Sunday, October 1, 2023

የካይሮው ቴአትር በካርቱም የሱዳን መፈንቅለ መንግሥትና የዓለም ማኅበረሰብ ግብረ መልስ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በዮናስ አማረ

ሱዳን ከ2018 እ.ኤ.አ. አንስቶ በተቃውሞ የፖለቲካ አለመረጋጋት ውስጥ ተዘፍቃ አሳልፋለች፡፡ በታኅሳስ 2018 በአርታባ ከተማ የተቀጣጠለው ሕዝባዊ አመፅ በሱዳን ፖለቲካ ላይ ፈላጭ ቆራጭ ሆነው ለ30 ዓመታት በፕሬዚዳንትነት የዘለቁትን ኦማር አል በሽርን ከሥልጣን ገረሰሰ፡፡ ለዳቦ ጥያቄና ለኑሮ ሁኔታ መሻሻል ወደ አደባባይ የወጡ የሱዳን ወጣቶች፣ ኦማር አል በሽርን ከረዥሙ የሥልጣን ማማ በማውረድ አብዮታቸውን ደመደሙት፡፡

በወቅቱ 246 ያህል ሱዳናውያን የሞቱበትና 1,300 ሰዎች የቆሰሉበት የሱዳን አብዮት ወራት አስቆጥሮ በሚያዝያ 2018 የሽግግር መንግሥት መመሥረት በሚያስችል ስምምነት መስከኑ ይታወሳል፡፡ የጦር ሠራዊት ከሲቪል መንግሥት ጋር ተጣምሮ ጊዜያዊ የሽግግር ጊዜ ምክር ቤት መዋቀሩ ታወጀ፡፡ ይህን ጊዜ የሱዳን የለውጥ ተስፋ ለመለመ፡፡ ወጣቶች የሞትንበት አብዮት ፍሬ ሊያፈራ ነው በሚል ተስፋ አደረጉ፡፡

ከቅኝ ግዛት ነፃ ከወጣች ጀምሮ ወታደራዊ አስተዳደር፣ የሃይማኖት አብዮተኝነትና የውጭ ፖለቲካ ጣልቃ ገብነት በሱዳን ፖለቲካ ላይ ሲፈራረቁበት ቆይተዋል፡፡ ከዚህ ሁሉ በኋላ የመጣው የ2018 አብዮት በሱዳን ፖለቲካ ላይ የዴሞክራሲ ዘር እንደሚዘራ ብዙ ተስፋ ተጥሎ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ሳይውል ሳያድር ወደ ወንበር ሽሚያ ፖለቲከኞቹ በመግባታቸው፣ ይህ ተስፋ እየጠወለገ መሄዱን ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡

የወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥቱ መሪ ሌተና ጄኔራል አብዲልፈታህ አል ቡርሃን መግለጫ በሰጡበት ወቅት

በሩሲያው አርቲ (RT) ላይ ሰፊ ትንተና ያስነበበው ሮበርት ኢንላኬሽ፣ ‹የካይሮው ፖለቲካዊ ቴአትር በካርቱም መደገሙን› ያለ ይሉኝታ ጽፎታል፡፡ የሱዳን ሰሞነኛ መፈንቅለ መንግሥት በግብፅ እ.ኤ.አ. በ2013 ከተከሰተው አብዮት ስልቀጣ በምን ይለያል የሚል ጥያቄ የሚያነሳው ጸሐፊው፣ ሌተና ጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን የአልሲሲን ገጸ ባህሪ ዳግም እንደተወኑ በስላቅ ትዝብቱን አስፍሯል፡፡

የሱዳን ሰሞነኛ አለመረጋጋትና መፈንቅለ መንግሥት ከዓለም ዙሪያ የተለያዩ ግብረ መልስ እየቀረበለት ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትን ጨምሮ ኢጋድ፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ የዓረብ ሊግ፣ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረትና ሌሎች ወገኖች በየፊናቸው መግለጫ ሲያወጡ ከርመዋል፡፡

ኅትመት እስገባንበት ማክሰኞ ምሽት ድረስ የሰባት ሰዎችን ሕይወት ቀጥፎ 140 ሰዎች የቆሰሉበት የሱዳን ፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ወዴት እንደሚያመራ ከግምት ውጪ ማንም አያውቅም፡፡ በመፈንቅለ መንግሥቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክን ጨምሮ በርካታ ባለሥልጣናት በጦር ሠራዊቱ ታስረዋል፣ ተግዘዋል፡፡ ብዙዎቹ የት እንደተወሰዱ እንኳ ማንም አያውቅም፡፡ የጦር ሠራዊቱ ዕርምጃ በሥልጣን ላይ ያሉ የሲቪል መንግሥቱን ሰዎች ብቻ ሳይሆን፣ ለተቃዋሚዎችም የሚመለስ አልሆነም፡፡ በሌተና ጄኔራል አብደልፈታህ አል ቡርሃን የሚመራው ጦር በወሰደው ዕርምጃ፣ የሱዳን ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ ፓርቲ (SPLMN) ሊቀመንበር ያሲር አርማን ጭምር ለግዞት ዳርጓል፡፡

ነገሮች በአንዴ እንዲህ እንደሚቀያየሩ የገመተ አልነበረም፡፡ በሱዳን ተቃውሞ ዳግም ተቀሰቀሰ ተብሎ መዘገብ ከጀመረ ገና ሁለት ሳምንት ቢያስቆጥር ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ተቃውሞና አመፁ ባልተጠበቀ ፍጥነት ተቀጣጥሎ፣ የሱዳን ጦር የሲቪሉን መንግሥት በትኖ ባለሥልጣናቱንም በአንድ ጊዜ መቆጣጠሩ ተዘገበ፡፡

‹‹አገሪቱ እየሄደችበት ያለው መንገድ በአገራችን እንዲሁም በወጣቶቻችን ተስፋ ላይ አሳሳቢ አደጋ የደቀነ ሆኖ ስላገኘነው ዕርምጃውን ለመውሰድ ተገደናል፤›› በማለት ነው የሱዳን ወታደራዊ ምክር ቤት የበላይ መፈንቅለ መንግሥት በማድረግ እየታሙ የሚገኙት ጄኔራል አል ቡርሃን የተናገሩት፡፡

አል ቡርሃን መፈንቅለ መንግሥት ባደረጉና ይህን በተናገሩ ማግሥት በሱዳን ሁለተኛዋ ትልቅ ከተማ ኦምዱርማን ከባድ ተቃውሞ ወጣቶች ያካሂዱ ነበር፡፡ ከወጣቶቹ አንዱ ለሚዲያ ሲናገርም፣ ‹‹ጄኔራል አል ቡርሃን እኛን ሊያታልለን አይችልም፡፡ ይህ ያፈጠጠ መፈንቅለ መንግሥት ነው፤›› ብሏል፡፡

መፈንቅለ መንግሥቱ በሱዳን ማኅበረሰብ ዘንድ ብቻም ሳይሆን በውጪው ዓለምም መከፋፈል ፈጥሯል፡፡ ከአንድ ወር ቀደም ብሎ በሲቪል መንግሥቱ ላይ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተደርጎ ነበር፡፡ ሙከራው የሲቪል አስተዳደሩን ከወታደራዊ ምክር ቤቱ ጋር ወደ ከፋ የፖለቲካ መካረር ውስጥ ከተተው፡፡ በዚህ የፖለቲካ መካረር መሀል አሜሪካ የአፍሪካ ጉዳይ  ችግር ፈቺዬ ያለቻቸውን ወኪሏን ጄፍሪ ፊልትማንን ወደ ካርቱም ላከች፡፡ ፊልትማን የሱዳንን ጉዳይ ለመፍታት ካርቱም ቆይተው ሱዳን ዳግም የመንግሥት ግልበጣ ተደረገባት፡፡

ይህን የዘነጉ የሚመስሉት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ግን፣ ‹‹በአንድ ሌሊት የሲቪል ባለሥልጣናትን ሰብስቦ ወደ እስር ቤት ማጎርና ሕጋዊ ዕውቅና ያለው መንግሥትን መበተን በፍፁም ተቀባይነት የለውም፤›› በማለት ነበር ከዋሽንግተን ዲሲ መግለጫ የሰጡት፡፡

ኔድ ፕራይስ ይህን ብቻም ሳይሆን አገራቸው አሜሪካ ካለፈው መስከረም ጀምሮ በሱዳን የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ስትደግፍ መቆየቷንም የዘነጉ ይመስሉ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. ጥቅምት 21 ቀን 2021 የራሳቸው መሥሪያ ቤት የሱዳን ተቃውሞን እደግፋለሁ የሚል መግለጫ መስጠቱ ይታወሳል፡፡ ቁጣውና ተቃውሞው የበለጠ በርትቶ ወታደራዊ ምክር ቤቱ የሲቪል አስተዳደሩን በማፍረስ በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣኑን ጠቀለለ፡፡ ይህን ጊዜ ግን ኔድ ፕራይስ፣ ‹‹እኛ የሱዳንን ሕዝብ ተገቢ ቁጣና ተቃውሞ የማሰማት መብት እንደግፋለን አልን እንጂ፣ ጦሩ መፈንቅለ መንግሥት ያድርግ አላልንም፤›› ሲሉ ነበር ነገሩን ለማስተባበል የተጣደፉት፡፡

በሲቪል አስተዳደሩ ላይ ባለፈው ወር መፈንቅለ መንግሥት ከተቃጣ በኋላ ወታደራዊ ምክር ቤቱ በሴራ ተጠምዶ መክረሙን ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ የሲቪል አስተዳደሩ ከሥልጣን ካልወረደ/ካልተበተነ የሚሉ ተቃውሞዎች በሱዳን ከተሞች በርክተው ነበር፡፡ ጦሩ ለራሱ ድጋፍ የሚሰጡ ሠልፎችን ያደራጃል የሚለው ሀሜታ ጎልቶ ከርሟል፡፡ የሲቪል አስተዳደሩን የሚያወግዙና ወታደራዊ ምክር ቤቱን የሚደግፉ ተቃውሞዎች ሲካሄዱ፣ እነ አሜሪካና የሱዳን ወዳጅ ነን የሚሉ አገሮች ጉዳዩን ‹የሱዳን ሕዝብ ተገቢና ዴሞክራሲያዊ ተቃውሞ› ነው ሲሉ መክረማቸው ለትዝብት የሚጥል መሆኑን ተቺዎቻቸው ያስረዳሉ፡፡

የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ባለፈው ወር ከተካሄደ ጀምሮ አገሪቱ በተቃውሞ ስትናጥ በከረመችበት ወቅት፣ በሲቪልና በወታደራዊ አስተዳደሩ መካከል መግባባት ለማስፈን ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ቢሮ ኃላፊ አደም ሂርካ እንዳረጋገጡትም፣ ሁለቱ ወገኖች ለስምምነት ቀርበው ነበር፡፡ ሆኖም በስተመጨረሻ የጦር ሠራዊቱ አለመግባባቱን መረጠ፡፡ ይህን ተከትሎ መፈንቅለ መንግሥቱ ዳግም መካሄዱን አደም ሂርካ ተናግረዋል፡፡

ጦሩ ወይም ጄኔራል አል ቡርሃን የሲቪል አስተዳደሩን አፍርሰው ሱዳንን በወታደራዊ አገዛዝ ሥር ለማዋል የደፈሩት፣ ከምዕራባውያንና ከዓረብ አገሮች ድጋፍ ስላገኙ መሆኑን የአርቲ ተንታኙ ሮበርት አንላኬሽ አስረድቷል፡፡ ‹‹ጦሩን የሚደግፉና የሲቪል አስተዳደሩን የሚቃወሙ ሠልፎች በሱዳን ጎዳናዎች ሲካሄዱ የከረሙት ለፖለቲካ ድራማ ነው፤›› በማለት ጸሐፊው ይናገራል፡፡

አርቲ ላይ ሰፊ ምልከታውን ያስቀመጠው ሮበርት ኢንላኬሽ በግብፅ የ2011 ሕዝባዊ አብዮትን ጄኔራል አብዱልፈታ አልሲሲ እንደቀለበሱት ሁሉ፣ ሌተና ጄኔራል አብዱልፈታ አልቡርሃንም ተመሳሳይ ፖለቲካዊ ትወና በካርቱም እየሠሩ መሆኑን በድፍረት ተናግሯል፡፡ ይህ የጄኔራል አል ቡርሃን ዕርምጃ ደግሞ የአሜሪካ፣ የአውሮፓና የሌሎች ዓረብ አገሮችን ድጋፍ ያገኘ መሆኑን ያስረዳል፡፡

አሜሪካ ለሱዳን ለመስጠት ቃል ገብታው የነበረን 700 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማገዷን አስታውቃለች፡፡ የአውሮፓ ኅብረት የሱዳን ጦር ያሠራቸውን የሲቪል ባለሥልጣናት በአስቸኳይ እንዲፈታ ጥብቅ ማሳሳቢያ ሰጥቷል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማክሰኞ ሌሊት ስለሱዳን በፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት በዝግ ሲመክርበት ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ግን ለይስሙላ የሚደረግ የካርቱም ፖለቲካ ድራማ አካል እንጂ፣ የሚለውጠው ነገር አለመኖሩን የሚናገሩ ሃያሲያን በርካታ ናቸው፡፡

‹‹ለኦማር አልበሽር ጥብቅ ወዳጅ የሆኑ የጦር ባለሥልጣናት ዳግም የሱዳን ሥልጣንን ጠቀለሉ፤›› በማለት ነበር ሱዳን ፖስት የተባለው ድረ ገጽ ክስተቱን የዘገበው፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2019 ጀምሮ የዓረብ አገሮች በሱዳን ፖለቲካ እጃቸውን አስረዝመው አብዮቱን ለመቀልበስ ሲሞክሩ ነበር የሚል ዘገባ የሚያስነብበው የቱርኩ ቲአርቲ ወርልድ (TRT) በበኩሉ፣ በሱዳን ፖለቲካ ቀውስ ውስጥ የውጭ ኃይሎችን ጣልቃ ገብነት አስነብቧል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ያወጣው መግለጫም ይህንኑ የሚያጠናክር ሲሆን፣ ‹‹የሱዳን ሕዝብ ሉዓላዊ ፍላጎት መከበር አለበት›› በማለት አስታውቋል፡፡ የሱዳንን ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ስለመደገፍና ከሱዳን ጋር ኢትዮጵያ ስላላት ወንድማዊ ግንኙነት መጠናከር የሚዘረዝረው መግለጫው፣ ‹‹የሱዳን ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እንደሚያሳስበውና በቅርበት እንደሚከታተለው፤›› ጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ባላንጣ ከሆነችው ከወደ ግብፅ የተደመጠው መግለጫ ደግሞ ጠንከር የሚል ይዘት ነበረው፡፡ የፖለቲካ ትወናቸውን ኮርጀዋል የሚል ትችት ስለሚሰማባቸው አል ቡርሃን መፈንቅለ መንግሥት አስተያየት የሰጡት ፕሬዚዳንት አብዱልፈታ አልሲሲ፣ ‹‹የሱዳን ፀጥታና መረጋጋት ለእኛም ሆነ ለቀጣናችን ፀጥታና መረጋጋት አስፈላጊ ጉዳይ ነው፤›› በማለት መናገራቸው በግብፅ ሚዲያዎች ተዘግቧል፡፡

በሱዳን ሰሞነኛ መፈንቅለ መንግሥትና ፖለቲካዊ ቀውስ ዙሪያ ከዓረብ ሊግ ጀምሮ እስከ አፍሪካ ኅብረትና ኢጋድ ድረስ ያሉ ቀጣናዊ ተቋማት ሁኔታውን አሳሳቢ ሲሉ አቋም አንፀባርቀዋል፡፡ ይህ ሁሉ ዓለም አቀፍና ቀጣናዊ ጩኸት እየተስተጋባ ባለበት ወቅት፣ ጄኔራል አል ቡርሃን የሚመሩት ጦር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ የሲቪል መንግሥቱን በትኗል፡፡ በአገሪቱ የንግድ ማኅበራት እንቅስቃሴም ታግዷል፡፡

የብሪታኒያ መንግሥት መፈንቅለ መንግሥቱን፣ ‹‹በሱዳን ሕዝብ ላይ የተፈጸመ ክህደት›› ሲል ኮንኖታል፡፡ ይሁን እንጂ ይህን ክህደት እነሱም ሆነ አጋር የምዕራባውያን አገሮች በመግለጫ ከመኮነን በዘለለ ለማስቆም ተጨባጭ ዕርምጃ አለመውሰዳቸው አስተዛዛቢ ነው ይላሉ ተቺዎች፡፡

የሱዳን መፈንቅለ መንግሥት ተቃውሞና ቁጣ አስከትሎ የሱዳናውያን ለውጥ ፈላጊዎች ሕይወትን እየነጠቀ ነው፡፡ ክስተቱ ከየአቅጣጫው የተለያየ ስሜትና ውዝግብ እያስከተለም ይገኛል፡፡

ይህ ሁሉ እየተስተናገደ ባለበትና ወደ ኅትመት ለመግባት በተቃረብንበት ሰዓት ግን አዲስ መግለጫ ከካርቱም ተደመጠ፡፡ ሌተና ጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን ማክሰኞ ወደ አመሻሽ በሰጡት መግለጫ ከሥልጣን ያነሷቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ፣ ‹‹በመኖሪያ ቤቴ ውስጥ ይገኛሉ፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሃምዶክን በመኖሪያ ቤቴ ያቆየሁት ለደኅንነቱ ሲባል ነው፤›› በማለትም ጄኔራሉ በመግለጫቸው አስታውቀዋል፡፡ ይህ የጄኔራል አል ቡርሃን መግላጫ በካርቱም የፖለቲካ ድራማ ላይ ሳቅ የሚፈጥር ቀልድ ከመሆን ባለፈ፣ በቀውስ ውስጥ ለምትገኘው አገር ሊፈጥር የሚችለው መፍትሔ ስለመኖሩ የሚጠራጠሩ በርካቶች ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -