Tuesday, February 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በሁለተኛው የሩብ ዓመት ወደ ውጭ ከሚላከው ቡና 165 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዷል

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ገቢ እያስገኘ ከሚገኘው የቡና ምርት በሁለተኛው የሩብ ዓመት 165 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዷል፡፡

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ዑመር ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ በሁለተኛው ሩብ ዓመት ውስጥ በሚገኙት ሦስት ወራት ውስጥ 52,756.5 ቶን ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ 164 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዷል፡፡ ከዚህም ውስጥ በተያዘው ጥቅምት ወር 21,226.5 ሺሕ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ 70.28 ሚሊዮን ዶላር፣ በኅዳር ወር ደግሞ 15,928 ሺሕ ቶን ቡና በማቅረብ 48.69 ሚሊዮን ዶላር፣ እንዲሁም በታኅሳስ ወር 15,602 ሺሕ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ 45.98 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ይገኛል ተብሎ በዕቅድ ተይዟል ብለዋል፡፡

ባለፈው ዓመት በነበሩት ሦስት ወራት ውስጥ የተላከው አጠቃላይ የቡና መጠን 38,368 ቶን ሲሆን የተገኘው ገቢ ደግሞ 120 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በተያዘው ጥቅምት ወር 21 ሺሕ ቶን ቡና ወደ ውጭ ለመላክ የሚደረገው እንቅስቃሴ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ እንደሆነ ያስታወቁት አቶ ሻፊ፣ እስካሁንም ከ12 ሺሕ ቶን በላይ ቡና ወደ ውጭ ገበያ መቅረቡን አስረድተዋል፡፡

በተያዘው ዓመት መጨረሻ 280 ሺሕ ቶን ቡና ወደ ውጭ ገበያ በመላክ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገቢ ከቡና ይገኛል የሚለውን ዕቅድ መሠረት በማድረግ፣ የተለያዩ ሥራዎች እየተከነወኑ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ እስካሁን የተገኙት ውጤቶችም ጥሩ አመላካች እንደሆኑና ለአብነትም በመጀመርያው ሩብ ዓመት ብቻ 330 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንደተገኘ ተጠቁሟል፡፡

እስከ ታኅሳስ ወር የሚላከው ቡና የ2013 ዓ.ም. ምርት እንደሆነ ያስረዱት አቶ ሻፊ፣ ከመጀመርያው ሩብ ዓመት በመጠን የመቀነስ ሁኔታው የመጣው በሁለተኛው የሩብ ዓመት ወደ ውጭ ገበያ የሚቀርበው የቡና ምርት ያለፈው ምርት ዓመት ቀሪ የቡና ምርት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ በተያዘው የበጀት ዓመት ሁለተኛ ሩብ ዓመት የሚላከው ቡና መጠን ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ብልጫ የታየበት እንደሆነ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀው፣ የጥር ወር ሲመጣ አዲስ የቡና ምርት ስለሚገባ ምርቱና የሚገኘው ገቢ በዚያው ልክ እያደገ እንደሚመጣ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቡና መዳረሻ አገሮች ቁጥር እየጨመረ እንደሆነ ያስታወቁት አቶ ሻፊ፣ ከዚህ ቀደም ከቀዳሚ ቡና ገዥ አገሮች ዝርዝር ውስጥ ያልነበሩ አገሮች ጭምር ወደፊት እየመጡ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ ለምሳሌ ቻይና ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያን ቡና ከሚገዙ አሥር አገሮች ዝርዝር ውስጥ ገብታ እንደምታውቅ፣ በዚህ ወቅት ሰባተኛዋ ከፍተኛ ቡና ገዥ አገር እንደሆነች ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ነባሩን ገበያ የማቆየት ሥራም እንዲሁ ትኩረት እንደተሰጠው ተናግረዋል፡፡

‹‹ቨርቲካል ኢንተግሬሽን›› የሚባለው አሠራር አርሶ አደርን በመጠቀም ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ እንዳሳደገው የተገለጸ ሲሆን፣ በተለይ አላስፈላጊ የግብይት ሰንሰለቶች እንዲወገዱና የቡና ጥራት ደረጃ እንዲሻሻል በማድረግ በተጨባጭ ውጤት እንዲገኝ አስችሏል ተብሏል፡፡ ለአብነትም ባለፈው ዓመት የደረጃ አንድ ቡና መጠን  በ33 በመቶ ጭማሪ የታየበት መሆኑን፣ የደረጃ ሁለትም እንዲሁ በስድስት በመቶና የደረጃ ሦስት ቡና መጠንም በ41 በመቶ እንዲጨምር አስችሎታል ተብሏል፡፡ ሌላው ትልቁ የማይረሳው ጉዳይ በአቅራቢና በላኪዎች መካከል የፈጠረው መቀራረብ እንደሆነ አቶ ሻፊ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ከፌዴራልና ከክልል ተቋማት ጋር የሚከናወኑ የቅንጅት ሥራዎች ትኩረት የተሰጣቸው እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ከጉምሩክ ኮሚሽን፣ አንድ መስኮት አገልግሎት፣ ከብሔራዊ ባንክ፣ ከትራንስፖርት ሚኒስቴርና ከሌሎቹም ጋር በየሳምንቱ በመገናኘት የቅንጅት ሥራው እየተከናወነ እንደሚገኝ ተጠቅሷል፡፡ ከዚህ ባሻገርም ከቡና አቅራቢዎች፣ ከላኪዎች፣ ከቡና ቆዪዎችና ላኪዎች ማኅበር ጋር አቅርቦት፣ ጥራትና ኤክስፖርትን በተመለከተ ተቀናጅቶ መሥራት ትኩረት እንደተሰጠው ተጠቁሟል፡፡

ባለሥልጣኑ አርሶ አደርን የሚጠቅም ፍትሐዊ አሠራር መተግበር የመጀመርያው ዓላማው እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ በቡና ላይ ምንም ዓይነት እሴት የማይጨምር ማንም አካል ለአርሶ አደሩ በቂ ገቢ እንዳያገኝ የሚያደርግ በመሆኑ፣ ቡና ውስጥ የሚገኝ ተዋናይ ትክክለኛ ተዋናይ ሊሆን ይገባል የሚለውን  ታምኖበት በቡናና ሻይ ባለሥልጣን በኩል አስፈላጊው ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አቶ ሻፊ ተናግረዋል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች