገመታል፡፡

ከሰሞኑ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራን ተከትሎ በሱዳን የደረሰው አለመረጋጋት ተጨማሪ ሥጋት ሆኖ ሳለ የተሰማው ሌላ ዜና ደግሞ፣ የሱዳንና የኢትዮጵያ ጉዳይ ዕልባት ለማግኘት ገና ብዙ እንደሚቀረው ያሳያል የሚሉ የፖለቲካ ተንታኞች አሉ፡፡

የማይተነበየው የሱዳን ፖለቲካ

ከሰሞኑ የሱዳን ገዳሪፍ ግዛት ግብርና ቢሮ ተጠባባቂ ሚኒስትር እንዳስታወቁት፣ ሱዳን በጉልበት በያዘችው የኢትዮጵያ ግዛት ከፍተኛ የተባለ የግብርና ምርት አግኝታለች፡፡ ሱዳን ሉዓላዊ ግዛቴ ነው በምትለው በዚህ የአልፋሽቅ አካባቢ ከ25 ዓመታት በኋላ ዘርቶ ለመቃም መብቃቷን ለዓለም ይታወቅልኝ ብላለች፡፡ የሱዳን ባለሥልጣናትም ከ142 ሺሕ ሔክታር በላይ ለም መሬታቸውን አርሰው ለፍሬ በቃልን ብለዋል፡፡ ለዚህ ኢትዮጵያ የምትሰጠው ምላሽ ገና አልታወቀም፡፡

ይህ ሁሉ ለውጥ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ባላት ግንኙነትና ጉርብትና ላይ የተደባለቀ ስሜትን የሚፈጥር ነው ይላሉ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ወገኖች፡፡ ሱዳን ከሦስት አሠርታት በላይ በኦማር አልበ ሽር ከመገዛት ነፃ ወጥታ የዴሞክራሲ ዳዴ ጀመረች ሲባል ለውጡ ወደ ነውጥ ተቀልብሶ ወደ ብጥብጥ እያዘገመች ትገኛለች፡፡ በአገሪቱ ዴሞክራሲ ሊያብብ ነው ሲባል የሱዳን ባለሥልጣናት ለወንበሩ እርስ በርስ ወደ መናከስ አምርተዋል፡፡ በሱዳን ዴሞክራሲ ብቻ ሳይሆን ሰላም ሰፈነ ተብሎ ሲነገር፣  የጎረቤቷን ኢትዮጵያ ድንበር ወረረች የሚል ዜና ይሰማል፡፡ የሱዳን ፖለቲካ ለምን አቅጣጫው የማይተነበይና በአጭሩ የማይቋጭ ሆነ ለሚለው መልስ ለማፈላለግ ሲሞከር የሚገኘው ማብራሪያ ሰፊ ነው፡፡

ሱዳኖች ከጎረቤቶቻቸው ብቻም ሳይሆን እርስ በርሳቸውም ተስማምተው በሰላም የኖሩበት ጊዜ ጥቂት ነው ይላሉ የሱዳን ጉዳይ አዋቂው ሰው አቶ ተስፉ የሺወንድም፡፡ ራሳቸውን የ1960ዎቹ ትውልድ ብለው የሚጠሩት አቶ ተስፉ ከረዥም ጊዜ በፊት ከወልቃይት ወደ ሱዳን ተሰደው እዚያው ሱዳን ታስረው፣ ተምረው፣ እንዲሁም ለረዥም ዓመታት ሠርተውና ከሕዝቡ ጋር ኖረው ስለሱዳኖች ብዙ ጉዳይ ማወቃቸውን ያስረዳሉ፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር (UNHCR) ውስጥ በሱዳን ሲሠሩ መቆየታቸውን የሚናገሩት አቶ ተስፉ የሱዳን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤል ሳዲግ ኤል ማሀዲ ጥብቅ ወዳጅ መሆናቸውንም ያስረዳሉ፡፡  የሱዳንን ወቅታዊ የፖለቲካ አለመረጋጋት በተመለከተ ሥረ መሠረቱ ረዥም ታሪክ ያለው መሆኑን የሚገልጹት አቶ ተስፉ፣ በቅርበት አውቀዋለሁ የሚሉትን የካርቱም ፖለቲካ ገጽታ በሰፊው ለመተንተን ሞክረዋል፡፡

የሱዳን ፖለቲካ ዓረባዊና አፍሪካዊ አብዮተኝነት የተጫነው ብቻ ሳይሆን፣ በጎሳ፣ በአካባቢና በቤተሰብ ጭምር በተፅዕኖ መውደቁን አቶ ተስፉ ይናገራሉ፡፡

ከሰሞኑ በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ላይ የተደረገው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በቋፍ የነበረውን የሱዳን መረጋጋት ዳግም አናጋው፡፡ ከተሞች በተቃውሞ መናጥ ጀመሩ፣ መንገዶች ተዘጉ፡፡ በፖርት ሱዳን፣ በካርቱምና በሌሎች አካባቢዎች አመፅ በረከተ፡፡

ወትሮም ተስማምቶ አገር መምራት ያቃታቸው ጥምር መንግሥት መሥርተናል ሲሉ የቆዩት የሲቪልና የወታደሩ አስተዳደር ልዩነታቸው በእጅጉ ሰፋ፡፡ ይህ በልዩነትና በተቃርኖ የተሞላ የፖለቲካ ድባብ ከመብረድ ይልቅ ከሰሞኑ የበለጠ ተጋግሎ ነበር የከረመው፡፡

ወቅታዊውን የሱዳን ፖለቲካ ጡዘት በተመለከተ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ተስፉ፣ የሱዳኖቹ ጊዜያዊ ጥምር የሽግግር መንግሥት መሥርተናል ባይነት ‹‹ድራማና ማስመሰል የሞላበት ነበር፤›› ብለውታል፡፡

‹‹በሱዳን ፖለቲካ ውስጥ ሦስት ዓይነት ዝግባሌዎች አሉ፡፡ አንዱ ወደ ግብፅና ዓረቦች እንጠጋ የሚል እስላማዊ የዓረብ ብሔርተኝነት ነው፡፡ ሁለተኛው አፍሪካዊና ጥቁር ሱዳኖች ነን የሚል ብሔረተኝነት ሲሆን፣ ሌላው ኮሙዩኒዝም ዘመም አብዮተኝነት ነው፡፡ በአፍሪካ ፓርቲ በመመሥረት ከቀደሙ አገሮች ሱዳን አንዷ ናት፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1922 ጀምሮ የተለያዩ ፓርቲዎችን መሥርተው ከቅኝ ግዛት ነፃ በመውጣት፣ የሱዳን ሪፐብሊክን ለመመሥረት ሱዳኖች ታግለዋል፤›› በማለት ነው የሱዳንን የአገረ መንግሥት ምሥረታ ሒደት አቶ ተስፉ የሚያስረዱት፡፡

አንዴ አገሪቱን እስላማዊት ሪፐብሊክ አድርገን ከግብፆች ጋር አንድ አገር ሆነን የዓረብ ሪፐብሊክን እንመሠርታለን የሚሉ ቡድኖች ሲያይሉ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ወታደራዊ አስተዳደሮች ሲፈጠሩ ሱዳን ለብዙ ዓመታት ባልተረጋጋ ፖለቲካ ማሳለፏን አቶ ተስፉ ያስረዳሉ፡፡

‹‹መሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ ወይም ጄኔራል ሄሜቲ በ1990ዎቹ መጀመርያ አንስቶ የጃንጃዊድ ሚሊሻዎችን አደራጅቶ ዳርፉርን ሲወጋ የኖረ ሰው ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ኦማር አል በሽር በተቃውሞ ተገፍቶ ከሥልጣን ሲወርድ የሱዳን መደበኛ ጦርን በትኖታል፡፡ አሁን ጠንካራ ኃይል ያለው ሄሜቲ የሚመራው በፊት ጃንጃዊድ ሚሊሻ የሚባለው ጦር ነው፡፡ ሄሜቲ ለአል በሽር ቅርብ ሰው ስለነበር ይህ የሚሊሻ ኃይል ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት ተብሎ ዘመናዊ መሣሪያ እንዲታጠቅ ተደርጓል፡፡ ጦሩ እስካሁንም ትጥቁን ያልፈታ ሲሆን፣ መሪው ጄኔራል ሄሜቲ ደግሞ የወታደራዊው ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል መሪ ሆኗል፤›› ሲሉ አቶ ተስፉ ያስረዳሉ፡፡  

‹‹በሱዳን ለውጥ መጣ ሲባል የታጠቀ ኃይለኛ ሠራዊት የሚመሩት እነ ሄሜቲ ከሱዳን መደበኛ ጦር ደካሞቹን እነ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃንን ከፊት በማሠለፍ፣ ወታደራዊ ምክር ቤት ብለው መሠረቱ፡፡ ለውጡን እንደግፋለንና ከሲቪል አስትዳደሩ ጋር ተጣመርን ብለው የሽግግር መንግሥት መመሥረቱን አወጁ፤›› ሲሉ የሚያስረዱት ተስፉ፣ ይህ ሁሉ ግን ግፋ ቢል ምዕራባዊያኑን ለማማለል የሚደረግ ጥረት እንጂ የለውጥ ፍላጎት እንዳልነበረ ይገልጻሉ፡፡

የዳርፉር ጦር ወንጀለኞችን ለሄግ ፍርድ ቤት እንሰጣለን፣ እንዲሁም ከእስራኤል ጋር እንታረቃለን በማለት የምዕራባዊያኑን ድጋፍ ወታደሮቹ ማግኘታቸውን አቶ ተስፉ ይገልጻሉ፡፡ አገሪቱን የሚያሾራትና የሚዘውራት እነ ሄሜቲ የሚመሩት የጦር ኃይል መሆኑን የሚናገሩት አቶ ተስፉ፣ የሲቪል መንግሥቱን ከጨዋታ ውጪ በማድረግ ብቻቸውን መምራት እንደሚፈልጉ ነው የጠቆሙት፡፡

‹‹የአል በሽር መንግሥት ከወረደ በኋላ ሱዳን ውስጥ ትጥቃቸውን ሳይፈቱ ጠንካራ ኃይል ይዘው የቀጠሉ ሌሎች ቡድኖችም አሉ፡፡ ከሱዳን ለመገንጠል የሚፈልጉትን የበለሉማ፣ ኑባ፣ ምልቅእዝረትን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ ብዙ የፖለቲካ ቡድኖች አሉ፤›› በማለትም የሱዳን ፖለቲካ ግለት፣ መገፋፋትም ሆነ ጡዘት ገና ተብላልቶ ያልወጣለት መሆኑን አቶ ተስፉ ያስረዳሉ፡፡

በሱዳን በአሁኑ ጊዜ በወታደራዊውና በሲቪል አስተዳደሩ መካከል ከፍተኛ መገፋፋት ይታያል፡፡ ከሰሞኑ በተለያዩ ከተሞች ለተቃውሞ የወጡ ሠልፈኞች የሲቪል መንግሥቱ እንዲበተን ሲጠይቁ ታይቷል፡፡ ሠልፈኞቹ የወታደራዊው ምክር ቤት አፍቃሪ መሆናቸውን የሲቪል መንግሥቱ ባለሥልጣናት ይናገራሉ፡፡ በእነዚህ ሁለት ኃይሎች መገፋፋት መካከል ደግሞ አቶ ተስፉ እንዳሉት፣ ያደፈጡና የየራሳቸው የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው ኃይሎች መሠለፋቸው በጊዜ ሒደት ገሃድ እየሆነ መምጣቱ የሚቀር አይመስልም፡፡

ይህ ሁሉ የፖለቲካ ተቃርኖ ባለባት በአሁኗ ሱዳን ውስጥ፣ ‹‹ከሁሉ በላይ ሰፊ ድጋፍ ያለው ወጣቶች ያነሱት የለውጥ ኃይል ነው፤›› ሲሉ አቶ ተስፉ ይገልጻሉ፡፡ የሱዳን ወጣቶች በአሁኑ ወቅት ወታደራዊውንም ሆነ ሲቪሉን ሳይሆን አዲስ ሐሳብ ይዘው የሚመጡ አዳዲስ ፖለቲከኞችን ማየት እንደሚሹ አስረድተዋል፡፡

በሱዳን ፖለቲካ ውስጥ ‹‹ዓረቦች ነን፣ አፍሪካ ነን›› የሚል የቆየ መገፋፋት መኖሩን የሚያስረዱት አቶ ተስፉ ኮርዶፋን፣ ዳርፉርና ምሥራቅ ሱዳን አካባቢ ያሉ የሱዳን ማኅበረሰቦች በፖለቲካው ከፍተኛ መገለል ሲደርስባቸው እንደቆየ ይናገራሉ፡፡

የመሐመድ አል መሀዲ ቤተሰብ በተለያዩ ትውልዶች የሱዳንን ፖለቲካ ሲጫነው መኖሩን አቶ ተስፉ ያስረዳሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እስከሆኑት ሚሪያም አል መሀዲ ድረስ ከሦስት ትውልዶች በላይ የመሀዲ ቤተሰቦች በሱዳን ፖለቲካ ውስጥ አንዴ በሥልጣን፣ ሌላ ጊዜ በተቃውሞ መዝለቃቸውን በሰፊው ተርከዋል፡፡

‹‹እኔ በሳዲግ አል መሀዲ በቤተሰብ ደረጃ የምጋበዝ ጥብቅ ቀረቤታ ነበረኝ፣ ሰውዬውን ብዙ ረድቼዋለሁ፤›› በማለት የሚናገሩት አቶ ተስፉ፣ ነገር ግን የሱዳኖች ፖለቲካዊ ባህሪ ተሙለጭላጭና የማይጨበጥ ነው ይላሉ፡፡  

‹‹በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ በቀጥታም በተዘዋዋሪም ተፅዕኖ ያላት ሱዳን ከእጃችን እንዳትወጣ አያያዙን አልቻልንበትም፤›› የሚሉት አቶ ተስፉ፣ አገሪቱን በቅጡ የሚረዳ ዲፕሎማት መመደብ አስፈላጊ መሆኑን ይመክራሉ፡፡

‹‹ግብፆችን ሲወጋ ከነበረ ቤተሰብ የወጣችው ሚሪያም አል መሀዲ ዛሬ ከግብፆች ጋር ተሠልፋ ኢትዮጵያን ልታወግዝ የቻለችው በእኛ ድክመት ነው፤›› በማለትም ያክሉበታል፡፡ ‹‹በሱዳን ጉዳይ ላይ አማክረን ተብዬ በአዲሱ የኢትዮጵያ መንግሥት ተጋብዤ ነበር፤›› የሚሉት እኚህ የሱዳን ጉዳይ አዋቂ፣ በሒደት ያቀረቡትን ምክረ ሐሳብም ሆነ እሳቸውን ባለሥልጣናቱ ገሸሽ ማድረጋቸውን አስረድተዋል፡፡

አቶ ተስፉ በአሁኑ ጊዜ የሚታየው የሱዳን የፖለቲካ ሁኔታ ባልተጠበቀ መንገድ የሚያዘግምና የማይተነበይ ሆኗል ይላሉ፡፡ የሱዳን ሕዝብ ሀቀኛ ዴሞክራሲና ዳቦ ፈልጎ ወደ አደባባይ ለለውጥ የወጣ ቢሆንም፣ በብዙዎች እምነት ያገኘው ምላሽ ጥይት ወይም የፖለቲከኞች ሽኩቻን ብቻ ነው፡፡ ለሱዳን ሕዝብም አልጨበጥ ያሉት የሱዳን ፖለቲከኞች በመካከላቸው የተፈጠረውን መቃቃር በቶሎ ለመፍታት ይችላሉ የሚለው እምነት በአሁኑ ጊዜ እየተመናመነ ነው፡፡ በዚህ መሰል ቀውስ ውስጥ ከምትገኘው ሱዳን ጋር ኢትዮጵያ በምን መንገድና እንዴት ትዘልቃለች የሚለውም ቢሆን ለመተንበይ አስቸጋሪ ሆኗል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -