Monday, July 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ጎህ ባንክ በመጀመርያ የሥራ ዓመቱ አንድ ቢሊዮን ብር ብድር ሊያቀርብ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

በቤት ግንባታና ግዥን ፋናንስ ለማድረግ የተቋቋመው ጎህ ቤቶች ባንክ በመካከለኛና ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ላሉ ዜጎች የመኖሪያ ቤት አቅርቦትን ለማሻሻል እንደሚሠራና በመጀመርያው ዓመት አንድ ቢሊዮን ብር ብድር እንደሚያቀርብ አስታወቀ፡፡

የመጀመርያው የግል ሞርጌጅ ባንክ የሆነው ጎህ ቤቶች ባንክ የመጀመርያውን ቅርንጫፉን በመክፈት ወደ ሥራም ገብቷል፡፡

የጎህ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አስማረ እንደገለጹት፣ በተለይ በመካከለኛና ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላሉ ዜጎች የቤት አቅርቦቱን ለማሻሻል አራት ዋና ዋና መንገዶች ይከተላል፡፡

ቤት መሥራትና ቤት መግዛት ለሚፈልጉ ዜጎች እስከ 30 ዓመት የሚደርስ የረዥም ጊዜ ብድር ማቅረብ አንዱ ክንውኑ መሆኑን የገለጹት አቶ ሙሉጌታ፣ ከተማዋ መስተዳድሮች ጋር በመቀናጀት መሬት ተረክቦ ከአገር ውስጥና ከውጭ አገር አልሚዎች ጋር በመሆን ቤቶችን በመሥራትና በሽያጭ ለቤት ግዥዎች በረዥም ጊዜ ብድር ለማስተላለፍ የተሰናዳ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ባንኩ በተለይ በዝቅተኛና መካከለኛ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ዜጎች ቤት አቅርቦትን ለማስፋት እጠቀምበታለሁ ያለው ዘዴ ከዓለም አቀፍ አበዳሪና ለቤቶች መገንቢያ በልዩ ሁኔታ ፈንድ ከሚያቀርቡ ተቋማት ጋር በመተባበር ደረጃቸውን የጠበቁ ቤቶች እንዲገነቡ በማድረግ በተመጣጣኝ ዋጋ ለቤት ፈላጊዎች በረዥም ጊዜ ብድር ማስተላለፍ እንደሚሆንም አክለዋል፡፡

የባንኩ አቅም እያደገ ሲሄድ በካፒታሉ ቤቶችን እየገነባ በረዥም ጊዜ ብድር ለተጠቃሚዎች በማስተላለፍ ችግሩን ለማቃለል ውጥን ይዞ እየሠራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡   

በኢትዮጵያ የቤት መሥሪያ ወይም ለቤት መግዣ የሚሆን ብድር በማቅረብ ረገድ ጎህ ቤቶች ባንክ የበኩሉን ይወጣል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ለዚህም ባንኩ የራሱን ዝግጅት በማጠናቀቅ ሥራ መጀመሩን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ በአሁኑ ወቅት ያለው የመኖሪያ ቤት ችግር እጅግ ከፍተኛ መሆኑን አመልክተዋል፡፡  

‹‹በኢትዮጵያ አሁኑ ወቅት በከተሞች ያለው የመኖሪያ ቤት ፍላጎት በጣም ከፍተኛ ሲሆን፣ በአንፃሩ አቅርቦቱ እጅግ አናሳ ነው፡፡ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፣ እስካሁን የከተማውን ውዝፍ የቤት ፍላቶች ለማርካት ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ቤቶች መሠራት አለባቸው፤›› ብለዋል፡፡

አሁን ላለው ብቻ ሳይሆን፣ አዳዲስ የሚፈጠሩ የቤት ፍላጎቶችን ለማሟላት በየዓመቱ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ከ100 ሺሕ በላይ ቤቶች መገንባት አለባቸው፡፡ በአዲስ አበባ ካሉት ቤቶች ውስጥ እስከ 70 በመቶ ያህል ደረጃቸውን ያልጠበቁና ለሰው ልጆች መኖሪያነት ምቹ ባለመሆናቸው፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እየተሻሻለና መካከለኛ ገቢ ወዳላቸው አገሮች ተራ ሲሸጋገር ፈርሰው እንደገና መገንባት ያለባቸው ናቸው፡፡ የቤቶች አቅርቦትን ለማስፋፋት ፋይናንስ አንዱና ዋናው ግብዓት በመሆኑ ጎህ ባንክ እዚህ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ይሠራል ተብሏል፡፡

የባንኩ ሥራ ማስጀመሪያ ፕሮግራም ላይ የተገኙት የከተማ መሠረተ ልማት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ፣ በአሁኑ ወቅት ያለው የመኖሪያ ቤት እጥረት የከፋ መሆኑን አመላክተው፣ በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለመሙላት ከአራት መቶ ሺሕ በላይ የሚሆኑ ቤቶች መገንባት ያለባቸው ስለመሆኑ ጥናቶቹ ያሳያሉ ብለዋል፡፡

አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን በየዓመቱ እየተገነቡ ያሉ የመኖሪያ ቤቶች ቁጥር ከሚፈለገው በእጅጉ ያነሰ እንደሆነ የገለጹት ሚኒስትሯ፣ በኢትዮጵያ በተለይ በከተሞች የመኖሪያ ቤት እጥረት ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ ልንፈታው ያልቻልነው የዘመናት ተግዳሮት ሆኖ ስለመቀጠሉ ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ ዕድሜ ጠገብ የሆኑ ታሪካዊና በተለያዩ ጊዜያት የመሠረቱት አዳዲስ ከተሞች ቢኖሯትም ከተማዋን ዘመናዊ ከማድረግና ለከተማ ነዋሪዎች ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር አኳያ ብዙ ሥራ ተሠርቷል ለማለት እንደማያስደፍር ተናግረዋል፡፡

ለችግሩ መባባስ ደግሞ በርካታ ምክንያቶች ያሉ ቢሆኑም፣ በተለይ የመሬት አቅርቦት አለመሳለጥና በቂ የፋይናንስ አቅርቦት አለመኖርን ጠቅሰዋል፡፡ ችግሮቹን ለመፍታት መንግሥት ከቀየሰው የአሥር ዓመት ዕቅድ ውስጥ በትኩረት የሚሠራበት ጉዳይ ይሆናል ብለዋል፡፡    

የጎህ ቤቶች ባንክ የመጀመርውን ቅርንጫፍ በክብር እንግድነት ተገኝተው የከፈቱት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፣ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን ቤት ችግር ለመቅረፍ መንግሥት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ እንደ ጎህ ያሉ ባንኮች መበራከት እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል፡፡

የመኖሪያ ቤት እጥረት በተለይ በአዲስ አበባና በሌሎች ትልልቅ የክልል ከተሞች እጅግ አንገብጋቢ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስ በመሆን የቀጠለ ሲሆን፣  መንግሥትም በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የመኖሪያ ቤቶች ችግር ለማቃለል ዛሬም ጥረቱን ቀጥሏል ብለዋል፡፡

የከተሞች የመኖሪያ ቤት ችግር በየጊዜው እየጨመረ ከመምጣቱና ከዜጎች ፍላጎት ጋር ተደማምሮ በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ዜጎች ላይ ከፍተኛ ችግር በመፍጠሩ ለመኖሪያ ቤት ግንባታና ግዥ ፋይናንስ የሚያቀርቡ ባንኮች ኢንዱስትሪውን መቀላቀል እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸዋል፡፡

የቤቶች ግንባታን በመደገፍ እስካሁን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰፊ ሚና እንደነበረው የጠቆሙት ወ/ሮ ጫልቱ፣ ዘርፉ ከሚያስፈልገው የፋይናንስ አቅርቦት አንፃር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የቻለ እንደማይመስላቸው ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ለቤት ብድር የሚያቀርቡ ባንኮች ከመቼውም ጊዜ በላይ አስፈላጊ መሆናቸውን በዕለቱ ፋናወጊ ሥራ እንደጀመረው ጎህ ቤቶች ባንክ ያሉ ተጨማሪ ባንኮች እንዲገቡ ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡

የቤት ልማትን ለሚደግፉ የፋይናንስ ተቋማት ድጋፍ ይሰጣሉ የተባሉ ሕግጋትንና አሠራሮችን በማሻሻል ጭምር ለዘርፉ ድጋፍ እንደሚደረግ ወ/ሮ ጫልቱ ጠቁመዋል፡፡   

በ1960ዎቹ መጀመርያ አካባቢ የሞርጌጅ ፋይናንስ አገልግሎት ይሰጡ የነበሩት፣ ‹‹ኢምፔሪል ሴቪንግ ኤንድ ሆም ኦውነርሽፕ ፐብሊክ አሶሴሽን›› እና ‹‹ዘ ሴቪንግ ኤንድ ሞርጌጅ ኦፕሬሽን ኦፍ ኢትዮጵያ›› ናቸው፡፡

እነዚህ ተቋማት ብዙ ርቀት ሳይጓዙ በ1966 ዓ.ም. የመንግሥት ለውጥ በመምጣቱ እንዲወረሱና በአንድ ላይ ተዋህደው ‹‹የቤቶችና ቁጠባ ባንክ›› በሚል ስያሜ የሞርጌጅ ፋይናንስ አገልግሎት ይሰጡም ነበር፡፡ ይህ ባንክ በ1987 ዓ.ም. ስያሜውን ወደ ‹‹ኮንስራክሽንና ቢዝነስ›› ባንክ ቀይሮ ከቤቶች ፋይናንስ ይልቅ መደበኛ የንግድ ባንክ አገልግሎት መስጠት ላይ በማተኮሩ የሞርጌጅ ፋይናንስ አገልግሎቱ በእጅጉ ተዳክሞ በመጨረሻም ባንኩ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በመቀላቀሉ ኢትዮጵያ በቤቶች ፋይናንስ ላይ ያተኩር የነበረውን ብቸኛ ባንክ እንድታጣ መደረጉ ይታወሳል፡፡  

ጎህ ቤቶች ባንክ በዋናነት ትኩረት ያደረገው በቤቶች ፋይናንስ ላይ ቢሆንም፣ በተጓዳኝ ሌሎች በመደበኛ የንግድ ባንኮች የሚሰጡ አገልግሎቶችን እንደሚያቀርብ ተገልጿል፡፡

እንደ አቶ ሙሉጌታ ገለጻ፣ ባንኩ በተያዘው የበጀት ዓመት እስከ 1.3 ቢሊዮን ብር የሚደርስ ቁጠባ ለመሰብሰብና ወደ አንድ ቢሊዮን ብር የሚሆን ብድር ለመስጠት አቅዶ ሥራ ጀምሯል፡፡ ዘንድሮ አዲስ አበባን ጨምሮ በክልል ከተሞች እስከ አምስት የሚደርሱ ቅርንጫፎችም ተከፍተው አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋል፡፡ በቀጣይ አምስት ዓመት ደግሞ የባንኩ ተቀማጭ በየዓመቱ በአማካይ በ30 በመቶ እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡

የተከፈለ ካፒታሉንም በሚቀጥሉት አምስትና ስድስት ዓመታት ወደ አምስት ቢሊዮን ብር ከፍ እንደሚል ታሳቢ ተደርጎ የሚሠራ በመሆኑ፣ የባንኩ የማበደር አቅም እስከ 6.4 ቢሊዮን ብር ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ ሙሉጌታ አስረድተዋል፡፡

ጎህ ቤቶች ባንክ እንደ ሌሎች ንግድ ባንኮች በርካታ ቅርንጫፎች የማይኖሩት ቢሆንም፣ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ እስከ 60 የሚደርሱ ቅርንጫፎች እንደሚከፍም ባንኩ አሳውቋል፡፡

ባንኩ ብቸኛው የሞርጌጅ ባንክ ሆኖ ኢንዱስሪውን ሲቀላቀል 1.1 ቢሊዮን ብር የተፈረመና 521.5 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል በመያዝ እንደሆነ ታውቋል፡፡  

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች