መንግስት አካሂዳለሁ ባለው ብሔራዊ ውይይት ለመሳተፍ አራት ቅድመ ሁኔታዎችን ማስቀመጡን የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) አስታወቀ።
መንግስት ለማካሄድ ያቀደው ብሔራዊ ውይይት የዘገየ ቢሆንም ተቀባይነት ያለው መሆኑን የገለጸው ኦፌኮ ፤
ብሔራዊ ውይይቱ ከመካሄዱ አስቀድሞ ግን መሟላት አለባቸው ያላቸውን ቅደመሁኔታዎች አስቀምጧል።
ካስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች መካከልም ፤ በሕግ ማስከበር ስም ተጀምሮ የሕልውና ማስጠበቅ ዘመቻ የተለባለው ጦርነት በሁሉም አቅጣጫ በአስቸኳይ ቆሞ ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ውይይቱ እንዲደረግ፣ ብሔራዊ ውይይቱ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብና በሁሉም ተሳታፊ ወገኖች ተቀባይነት ባላቸው ገለልተኛና ተዓማኒ አካላት እንዲመራ የሚሉት ይገኙበታል።
በተጨማሪም ፤ ብሔራዊ ውይይቱ የታጠቁ ተቃዋሚ ቡድኖችን ጨምሮ ሁሉንም የፖለቲካ ቡድኖች ያካተተ እንዲሆን ፤ የእነዚህን ቡድኖች ውክልና ለማንቃትም የሕጋና የደህንነት መሰናክሎች ከወዲሁ እንዲወገዱ እና የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞች በሙሉ ተፈትተው በውይይቱ እንዲሳተፉ እንዲፈቀድ ሲል ኦፌኮ ቅድመ ሁኔታዎችን ማስቀመጡን በመግለጫው አስታውቋል። ኦፌኮ በመረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር) እንደሚመራ ይታወቃል።